Saturday, 22 October 2022 16:40

የዋጋ ንረትና የዶላር እጥረት የዓመቱ ፈተናዎች ናቸው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የስኳር ምርት ላይ ለውጥ ማምጣት ባይቻልም፣ የስንዴ እርሻ እንደተሻሻለ ተገልጿል።
የስንዴ ምርት ላይ እየታየ የመጣው እድገት በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል- የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት።
በዓመት ለውጭ ዕዳ 2 ቢሊዮን ዶላር መንግስት ከፍሏል (ለወለድና ለዋናው)።
እንዳለፉት ዓመታት ባለፈው ዓመትም፣ 500 ሚሊዮን (ግማሽ ቢሊዮን) ዶላሩ ለወለድ የተከፈለ ነው።
እስከ ዛሬ ባልታየ ሁኔታ፣ የመንግስት የውጭ እዳ፣ በግማሽ ቢሊዮን ዶላር ገደማ ቀንሷል።
ነገር ግን፣ ከዚህ ጎን ለጎን ከፍተኛ የዶላር እጥረት ተፈጥሯል።

የመንግስት የውጭ እዳ ሪፖርት ላይ እንደተገለጸው፤ ባለፈው ዓመት ከውጭ አገራትና ከዓለማቀፍ ተቋማት የተገኘው ብድር፣ ከ800 ሚሊዮን ዶላር በታች ነው።
ቀደም ባሉት ዓመታት፣ መንግስት በየዓመቱ ከ2 ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ ብድር ያገኝ ነበር።
በየዓመቱ ለእዳና ለወለድ ከሚያወጣው ወጪ ጋር የተቀራረበ ወይም የበለጠ ብድር ሲያገኝ የነበረው የኢትዮጵያ መንግስት፣ ባለፈው ዓመት በብድር እጥረት ክፉኛ ተቸግሯል። የዕዳ ክምችቱን ለማርገብ ብቻ ሳይሆን፣ ለመቀነስም ችሏል።
ነገር ግን፣ በዶላር እጥረትም ክፉኛ ተወጥሯል። ከሰሞኑም በበርካታ ቁሳቁሶች ላይ፣  የውጭ ንግድ ጊዜዊ እገዳ ጥሏል።
ከዚህ ጎን ለጎን፣ ከውጭ የሚመጣ ብድርና ወደ አገር የሚገባ ሸቀጥ ሲቀንስ፣ የገበያ እጥረት ላይ የራሱን ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም።
የኮረና ወረርሽኝ፣ የአገር አለመረጋጋትና ግጭት፣ ከዚያም የጦርነት ምስቅልቅልተጨምሮበት፣… የራሺያና ዩክሬን ግጭትም ከአለማቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ ጋር ተደማምሮ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ብዙ ፈተናዎች ተደራርበውበታል።
ትልቁ ፈተናውም፣ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ሆኗል።
በ2010 ዓመተ ምህረት፣ 100 ብር ገደማ የሚፈጅ ሸቀጥ፣ ዛሬ በአማካይ ከ300 ብር በላይ ዋጋው እንደናረ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን ወርሃዊ መረጃዎች ይገልጻሉ።
ከቅርብ ወራት ወዲህ፣ የዋጋ ንረቱ ባይቀንስም፣ የንረቱ ግልቢያ የመርገብ ምልክት ያሳያል።
እንዲያም ሆኖ ዓመታዊው  የዋጋ ንረት፣ አሁንም 30 በመቶ ገደማ ላይ እንደሆነ የመስከረም ወር ሪፖርት ያመለክታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዶላር እጥረትንና የዋጋ ንረትን ለማቃለል፣ የአገር ምርትን ማሳደግና የኤክስፖርት እድሎችን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ባንክ ጠቅሷል።
የስኳር ምርት ለውጥ ባይታይበትም፣ የስንዴ ምርት ግን ለኤክስፖርት ሊተርፍ ይችላል ብለዋል።

Read 11230 times