Tuesday, 18 October 2022 06:05

የዓለምን ስፖርት ከ60 ዓመታት በላይ ያገለገሉት ጋሽ ፍቅሩ ኪዳኔ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 በሳምንቱ አጋማሽ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ይፋ ባደረገው መግለጫ በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ በፈርቀዳጅና የላቀ አስተዋፅኦቸው የሚታወቁት ጋሽ ፍቅሩ ኪዳኔ በ87 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን አስታውቋል፡፡ የስፖርት ማህበሩ በመግለጫው እንደጠቀሰው ጋሽ ፍቅሩ፤  የቅዱስ ጊዮርጊስ የተመዘገቡ የልብ ደጋፊና ባለታሪክ፣ በስፖርት ጋዜጠኝነት፣ በአለም አቀፍ የስፖርት ተቋማት በሀላፊነትና በከፍተኛ ሞያተኛነት በማገልገል ከፍተኛ እውቅናን የተጎናፀፉ፤   ታላላቅ ሽልማቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀዳጁና የፒያሳ ልጅ መፅሀፍ ደራሲ ነበሩ፡፡  ማህበሩ በነገው ዕለት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ለመታሰቢያ የአበባ ማስቀመጥና የሻማ ማብራት ስነስርዓት ያከናውናል፡፡
ጋሽ ፍቅሩ ኪዳኔ በ1935 አዲስ አበባ ውስጥ የተወለዱ ሲሆን አባታቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊ በመሆናቸውና የክለቡን ተጨዋቾችን በትራንስፖርት ያመላልሱ ስለነበር ከስፖርቱ ጋር ለመተዋወቅ በቅተዋል። ከዚህ በኋላ በስፖርት ማጎልመሻ መምህርነት ለመስራት በቅተዋል፡፡   በ1957 ላይ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ለመሆን በቅተዋል። አግር ኳስ በኮሜንታተርነት ከተለያዩ ስታዲየሞች ማሰራጨት በመጀመር ፈርቀዳጅ ሲሆኑ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ላይም  የስፖርት ፕሮግራሞችንም በመቆርቆርም ሰርተዋል። በኢትዮጵያ መንግስት ይታተሙ በነበሩ ሁሉም ጋዜጦች ላይ ስፖርትን የሚመለከቱ መጣጥፎችን በመፃፍና በማሳተምም ፈሩን ቀድደዋል፡፡ በስፖርት ዙሪያ ጽሑፎችን  የሚቀርቡባቸውን አምዶች እንዲመሰርቱ እና እንዲያሳትሙ የጋዜጣ አዘጋጆችን በመገፋፋትም ስኬታማ ሆነዋል፡፡
ጋሽ ፍቅሩ ኪዳኔ የመጀመርያ መፅሃፋቸውን የፃፉት በ1960 ኦሎምፒክ  ላይ ነበር፡፡ ከዚያም ከሚሰሩበት የማስታወቂያ ሚኒስቴር በመልቀቅ በተባበሩት መንግስታት ተልዕኮ  ስር ወደ ኮንጎ ተልከው ሰርተዋል፡፡ ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱ በኋላ በኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽንን በተለያዩ የሃላፊነት ድርሻዎች ሰርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ዋና ፀሃፊ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ፀሃፊ በመሆንም አገልግለዋል። በቴኒስ እና በእግር ኳስ ፌደሬሽኖችም ለመስራት በቅተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በ1968 እና 1976 እኤአ ላይ ባዘጋጀቻቸው የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ በሙያቸው ከፍተኛ እገዛ አድርገዋል፡፡  በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የኢትዮጵያ እግር ኳስና የአህጉሪቱ የስፖርት እንቅቃሴ ከፍተኛ ልዑክ ሆነው  ብዙ አገራትን አማክረዋል፡፡  
ጋሽ  ፍቅሩ ኪዳኔ በኢትዮጵያ ስፖርት ሚዲያ ፈር ቀዳጅ፣ ለኢትዮጵያ እና አፍሪካ ስፖርት እድገት ባበረከቱት አስተዋፅኦ እንደምሰሶ የሚታዩ ታላቅ የስፖርት ሰው ነበሩ፡፡ በመምህርነት፣ በጋዜጠኝነት፣ በአዘጋጅነት፣ በአማካሪነት፣ በአማካሪነት፣ በዳይሬክተርነት፣ በጸሐፊነት፣ በሊቀመንበርነት እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በፕሬዚዳንትነትየዓለምን ስፖርት ከ60 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ ለዓለም ስፖርት ባበረከቱት አስተዋፅኦም ከተለያዩ አካዳሚዎች፣ ተቋማት እና ዩኒቨርሲቲዎች ከአስር በላይ ሜዳሊያዎችን እና ሽልማቶችን አግኝተዋል። በስራ ዘመናቸው ላይ ከፊፋ፤ ከኦሎምፒክ እና ከካፍ ፕሬዝዳንቶች ጋር የቀረበ ግንኙነት ነበራቸው፡፡ ከኔልሰን ማንዴላ፣ ከኮፊ አናን፣ ፊደል ካስትሮ እና ታላላቅ የዓለማችን ግለሰቦች ጋር ወዳጅነት ነበራቸው፡፡Read 103 times