Tuesday, 18 October 2022 06:28

“አንድ ልጅ አዝማሪ...” (የመጽሐፍ ዳሰሳ)

Written by  በድረስ ጋሹ
Rate this item
(3 votes)

 በገጣሚው ውብ ቃል  የተሸመነ ግጥም አንባቢውን ወደ ምናባዊ ዓለም (“ከፍቅር አስፈንግጦ ሳይሆን፤ በፍቅር አስፈንግጦ ያጓጉዛል” )፤ ይህም የአንድ ጥሩ ገጣሚ ምልክት ነው። በእንባ የሚያራምዱ ፣ በፍርሃት የሚያርዱ፣ በሀሴት የሚያሳብዱ ምስጣሬዎችን ጀባ የማለት መክሊት ለገጣሚ ተሰጥቶታል። ለማይታየው ዓለም ቄስ ሆነው... ከሐሳቦች ጋር ጥምረትን፣ ከስሜቶች ጋር ቁርኝትን ያላምዱናል። ውበትን በለዛ ገልቦ ከገጣሚ በቀር እርቃኗን ማን ያያል? ጉልቻ የተጫናትን እውነት ማንስ በዜማ ፈንቅሎ እንድንሞቅ ይጀባናል? ያየነው እንዳላየነው፣ ልብ ያልነው ልብ እንዳላልነው፣ የገባን እንዳልገባን የሚጋለጥ እውን በግጥም አይደለምን? ነው እንጅ! ገጣሚው፤ የፈጠረውን ዓለም ለሕዝብ የማድረስ፣ ተነሽጦ የማስነሸጥ፣ ተነክቶ የማስነካት አቅሙ እንዳለው የታመነ ነው።
በብርሃኑ ገበየሁ አተያይ፤ ለአንድ ነጠላ የጥበብ ሥራ መጠሪያ ሆኖ ስለሚያገለግለው “ግጥም” እና  ስለአገጣጠም ብልሃት እና ስልት፣ ቅርጻዊ ገጽታዎች ሳይቀር ስለሚያትተው የጥናት መስክ “ሥነ-ግጥም” ዋኖቻችን ምን ይላሉ?  የዚህች መጽሐፍ ጌታ የሆነውስ ወጣቱ ገጣሚ መዘክር ግርማ ምን ይላል የሚሉትን ቃኝተን ወደ ድግሱ እናመራለን...
ሰለሞን ደሬሳ፤  ‹‹ልጅነት››  በሚለው  የግጥም  መፅሀፉ  መግቢያ  ላይ   ‹‹የግጥም  ፈንታ  የሰው    ልጅ  [የኑሮ  አላማውን  ለማሳካት የሚያደርገውን  ]  ግላዊ  መፍጨርጨር መሆኑን ሲያመላክተን ...  ፀጋዬ  ገብረ  መድህን ፤  ‹‹እሳት  ወይ  አበባ›› በተሰኘው  የግጥም  መድበሉ  መግቢያ  ላይ  ‹‹ በቃለ  ውበቱና  በቃለ  ኃይሉ፤  ወይም  በድቀቱ  ስምረት  ለአዕምሮ፣  ለልቦናና ለስሜት  የሚመስጥ  ባለስልትና  ባለድንጋጌ  የቋንቋ  አደራደር  ሁሉ  ሥነ-ግጥም (ፓኤተሪ) መባሉን ሲያረዳን... አያልነህ ሙላቱ (ባለቅኔ) ፤ማን ይሆን የበላ? በተሰኘ ሥራው ግጥም  ጥልቀት  ያለው  ኃሳብ፣  እጥር  ምጥን  ባሉ  የተዋቡ  ቃላት የሚገለጽበት  የሥነ-ፅሁፍ  ዘርፍ  ነው ሲለን.. ኃይሉ  ገ/ዮሐንስ፤ በበረከተ መርገም መጽሐፉ የአካባቢ  ልዩ  ኃይሎች  በመንፈስ  ላይ  በሚያሳድሩት  ተጽእኖና በሚያስከትሉት  የህሊና  ጭንቀት፣ የተለየ  ሀሳብ  በልቦና  ውስጥ  ይጸነሳል፡፡ ያም  ጽንሰ-ሀሳብ  ሲብላላና  ሲጋጋል  ከቆየ  በኋላ  በልዩ  ልዩ  መልክ  በአንደበት በኩል  ይፈነዳል፡፡  አንደበት  ኃሳብን  ከሚገልፅባቸው  አይነቶች  አንደኛው  ግጥም ነው  ብሎናል። ዘሪሁን አስፋውን ተመርኩዘን ወደ ውጭ ያየን እንደሆነ ‘ሥነ-ግጥም በሥነ-ግጥማዊ እውነትና ውበት ድንጋጌ ላይ በተመሰረተ ሁኔታ የተቀነበበ የሕይወት ኂስ ነው |ማቲው አርኖልድ|፣ሥነ-ግጥም ምት ያለውና ምናባዊ የሆነ የብርቱ ስሜት መግለጫ ሲሆን በለሆሳስ የታወሱ ጠንካራ ስሜቶች ከውስጥ ገንፍሎ መውጣት ነው |ዊሊያም ወርድስወርዝ|፣ሥነ-ግጥም በሌላ መልክ የማይባልን ነገር ከሞላ ጎደል ስሜት- ነክ በሆነ ስልት የሚነግረን ቋንቋ ነው |አርሊንግተን ሮቢንሰን|፣ ሥነ-ግጥም ደስታን ከእውነት ጋር የማጣመር ኪነ-ጥበብ ነው |ዋልተር አለን|ን ጠቅሰን ... የ‘አንድ ልጅ አዝማሪ..’ ወላጅ መዘክርስ ስለ ግጥምና ሥነ-ግጥም ምን ይለናል?
“’በዚያኛው ዓለም ያልተዋደዱ ነፍሶች እዚህም አይዋደዱም‘ እንዲሉ ረሱል ...ከመወለድ በፊት መፈጠር ነበር፤ ሥነ-ግጥምም ያንን ማስታወስ ነው። ሥንሞት ብቻ መሞታችንን እናምናለን፤ ስንኖርስ ማለት ነው ሥነ-ግጥም። የቃል መሰቀል ነው ግጥም። እንደ ጌታ ከፍ ብሎ ለመታየት፤ በትንሳኤም ለመነሳት። ገዳዮችን ይቅር በላቸው ብሎም እንደመጸለይ። የሥነ-ግጥም ግኝቷ አዳም በ ፴፯ ዓመቱ ከዔደን ገነት ተባሮ ከፈጣሪ ጋር መነጋገር በጀመረበት ወቅት ነው። ምጥን ቃላትን ከፈጣሪው እንደ መስማት ያለ።...ምጥ የማህጸን በርን ለማስፋት እንዲበረታ፤ ቃልም የሕይወትን በር ለማስፋት እንዲታገል ያውቃል።  ቃል ስምምነታችን ፣ቃል የባህሪያችን መመኪያ ነው ይለናል። እንዲሁ ሕይወት ያለ ግጥም ኦና መሆኗን በቦድሌር ይቃኛታል፤ “ማንኛውም ጤነኛ ሰው ያለምንም ምግብ ሁለት ቀናትን ሊሻገር ይችላል። ያለ ሥነ-ግጥም ግን አንድም ቀን አይችልም “...ምነው ብዙ ሰዎች ግጥምን ሳያውቁ እየኖሩ ቢሉት “ለዚያኮ ነው ጤነኛ ያልሆኑት” እንዳለው። የዳዊትን ፣የሙሴን ፣የሙሐመድን፣ የፓን ን፣ የእልወይ ባዮች እረኝነት አልፎም የፈጣሪ እረኝነት ...እረኝነት አዝማሪነትን እንዲወልድ፣ መሰንቆም በመስቀለኛ እንዲመታ ...አስተማሪም እንደሚሆን ...ግጥምም በዚያ እንዳለች አሳውቆናል። “በዕደ ዮሐንስ ተጠምቀ ኢየሱስ ናዝራዊ” እንድንል፣ ልጅም ለእናቱ ምጥ እንዲያስተምር ...ሐዲሱም ኦሪቱን እንዲያወሳ ይሸነቁጣል። ግጥም ወጣት ላይ እንድትበረታ ፣የከሸፈ ገጣሚም ፖለቲከኛ እንደሆን ..ግጥም ከሞሶሎኒ እና ከስታሊን፣ ሰዓሊነት ከሂትለር፣ ሞዛርትና ቤትኋቭን ከአዶልፍ ኤኽማን ልብ፣ ጊታር ከ ኤዲ አሚን ዳዳ፣ ኪነት ወዳድነትም ከኔሮ እንደነበሩ ...ሲከሽፉም የሆኑትን እንድናስብ (የጸጋዬን ብዕር ተውሶም “አሟሟታቸው ከውስጥ ነው እንደ ጋን መብራት" እያለ ከውስጥ የሞተ ወደ ውጭ መከርፋቱን የሚያመላክት ቀጭን ውላ አበጅቷል መዘክር።
ወደ ውጭ የሚከፈት በር ግብሩ ሁለት አንድም ለማስገባት - አንድም ለመገፍተር እንዲለን መዘክር፤ ጆን ክርስቶፍ ራፋ በThe Abyssinian መጽሐፉ ማስንቆ ሁለት ግብር አለው አንድም የተወደደ ዜማን ለማንቆርቆር ፤አንድም ፊቱን አዙሮ ለቀስትነት ለማገልገል እንዳለን፣ ከማን እንደ ተዋስኩት ባላውቅም ማስታወሻ ደብተሬ ላይ ያሰፈርኳት ግጥም ስለ ፍየል ቆዳ  የምታወረዋ ..የፍየል ቆዳ ሁለት ግብር አለው አንድም ወናፍ ሆኖ ለወንድሙ መታረጃ ቢላ መስራት፤ አንድም አጎዛ ሆኖ ለመቀመጫ ማገልገል እንደምትለዋ ...እልፍ ሲልም በረከት በላይነህ በግብረ - ሞረድ ግጥሙ የሰላ ቢላ ሁለት ግብር እንዳለው አንድም ነገሮችን ቶሎ ለመቁረጥ፤ አንድም ለመሸረፍ እንዳለን እንደሰማንም ... ይሄ ዳሰሳ ሁለት ግብር አለው። አንድም በመዘክር ግጥም ሐሳብ እጅጉን መደሰቴንና፤ አንድም አንባቢ አንብቦ በገጣሚው ጫማ ስር ሆኖ እንዲያስብ፣ እንዲናጥ፣ እንዲያ ...እንዲያ እንዲያደርገው ነው። እንጅማ ሥራ ለሠሪው እንደሆነ መች ጠፍቶን።
ወደ ጥልቁ...
የግጥምን (imaginary (show don’t tell part), rhyme, sound ,density, line”) ለመለየት empathy ያስፈልገናል። የመዘክርን ተናግሮ (persona)፣ የዘይቤ ምጥቀቱን (metaphore/rsonification,symbolizm,hyperbole,paradox,metonymy,Irony,Illusion,) እና  የምሰላ አቅሙን (smile) አደነቅሁ። የግጥሙን ዘውግ አካላት (የግጥምን ነገር፣ የግጥምን ተናጋሪ፣ የግጥምን ዝንባሌ፣ የግጥም ጭብጥ፣ የስሜት ቁጣ)፤ ሪሜ፣ ስታንዛ፣ የጥቅሶችን መለኪያ እያንዳንዱን ቅንጣት ለመደርደር/ለመተንተን ጊዜ እና ቦታ ይወስናል። ወይም፤ “ሩጫዬን ጨርሻለሁ” አለ ጳውሎስ ...ሩጫን ለመጀመር እርምጃን መጨረስ ያሻል ...ይህም ቀላል  አይደለም ትግሉ ..ወገን አለንልህ በሉ! እንዳለው ነው መዘክር እላችኋለሁ...ጠቅለል አድርጎ ለመረዳት ያህል (“|አነጋጋሪ/Allegorical| - የግጥም ተናጋሪው  በሦስተኛው ሰው ውስጥ ወደ ራሱ ውጫዊ/ውስጣዊ ሁኔታ ወይም ንጥረ ነገር ሲጠቅስ ፡...|ሐዋርያዊ/apostolic| - የግጥም ተናጋሪው ወደ ሁለተኛው ሰው (interpellation) የሚያመለክተው ከቅኔ ነገሩ ጋር ሊገጥም ወይም ላይሆን ሲችል.. |ካርሚን/Carmine| - የግጥም ተናጋሪው መገለጥ ከውስጣዊ ማንነት ሲመጣ። እሱ በአብዛኛው በአንደኛው ሰው ውስጥ እና በተጨባጭ አመለካከት የተመሰረተ” እያልን ለራሳችን በፈርጅ ማንበብ እንደምንችል ለመጠቆም ወደድኩ።
“አንድ ልጅ አዝማሪ...” ወደ ፍልስፍናዊ ግጥም ያዘነብላል። የዜማ፣ የቀለም፣ የምት፣ የምጣኔ፣ የቤት ነገሮችን ለእኛ የተወ ይመስላል። አንባቢ በራሱ ዜማ እንዲያዜም፣ እንዲያስብ የፈቀደ መሆኑን ከራሱ አንደበትም ሲናገር ይደመጣል። ፍልስፍና እና ግጥም፣ ፍልስፍና እና ልብ-ወለድ  የሚለያዩ ነገሮች እንዳልሆኑ ቀዳሚዎች እነ አልበርት ካሙ ያነሱትን ማሰላሰል በቂ ይመስለኛል። A novel is never anything but a philosophy expressed in images (“ልብወለድ በዐይን የሚታይ ምሥል ሆኖ የቀረበ ተጨባጭ ፍልስፍና እንጂ ሌላ ጉዳይ አይደለም።” እንዳለው)። እነሆ እንደተገረምኩ ላስገርማችሁ፣ ከማዕዱም ላስቆርሳችሁ (እኔ የቆሎ ተማሪ እንጅ የእንጀራ ተማሪ አይደለሁም ስላለ ‘ራሱ ላስቆርሳችሁ የሚለውን ላዘግናችሁ በሚል ተክቻለሁ...)
፩. ስለ ሴት (እናት፣ እህት፣ ፍቅረኛ)
 አዳም ማወቁ እንዲታወቅለት ለሕያዋን ኹሉ ስም አወጣላቸው። ለሔዋን ግን ስም ቸገረው፤ ለዚህም የመጀመሪያዋ ግጥም ርእስ ሴት ሆነች ይላታል። የሕያዋን ሁሉ እናት ልትሆን ሔዋን!  መላ ለሴት፤ ሴት ደግሞ ለወንድ እንደተሰጠች፣ ወንድ መላን ያግኝ ዘንድ መሻቱን ይገልጻል። ውበትን ለሴት ይሰጣታል (ከቴዎድሮስ ቁንጅና ማወደደር እስካሁን በውበት በመለጠጧ ፍትሐ-ነገሠት እንዲገለጥባት ይመኛል)። ተራራው ላይ፣ ውኔ - እንቅልፌ ውስጥ ባ’ደራ ያኖረሽ፣ ትንሽ እኅት (እህትነት)፣ እግር እና እግሯ መሐል (እናትነት)፣ ባለ እጅ ነሽ አሉ፣ አሁንስ ናፈቀሽኝ እና ሌሎች የሴትን ውበት፣ ሐሳብ፣ ፍቅር፣ ስሜት የሚያጎሉ....
ተወው አታስታውሰኝ፣ ግዴለህም እርሳኝ
ግን ለራስህ ስታልፍ፥ እግረ-መንገድ አንሳኝ
አንሳኝና ጣለኝ
ጣለኝና ልውደቅ
በጠየቁኝ ጊዜ “እሱ ነው የጣለኝ
                      ብዬ ደስ እንዲለኝ”።
፪.ከልብ የተቸሩ ሥጦታዎች
በእኩል ያየነውን እኩል እንዳንረዳው የሚያደርገን ጥበብ በመሐከላችን አለ። እውነተኛ ገጣሚዎች ደግሞ ለማመስገን፣ ለማመስጠር፣ ለመተንበይም  በሦሥተኛው ዓይን ማየት የጀመሩ፣ በስድስተኛው የስሜት ሕዋስም መጠቀምን የተሰጣቸው ናቸው። ለሥጋም ይሁን ለመንፈስ እህቶቹ (ትንሽ እኅት)፣ አፈር ለዘራኸው ገበሬ፣ ለአባዬ (ትዝታ)፣ አመሰግናለሁ፣ ለፍስሐ በላይ ይማም (ሐምራዊ ብሶት)፣ ለወደፊቶቹ ገጣሚ (ለወደፊቱ ፊት)፣ ለኤልያስ መልክዓ (ሰው እግዚኦ) እና ለአብርሃም አፈወርቂ (የከያኒ ጥሪ) አብነቶች ናቸው።
ሰዎችማ፤ “አበባ ይረግፋል “ይላሉ
ኧረ አይረግፍም፤ እ’ታበባ ከተከሉ። (ገጽ 26)
፫.ሀገራዊ ስሜት
ግጥም እና ገጣሚ ከወታደር ቀጥለው ለአገር ድንበር ማስጠበቂያነት ሲያገለግሉ ኖረዋል። ለጦር የዘመቱ እንደሁ አዝማሪ ይጠራል (ከነግጥሙ)፣ ድል ያደረጉ ዕለትም ለማጉላት ይኸው አለ። ሀገርም መንፈሳዊ እና አካላዊ ይዞታዋ ከሰባኪ በላይ በግጥም የደቆኑት ...የቀሰሱት ሲለፉት ይጥማል።  መዘክር እንኪስላንቲያ ኢትዮጲያ፣ መስተጋብእ፣ እንደ ኢትዮጵያ ወንዞች፣ አደዋ ክበበ ጌራ፣ ብሔርተኝነት እና በመሳሰሉት አርዕስቶቹ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ፣ ስጋቱን፣ ኩራቱን፣ ትዝብቱን ሳይቀር በብዕሩ እንካችሁ ብሎናል።
የሴተኛ አዳሪሽ ቀሚስ፤ ባ’ላማ ሰንደቅ ተውቦ
ኋላ ሰካራም ሲመጣ፤ ይተኛታል አንቺን ገልቦ። ገጽ (40)
፬. ስለሚመስሉን ነገሮች ሌላ ገጽ
ብዙ ጊዜ የሚመስሉን ነገሮች አሉ። እንደ ምሳሌ “ሊነጋ መምሸቱን እናውቃለን፤ ሊመሽ መንጋቱን ግን ገምተናል?”፣ እግዜርን ይሉታል ወይ ውረድ ወይ ፍረድ ...ቢወርድ ከፊቱ የሚቆም፣ ቢፈርድ የሚተርፍ ያለ ይመስል እንዳለው ነው ረድኤት አሰፋ። በመዘክር በኩል ምን አለ? ...ሰዎች በሽተኛ ብቻ ይመስላቸዋል መድኃኒት ካ’ጣ የሚሞት፤ መድኃኒት በሽተኛ ካ’ጣ መሞቱን ማን ገመተ? እግዜርን ለመጣል አንድ አፍታም አትፈጅ፤ ምድር ለመውደቂያ አትበቃውም እንጅ ይለናል።
ጥበብ መጀመሪያው “እግዜርን መፍራት ነው”ብለው ስለአሰቡ እግዚአብሔርን ፈርተው፣ ሰይጣንን ቀረቡ (ገጽ114)
፭. ስለ ፍቅር
ፍቅር በገጣሚ ብዕር በኩል ሲመጣ ሌላ መልክ አለው። ማርቀቅም፣ ማጉላትም ለግጥም የተተወ ነው። እውነትን ያለበሰቻት ውበት ቀለም ውስጥ አለች። ውበትን ከልብ የገለጧት እንደሁ እውነት ከሽሽጎሿ ትወጣለች። ከብዙ ግጥሞቹ ጥቂቱን ላዘግናችሁ...
ለመደማመጥ ምሽት ይመጣል
ለመቀማመስ ምሽት ይበልጣል
ተይ ሻማ!- ብርኀንማ ይቀልጣል! ( ገጽ 97)
----
ዓለም ራሷ፣ እኛ ያልነውን፣ መልሳ እንድትል
ገደል ማሚቶ እናስከትል። (ገጽ 88)
----
አንቺን ለማመን ቤተስኪያን ሠራሁ
ሁሉ እየሔደ ሲያመልክሽ ፈራሁ (ገጽ 81)
---
የሰነፍ ሥራ ነው፥ ተይው የኔን ነገር
ከጎኔ ተገኝተሽ፥ ስፈልግሽ ነበር  (ገጽ 74)
ያልገባበት ጓዳ፣ ያልዳሰሰው ልብ የለም። ሁሉን ጠቅሶ፣ አወድሶ አይቻልና እንደ ማሟሻ ይሆናችሁ ዘንድ በልዩነት ‘መስተጋብእ (ገጽ 67)፣ ምንየታዊቴ ሆይ (ገጽ 103)፣ ጣዕመ ሽነት ጠባየ ኪነት (ገጽ 123)ን አጣጥሟቸው (ሕይወት እዚያ ተገልጣለች)።
አንድ ልጅ አዝማሪ ከበኩር ስራው (ወደ መንገድ ሰዎች) ቀጥላ የተወለደች ናት። ግጥሞቹ ወደ ወለሎቱ ቢያደሉብኝ ጊዜ እኔም ወለሎትን ልዋሓዳት ቃጣኝ - ሙክርታዬም ይኸው (ይኼ ዳሰሳ የጸሐፊው እምቅ አቅም ስለገረመኝ ትነበብ ዘንድ እንጅ የበሰሉ ኃያሲያን ገብተው ሓሳቡን ድጋሜ ቢያስቃኙኝ አፌን ከፍቼ የምሰማ ስለመሆኔ አልክድም)።የአንዳንድ ግጥሞቹ ቀለም (ሜትር) ለመቁጠር፣ የግጥምን የልብ ትርታ (ምት)፣ የሀረጋት ምጣኔ (የግጥም ሙዚቃነትን) ተቆጣጥሮ ለመንገር ያዳግታሉ (ለዚህ መድኃኒቱ በእናንተው አዜዚያም አዚሙት ማለቱን መውሰዱ ይበጃል)። ከ1300 እስከ 1400 የነበረው የግእዝ ሥነፅሁፍ ወርቃማ ዘመን፤ የ1960 እና 1970ዎቹ የነበረውን የአማርኛ ሥነፅሁፍ ወርቃማ ዘመን  በዘመናችን ለማየት ምን ከል ሆነብን? ብዬ ራሴን ጠይቄ (ያልታዩ ወጣት ገጣሚዎች እና ወጣት ጸሐፊዎችን ወደ ሜዳው ያለመሳብ ጉዳይ ሆኖ ተሰምቶኛል)። ግጥምን በቅርጽም ይሁን በይዘት በዘመኔ የሚያሽሞነሙኗት ወጣት ገጣሚያን እና ደራሲያን አሉን፤ በቻልኩት መጠን ወደፊት ላስተዋውቃችሁ ቃሌ ነው።
ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን “ሥነግጥም የፈጠራ ሁሉ፤ የሥነጽሑፍ ሁሉ የደም ጠብታ ነው።”ይላል። ግጥም እንደ ወግ (anecdote)፣ አፈ-ታሪክ (folkatale)፣ ተአምራዊ ታሪክ (parable)፣  (fable) የሚዘረዘር፣ የሚተነተን አይደለም፡፡ ቁጥብ፣ ቅንብብ፣ ረቂቅም ነው (ለቻለበት)። ፍንገጣም ገንዘቡ ነው (“ከፍቅር ሳይሆን በፍቅር”)። ገጣሚ መዘክር ግርማ እርምጃውን ወደ ማጠናቀቁ፤ እሩጫውን ወደ መጀመሩ ይመስላል። ሩጫውን እንዳልጨረሰ ነግሮናል (ሽኝት ተለያይቶ ለመገናኘት ብሎም እንዳጸናው)። ዘይቤዎቹ ይደንቃሉ። እንደ ንስር ዓይኑ ሩቅ ያያል (ከመወለድም በፊት ስላለው መፈጠር |ረሱልን ተመርኩዞ)፣ ማህበረሰባዊ እሳቦቱ የሰፋ ነው። ግጥምን በራሱ ዘዬ፣ ከጥቃቅን ነገሮች እያነሳ ነፍስ ያላብሳቸዋል  (አዳም ረታ እንጀራ እና የእንጀራ ዓይኖችን እንደሚተነትን  ሁሉ)። በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ያለው “አንድ  ልጅ አዝማሪ ሥነ-ግጥም “ መባሉ እንዴት ነው ቢሉ? ብርሃኑ ገበየሁ” ሥነ -ግጥም” የአገጣጠም ስልትን፣ ቅርጽንና አጠቃላይ ሁኔታን የሚያስቃኝ ሳይንስ እንደሆነ ነገሮናል። (በእማሬው ሳየው መዘክር ይህንን መጽሐፍ ሥነ -ግጥም ብሎ ማቅረቡ የሥነ -ግጥምን ትንታኔ ያወቁ ሰዎች ስለ ግጥም ሳይንስ ለመማር ጥባቆት እንዳይኖራቸው እሰጋለሁ። (በፍካሬው ካየነው ግጥምን ለመማር ቢገቡስ የሚያጡት የታል?...ፍቅር፣ ሐሳብ፣ ትዝብት፣ ውዴታ እስከዚህም ይገለጻሉ እንዴ? ይላሉ እንጅ!)።
ይህን ሁሉ እለፍ ዘንድ በገጣሚው ጫማ ስር ሆኜ ማማጥ፣ መናጥ ነበረብኝ፤ አድርጌዋለሁ (የራሴን ለራሴ ትቼ)። ክስተቶቹን ክስተቴ፣ ደስታውን ደስታዬ አድርጌ ወጥ ቅርጽ፣ ወጥ ዜማ፣ ወጥ ምት፣ ወጥ ምጣኔ  ስለሌለው በራሴ ዜማ፣ በራሴ ስልት ፎክሪያቸዋለሁ። ተመቹኝ እንጅ አልጎረበጡኝም። ልስልስ ማህበረሰባዊ ቋንቋው ጋር ተዋደድኩ ...ወደፊቱን ብሩህ ያደርግለት ዘንድ እየተመኘሁ፤ ይኼን የግጥም ስብስቡን የሚንቅበትን ደረጃ እየተመኘሁ ...የመሰነባበቻ ጥያቄዬን እንካችሁ..
“ሚስት ከእግዜር ናት!” ከተባለ
ግጥምስ? ከየት ብትሆን ተሻለ...(ገጽ 67)Read 281 times Last modified on Tuesday, 18 October 2022 07:51