Saturday, 22 October 2022 14:15

በማሊ የስደተኛ ኢትዮጵያውያን ተጨማሪ አስክሬን እየተገኘ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

- በጅምላ ግድያ የተጠረጠሩት፣ በአካባቢው የነበሩ ኢትዮያውያን ናቸው።
- ከግድያው ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 72 ኢትዮጵያውያን እንደታሰሩ የአገሪቱ ፖሊስ ተናግሯል።
-የኢትዮጵያ መንግስት ስለ ጉዳዩ ምርመራ እያደረግኩ ነው ብሏል።
- ተጨማሪ የጅምላ መቃብር እንደተገኘና የአራት ኢትዮጵያውያን አስክሬን መውጣቱም ተገልጿል።

የ25 ስደተኛ ኢትዮጵያውያን አስክሬን በጅምላ መቃብር በተገኘበት በሰሜን ማላዊ የጅምላ መቃብርና አስክሬን እየተገኘ እንደሆነ ተገለፀ፡፡ ከዋና ከተማ ከሉሎንግዌ  250 ኪሜ ርቀት ላይ በሚገኝ  ጥብቅ ደን ውስጥ የጅምላ መቃብር ያገኙት፣ በዱር ማር ለቀማ ላይ የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው፡፡
ሟቾቹ ወጣቶች ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ በማላዊ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሻገር የሞከሩ ህገ-ወጥ ስደተኞች ናቸው ብለዋል። የማላዊ ፖሊስ ቃል አቀባይ አስክሬኖቹ ከተቀበሩ በርካታ ቀናት በማስቆጠራቸው ሳቢያ እየፈረሱ ቢሆንም ቡድኑ ተቆፍሮ ከወጣ በኋላ ምርመራ እየተካሄደ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በ1 ወር ጊዜ ውስጥ የተፈጸመ ተግባር ይመስላል ብለዋል፡፡  ስደተኞቹ የሞቱት በተሸፈነ መኪና ውስጥ ሲጓዙ በአየር እጥረት ታፍነው ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ከአህጉሪቱ በተሻለ በኢንዱስትሪ የበለፀገችው ደቡብ አፍሪካ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከምስራቅ አፍሪካ ጭምር ድህነት የተጫናቸው ወጣቶች የሚሰደዱባት ቀዳሚ አገር ነች፡፡ ማላዊ ደግሞ ተመራጭ አቋራጭ ነች፡፡ ባለፈው ሀምሌ ወር የሀገሪቱ ፖሊስ በአንድ ሽፍን የጭነት መኪና ተሳፍረው የነበሩ 42 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን እንደያዘ ገልጾ ነበር።  ከጥር እስከ መስከረም ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ 221 ስደተኞች የማላዊን ድንበር አቋርጠው ሲያልፉ ተይዘዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 186ቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡
እንደ ከብት  ገበያ ታዳጊ ልጆች በግላጭ እየተሸጡና ለግዳጅ ስራ እና ለወሲብ ንግድ  እንደሚዳረጉ በተባበሩት መንግስታት የመድኃኒትና የወንጀል ጽ/ቤት (ዩኤን ኦዲሲ) ገልጿል።
ከ25 ዓመታት በፊት የተቋቋመው የድዜሌካ የስደተኞች ካምፕ በማላዊ ትልቁ ሲሆን 50 ሺህ ስደተኞችን ይዟል፡፡ ካምፑ የተቋቋመው አስር ሺህ ሰዎችን ለመያዝ ነበር፡፡   



Read 10993 times