Print this page
Tuesday, 18 October 2022 07:53

የህፃናቱ ግድያ ከሥነልቦና አንፃር ሲታይ

Written by  ከአልታ ካውንስሊንግ
Rate this item
(1 Vote)

  መወሰድ የሚገባቸው እርምጃዎችና ጥንቃቄዎች
                     
         ክፍል- 3
በዚህ የመጨረሻ ክፍል ግድያ በሚፈፅሙ አካላት ላይ መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች፤ ወላጆች፣ ማህበረሰብ፣ የድለላ ስራ የሚሰሩ፣ የህግ አካላት ወዘተ ምን አይነት ሃላፊነትና ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው የአለም አቀፍ ተሞክሮን ጨምረን እናቀርባለን፡፡
በመጀመሪያ ግን እንደዚህ አይነት አሰቃቂ ግድያዎች ሲፈጠሩ በወላጆችና በማህበረሰብ ላይ የሚፈጥሩትን አሉታዊ ተፅእኖዎች በጥቂቱ እንመልከት፡፡
ወላጆች ልጆችን ለሰራተኛ ጥሎ መሄድ እንዲፈሩና እንዲሰጉ ያደርጋቸዋል፡- ዜናውን የሰሙ ወላጆች ልጆቻቸው በቤት ሰራተኞቻቸው ተመሳሳይ ጉዳት የሚደርስባቸው ስለሚመስላቸው ይፈራሉ፤ ይሰጋሉ፤ ይጨነቃሉ። አንዲት ያነጋገርናት የሰባት ወር ነፍሰጡርና የሁለት ልጆች እናት አንዲህ ብላለች፡- “የሰሞኑን የህፃናቱን ግድያ የተመለከትኩት ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ  እንቅልፍ እንቢ ብሎኝ የእጅ ስልኬን አንስቼ ፌስ ቡክ ስከፍት ነበር፡፡ ዜናውን እንዳነበብኩ በፍጥነት  ከተኛሁበት ተነስቼ ሌላ ክፍል የተኛችውን የ9 ዓመት ልጄን ከእንቅልፏ ቀስቅሼ እኔ ያለሁበት ክፍል እየጎተትኩ አምጥቼ አጠገቤ አስተኛኋት፤ ልጄን ጎትቼ አጠገቤ ሳስተኛት በቅጡም ከእንቅልፏ አልነቃችም፤ በጣም ተረበሽኩ፤ ፈራሁም፡፡” ብላለች፡፡
ማህበረሰቡ ለቤት ሰራተኞች  መጥፎ የሆነ (አሉታዊ ) አመለካከት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡  ይሄም የማህበራዊ ድሩን (Social fabric) እንዲሳሳ ያደርገዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን በሐገር ውስጥም ሆነ በተለያዩ የውጭ ሀገራት ለሚኖሩ የቤት ሰራተኞች መጥፎ አመለካከት እንዲኖር ያደርጋል፡፡ በተለይም በዚህ በግሎባላይዜሽን ዘመን ዜናዎች በፍጥነትና በስፋት ስለሚሰሙ  በአረብ አገር ለሚኖሩና ለሚሰሩ ሴት እህቶቻችን በመጥፎና በጭካኔ እንዲሳሉ የሚያደርጋቸው ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አረብ ኒውስ (Arab News) እ.ኤ.አ. ጁላይ 20, 2013 ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት ባወጣው ዘገባ፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያዊ የሆኑ የቤት ሰራተኞች አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ሁለት ሴት ህፃናትን በመግደላቸው የተነሳ  በርካታ ቁጥር ያላቸው የሳውዲ ቤተሰቦች ከኢትዮጵያ የመጡ የቤት ሰራተኞችን ከሥራ ያሰናበቱ መሆኑን በድረ-ገፁ ዘግቧል፡፡ የሥራና የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ግድያው እስኪጣራ ድረስ ከአፍሪካ አገራት ለቤት ሰራተኞች የሚሰጥ አዲስ ቪዛ ለጊዜው እንዲታገድ መወሰኑን ገልጾ ነበር። የመጀመሪያው አጋጣሚ የግድያው ሰለባ የሆነችው የሳውዲ ዜግነት ያላት ላሚስ አል ሳልማን (Lamis Al-Salman)   የተባለች የ6 ዓመት ህፃን ስትሆን፤ ሁለተኛዋ ደግሞ የ10 ዓመት እድሜ ያላትና የሶርያ ዜግነት ያላት ኢስራ (Israa) የተባለች ህፃን እንደሆነች ዘግቧል። ሁለተኛዋ ህፃን የተገደለችው በብረት አናቷ ላይ ተመትታ መሆኑን ዘገባው ጠቅሷል፡፡ ሆኖም ዘገባው በገዳዮቹ ላይ የተፈፀመውን ፍርድም ሆነ ስነልቦናዊ ትንታኔ አልሰጠም፡፡
የቤት ሰራተኞችን ለስራ አጥነት ሊዳርግ ይችላል፡- እንዲህ አይነት የጭካኔ ድርጊቶች አንዳንድ ወላጆች የቤት ሰራተኛ መቅጠርን እርም አድርገው የመተው ነገር ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል፡፡ የቤት ሰራተኞችም ተቀባይነታቸው እየቀነሰ ስለሚሄድ ቶሎ ሥራ የማግኘትና የመቀጠር ሁኔታን ይቀንሳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሙያቸው ጠዋት ወጥተው ሰርተው ማታ ተረጋግተው ሲመለሱ የነበሩ እናቶች፤ የሚሰሩትን ስራ በመተው (በመልቀቅ) ቤት ቁጭ ብለው ልጆቻቸውን የማሳደግ ሃላፊነት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡
ችግሩን ለመፍታት ምን መደረግ አለበት?
እንዲህ አይነት አሰቃቂ ግድያዎች ሲፈፀሙ በወላጆች ላይ የሚደርሰው ስነልቦናዊ ጉዳት በቃላት መግለፅ ይከብዳል፣ ህመማቸውንና ስቃያቸውን በእነሱ ጫማ ውስጥ ሆኖ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በሰራተኞች የሚሰጡት ምንም አይነት ምክንያቶች እንኳን ቢኖሩ ፈፅሞ ለእንደዚህ አይነት ድርጊት ሊዳርጉ አይገባም። ይህ በቀላሉ የማይታይ አሰቃቂ ወንጀል ነው። አንዳንዴም ከአሰሪዎች በኩል ምንም አይነት አሉታዊ ተፅእኖ በሰራተኞች ላይ ሳይደርስ በሌላ ፍላጎትና ረብ በሌለው የግል ፍላጎት እንደዚህ አይነት ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ሊፈፀም ይችላል፡፡
እንዲህ  የተከሰቱትንም ሆነ ሊከሰቱ የሚችሉ  ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ አካላት ሊወጡ ስለሚገባቸው ሃላፊነት ከዚህ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡
ከሕግ አንፃር
የፖሊስ አካላት ለሚደርሷቸው ጥቆማዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል፡:
የህክምና ተቋማት ለወንጀል ምርመራ የሚያግዙ ተግባራትን በወቅቱ፣ በብቃትና  በታማኝነት ሊያቀርቡ ይገባል፡፡
በፍርድ ቤት የሚወሰኑ ውሳኔዎች ለሌሎችም ትምህርት ሊሆን በሚያስችል መልኩ መወሰን ይኖርባቸዋል፡፡ ማጤን የሚገባው አብዛኛዎቹ እንዲህ አይነት ግድያዎች የአዕምሮ ህመም ባለባቸው ሰዎች የሚፈፀሙ  ባለመሆናቸው ተገቢውን ምርመራ ማድረግና አስተማሪ ቅጣት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም የህግ አካላት በስነልቦና ባለሙያዎች ቢታገዙ የተሻለ ይሆናል፡፡
ከስነልቦና አንፃር
ጉዳት የደረሰባቸው ወላጆች ድህረ-ቀውስ እርዳታ (Post Traumatic stress Disorder) እንዲያገኙ ማድረግ፡፡ በዚህ አጋጣሚ አልታ ካውንስሊንግ በዚህ ሁኔታ ላለፉ ወላጆች በራሱ ባለሙያዎች  ነፃ የስነልቦና ህክምና እንዲያገኙ ፈቃደኛነቱን በክፍል 1 ፅሑፋችን ገልጧል፡፡
ወላጆች ለሰራተኞቻቸው ተገቢውን ፍቅርና እንክብካቤ እንዲሰጡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በአንድ ቤት ውስጥ  በዳይና ተበዳይ እንዳይኖር ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ወላጆችና የቤት ሰራተኞች ልዩነቶቻቸውን ሁልጊዜ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መሞከር ያስፈልጋቸዋል፡፡ አብሮ መኖር የሚያስችል ሁኔታ የሌለ መስሎ ሲታይ አስፈላጊውን ክፍያ ፈፅሞ ለመለያየት መወሰን ያስፈልጋል፡:
ልጆች ስለደረሰባቸው ጉዳት ለወላጆች እንዲያሳውቁ ማሰልጠን ያስፈልጋል። ከሞት መለስ በርካታ ጉዳቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ ወላጆች ልጆቻቸው በግልፅና በድፍረት የደረሰባቸውን  ነገር እንዲያወሩ ስልጠና መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡
ከሰራተኛ አገኛኝ ኤጀንሲዎች ደላላዎች አንፃር  
የቤት ሰራተኞችንና አሰሪዎችን የሚያገናኝ አካል በተቋም ደረጃ  የተደራጀ ቢሆንና  የቤት ሰራተኞች ስለሚጠበቅባቸው ሃላፊነቶችና ግዴታዎች  ስልጠና  እየሰጠ፣ አስተሳሰባቸውና ባህሪያቸው ላይ በአግባቡ ሰርቶ ቢያሰማራቸው  ይመከራል፡፡
አሰሪዎችም ስለሚጠበቅባቸው ሃላፊነቶችና ግዴታዎች (የደመወዝ ክፍያ ቀንን፣ የዕረፍት ቀንን ወዘተ) በተመለከተ ግልፅ ንግግርና ውል ቢደረግ፡:
ወላጆች ማወቅና መተግበር የሚገባቸው ነገሮች፡-
አሰሪዎች ከሰራተኞች  የሚጠበቁትን ነገሮች በግልፅ ማሳወቅና መሰረታዊ ህጎችን በመሃላቸው ሊያዘጋጁ ይገባል፤
ለሰራተኞቻቸው ክብርና ነፃነት  መስጠት ይኖርባቸዋል፤ መብቶቻቸውንም ማክበር ያስፈልጋል፤
ግልፅ የሆነ ተግባቦት በመሃላቸው ሊኖር ይገባል፤
የእርስ በእርስ መተማመንና መረዳዳትን ማዳበር ይኖርባቸዋል፤
ሰራተኞቹ የመጡበትን ባህልና ማህበረሰብ መረዳት ያስፈልጋል፤
ቤት ውስጥ የሚታዩ ፊልሞችንና የሚዲያ ውጤቶችን መወሰን ይጠበቅባቸዋል። አንዳንዴ ጠብ አጫሪነትንና ወንጀልን የሚያበረታቱ የቴሌቪዝን ፕሮግራሞች ተመሳሳይ ባህሪን በሰዎች ላይ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ቤት ውስጥ እነዚህ የቤት ሰራተኞች ከህፃናቱ ጋር ሲውሉ ምን እያዩና እየሰሙ  እንደሚውሉ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
መልካም የቤት ሰራተኞች እንዳሉ ሁሉ መጥፎዎችም እንደሚኖሩ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በመጨረሻም የሚዲያ አካላት እንዲህ አይነት ጭካኔ የተሞላባቸው ድርጊቶች ሲፈፀሙ የፍርድ ሂደቱን ተከታትለው ለህዝብ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፤ ድርጊቱንም መኮነንና በድርጊቱ ዙሪያ የተለያዩ ባለሙያዎችን በማወያየት ችግሩን እንዲቀንስና ዘለቄታዊ መፍትሄ እንዲያገኝ  ተግተው መስራት  ይጠበቅባቸዋል እንላለን፡፡
ቸር እንሰንብት!
አልታ ካውንስሊንግን በኢ-ሜይል አድራሻው: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡
ማስታወሻ፡- በዚህ ጽሁፍ ሃዊ ሽጉጥ- ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት፣ ብሩክ ገ/ማርያም- ዴቨሎፕመንታል ሳይኮሎጂስት፣ ወንድወሰን ተሾመ- ካውንስሊንግ ሳይኮሎጂስት ተሳትፈዋል።




Read 1826 times