Print this page
Saturday, 22 October 2022 17:01

22ኛው የዓለም ዋንጫ በኳታር

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 አዳዲስ ታሪኮችና ክብረወሰኖች ይመዘገቡበታል፡፡
አዲስ አድማስ ከኢትዮጵያ ከተጋበዙት ሚዲያዎች አንዱ ነው፡፡
በትንበያ እየተሟሟቀ ነው፡፡ አርጀንቲና፤ ብራዚል፤ ፈረንሳይና ጀርመን ለዋንጫው ተጠብቀዋል፡
 

ከ5 ቢሊዮን በላይ ተመልካች፤ ከ7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ
22ኛው የዓለም ዋንጫ አንድ ወር የቀረው ሲሆን አዘጋጇ ኳታር በአረቡ ዓለም በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ዓለም ዋንጫን በማስተናገዷ አዳዲስ ታሪኮችና ክብረወሰኖችን የምታስመዘግብ ይሆናል፡፡ በኤስያ አህጉር ዓለም ዋንጫውን በማስተናገድ ሶስተኛዋ አገር ናት፡፡  በ2002 እኤአ ላይ 17ኛውን የዓለም ዋንጫ  ደቡብ ኮርያና ጃፓን  በጋራ ማስተናገዳቸው ይታወቃል፡፡
የዓለም ዋንጫው በፈረንጆች አዲስ አመት ዋዜማ ባሉት ወራት መካሄዱም የመጀመርያው ነው፡፡ ኳታር በአዘጋጅነት ለመጀመርያ ጊዜ የዓለም ዋንጫን በመሳተፍ በታሪክ መዝገብ  ከመስፈሯም በላይ በውድድሩ ታሪክ በቆዳ ስፋቷ ትንሿ አገር ሆናም ትጠቀሳለች፡፡ የኳታር የቆዳ ስፋት of 11,000 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ሲሆን የህዝብ ብዛቷ 2.6 ሚሊዮን ነው፡፡ በ1930 እኤአ 1ኛውን የዓለም ዋንጫ ያዘጋጀችው ኡራጋይ  በ3. 5 ሚሊዮን የህዝብ ብዛቷ የያዘችው ክብረወሰን ነበር፡፡
22ኛው የዓለም ዋንጫ በከፍተኛ ወጭው   የመጀመርያ ደረጃ ላይ የሚቀመጥም ይሆናል፡፡ በስምንት ስታድዬሞች በ28 ቀናት ውስጥ ሊካሄድ በመታቀዱም አዲስ ታሪክ የሚሰራበት ነው። የዓለም ዋንጫውን መሰረተ ልማቶች ማለትም ስታድዬሞች፤ ሆቴሎች፤ የትራንስፖርት አውታሮችና መንገዶች ለመገንባት ከ220 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል 64 ጨዋታዎችን የሚያስተናግዱት ስታድዬሞች በ60 ኪሜ ራድዬስ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ይህም በተቀራራቢ የዓለም ዋንጫ አስተናጋጅ ከተሞች በመካሄድ ልዩ ያደርገዋል፡፡ ለዓለም ዋንጫው ወደ ኳታር የሚገቡ ጎብኝዎች ብዛት ከ1.5 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ተጠብቋል፡፡ በውድድሩ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ሆኖ  የሚሰፍርም ነው፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ በ22ኛው የዓለም ዋንጫ በድምሩ እስከ 5 ቢሊዮን ተመልካች እንደሚያገኝም የገመተ ሲሆን  እስከ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ሊያስገኝ እንደሚችል መጠበቁ  በውድድሩ ታሪክ አዲስ የገቢ ሪከርድ ሆኖ ሊመዘገብ የሚችል ነው፡፡
የዓለም ዋንጫው 1 ወር ሲቀረው የተሸጡት ትኬቶች ብዛት ከ3 ሚሊዮን በላይ ሆኗል፡፡ የስታድዬሞቹ ዘመናዊነት፤ የልምምድ ሜዳዎቹ መሟላት፤ ስምንቱንም ስታድዬሞች የሚያገናኙት የሜትሮ ባቡር አገልግሎቶች፤ ሰፊ የስፖርት መሰረተ ልማቶችና የአገሬው ህዝብ የመስተንግዶ ጉጉት ዓለም ዋንጫውን ስኬታማ እንደሚያደርገው ተጠብቋል፡፡ አዘጋጆቹ ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ ለዓለም ዋንጫ ጎብኝዎች ተጨማሪ 30ሺ የማረፊያ ክፍሎች ማዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል። በእነዚህ ባለሁለት መኝታ ክፍሎች በቀን እስከ 80 ዶላር ለማስከፍል ታስቧል፡፡  ሆቴሎች፤ አፓርትመንቶችና የደጋፊዎች መንደሮች ለስፖርት አፍቃሪዎች በተሟላ መንገድ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል፡፡
በትኬት ሽያጩ ላይ ከፍተኛውን ብዛት ያስመዘገቡት አገራት ኳታር፤ አሜሪካ፤ ሳውዲ አረቢያ፤ እንግሊዝ፤ ሜክሲኮ፤ ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ፤ አርጀንቲና፤ ፈረንሳይ፤ ብራዚልና ጀርመን ናቸው፡፡
  በዓለም ዋንጫ የተሟላ የጉዞ ፓኬጅ ከ240ሺ በላይ ደንበኞች መመዝገባቸው እና 64 በመቶው ከተለያዩ ዓለም ክፍሎች መውጣጣታቸው አዲስ ታሪክ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በፊፋና የኳታር ዓለም ዋንጫ የተዘጋጁት ከ168 በላይ የዓለም ዋንጫ መናሐርያ የሚሆኑ መሰረተልማቶች መስተንግዶውን የተሟላ ለማድረግ በሚችሉበት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡   ከፊፋ የደጋፊ ፌስቲቫሎች አንዱ በአል ቢዳዳ ፓርክ የተዘጋጀውና በግዙፉነቱ የሚጠቀሰው ሲሆን በየቀኑ እስከ 40ሺ ተመልካች የሚያስተናግድ ይሆናል፡፡
አዲስ አድማስን ጨምሮ  ከ12 ሺ በላይ የዓለም ሚዲያዎች
በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ከ12,000 በላይ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞች፤ ቴክኒሻኖች፤ ፎቶግራፍ አንሺዎችና እንደሚገኙ ይጠበቃል። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ለአባል አገራቱ በሚሰጠው ኮታ ከኢትዮጵያ የህትመት ሚዲያዎች መካከል ሳምንታዊው የአማርኛ ጋዜጣ አዲስ አድማስና ታዋቂዎቹ የስፖርት ጋዜጦች ሃትሪክናና ሊግም ውድድሩን በስፍራው ተገኝተው እንዲዘግቡ በፊፋ እና በእግር ኳስ ፌደሬሽን ተጋብዘዋል፡፡
22ኛውን የዓለም ዋንጫን በኳታር ተገኝቶ ለኢትዮጲያውያን በልዩ ሁኔታ ለመዘገብ በኢትዮጵያ  እግር ኳስ ፌደሬሽን የተመረጥኩት የዚህ የስፖርት አድማስ አዘጋጅ ግሩም ሰይፉ ነኝ፡፡ እግር ኳስ ፌደሬሽኑ ለሚመለከው ሁሉ ብሎ በፃፈልኝ የድጋፍ ደብዳቤ በተሳካና ባማረ መልኩ የውድድሩን እውነታ ፍንትው አድርጎ ለመዘገብ ብቁ ዝግጅት እንዳደርግ አሳስቦ፤ በዝግጅት የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን ለማሟላት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ አስፈላጊ ድጋፍ እና ትብብር እንዲያደርጉ በስፖርት ቤተሰቡ ስም በአክብሮት ጠይቋል፡፡ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበርና (FIFA) በኳታር የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴም በተላከ ኦፊሴላዊ አክሪድቴሽን  ኢትዮጵያን በሚዲያው ዘርፍ ወክዬ እንድሰራ በደብዳቤ የተጋበዝኩ ሲሆን፤ በ2022 የፊፋ የዓለም ዋንጫ ላይ እርስዎን ለማየት በጉጉት እንጠባበቃለን የሚል መልዕክት አድርሰውኛል።
በኢትዮጲያ እግር ኳስ ፌደሬሽን፤ በፊፋና በኳታር ዓለም ዋንጫ የተገኘውን እድል በመጠቀም ከአዲስ አድማስ ጋር በስፖንሰርሺፕ ድጋፍ የሚሰሩ ኩባንያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ በዓለም ዋንጫ ላይ በሚዲያ ዘርፍ ለመስራት እነዚህን ድጋፍ ሰጭ ተቋማት ማፈላለጉ ፈታኝ ነው፡፡ ስፖንሰሩ የሚዲያ ተቋሙን የየደርሶ መልስ የአየር ትኬት፤ በኳታር ለ1 ወራት የሚደረግ ቆይታና ሌሎችንም ወጭዎች በመሸፈን ብዙ ጥቅም ሊያገኝ ይችላል፡፡ ከዓለም ዋንጫው በፊት፤ በዓለም ዋንጫው ወቅትና ከዓለም ዋንጫ በፊት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ፤ በድረገፁና በተያያዠ የማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች በሚቀርቡ ትኩስና ምርጥ የዓለም ዋንጫ ዘገባዎች ይመሰገናል ይተዋወቃል፡፡ በየአራት ዓመቱ ለሚካሄደው ዓለም ዋንጫ ፊፋ ለአባል አገራቱ የሚዲያ ተቋማት በሚሰጠው የተሳትፎ ኮታ  ኢትዮጲያ እንድትጠቀም ያግዛል፡፡ ለስፖርት ሚዲያው እድገት፤ ዓለም አቀፍ ግንኙነት መጠናከርና ግዙፍ የስፖርት መድረኮችን ለማስተናገድ ለሚገኘው ተመክሮ ትኩረት ያስገኛል፡፡ ኢትዮጵያ ወደፊት ዓለም ዋንጫን የምትሳተፍበትን ሁኔታም በማነቃቃት ልዩ አስተዋፅኦ ያደርጋል። ስለሆነም በኳታር 22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ከአዲስ አድማስ ጋር ለመስራት የሚፈልጉ ኩባንያዎች በዚህ አጋጣሚ ጥሪ ተደርጎላቸዋል፡፡
ዓለም ዋንጫው በቀጥታ ከኳታር የዘገባ ሽፋን የሚያገኘው በእኔ ግሩም ሰይፉ ነው፡፡ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የስፖርት አምድ አዘጋጅነት እንዲሁም በሌሎች የስፖርት ጋዜጦች በመስራት ከ20 ዓመታት በላይ ልምድ አለኝ፡፡ በኳታር ከሚካሄደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ በፊት በ2008 እኤአ ላይ ቤጂንግ ባስተናገደችው 29ኛው ኦሎምፒያድ፤ በ2010 እኤአ ላይ ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችው 19ኛው የዓለም ዋንጫ፤ በ2013 እኤአ ላይ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ፤ በ2013 እኤአ ላይ በራሽያዋ መዲና ሞስኮ በተከናወነው 14ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፤ በ2014 እኤአ ላይ ደቡብ አፍሪካ ላይ  በተካሄደው 5ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ቻን  እና በ2018 እኤአ ላይ ራሽያ ባስተናገደችው 21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ለመስራት በቅቻለሁ፡፡
ከ4 ዓመታት በፊት  በፊፋ ያገኘሁትን እድል በመጠቀም ኢትዮጵያን በመወከል በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ በፍሪላንስ የፎቶ ጋዜጠኛነት ሰርቻለሁ።  ለ33 ቀናት በራሽያ  በነበረኝ ቆይታ በዋና ከተማዋ ሞስኮ በሚገኘው ሉዚሂንኪ ስታድዬምና ዓለም ዋንጫውን ባስተናገዱ ሌሎች 4 የተለያዩ ከተሞች ስፓርታክ ሞስኮ፤ ኒዚሂኒኖቭጎሮድ፤ ሴንትፒተርስበርግና ሶቺ ላይ በሚገኙ አምስት  ዘመናዊ ስታድዬሞች በመንቀሳቀስ ታሪካዊ ዘገባዎችን ሰርቻለሁ፡፡ በኢትዮጲያ የስፖርት ሚዲያ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ 12 ብሄራዊ ቡድኖችን በማሳተፍ የተካሄዱ 15 የዓለም ዋንጫ ግጥሚያዎችን ከምድብ ማጣርያው እስከ ዋንጫ ጨዋታው ተመልክቻለሁ፡፡ በፊፋ ባገኘሁት ፈቃድ መሰረት በየስታድዬሙ ገብቶ ውድድሩን በፎቶ እና በፅሁፍ ከመዘገብ ባሻገር የራሽያ ታላላቅ ከተሞችን ተዟዙሬ በመጎብኘት ከዓለም ዋንጫ ጋር የተያያዙ ከ5ሺ በላይ ፎቶዎችን አንስቻለሁ፡፡ ከዓለም ዋንጫው በፊት፤ በዓለም ዋንጫው ወቅት እና ከዓለም ዋንጫ በኋላ ሰፋፊና ልዩ ዘገባዎች፤ የጉዞ ማስታወሻዎችን በማዘጋጀት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ፤ በድረገፁ እና በሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች በተከታታይ ለንባብ አብቅቻለሁ፡፡
ብራዚል፤ አርጀንቲና፤ ፈረንሳይና ጀርመን ለዋንጫ መጠበቃቸው
22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ የሻምፒዮናነቱ እድል አውሮፓና ደቡብ አሜሪካን ከወከሉ አገራት ውጭ እንደማይሆን ነው የተጠበቀው፡፡ የዓለም ዋንጫን ውጤቶች በተለይ ደግሞ የዋንጫውን አሸናፊ የመተንበይ ባህል በ2010 እኤአ ላይ በደቡብ አፍሪካ ከተካሄደው 19ኛው የዓለም ዋንጫ ወዲህ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ዓለም ዋንጫውን በትንታኔ ከመተንበይ ባሻገር፤ ኢኮኖሚ፤ የውጤት ታሪክ፤ ወቅታዊ አቋም እና ሌሎች መሰረታዊ መስፈርቶች በማውጣት የሚሰሩ ግምቶች ለታላቁ የስፖርት መድረክ ልዩ ገፅታን እያለበሱም ቆይተዋል፡፡ ባለፉት 3 ዓለም ዋንጫዎች ትንበያው ሲካሄድ ከእንስሳት ጋር መያያዙ ያስገርማል፡፡ በ19ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ ፖል የተባለ ኦክቶፐስ ባለስምንት እግር የባህር እንስሳ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን ውጤት በመተንበይ ዝነኛ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡ ከዚያም በኋላ በብራዚልና በራሽያ በተካሄዱት 20ኛውና 21ኛው የዓለም ዋንጫዎችም የተለያዩ እንስሳት በዓለም ዋንጫ ትንበያቸው እግር ኳሱን ልዩ ድምቀት አላብሰውታል፡፡ ከ4 ዓመት በፊት በራሽያ በተዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ራብዮ የተባለ የባህር እንስሳ ከጃፓን፤ ማርከስ የተባለ አሳማ በእንግሊዝ፤ አኪሊስ የማትሰማው የተባለች ነጭ ድመት እና ሌሙር የተባለ እንስሳ በራሽያ ትንበያቸውን በማቅረብ አነጋጋሪ ሆነው ነበር፡፡
በጉግል ድረገፅ በተሰራ ትንበያ ዓለም ዋንጫው ብራዚል ከፈረንሳይ በሚያደርጉት የዋንጫ ጨዋታ እንደሚፈፀም ተገምቷል፡፡ የመረጃ ማፈላለጊያው ድረገፅ ጉጉል ይህን ትንበያ ለመስራት የተጠቀመው አሰራር  ደግሞ የተለየ ነው፡፡ የዓለም ዋንጫውን ሻምፒዮን ለመተንበይ የድረገፁ ተጠቃሚዎች  “Lusail stadium events” የሚለውን ቃል በመጨመር እንዲጠይቁ አድርጓል፡፡ የበረሃው ጌጥ በተባለው የሉስሊ ስታድዬም ለዋንጫው ጨዋታ እነማን ይገናኛሉ የሚለውን ለመገመት የተፈጠረ አሰራር ነው፡፡ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ብዙ ሰዎች ባደረጉት ጉግል ለ22ኛው የዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ብራዚል ከፈረንሳይ እንደሚፋለሙ ዜና ሆኖ በመላው ዓለም ተሰራጭቷል፡፡
በሌላ የዓለም ዋንጫ ትንበያ በተፈጠረው የአሰራር ሞዴል ደግሞ 22ኛው የዓለም ዋንጫን አርጀንቲና አሸንፋ ሜሲ ዋንጫውን እንደሚስም ነው የተጠበቀው፡፡ ተቀማጭነቱን በለንደን ያደረገው Liberum Capital Ltd  ያለፉትን ሁለት ዓለም ዋንጫዎች በሰራው የትንበያ ሞዴል በትክክል የገመተ ነው፡፡ 20ኛውን የዓለም ዋንጫ ጀርመን እንዲሁም 21ኛውን የዓለም ዋንጫ ፈረንሳይ እንደተጎናፀፏቸው ይታወቃል፡፡ በአክሲዮን ድለላ ላይ የሚሰራው  ተቋም በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ለፍፃሜ አርጀንቲና ከእንግሊዝ ለፍፃሜ እንደሚገናኙ ጠቅሷል፡፡ አርጀንቲና ከ36 ዓመታት በኋላ የዓለም ዋንጫን ታላቋን ተቀናቃኝ እንግሊዝ ትወስዳለች በሚልም ገምቷል፡፡ ለ20 ዓመታት በፋይናንስ መስክ የሰራው የኩባንያው ሰው እንደገለፀው ለዓለም ዋንጫ ትንበያው የቀረበው ሁሉ የማይሳካ ቢሆንም እንደማይገርም ነው ያብራራው፡፡ በትንበያው ሞዴል  የብሄራዊ ቡድኖችን ወቅታዊ የብቃት ደረጃ፤ የየአገራቱን ማህበራዊ ገፅታዎች፤ የአየር ሁኔታ፤ ህዝብ ብዛት፤ ኢኮኖሚና የነፍስ ወከፍ ገቢ በተለያዩ ቀመሮች እያሰላ ከምድብ ጨዋታዎች እስከ ፍፃሜው ያለውን ሂደት በመገመት ነው፡፡ ሂሳባዊ አልጎሪዝም በመጠቀም ኩባንያው ለሶስተኛ ጊዜ ዓለም ዋንጫውን በትክክል በመገመት ሃትሪክ ሊሰራበት አስቧል፡፡ በባንክ ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ በርካታ ኩባንያዎች ትልልቅ የእግር ኳስ ውድድሮችን በመተንበይ መስራታቸው ባለፉት 20 ዓመታት እየተለመደ መጥቷል፡፡
በዓለም ዋንጫ ውጤት ከፍተኛውን ክብረወሰን የያዘችው ለአምስት ጊዜያት  ያሸነፈችው ብራዚል ስትሆን 1958, 1962, 1970, 1994ና 2002 ላይ ነው፡፡ጀርመን በ1954, 1974, 1990ና 2014 እንዲሁም ጣሊያን  1934, 1938 , 1982ና 2006 ላይ ዋንጫውን ለአራት ጊዜያት በማንሳት በሁለተኛ ደረጃ ይከተላሉ፡፡ ኡራጋይ በ1930ና 1950፤ አርጀንቲና በ1978ና 1986 እንዲሁም ፈረንሳይ በ 1998ና 2018 የዓለም ሻምፒዮን ሆነዋል፡፡ እንግሊዝ በ1966 እና ስፔን  በ2010 እኤአ የዓለም ዋንጫ ባለድል ናቸው፡፡
ለ22ኛው የዓለም ዋንጫ በወጣው የምድብ ድልድል 32 ብሄራዊ ቡድኖች በስምንት ምድብ ተቀምጠዋል፡፡ ስምንቱ ምድቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡

Read 1719 times
Administrator

Latest from Administrator