Tuesday, 18 October 2022 06:09

ጨርሶ ከመቅረት..“አይ ፐሲዜ”

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(0 votes)

 “--ጋዜጣዋ በአሰፋ ተጠንስሳ መነበብ ከጀመረች በመጪው ታሕሳስ ወር 23 ዓመት ይሞላታል፡፡ የጋዜጣዋ መስራች አሰፋ ጎሳዬ (በህይወት ባይኖርም) ስለእርሱ የሰፈረ ማስታወሻ እስካሁን በንባቤ አላጋጠመኝም፡፡ አሰፋን በመሰረታት ጋዜጣ ላይ እናውቀዋለን የሚሉ ዘመነኞቹ አልፎ አልፎ ሲዘክሩት እንጂ የኔ ትውልድ ታሪኩን በዝርዝር አያውቅም፡፡--”
        
       በራሱ ስልት የሚቀርብ አቻና ተወዳዳሪ የሌለው አሪፍ ወገኛ ነው፡፡ የማያልቅበት የወግ ባለፀጋ፡፡ ሲያወጋ የራሱ የሆነ ፍሰትና ዜማ አለው፡፡ አወራረዱና ፅህፈቱ ውብና ተነባቢ ነው፡፡ በጨዋታ መልክ እያነሳ በወግ ስልት ሲዘግብ ከልቡ ነው፡፡ ጨዋታውን በእውቀት ሞሽሮ በአስገምጋሚ ድምፁ ከእነ ለዛው ሲያፈሰው በል ያሰኛል፡፡ ከኑሮ ዚቅ ከንባብ ጥልቅ የሚቀዳቸው ታሪኮቹ ባደመጥናቸው ቁጥር፣ ዘወትር የማይለመዱና እንግዳ ናቸው። ወሬው ሁሉ ቢጻፍ ጥዑም ወግ ይወጣዋል፡፡ ያምርለታል፣ ይጣፍጥለታል፡፡
አንብቤ ከተማርኩባቸው አምስት መጽሐፍቶቹ ይልቅ ውስጤ የቀሩ ወጎቹ አያሌ ናቸው፡፡ (ከ97.1 አዲስ ዜማ እስከ ጄ.ቲቪ) የቁመቱን እንጃ’ንጂ ፍቅረአዲስ ነቅዓጥበብ አንድ ቆየት ያለ ዘፈኗ ውስጥ የተቀኘችለት ለዘኔ ይመስለኛል፡፡ “ወለላ ነው ወግህ…ጥንቅሽ ነው ቁመትህ፡፡” ወጎቹ ታትመው ማየት ከሚያጓጓቸው ተደራሲያን መሀል አንዱ ነበርኩ።
እንደ’ኔ እንደኔ ከግለ-ታሪክ ላፍታ ሰክኖ ከወግ ሙላቶቹ መሰነድ ላይ ቢተጋ በመጻህፍት ሊያጥለቀልቀን ይችል እንደነበር እምነቴ ሙሉ ነው፡፡ እድሜውን ከፈጀበት ግለታሪክ በላይ ወግ ይዋጣለታል፡፡ ቀድሞ በራሱ ላይ ነቅቶ መልህቁን ቢያስተካክል፣ በወግ መርከቡ እሩቅ እሚያስጉዘን ሁነኛ ካፒቴን በወጣው ነበር፡፡ ግን አላደረገውም፣ አልተገበረውም፡፡ ይሁን እንጂ ሟቹ ሀያሲ አብደላ እዝራ፣ ይህን ተሰጥኦውን ቀድሞ አይቶለት ኖሮ፣ ለህልፈት ከመብቃቱ በፊት እንዲህ ሲል ጠቁሞት ነበር፤ “…ነፍሱን ይማረውና ወዳጄ አብደላ እዝራ በኤፍኤም 97.1 በአዲስ ዜማ አወጋቸው የነበሩትን ወጎች አድምጧቸው ኖሮ፣ የመጨረሻችን በሆነችው አንዷ እለት ብሄራዊ ትያትር መናፈሻ ውስጥ ተገናኝተን ይህንን የሬዲዮ ወጌን እንዳስጠርዘው አሳሰበኝ…” (ገጽ6) ዘነበ ግን በወቅቱ እሞክራለሁ ይበል እንጂ ለዚህ ጥቆማ አፀፋዊ ምላሹ ቸልታ ነበር፡፡ አልወጠነውም- አላውጠነጠነውም፡፡
ይሁንና ቢዘገይም ጨርሶ ከመቅረት አረፋፍዶም መድረስ ይበጃልና በስተመጨረሻ “አይ ፐሲዜን” ለገፀ ንባብ ማብቃቱ ቢያስመሰግነው እንጂ አያስነቅፈውም፡፡ ለወትሮ ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም እንዲሉ፣ የዘነበን ወግ ከአንድ ሚዲያ ሳንሰማ አሮጌው አመት አይጠናቀቅም ነበር፡፡ እነሆ ለአዲስ አመት ማዝገሚያ እንዲሆነን ጥሩ ስንቅ ቋጥሮልናል፡፡ መጽሀፋን ከመግለጣችን የወጎቹ ጠረን እንደ አሪቲው፣ ሉባንጃው፣ እጣኑ ገና ስንገባ ያውደናል፡፡
እስኪ አብረን እንዝለቅ፡፡
ዘነበ ወላ የስብሃት ለአብ መልካም ደቀ መዝሙርና ጥሩ ባለሟል እንደመሆኑ የወግ እርፍናው ማማሩ ከዚህ የመነጨ እንደሆነ መገመት አይገድም፡፡ ከዚህ ባሻገር ብርቱ የስነ-ጽሁፍ ሰው ስለሆነ እንደ ብቁ መካኒክ ከአናቱ እስከ ሰበከቱ በወጎቹ የማይዳስሰው ርዕስ ጉዳይ የለም፡፡ ወግ ጠራቂ አይገልፀውም…የወግ ሊቅ አይደርሰውም፡፡ ይህም ያለውን ተፈጥሯዊ መሰጠት በበቂ አመላካች ነው፡፡ ይህን ገለጻዬን (ለሁለት አስርታት) በላይ ወጎቹን ያደመጡ ሁሉ የሚጋሩኝ ይመስለኛል፡፡ ወደ ጽሁፍ ቀይሮ ለገፀ-ንባብ ሲያበቃ ይዘትና ቅርጽ በመስጠት ይበልጥ ማለፊያ የወግ ቁመና እንዲኖራቸው የበኩሉን የአርትኦት አሻራ ማኖሩን ከንባባችን የምንረዳው ሀቅ ነው፡፡
የወግ እጥረት ለሚፈራረቅበት ስነ-ጽሁፋችን የዘነበ አይነት ለዛ ያላቸው የጨዋታ ትርክቶች ወደ መጽሐፍ ተቀይረው ቢታተሙ ይህን ክፍተት ሊታደጉ እንደሚችሉ አያጠያይቅም፡፡
እንደ ዘነበ ሁሉ በሀገራችን ታሪክ ውስጥ ስማቸው ከሚጠቀስ ምሁራን እጓለ ገብረ ዮሃንስ የረጅም አመታት ከፍታ ያላቸው ሀገር በቀል ፍልስፍናዊ የሬዲዮ ንግግሮቻቸው ከተደመጡ ከአመታት በኃላ ተሰብስበው “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” በሚል ርዕስ ተሰንደው የህትመት ብርሃን እንዳዩላቸው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ዛሬ-ዛሬ  ይህንኑ ተንተርሰው የወግ አፃፃፍን ማዕከል ያደረጉ ሸጋ ስራዎች አልፎ-አልፎም ቢሆን ብቅ ብለው መታየታቸው አልቀረም፡፡ ለአብነት የቅርቦቹን ብንጠቅስ ፍሬዘር የተባለ ፀሃፊ “አለቃና ምንዝር” እንዲሁም ቴዎድሮስ መዝገቡ “ንስር እና ምስር” የተሰኙ የወግ ስብስቦቻቸውን ያስነበቡን ባሳለፍነው አመት ነበር፡፡
የወግ አፃፃፍ ዘይቤ አንድ የስነ- ጽሁፍ ዘውግ እንደመሆኑ መጠን አዲስ አቅጣጫ ይዞ ራሱን ችሎ በሁለት እግሮቹ መራመድ የጀመረው በመስፍን ሀብተማርያም የጫወታ ስብስብ ስራዎች “የቡና ቤት ስዕሎች”፣ በደበበ ሰይፉ ዘይቤውን ወግ በሚል ስያሜ ቀንብቦ ብይን በመስጠት እንደሆነ ለዘመኑ ቅርበት የነበራቸው የሥነ-ጽሁፍ አጥኚዎች ያስረዳሉ፡፡ ወግ በራሱ ምሉዕና ሁሉን አካታች ነው፡፡ ይህ ቀረሽ የማይባል! የዘነበ ወላ አይነት ብዙ ያነበበና የመረመረ ባለልምድ ሲያገኘው ደግሞ ሚናውን የላቀ ያደርገዋል፡፡
በወግ ውስጥ አይነተኛ የስነ-ጽሑፍ ባህሪያት በጉልህ ይታያሉ፡፡ ከነዚህ ባህሪያት መካከል ትዝታዊ.ነት (ኢምፕሬሽኒዝም)፣ ሥነ ውበታዊነት (ኢስቴቲሲዝም)፣ ተምሳሌታዊነት (ሲምቦሊዝም) የመሳሰሉት ይገኙባቸዋል፡፡ የዘነበ ስብስብ እዚህ ከዘረዘርኳቸዉ አላባውያን በላይ አካተው እናገኛቸዋለን፡፡ የአዲስ አድማስ መስራች አሰፋ ጎሳዬን ከትውስታው ማህደር መዞ በዘከረበት “ድንቅ ሰው” ትዝታዊነትን ፣ አልማዜ ስለተባለች የጋሞ ሴት ተርኮ በዚያው የቻይና ጉብኝቱን ያወሳበት “አይፐሲዜ” ውስጥ  ሥነ-ውበታዊነትን ፣ አምባሳደርና ጋዜጠኛ አሀዱ ሳቡሬን “አሀዱ ሳቡሬ አጠገበን ወሬ”፣ በፍቃዱ ሞረዳን “በብዕር ተፋላሚው ጋዜጠኛ” ስንዱ አበበን “ሳይለምኑኝ” ተምሳሌታዊነትን፣ ስለ ጋሽ ማሞ ውድነህ ያጠናቀረው ዘገባ “50 መጻህፍትን በ 44 አመታት” እንዲሁም አርበኛ እና ዲፕሎማት ክቡር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁን በግንባር ያናገረበት “ህያው ደራሲ” ተምሳሌታዊነትን… መመልከት እንችላለን፡፡
የዘነበ አይ ፐሲዜ…. ከመርከበኝነት ጠንካራ የህይወት ልምምዱና የኑሮ ገጠመኙ ባሻገር ጉድ የሚያሰኙ ለጀብድ የቀረቡ ወሳኝ (ደግመን የማናገኛቸው) ሰነዶችን ትቶልናል፡፡ ከሞላ ጎደል ወጎቹን የፃፈበት አቅምና ጉልበት የደራሲውን የንባብ ክምችት በጉልህ አንፀባርቆታል ማለት ይቻላል፡፡ ለወትሮ በማስታወስ ችሎታውም፤ በማስታወሻ አያያዙም የማይታማው ዘነበ፤ ለዚህም ወግ ጠንካራ መሠረት ሆኖለታል፡፡ ወጎቹ ዘርፈ ብዙ ችግር ያለበትን ርዕሰ ጉዳይ በኩርማን ገጠመኙ ለውሶ መፍትሄውን በመጠቆም፤ ቁም ነገር በማስጨበጥ የተዋጣለት ደራሲና ወገኛ ያደርገዋል፡፡ በቃል ያለ እንዳይረሳ (በሚድያ) ይተርክልናል፤ በጽሑፍ ያስቀረውን በወግ መልኩ ያወርሰናል፡፡ በኔ ንባብ ከዘነበ የወግ ስብስቦቹ መካከል በሙላት ሊባል በሚችል ሁኔታ ክፍተታችንን ሞልቶልናል ብዬ አፌን ሞልቼ በተለየ የምጠቅሰው “የአሰፋ ጎሳዬና የሀዲስ አለማየሁ” ከህልፈታቸው ጥቂት ቀናት በፊት የተዉልን (እርሱ ያስቀረልን) ቁም ነገር አዘል የመጨረሻ ቃላቸው ነው፡፡ ሀዲስ ከፃፉልን ልብወለዶች ውጪ እርሳቸውን በተመለከተ የተጻፉ ጽሁፎች እምብዛም በማናገኝበት ሁኔታ “ትዝታ”፣ የአርበኝነት ዘመናቸውን ነው በአመዛኙ የምትዳስሰው፡፡ ወገኛው መኖሪያ ቤታቸው በግንባር ሄዶ ያደረገው ልዩ ቃለ ምልልስ አጥጋቢ ነው ተብሎ ሊደነቅ የሚገባው ለዚህ  ነው፡፡ ሌላኛው የተደመምኩበት የአሰፋ ጎሳዬ ነው፡፡
የህልሙና የውጥኑ ፍሬ ናት፡፡ ሳናውቀው የምንወደው፣ ስናውቀው የምንሳሳለት፡፡ ምነው በኖረልን! ብለን የምንቆጭለት የሀገር ዋርካ ነው፡፡ መንፈሱን ከጋዜጣዋ ተጋርተን ኖረናል። ህልሙ በጋዜጣው በኩል ውስጣችን ሰርፆ ጥበብን - እውቀትን ሲዘራብን እዚህ ደርሷል። የሀገራችንን የህትመት ውጤቶች ከጎረቤት አገር ኬንያ ጋር እያወዳደረ ይቆጫል። “…ተመልከት እስኪ በሀገራችን የመንግስት፤ የግል፤ የሀይማኖት ልሳናት፤ የተለያዩ ድርጅቶች ህትመት ተሰባስበው ቢቆጠሩ እኮ 250 ሺ ኮፒ አይሞሉም፡፡ ኬንያ ሄደህ “ኔሽን” የተባለ ጋዜጣቸውን ብትመለከት በሳምንት 500 ሺ ኮፒ ለህትመት ይበቃል፡፡ የኛ አያሳዝንም …” (ገጽ 204) በዚህ ቁጭቱ የቆየ-የሰነበተ ጋዜጣ የማዘጋጀት ህልም ነበረው፡፡ በርግጥ በድንቅ ጥረቱ ተነባቢ ጋዜጣ ፈጥሯል፡፡ ለዚህ እኔም- ሚሊዮኖችም ምስክር ናቸው፡፡ እልፎች የታነፁባት-የተማሩባት ለመሆን በቅታለች፡፡ ለሁለት አስርታት አያሌ ፈተናዎችን ተቋቁማ ዛሬም ህትመት ላይ አለች፡፡ የጥበብ አይናችንን የገለጥንባት አንጋፋ ጋዜጣ ነች - አዲስ አድማስ። ጋዜጣዋ በአሰፋ ተጠንስሳ መነበብ ከጀመረች በመጪው ታሕሳስ ወር 23 ዓመት ይሞላታል። የጋዜጣዋ መስራች አሰፋ ጎሳዬ (በህይወት ባይኖርም) ስለእርሱ የሰፈረ ማስታወሻ እስካሁን በንባቤ አላጋጠመኝም፡፡ አሰፋን በመሰረታት ጋዜጣ ላይ እናውቀዋለን የሚሉ ዘመነኞቹ አልፎ አልፎ ሲዘክሩት እንጂ የኔ ትውልድ ታሪኩን በዝርዝር አያውቅም። አሴ አድማስን ገና በማለዳው ሲያበጃጃት ጀምሮ አብረውት ብዙ ትዝታዎችን፤ ምሽቶችን የተጋሩት ጓደኞቹ… ዘመነኞቹ  ነበሩ፡፡ ዘነበ ከነዚህ አንዱ ነው፡፡ ይሁንና ዘነበ ወዳጁን የሚያሳየን ከሁለንተናውና ከብዙ አቅጣጫ ነው፡፡ በቸርነቱ፤ በፈጣን አንባቢነቱ፤ በድንቅ አርታኢነቱና በሳቅ ምንጭነቱም ጭምር፡፡ ገና ከጅምሩ ጽሁፍ ከማውጣትና ከማሰባሰቡም በላይ የሰውየውን ራዕይና የላቀ ሰብዕና በቅርበት ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ በአንክሮ አይቶታል፤ በማስተዋል ውስጥ ሆኖ ልብ ብሎ ተመልክቶታል፡፡ ሊነገርለት ይገባል ያለውን ታሪክ በመጽሐፉ በሚገባ ፅፎለታል፡፡ በርግጥ አርቆ አሳቢው አሴ (እስካሁን በህይወት ቢቆይልን) በነበረው የላቀ የአመራር ብቃት እንኳን አንድ ጋዜጣ ሀገር የመምራት ታላቅ ሰብእና እንደነበረው ዘነበ ካሰፈረው ከታሪኩ ቁንፅል ማስታወሻ እንረዳለን።
“…ሰርቶ ያሰራል፤ ፀሐፍትን ያተጋል። በማንኛውም ሁኔታ ሲቸገሩ ወይም ጊዜያዊ ችግር ሲደርስባቸው፣ ኑሮ አላራምድ ስትላቸው ጎናቸውን ይዳብሳል፡፡ አብዝቶ ለህይወታቸው ይሳሳል፡፡ ኪሱ እንደየፍላጎታቸው ያስተናግዳቸዋል፡፡ ለቀጠራቸው ጋዜጠኞችና ፀሐፊዎች ቀለብ አሳምሮ ይቆርጥላቸዋል፡፡ የተበደሩትን ገንዘብ ለመክፈል አሰፋ ቢሮ ጎራ ሲሉ ይሄኔ አሴ ወይ ሁሉንም አልያ ግማሹን ይምራቸዋል፡፡ በተለያዩ ሰበባት የእዳ ምህረት ይወርዳል፡፡ አሰፋ “ሰው ኑሮው ከደላው ከልቡ ይሰራል፡፡ ከልቡ ከሠራ ከቋት ጠብ የሚል ተግባር ያከናውናል፡፡ በዚህም አንባቢው እርባና ያለው ነገር ከጋዜጣዋ ገብይቶ በየፊናው አገር ለመገንባት የበኩሉን ጥረት ያደርጋል” … የሚል እምነት እንደነበረው ዘነበ ከትውስታው ያወጋውን ከመጽሐፋ እናነባለን፡፡
ለአብነት ብንወስድ አሰፋ ህልሙን እንዴት ተግብሮ አድማስን እውን እንዳደረጋት እንዲህ ሲል እንደሚከተለው አስቀምጧል፡፡. “. ጋዜጣዋ ለህትመት ከመብቃቷ በፊት ምናልባት ከአንድ ዓመት በላይ አሰፋ ስንቅ የሚሆናትን የጽሁፍ ማሰባሰብ ስራ አከናውኖ ነበር:: ከዚህም ባሻገር አንድ ሰው አሪፍ ወሬ ካወራለት “በል ይህንን ቁጭ በልና ፃፍ… ይህንን ያህል ብር እከፍላለሁ” …ይላል፡፡ የገንዘቡ መጠን አሁን ተዘነጋኝ፤ ሁለትም ሶስትም መቶ ብር ሊሆን ይችላል። ሀሳብ ገንዘብ እንደሚያመጣ የገባው ግለሰብ ሳውቅ፣ አሰፋ ጎሳዬ የመጀመሪያዬ ነው፡፡” (ገፅ 102)
ዘነበ ወላ ወጋ ቂርቆስ ተወልዶ ያደገ ጋሞ ጎፋ ነው፡፡ ባህሉንና ቋንቋውን ያውቃል፣ ስርአቱን ይጠብቃል፡፡ ከዘር ሀረጉ የምትመዘዘውን የአልማዜን ታሪክ በተዋበ የትረካ ጥበብ የዘገበበት ልቀት ጉድ ያሰኛል፡፡ ከእንግዲህ ወግ በወጉ ጣፍጦ ሲቀርብ እንዴት ያለ እንደሆነ በ“አይፐሲዜ” አይተናል፡፡ በእውነቱ ለወግ አፃፃፍ አዲስ አቅጣጫና መንገድ ነው፡፡ ወግን በምልአትና በተጨባጭ የሚያሳይ ዝነኛ ሥራ እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ በመለጠቅ አከታትሎ አንድ ሁለት ቢደግመን ወጎቹ ለታሪክ ማጣቀሻነት ግልጋሎት መዋላቸው ላይ ጥያቄ የለኝም፡፡ እስካሁን ከፃፈልን ግለ ታሪኮችና ወደፊት ለመፃፍ ስለሚያስበው እንደ “መልሕቅ” አይነት በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ልብወለድ በበለጠ ዛሬ በቀደደልን የወግ ገበታ ፈለግ ከቀጠለ መጪው ጊዜ ዘነበን የምንፈርጀውና የምንሰፍረው ከዚህ አንፃር ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ደራሲው በዚህ ዘርፍ ክህሎቱና አቅሙ እንዳለው እንደሚገነዘብ በማመን፣ ከዚህ በኋላ የበኩሉን አሻራ እንዲያኖር ስጠቁም ከታላቅ አክብሮት ጋር ነው፡፡ እኔም ቅኝቴን የምቋጨው የርሱ የዘመናት የወጎቹ መዝጊያ በሆነችው፣ ከአፉም - ከመጽሐፉም በማትለይ መርህ ይሆናል፡፡ ነጮቹ፤
“May peace prevail on earth” ይሏታል:: ሠላም በምድራችን ላይ ይስፈን!!!Read 271 times