Tuesday, 18 October 2022 06:42

የሸገሩ “ማንን ምን እንጠይቅልዎ?” ፕሮግራም

Written by  በአስናቀው አሰፋ
Rate this item
(2 votes)


       “--አንዳንድ ተመሳሳይ ፕሮግራሞች በቴሌቪዥን አይቻለሁ። አቀራረባቸው ግን “የትግል” አይነት ነው።  ጋዜጠኛው ዓይኑን አፍጥጦ፤ አንገቱን አስግጎ፤ ተጠያቂውን “አንተ ሌባ ዛሬ እጄ ላይ ጣለህ!” አይነት ጥያቄ ይጠይቀዋል።--”
      
      ብሶተኛ ይደውላል --- “ሃሎ ሸገር ነው?” ---- ግርምሽ ይመልሳል --- “አዎ - ማንን ምን እንጠይቅልዎ?” --- ብሶተኛ በደሉን ይተነትናል። አልፎ አልፎ የማብራሪያ ጥያቄ ከመጠየቅ ውጭ፤ ግርምሽ በትህትናና በትዕግስት ያዳምጣል። --- ጉዳዬ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ እንደገና ሲዋቀሩ የተከሰተ ነው። የአገር ተሻጋሪ ሾፌሮች መንጃ ፈቃድ እድሳት ለየትኛው የመንግስት አካል እንደተሰጠ ግልጽ ባለመሆኑ የእድሳት ጊዜው ያለፈባቸው ደዋይ ግራ ተጋብተው ነው “ሃሎ ሸገር!” ያሉት።
ግርምሽ እንደተለመደው “እንደውልላቸዋ!” ብሎ ደዋዩን ያሰናብታል። --- “ሃሎ” ይላል ግርምሽ፤ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ለሚላቸው የመንግስት ባለስልጣን። ግርምሽ ላድማጮቹ የሚያናግራቸውን ባለስልጣን ያስተዋውቃል። በጠዋት ደውሎ ለጥያቄው መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ በመሆናቸው አመስግኖ፤ ወደ ተጠያቂው ይዞርና “አቶ፤ ዶ/ር፤ ኢ/ር ---- እከሌ፤ ጥያቄውን ሰምተዋል አይደል?” ብሎ ይጠይቃል። ማረጋገጫ ሲያገኝ፤ “እባከዎት ይመልሱላቸው” ብሎ ለመላሹ እድሉን ይሰጣቸዋል።
ከላይ እንደ ምሳሌ ያነሳሁት ከሰኞ እስከ አርብ በየዕለቱ ጠዋት 2፡20 አካባቢ በሚደመጠው የሸገር ሬድዮ “ማንን ምን እንጠይቅልዎ?” ፕሮግራም የተላለፈ ነበር። በግርማ ፍስሐ ከሚዘጋጀው ከዚህ ፕሮግራም ብዙ አስተማሪ ነገሮችን አግኝቼበታለሁ።
አሁን ወደቀደመው ልመልሳችሁ--- ባለስልጣኑ ለጉዳዩ መልስ መስጠት ይጀምራሉ። ወጣ ሲሉ፤ ግርማ በትህትና ይመልሳቸዋል።  በመጨረሻም መላሹ ለጉዳዩ መፍትሄ ለመስጠት እየሰሩ እንደሆነና በቅርቡ መፍትሄ እንደሚያገኙ ይደመድማሉ። “የመዋቅር ለውጡ ከተደረገ ቆየ፤ እስካሁን ለምን መፍትሄ አልተሰጠም?” ግርምሽ ይጠይቃል፡፡ መላሹ “በሰው ቁስል እንጨት ቢሰዱበት“ ዓይነት መልስ በመመለሳቸው ግርምሽ አልረካም። ግርምሽ ጋ ትህትና በሽ ነው፤ ቀልድ ግን የለም።  መላሹ “ከራዳር” ውጭ ሲወጡበት በትህትና ይመልሳቸዋል።  “ደግሞስ ጊዜያዊ መፍትሄስ ለምን አልተበጀም?” እንደገና ይጠይቃል። መላሹ የመንግስት ሃላፊ ጥያቄውን ወደ ግርምሽ መልሰው ወረወሩት፤ “አንተ ብትሆን ምን ታደርጋለሀ?”  በሚያስደንቅ ፍጥነት፤ “ለምሳሌ ጊዜያዊ ፈቃድ ቢሰጣቸው አንድ መፍትሄ ይሆናል” አላቸው።
የመሪ ሚና ከፊት ሆኖ መምራት ነው፤ እኝህ ሰው ግን ሃሳብ አዋጡልኝና እኔ እኮረጃለሁ እያሉን ነው።  ለወራት ተሽከርካሪ ወንበራቸው ላይ ተቀምጠው ሊያፈልቁት ያልቻሉትን መልስ፤ ግርምሽ በቅጽበት አቀበላቸው። ከተገበሩት መልካም ነው።  ግን በእንደዚህ አይነት ጥቃቅን ምክንያቶች ስንቱ መስራት የሚገባው ቦዝኖ ይውላል? የስንቱስ ቤተሰብ ኢኮኖሚ ተናግቶ ይሆን? እንደዚህ አይነት የመዋቅር ለውጥ ሲደረግ ወይንም ፕሮጀክት ሲነደፍ፤ ጥቃቅን ነገሮች ሳይቀር በዝርዝር መጠናት አለባቸው። ድንገት የተረሳ እንኳ ቢኖር ተብሎ በፍጥነት መፍትሄ የሚሰጥ ኮሚቴ ማቋቋም ይኖርበታል።  እኛ ግን እንኳን ለጥቃቅኖቹ ለትልልቆቹም ቁብ አንሰጥም።  የኢንዱስትሪ ዞኖች ሲቋቋሙ ስለ ኤሌክትሪክ ሃይል ምንጭ ታስቦ እንዳልነበር በዚሁ ፕሮግራም ሰምቼ  ገርሞኛል።
ሌላ ጊዜ ሌላ አድማጭ እንዲጠየቅለት ለፈለገው መሥሪያ ቤት ሀላፊ የእጅ ስልክ ላይ ግርምሽ ሆዬ ይደውላል። ማን ቢያነሳው ጥሩ ነው? --- ሾፌራቸው!  --- ጉድ በል!  --- ከሹፌሩ የስራ ዝርዝር ውስጥ ተካቶ ይሆን? እኒህ የምላችሁ ሰው እንዲህ ተራ የኔ ቢጤ ሁለትና ሦስት የበታች ሰራተኞችን የሚመሩ እንዳይመስላችሁ።  ከጠቅላዩ ባንድ ወይም በሁለት እርከን ብቻ ዝቅ ያሉ ናቸው።  ታሪኩን እንደነገረን፤ ደጋግሞ በመደወል ባለስልጣኑን አገኛቸው። ግን መልስ የለም።  ጠቅላዩ አሳዘኑኝ። “ለምን?” አላችሁኝ? --- ባለፈው ስለ የምርመራ ጋዜጠኝነት ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ሁሉም መሥሪያ ቤቶቸ ለጋዜጠኞች በራቸውን ክፍት ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረው ነበር። ግን ምን ያህሉ ዝግጁ ናቸው? ቃላቸው ተግባር ላይ መዋሉንስ በምን መልኩ ይከታተሉ ይሆን?
ምኒልክ ባንክ ለአገሬው ሲያስተዋውቁ፤ ከባላባቱና መኳንንቱ ነበር የጀመሩት። ሹማምንቱ ገንዘባቸውን አውጥተው መስጠቱ ቢከብዳቸውም፤ የንጉስ ትዕዛዝ ነውና አደረጉት።  የባንክ መመሪያው በፈለጉት ጊዜ ያጠራቀሙትን ገንዘብ አውጥቶ መውሰድ ስለሚፈቅድ፣ እንቅልፍ አጥቶ ያደረ ደንበኛ፣ በጠዋት ወደ ባንኩ ሂዶ ፎርም ይሞላል፤ ባንክ ያስገባውን ገንዘብ በሙሉ ወጭ ለማድረግ። የባንኩ ሰራተኛ በትዕዛዙ መሰረት ለመስጠት ብሩን ፊትለፊቱ ከምሮ መቁጠር ሲጀምር ደንበኛው፤ “ካለማ ተወው! ተወው!” ብሎ ፎርሙን ቀዳድዶ ይሄድ ነበር አሉ። በዚህ መልኩ የተጀመረው የባንክ አገልግሎት ነው አሁን ካለበት የደረሰው።
አሁን ዘመኑ በጣም ተለውጧል። ቴክኖሎጂ ተራቆ መረጃን በጃችን እያቀበለን ነው ያለው - እኛ ለመቀበል ከተዘጋጀን። የህዝብ አስተዳደር ሙያተኞች መሪዎችን “ከገዥነት ወደ አገልጋይነት ተለወጡ” እያሏቸው ነው። ምን ዋጋ አለው፤ ምክሩን ተቀብሎ የሚለውጠው ጥቂቱ ነው። የመንግስት መኪና የተመደበለት ሰው፣ ምን አለ ሾፌር ባይጠይቅ? ምን አለ እራሱ ቢያሽከረክር? ለነገሩማ ለአስቤዛ አንድ መኪና፤ ለልጆቹ ት/ቤት ማመላለሻ ሌላ አንድ መኪና ያስመደበ ባለስልጣን ሳይኖር ይቀራል? ይሄ ታዲያ አገልጋይነታቸውን ነው ወይንስ ገዥነታቸውን የሚያሳየን?
ግርምሽ ጆሮ ላይ ስልክ የሚዘጉ እንዳሉ ሁሉ በትህትና የተጠየቁትን መልሰው ሸገር ስራቸውን ስላቃናላቸው የሚያመሰግኑ፤ ተጠያቂነት ምን ማለት እንደሆነ በተግባር የሚያሳዩ እንዳሉ መጥቀሱ ተገቢ ነው።  እናመሰግናችኋለን፤ እናከብራችኋለን። ቁምነገሩ ግን ከህዝብ ጆሮ ሳይደርስ መፍትሔ ማግኘቱ ላይ ስለሆነ፤ ሲስተም ላይ ብትሰሩ መልካም ነው። ለምሳሌ የውሃ ፍጆታቸው ክፍያ ከባንክ ደብተራቸው ጋር የተያያዘ ደንበኛ፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ብር ተቆርጦባቸው፣ ከብዙ ጊዜ እንግልት በኋላ እንደተመለሰላቸው በዚሁ ፕሮግራም ተከታትያለሁ። ስህተቱ የቆጣሪ አንባቢው ነው ተብሏል።  የሰው ልጅ ሆኖ የማይሳሳት የለምና አይገርምም።  ግን ሲስተም ሲዘረጋ ሊከሰቱ የሚችሉትን ችግሮች ቀድሞ ተንብዮ መፍትሄ ማስቀመጥን ይፈልጋል። የቆጣሪ ንባብ ስህተት በጥሬ ገንዘብ ክፍያ በሚደረግበት ጊዜም የነበረ ነው። አዲስ ሲስተም ሲዘረጋ ሁልግዜም ችግር ፈች እንዲሆን ይጠበቃል፤ በኛ አገር ግን በተለይ ከክፍያ ጋር በተያያዘ በተለምዶ “ሲስትም የለም” እየተባለ በኢንተርኔት ኮኔክሽን መቆራረጥ ምክንያት ስንቱ ሰው ተጉላልቷል። ሲስተሙን የዘረጉት ሰዎች ኢንተርኔት ሲቋረጥ ምን መደረግ እንዳለበት አማራጭ ስላላዘጋጁ፤ ሰራተኛውም ተጠቃሚውም ተፋጦ ይውላል። ሲስተም የስራ ማነቆ የሆነባት ብቸኛ አገር ሳትሆን ትቀራለች፤ ኢትዮጵያ!
ጉዳዬን አላወኩትም እስኪ ላጣራ፤ ባለጉዳዩን እኔ ቢሮ ድረስ ላካቸው፤ ወዘተ አይነት መልሶች ባንዳንድ ሃላፊዎች ይሰጣል። መልካም ነው። ግን የበታቾቻቸውን አንዳንዴ ቢጎበኟቸው፤ የገጠማቸው ችግር ካለ ቢጠይቋቸው፤ አልፎ አልፎም ቢሆን የተገልጋዮችን አስተያየት ቢጠይቁ ችግር የተባሉ ነገሮች አደባባይ ላይ አይውሉም ነበር። ሁላችንም እንደምናውቀው ሃኪሞች ታመው አልጋ ላይ የዋሉ ታካሚዎቻቸውን በጠዋት እየዞሩ ያያሉ። የታማሚውን በጎ  መሆንና አለመሆን፤ መቀየር ያለበት መድሃኒት መኖሩንና አለመኖሩን፤ ወዘተ ይፈትሻሉ።  በየቢሮው ያሉ አለቆች አብዛኛውን ጊዜ “ጊዜ” የላቸውም። በሌላ አነጋገር በወረቀት ሥራ ይዋጣሉ ወይም ለወረቀት ሥራ ቅድሚያ ይሰጣሉ። አንድ ግብር ሰብሳቢ መ/ቤት ሄጄ ወረፋው ለጉድ ነው። ይባስ ብሎ ካሉት አራት የማስተናገጃ ወንበሮች አንደኛው ብቻ ላይ ነበር ሰራተኛ የነበረው። አራቱም ሰዎች ቢኖሩ እንኳ ለነበረው ተስተናጋጅ ብቁ አልነበሩም። የሚገርመው ደግሞ አለቅየው ከዚያው ፊት ለፊት ነው የሚቀመጠው። የተስተናጋጁ ሰው መጉላላት የደነቀውም አይመስል። በቃ የተለመደ ነው! አለቀ! --- የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም።
የሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽንስ ቢሮ ሆኖ እየጠበቀን ነው? “ማንን ምን እንጠይቅልዎ?”ን የመሳሰሉ ፕሮግራሞችን የሚከታተል ክፍል ይኖር ይሆን? መስሪያ ቤቶች የሶሻል ሚዲያ አድራሻ (account) አላቸው። የተጠቃሚውን አስተያየት የሚከታተልና ጥፋተኛ ሲገኝ የሚቀጣ አካልስ ተቋቁሞ ይሆን? ወይንስ እንደ ድሮዎቹ የአስተያየት መስጫ ሳጥኖች የይስሙላ ናቸው? ፈረንጆቹ “proactive” እና “thinking out of the box” የሚሏቸው ደስ የሚሉ ቃላቶች አሏቸው።  ሁሉም መ/ቤቶች እንደ መርህ ቢወስዷቸው መልካም ነው።
በነገራችን ላይ፤ ግርምሽ፤ ደራርቱ አደባባይ (አያት) መገናኛ የሚወስደው መንገድ በየሁለትና ሶስት ወሩ ነጭ ቀለም እየተቀባ ነው። “ሶስተኛው ዙር” መቼ እንደሆነ እባክህ የሚመለከተውን አካል ጠይቅልን። --- ቀልድ ይመስላል አይደል? ነገሩ እንዲህ ነው። የመንገድ ማካፈያው ነጭ ቀለም ስለፈዘዘ ካልተሳሳትኩ፣ ባለፈው አመት ህዳር ወር አካባቢ ይቀባል/ይታደሳል። ሁለት ወር ሳይሞላው ሙልጭ ብሎ ይለቃል። እንደገና ይቀባል፤ አሁንም ሙልጭ ብሎ ለቋል። ለዚህ ነው ሦስተኛው ቅብ መቸ እንደታሰበ ጠይቅልን ያልኩህ። “ስትሄድ ያነቀፈህ ድንጋይ ስትመለስ ከደገመህ፤ ድንጋዩ አንተው ነህ” ነው የሚባለው? ደጋግሞ “ኖራ” ከመቀባት፤ አንድ ጊዜ የዘይት ቀለም ቀብቶ መገላገል አይሻልም ወይ በልልኝ።
በአሁኑ ጊዜ ማህበራዊ ሚዲያ፣ መደበኛውን መገናኛ ብዙኃን እየተገዳደረው ይገኛል። ”ማንን ምን እንጠይቅልዎ?” አይነት ፕሮግራሞች የመደበኛውን መገናኛ ብዙኃን ተወዳጅነት/ሳቢነት ይጨምሩለታል። አቀራረቡ ግን ወሳኝነት አለው። አንዳንድ ተመሳሳይ ፕሮግራሞች በቴሌቪዥን አይቻለሁ። አቀራረባቸው ግን “የትግል” አይነት ነው።  ጋዜጠኛው ዓይኑን አፍጥጦ፤ አንገቱን አስግጎ፤ ተጠያቂውን “አንተ ሌባ ዛሬ እጄ ላይ ጣለህ!” አይነት ጥያቄ ይጠይቀዋል። አንዳንዱ መላሽ ድንብርብሩ ወጥቶ እውነታ እንኳ ቢኖረው ምላሱ ተሳስሮ ላብ ያጠምቀዋል። ሌላው ጮሌ “እንኳን ላንች ለእነ እንቶኔ አልተበገርኩም!” በሚመስል መንፈስ ከጋዜጠኛው ጋር “ግብ ግብ” ይገጥማል። እንዲህ አይነት ፕሮግራሞች ዋናው አላማቸው ስርአትን ማስተካከልና ስህተትን ማረም መሆን አለበት።  መርሳት የሌለብን ዋናው ጉዳይ፣ ሁላችንም ከስህተት እንደማንጸዳ ነው።
አንዳንድ ጋዜጠኞች ደግሞ አሉ፤ ሁሌም ወደ እነሱ ለሄደ የሚያዳሉ የሚመስሉ። አስታውሳለሁ “የስኳር ህመም መድሃኒት አግኝቻለሁ፤ ነገር ግን የሚመለከተው የመንግስት አካል እውቅና ነፈገኝ” ብሎ አንድ ግለሰብ ወደ አንድ ሬድዮ ጣቢያ ይሄዳል። ከዚያ በኋላማ ምን እላችኋለሁ! ጋዜጠኛው ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ ሆኖ ቀረበ። ህዝቡን ምቀኛ፤ የመንግስት ሃላፊዎችን ጉቦኛ አድርጎ ሳለንና አብጠለጠለን። ባጠቃላይ “ገነፈለ” ማለት ይሻላል። በተቻለ መጠን ጋዜጠኞች የሚሰጡት አስተያየት በእውቀት ላይ የተመሰረተ ካልሆነ ባለሙያዎችን ያሳተፈ መሆን አለበት። መድሃኒት አገኘሁ ያሉት ሰው ዝናብም ማዝነብ እንደሚችሉ አንድ ጋዜጣ ላይ ወጥቶ አንብቤአለሁ። ነፍሳቸውን ይማረውና የቀድሞው ፕሬዚዳንት ፈቅደውላቸው ግቢ ውስጥ እንዳዘነቡ ጠቅሰው ነበር፡፡ አሁን የት ደርሰው ይሆን? ”ማንን ምን እንጠይቅልዎ?” ፕሮግራም ላይ ግርምሽ ጉዳዩ እስኪጠናቀቅ እስከ መጨረሻው ይከታተላል። ይሄም ከሌሎቹ ልዩ ያደርገዋል። አስፈላጊ ከመሰለው ሃላፊዏችን ቢሯቸው ድረስ ሄዶ ያናግራቸዋል።
እግረ መንገዴን ለጋዜጠኞች አንድ ነገር ላቀብላችሁ፤ አንድ ሰውየ ማሽላን ወደ ቋሚ አትክልትነት (ልክ እንደቡና በያመቱ የሚለቀም ማለት ነው) የሚቀይር ምርምር ሰርቼ እውቅና የሚሰጠኝ አጣሁ ብለዋል።  እባካችሁ ፈልጋችሁ የት እንደደረሱ አናግሯቸው። ይህ ጉዳይ “እውነት” ከሆነ፤ አገሪቱ በምግብ እህል እራሷን ለመቻል በምታደርገው ጥረት  ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል። እናንተም “በልማታዊ ጋዜጠኝነት” ተሸላሚ ትሆናላችሁ። ካልሆነም ከመንግስት ካዝና ለተደረገላቸው ድጋፍ (ካለ) ተጠያቂ ናቸው። ማንም ድንገት እየተነሳ እንዲህ እንዲያ አደርጋለሁ እያለ እንዲያጭበረብረን መፍቀድ የለብንም፡፡
የ”ማንን ምን እንጠይቅልዎ?” ፕሮግራም መደበኛ ተከታታይ ነኝ። በሆነ ምክንያት ሳላዳምጥ ከቀረሁ፤ ቅር ቅር ይለኛል። ግርማ ለፕሮግራሙ ወይም ፕሮግራሙ ለግርማ በልኩ የተሰፋ ነው የሚመስለው። አንድ ጊዜ የአንድ መሥሪያ ቤት ተግባቦት (communication) ባለሙያ ከብዙ ክርከር በኋላ “የተሸነፉ” ሲመስላቸው፤ ግርምሽን “አንተን ምን አገባህ” አይነት ጥያቄ ይጠይቁታል። ግርሜ አልተበሳጨም። አሁንም በትህትና ያናግራቸዋል። “በጠዋቱ ደውዪ ጨከጨኩዎት አይደል?” ይላቸዋል በለሰለሰ አንደበት። እኔ በሱ ቦታ ብሆን ብዬ አሰብኩ።  መጀመሪያ ልክ ልኩን እነግረው ነበር ብዬ አሰብኩ። ቀጥዬ፤ አየር ላይ ስላለሁ ቁጣዬን አስታግሼ፣ ለዘብ አድርጌ እንደማናግራቸው አሰብኩ። ማስመሰሌ እንደሚያስታውቅብኝ ግን እርግጠኛ ነበርኩ። ግርምሽ ግን የሚናገረው ነገር ሁሉ ከልብ መሆኑ ያስታውቃል። ውይይቱ ቀጥሏል፤ የኔም ንዴት እና ሃሳብ እንደዚያው። ሦስተኛው ሃሳቤ ላይ ተረጋጋሁ።
በርሱ ቦታ እራሴን ለማስቀመጥ ሞከርኩ እንጂ አልተሳካልኝም። ግርምሽ በየቀኑ ከሚደውልላቸው ሰዎች ጋር የግል ቂም የለውም። እኛን ወክሎ የኛው ጉዳይ መፍትሔ እንዲያገኝ ነው ጥረቱ። ለዚህ ደግሞ ከተበሳጨ ነገር ተበላሸ መሆኑን ያውቃል። እኔም እኔኑ ሆኜ እንደ አንድ ባለጉዳይ ተበሳጨሁ እንጂ እንደ ግርምሽ መሆን አልተሳካልኝም። የተግባቦት ባለሙያውም አስገረሙኝ። “እንዲህም ብሎ ተግባቦት የለ” አልኩ በልቤ። ባያገናዝበው ነው እንጂ “ደንበኛ ንጉሥ ነው” ብሎ ቢሮው ግድግዳ ላይ ለለጠፈልን ሰዏች ጥያቄ እየመለሰ ነው። ጥሩነቱ በሌላ ጊዜ ይቅርታ በመጠየቃቸው ደስ አሰኙኝ።  ሰው መቸም አትሳሳት አይባልም፤ ስህተቱን በይቅርታ እንዲሽረው እንጂ የሚጠበቀው።
ከተገልጋዮቹ ከኛስ ምን ይጠበቃል? ከሦስት ወር በኋላ የተፈታ ጉዳይ ነበር። በዚሁ እለት አንድ አድማጭ (ከሃላፊነት ካለበት መስሪያ ቤት ውጭ የሆኑ) ደውለው ቅሬታቸውን በግርምሽና ተበደልኩ ባዩ ላይ አቅርበው፣ ለጥያቄዎቹ መልስ ለመመለስ ሞክረው ነበር። እንደ እኔ ቅሬታ ከቀረበ ቅሬታ የቀረበበት መ/ቤት ተወካይ ብቻ ነው መልስ መስጠት ያለበት። ግለሰቡ እኔ የበለጠ መረጃ አለኝ ብለው የሚያሰቡ ከሆነ፤ መ/ቤቱን ሊያማክሩ ይችላሉ። ይህን የምልበት ምክንያት፤ 1ኛ/ ሁሉም ነገር በደንብና በስርአት መገዛት ስላለበትና 2ኛ/ ይበል በርታ መባል የሚገባውን የኛኑ ፕሮግራም፣ በሆነ ባልሆነው ጊዜውን እንዳንሻማ በማለት ነው። የምናውቃቸው ሰዎች ስም በሚዲያ ከተነሳና መልስ መስጠት ያለባቸው ጉዳይ እንዳለ ከተሰማን፤ ለዚሁ ሰው መንገር መልካም ነው። ሰውየው መልስ መስጠት በማይችልበት ሁኔታ ላይ ካልሆነ በስተቀር፤ ሰውየውን ወክለን መልስ መስጠት ግን አግባብ  አይመስለኝም። “የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ” እንዳይሆን ነገሩ።
መንግስት “የአገልጋይነት መንፈስን” እያቀነቀነ ነው። እኛም ይሄን “ዜማ” መዘመር አለብን። መንግስትን ቃሉን እንዲተገብር መወትወት፤ ማበረታታትና ማገዝ ተገቢ ይሆናል።  የምንሰጠው አስተያየትና ድጋፍ የሚያጎብጠው ሳይሆን፤ የሚያቃናውና እንዲበረታታ የሚያደርገው መሆን አለበት። ነገሮች መስመር ሲስቱ ደግሞ የተጠያቂነት በትራችንን ማንሳቱ ተገቢ ይሆናል።
ሸገርን በጥሩ ተምሳሌትነት አነሳሁ እንጂ ሌሎች ጣቢያዎችም ተመሳሳይ ፕሮግራሞች እንዳሏቸው በጨረፍታም ቢሆን አውቃለሁ። እነዚህን ፕሮግራሞች ማበረታታት፤ ትክክለኛ መረጃ መስጠትና አስፈላጊውን የገንዘብም ሆነ የቁስ ደጋፍ ማድረግ የኛ የተገልጋዮቹ ሃላፊነት ሆኖ ይሰማኛል።
በመጨረሻ ማንሳት የምፈልገው ስለ ስፖንሰር አድራጊዎቹ ድርጅቶች ነው። በእውነቱ የአዲስ ባንክ ማስታወቂያ ስሰማ የ”ማንን ምን እንጠይቅልዎ?” ፕሮግራም የሚከተል እየመሰለኝ ደስ ደስ ይለኛል። እንዲህ ነው እንግዲህ አዕምሮን መግዛት ማለት። ልክ እንደ “ሃይላንድ፤ ኦሞ፤ አምቦ ውሃ” ማለት ነው። ስለ ስፖንሰር ምን አልባት ወደፊት እጽፋለሁ። አዲስ ባንክ ”ማንን ምን እንጠይቅልዎ?” ፕሮግራምን በመደገፍ በጥሩ ምሳሌነት ይጠቀሳል፡፡ አሁን ደግሞ ጸሃይ ሪል እስቴት ተቀላቅሎታል። ሁለቱም ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
ማስታወሻ፡ ይህ መጣጥፍ ከአራት ወራት በፊት የተጻፈ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሸገሮች እንኳን ለ15ኛ አመት ልደታችሁ አደረሳችሁ፡፡

Read 8034 times