Saturday, 15 October 2022 11:32

“ግሪን ሌጋሲ” እና ጦርነት ጎን ለጎን!

Written by  ትዕግስቱ በለጠ
Rate this item
(3 votes)

   • ውጊያ ለማካሄድም ጦርነትን የሚሸከም ኢኮኖሚ ያስፈልጋል
             • ለአማጺው ቡድን ልማት ማለት ምሽግ መቆፈር ነው
             
         ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት የተጋፈጠችውን ያህል መከራና ተግዳሮት መቼም ገጥሟት የምታውቅ አትመስልም። የመከራ ዓይነቶች እንደ ጉድ ተፈራርቀውባታል - ተራ በተራ።  ሆኖም እጅ አልሰጠችም። አልተሸነፈችም፡፡
 ባለፉት 27 ዓመታት በኢህአዴግ መራሹ መንግስት ታልሞና ታቅዶ በመላው አገሪቱ ሲዘራ የከረመው የዘረኝነት ፖለቲካ ለፍሬ በቅቷል፡፡ አዎ፤ ብዙ ሺ ዜጎች በማንነታቸው በጅምላ ተጨፍጭፈዋል፡፡ አያሌ ሺዎችም ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። ሃብትና ንብረታቸውን አጥተውም እርዳታ ጠባቂ ለመሆን በቅተዋል - ዕድሜ ለዘረኞች!  አሁንም ድረስ ዘር - ተኮር ጥቃቱ ቀጥሏል። አሁንም ድረስ  ብዙዎች የሞትና መፈናቀል አደጋ ተጋርጦባቸዋል።
የዛሬ 4 ዓመት ግድም በግፉና በጨካኝ አገዛዙ ሳቢያ በህዝብ አመጽ ከሥልጣኑ ተገፍትሮ መቀሌ የሸሸገው ጽንፈኛው የህወኃት ቡድን፣ ኢትዮጵያን አፈራርሳለሁ ብሎ የቆሰቀሰው ደም አፋሳሽ ጦርነት እነሆ 2 ዓመቱን እየደፈነ ነው፡፡ አማፂው ቡድን በእነዚህ ዓመታት በአማራና አፋር ክልሎች በሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ላይ አሰቃቂ ግፍና በደል ፈጽሟል። ንጹሃንን በጅምላ ጨፍጭፏል፡፡ ሴቶችን በቡድን አስገድዶ ደፍሯል - ከህጻናት እስከ አዛውንት እናት፡፡  በርካታ ት/ቤቶችንና የጤና ተቋማትን አውድሟል።  (በነገራችን ላይ ጦርነቱም የተለኮሰው በዘረኝነት እሳት ነው!)
የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ ታዲያ መጀመሪያ ላይ የለውጡ መንግስት ሁነኛ ወዳጅና አጋር መስለው የታዩት ምዕራባውያን፣ ከአሸባሪው ቡድን ጋር በመወገን ማንነታቸውን ፍንትው አድርገው አሳይተዋል፡፡ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሥልጣን ከያዘ ህጋዊ መንግስት ይልቅ አሸባሪ ጦረኛ ቡድንን እንደሚመርጡ አረጋግጠዋል፡፡ በነቢብም በገቢርም። ለዚህ ነው በኢትዮጵያ ላይ ዓለማቀፍ  ዲፕሎማሲያዊ ጫናው በእጅጉ በዝቶ የታየው፡፡ ባለፈው ዓመት የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ም/ቤት፣በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ብቻ ለ13 ጊዜ ያህል መሰብሰቡ ታሪክ ሆኖ ተመዝግቧል - አሳዛኝ ታሪክ!
የአማፂው ቡድን አፍቃሪ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት፣ “በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ሳይጣል ዓመቱ ማለፉ ያስቆጨኛል” ሲሉ መናገራቸውም አይዘነጋም። (ሌላ አግራሞት!)
ከትግራይ ጦርነት ጋር ተያይዞ በንፁሃን ላይ ተፈጽሟል ባሉት ግድያና  የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግስት ላይ የተለያዩ ማእቀቦችን ሲጥሉ፤አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ግን እንዳላየ አልፈውታል፡፡ (እንደ አደራ ልጃቸው!)
በሌላ በኩል፤በውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ በዋጋ ግሽበት፣ በንግድ ስርዓት መዛባት፣ በዓለማቀፍ የነዳጅ ዋጋ መናር፣ በኢኮኖሚ አሻጥር፣ በዝርፊያና በሙስና ወዘተ---ሳቢያ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች ገጥመውታል።
ከሰሜኑ ደም አፋሳሽ ጦርነት ባሻገር ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ጨምሮ የተለያዩ ተፈጥሮአዊ አደጋዎችንም ተጋፍጣለች- ድርቅ፣ አንበጣና ጎርፍ ተጠቃሽ ናቸው።
በዚህ ሁሉ ምስቅልቅልና አለመረጋጋት ውስጥ ታዲያ ኢትዮጵያ አስደማሚ ስኬቶችን አስመዝግባለች ጨርሶ የማይታሰቡ። በዋነኝነት የሚጠቀሰው ደግሞ ከግብፅና ሱዳን ጋር ውዝግብ ውስጥ ያስገባን የታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መከናወንና ሃይል ማመንጨት መጀመሩ ነው። በቀጣዩ ዓመት ለውጭ ገበያ መቅረብ ይጀምራል የተባለው የስንዴ ምርት ሌላው የኢትዮጵያ ስኬት መገለጫ ነው። ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያን የጎበኙት አዲሱ የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶም፣ከኢትዮጵያ ስንዴ ለመግዛት ስምምነት መፈጸማቸው ተረጋግጧል። የኢትዮጵያ የስንዴ ምርት ስኬት በአፍሪካ ልማት ባንክ ጭምር አድናቆት ተችሮታል። ኢትዮጵያ በግሪን ሌጋሲም ባለፉት ዓመታት ባከናወነቻቸው ሥራዎች ፈር ቀዳጅ ሆናለች። ዓለማቀፍ ዕውቅናም  አግኝታለች።
ሸገርን  በማስዋብ ፕሮጀክት አንድም ፓርክ ያልነበራት የአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ፤ ሁለትና ሦስት ደረጃቸውን የጠበቁ ምርጥ ፓርኮችን ማግኘት ችላለች። በአገሪቱ የመጀመሪያው ግዙፍና ዘመናዊ የተባለው የአብርሆት ቤተ-መጻህፍት ተጠናቆ አገልግሎት ከጀመረም ከራርሟል። ባለፈው ሳምንት ደግሞ  ብዙዎችን ያስደመመው የሳይንስ ሙዚየም በይፋ ተመርቋል።
የዛሬ አራት ዓመት ግድም በህዝብ አመጽና በውስጥ የፓርቲ ትግል ከራሱ ከኢህአዴግ ወጥተው የለውጡን መንግስት መምራት የጀመሩት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ አስደማሚ ፕሮጀክቶችን ባልተለመደ ፍጥነት በማጠናቀቅ ኢትዮጵያውያንን በተደጋጋሚ አስደምመዋል፡፡ “የሰው ህይወት  እየተቀጠፈ አበባና ችግኝ መትከል ምን የሚሉት ሙያ ነው?” በሚል ለሚነቅፉና ለሚያጥላሉ ወገኖች የጠ/ሚኒስትሩ መልስ አጭር ነው፡፡ “ለመጪው ትውልድ የበለጸገች-በምግብ ራሷን የቻለች - ነጻነቷና ሉአላዊነቷ የተረጋገጠ አገር ማስረከብ አለብን።” ይላሉ፤በተደጋጋሚ፡፡
´አቧራን ሳይሆን አሻራን እናኑር´ በሚል ንግግራቸው የሚታወቁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ከጊዜ ጋር እሽቅድምድም የያዙ ነው የሚመስለው። ከዕቅዳቸውና ፕሮጀክቶቻቸው ብዛትና ዓይነት አንጻር ተኝተው የሚያድሩም አይመስሉም የሚሏቸው ብዙዎች ናቸው። (በየትኛው ጊዜያቸው?!)
የጠ/ሚኒስትሩን አዳዲስ ፕሮጀክቶችና የልማት ሥራዎች በአድናቆት የሚከታተሉ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን፤ በእንዲህ ያለ ውጥረትና ጦርነት ውስጥ ይሄ ሁሉ ልማትና ውበት ተዓምር እንደሆነባቸው ይናገራሉ። ኢህአዴግ ነፍሴ በ27 ዓመት ያልሰራውን የጠ/ሚኒስትሩ መንግስት በ4 ዓመት ውስጥ ማከናወኑንም በድፍረት ይናገራሉ።
የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት ማስከበርና ደህንነታቸውን ማረጋገጥ የመንግስት ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን መንግስት ራሱን ጨምሮ ብዙዎች ያምናሉ - በህገ መንግስቱም ሰፍሮ ይገኛል። በተመሳሳይ መልኩ ልማቱን መከወን፣ የአገር ሉአላዊነትን ማስከበር፣ ህዝብ ከልመና ስንዴ ወጥቶ በምግብ ራሱን እንዲችል ማድረግ፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ፣ የንግድ ስርዓቱን ማረቅና የዋጋ ግሽበቱን ማረጋጋት፣ የሥራ ዕድሎች መፍጠርን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ተግባራትም ከመንግስት ይጠበቃሉ። በዚህም የተነሳ የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግስት፣ ራሱን ከልማት ሥራዎች ሙሉ በሙሉ አቅቦ እንደ ደርግ  መንግስት “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር!” የሚል መፈክር ያቀነቅናል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡
መንግስት ጦርነቱንም ልማቱንም ጎን ለጎን ማስኬድ አለበት ይላሉ - የፖለቲካ ተንታኞች። ሩሲያና ዩክሬንም የሚዋጉት እኮ ስንዴና ነዳጃቸውን በጎን  እየሸጡ ነው- ዶላራቸውን እያጋበሱ።
አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንጋፋ የኢኮኖሚ ባለሙያ፣ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ  ነው ይላሉ። ያለፉት ሁለት ዓመታትን ማለታቸው ነው። የኢትዮጵያ መንግስት የኮቪድ ወረርሽኝ እስኪገታ ድረስ እንቅስቃሴዎችን ሁሉ ገድቦና ቆልፎ፣ ህዝቡን ቤቱ እንዲቀመጥ ቢያስገድድ ኖሮ፣ ማህበራዊ ቀውስ መከሰቱ አይቀርም ነበር። ምናልባት በቫይረሱ ከሚሞተው ሰው የበለጠ በረሃብ የሚሞተው ሊልቅም እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ኮሮናን ያለብዙ ጥፋትና ቀውስ የተወጣነው አስፈላጊውን የመከላከል ጥንቃቄ እያደረግን፣ ስራችንን በማከናወናችን ነው ያሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፤ የጦርነቱም ሁኔታ ከዚህ ብዙ አይለይም፤ እየተዋጋን ማረስ - ማልማት፣ መገንባት፣ መነገድና ማምረት ይኖርብናል ብለዋል፤ የማታ ማታ ለመዋጋትም ጦርነትን የሚሸከም ጠንካራ ኢኮኖሚ እንደሚያስፈልግ በመግለፅ። (እውነት አላቸው!) እያንዳንዱ ጥይት እኮ ዶላር ማለት ነው - ያውም በጠፋ የውጭ ምንዛሬ።
በነገራችን ላይ በየክልሉ የሚገኙ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች (ክልላዊ መንግስታትን ጨምሮ!) ለሰራዊቱ ሰንጋና ሙክት የሚልኩት ከሥራቸው ባለመስተጓጎላቸው ነው። ከዚህ አንጻር ወደድንም ጠላንም፤ “ግሪን ሌጋሲ” እና ጦርነቱ ጎን ለጎን መካሄድ አለባቸው! እያመረትን ለሃገራችን ሉአላዊነት መዋጋት ማለት ነው፡፡
አንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ በሰጡት አስተያየት፤በዚህ ሁሉ የዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና ጦርነት ውስጥ መንፈስ የሚያነቃቁና ተስፋን የሚፈነጥቁ ውብና አማላይ የልማት ፕሮጀክቶችን (የሳይንስ ሙዚየሙንና ፓርኮችን ይጠቅሳሉ!) በመዲናችን ማየት ባንችል ኖሮ፣ ህይወታችን ፍጹም የጨፈገገ ይሆን ነበር ብለዋል፡፡
በመጨረሻም አንድ ለደህንነታቸው ሲሉ ስሜ አይጠቀስ ያሉ አንጋፋ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር  እንደተናገሩት፤ ባለፉት ዓመታት በጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚመራው የለውጥ መንግስት፣ በአስደማሚ ፕሮጀክቶችና የልማት ሥራዎች ሲጠመድ፤ መቀሌ የመሸገው አማፂው ቡድን ደግሞ ምሽግ በመቆፈርና ጥላቻ  በማራገብ ተጠምዶ እንደነበር ያስታውሳሉ- የመንግስትንና የአማፂውን ቡድን ልዩነት በአጭሩ ሲገልፁ!!
በአዲሱ ዓመት መንግስት  የዜጎችን ህይወት ከሞት ከአካል ጉዳትና መፈናቀል እየታደገ፣ ልማትና ዕድገቱን አፋጥኖ የሚቀጥልበት ይሆን ዘንድ እንመኛለን፡፡ ፈጣሪም ያግዘናል ብለን እናምናለን፡፡
 ሰላም ለኢትዮጵያና ለመላው ዓለም!

Read 747 times