Saturday, 22 October 2022 16:59

አጎንብሶ የሚበላን ተኝተህ ቀላውጠው!

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ለምድር ለሰማይ የከበዱ፣ እጅግ ሀብታም ፊታውራሪ በአንድ ከተማ ይኖሩ ነበረ። የእኚህ ባለፀጋ ላሞችና ከብቶች ሥፍር ቁጥር የላቸውም ይባልላቸው ነበር። ታዲያ ከብቶችንና ላሞችን ጠዋት ከግቢው የሚያስወጣና የሚያሰማራ፣ ማታም ወደ ውሃ መጠጫቸው ቢርካ ወስዶ አጠጥቶ የሚመልሳቸው፣ ከፊታውራሪ ዘንድ የሚኖር ሠጠኝ የሚባል ታማኝ አገልጋይ እረኛ አለ።
አንድ ቀን ፊታውራሪ፡
“ሠጠኝ” ሲሉ ይጠሩታል።
ሠጠኝ፣
“አቤት ጌታዬ ምን ልታዘዝ?” ብሎ መጣ።
ፊታውራሪ፤
“ለብዙ ጊዜ እኔን በታማኝነት አገልግለሃል። አንድም ቀን ምንም ጉድለት ሳይታይብህ፣ በጨዋነት ከብቶቼን ስታግድድ ኖረሃልና ሽልማት ይገባሃል። በል ይቺን ጥጃ ወስደህ አሳድገህ ተጠቀምባት። ከዛሬ ጀምሮ ንብረትህ ናት” ብለው አንድ ቆንጆ ጥጃ ሸለሙት።
ሠጠኝም ከዚያን ጊዜ ወዲህ ያቺን ጥጃ ከፊታውራሪ ከብቶች ጋር ቀላቅሎ እያገደ ኑሮውን ቀጠለ።
አንድ ቀን አንድ የሌላ አገር ደጃችማች፣ በእንግድነት ወደ ፊታውራ ሰፈር መጡ። በፊታውራሪ ከብቶች ብዛት እጅግ ተደንቀው፤
“ሰማህ ወይ! የኔ ልጅ?” አሉ።
ሠጠኝም፤
“አቤት አባባ?”
ደጃዝማች፣
“ለመሆኑ የነዚህን ከብቶች ቁጥር ታውቃለህ?”
ሠጠኝ፣
“አዎን ጌታዬ፣ አሳምሬ አውቃለሁ”
ደጃዝማች፤
“ስንት ይሆናል?”
“ከሁለት መቶ ከፍ፣ ከሶስት መቶ ዝቅ ይላል”
“ለመሆኑ ከብቶቹ የማን ናቸው?”
ሰጠኝም በኩራት ትከሻቸውን ከፍ ዝቅ እያደረገ፣
“የእኔና የፊታውራሪ ናቸው!” አለ ይባላል።
***
ሰው ምንጊዜም ለራሱ አዎንታዊ ምልክት መስጠቱ የተለመደ ነው።
አዳም ስሚዝ የተባለው ዕውቅ የኢኮኖሚ ባለሙያ፤
“Human wants are unlimited” ሲል ነው ትንታኔውን የሚጀምረው። የሰው ልጅ ፍላጎት ወሰን አልባ ነው፤ እንደማለት ነው።
 አንድ ህጻን ልጅ “አሻንጉሊት እፈልጋለሁ” ብሎ አሻንጉሊት ሲገዙለት በዚያ አያቆምም። ደግሞ “ብስክሌት ግዙልኝ” ይላል። ብስክሌት ሲገዙለት ሞተር ብስክሌት ይጠይቃል። ከሞተር ብስክሌት ወደ መኪና ጥያቄም ይሸጋገራል።
ፍላጎት ቋሚ አይደለም። የሰው ልጅ ፍላጎት ወሰን የለሽ ነው። ከላይ የጠቀስነው እረኛም በአንዲት ጥጃ ተወስኖ አይቀርም።
ከዚህ የኢኮኖሚ ጠበብት ትንታኔ ተነስተን በአገር ደረጃ የሚታየውን የፍላጎትና የአቅርቦት አለመመጣጠን ለማስተዋል ቀላል ነው።
የዋጋ መናርና የሰው የመግዛት አቅም ማሽቆልቆል ሲታይ ህዝብን ማስመረሩ አያጠራጥርም። መንግስትን መጠየቁ መልስ ካላገኘንም ለአመጽ መነሳሳቱ በታሪክ የታየ እውነታ ነው።
የኢኮኖሚያዊ ብሶት ሲጠራቀም ወደ ፖለቲካዊ ቀውስ ያመራል። ውሎ አድሮም ዋነኛውን የመንግስት መቀመጫ ወንበር መነቅነቅና የስልጣኑን መንበር ማናጋት መጀመሩ አይቀሬ ሀቅ ይሆናል።
 በ1966 ዓ.ም የነበረው የአብዮት እንቅስቃሴ እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ ዙፋኑን እስከመገርሰስ የደረሰው በመሰረቱ በኑሮ ውድነት ሳቢያ ነው።
የወጣት ተማሪዎች፣ የመምህራን፣ የሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማም፣ የሃይማኖት ቅሬታ ሰላማዊ ሰልፎች መባባስ፣ የጭቁን ወታደሮች ንቅናቄ ወዘተ… ነባራዊውንና ህሊናዊውን እንቅስቃሴ እያጎመራው መምጣቱ፣ በየቦታው ከተከሰተው የአርሶ አደሮች እምቢተኝነት ጋር ተደምሮ ለገዢው መደብ እንቅልፍ ማጣት ምክንያት ሆነ።
በዚያ ላይ የአርነትና የነጻነት እንቅስቃሴዎች ከቀን ቀን እየተጋጋሉ መሄዳቸው እስከዛሬም ያልበረደ እሳትና እስከዛሬም ያልተዘጋ ፋይል እንደሆነ ይታወቃል።
ማናቸውም መንግስት ያለፈውን ታሪክ መለስ ብሎ ማጤን ግዴታው ነው።
የታዩ ድክመቶችን መመርመርና ማከም፣ ጠንካራ ጎኖችን ለይቶ ማጎልበት አለበት። በየጊዜው በተደጋጋሚ የታየው የገዢው መደብ ህጸጽ አንድም ከንቀት፣ አንድም ከምንግዴነት፣ ሁለትም ከአምባ ገነናዊ እብሪት የመነጨ ነው ለማለት ያስደፍራል። የዕውቀት ብቃት ማነስ ሌላው ግዙፍ አባዜ ነው! ይህን አባዜ ሠንኮፉን ነቅሎ በመጣል ረገድ የትምህርት ሚና አሌ አይባልም።
ምንጊዜም መማር፣ መማር አሁንም መማር ግዴታ ነው!
በመማር ላይ ጥበብን (Wisdom) ካከልንበት ወደ ብስለትና ልማት መሸጋገሪያውን መሰላል ጨብጠናል ማለት ነው!
ያለ መላ፣ ያለ ዘዴ ግብን ለመጎናጸፍ አይቻለንም። “ከጋላቢ ፈረስ፣ መንገድ የምታውቅ አይጥ ትበልጣለች” ይባላል።
ምንጊዜም ብልሃትን መንተራስ ወደ አለምነው ሰፈር ያደርሰናል። ጉልበት አብዛኛውን ጊዜ አዋጭ ስልት አይሆነንም።
ጉዟችን ሩቅ ነው የምንል ከሆነ ትዕግስት ብልሃት ነው መፍትሄአችን። ሳናስብና ሳናስተውል አንጓዝ።
ሌሎች ሊጠቀሙብን ሲያስቡ መፍጠንና መቅደም ይገባናል።
 “አጎንብሶ የሚበላን ተኝተህ ቀላውጠው” የሚባለው የአበው ብሂል የተተረተው ይሄንን ሁሉ አካቶ መሆኑን አንዘንጋው!


Read 11689 times