Saturday, 22 October 2022 17:10

የዩክሬን ዓይንና ጆሮ - ስልክና ኢንተርኔት - የዓለማችን ቱጃርና ኩባንያው!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

(የመጀመሪያው ዓለማቀፍ የኢንተርኔትና የስልክ ኩባንያ፣ “እግረ መንገድ” የተፈጠረ ኩባንያ ነው)

ዮሃንስ ሰ


የኃያል መንግስታት ጦር ለወረራ ሲዘምት፣ ከቻለ በዋዜማው፣ ካልተሳካም ውሎ ሳያድር፣ ክንዱን የሚያሳርፍባቸው ኢላማዎች አሉ። የራዳር ጣቢያዎች፣ የአየር መከላከያ መሳሪያዎች፣ የጦር አውሮፕላን ማዕከላት፣… የማዘዣ እና የመገናኛ ተቋማት፣…
የዋዜማና መባቻ ጥቃት በአንድ በኩል የወረራ የጥቃት ዘመቻውን ለማቀላጠፍ ነው። የተቀናቃኝ ወገን ራዳሮች ከጥቅም ውጭ ከሆኑ፣ ዓይን እንደማጣት ነው። ለጥቃት የሚመጡ አውሮፕላኖችን ከርቀት ማወቅ፣ ገና ድንበር ሳይሻገሩ በፊት ማየትና መከታተል ያልቻለ  አገር፣ እንዴት ራሱን ከወረራ መከላከል ይችላል? የአየር መከላከያ መሳሪያዎችና ሚሳየሎች፣ በመጀመሪያው እለት ከወደመበት፣ የአየር ሃይል ጣቢያዎቹ ተደብድበው ከጋዩበት፣… አውላላ ሜዳ ላይ እርቃን እንደመቆም ይሆንበታል።
ሰማዩን ሁሉ በዘመቻ ዋዜማ የተቆጣጠረ ወራሪ ጦር፣ ግስጋሴውን የማሳለጥ ሰፊ እድል ያገኛል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የተቀናቃኝን እንቅስቃሴ ለማሰናከልና ለማቃወስ፣ ከተቻለም ለማፍረክረክና ለማሽመድመድ ታስበው የሚሰነዘሩ የዋዜማ ጥቃቶችም አሉ። የማዘዣና የመገናኛ ተቋማትን በፍጥነት ክፉኛ ማውደም ከተቻለ፣… የተቀናቃኝ ወታደራዊ አቅም ይፈራርሳል ማለት አይደለም። ነገር ግን፣ በተቀናጀና በተቃኘ መንገድ ወረራን መገዳደር የሚችል ቁመናው ይሰነጣጠቃል፤ መንፈሱ ይደፈርሳል። ራሱን የመግዛት ኃይል አይኖረውም።
የመንፈስ ዝግጁነትና ጽናት ቢኖረው እንኳ፣ ይደናበራል፣ ይዳከማል፤ ይንቀረፈፋል፤ ይደናቀፋል። በየት ቦታ ምን እንደፈፀመ በየት በኩል ምን እየመጣ እንደሆነ ካላወቀ፣ ወራሪዎችን የመግታት አቅም ያጣል። እውነተኛ መረጃ ካላገኘና ካልተለዋወጠ፣ አስፈላጊ ነገሮችን መጠየቅና ማሟላት፣ ትዕዛዝ ማስተላለፍና መከታተል፣ ማጓጓዝና መቀባበል ያልቻለ ጦር፣… ቆሌው የተገፈፈ፣ “የጦር ኃይል” የሚል ስያሜውን የተነጠቀ መንጋ ይሆናል። በየቦታው የተበታተነ የታጣቂ ቡድኖች ስም ዝርዝር እንጂ፣ ቅጥና ስርዓት ይዞ፣ የጊዜ ቅደም ተከተልና የቦታ ስብጥርን በህብር አቀናጅቶ የሚንቀሳቀስ ጦር ሊሆን አይችልም።
አይኑ የተጋረደ፣ አንደበቱ የተለጎመ፣ እጅና እግሩ የተሳሰረ፣ አከርካሪውና ሕብለ ሰረሰሩ የተሰበረ ይሆናል።
የራሺያ ጦር፣ አምና መጋቢት ወር ላይ በዮክሬን ላይ ለወረራ ሲታዘዝ፣ ከመጀመሪያ ተግባሮቹ መካከል፣ በአየር ኃይልና በተምዘግዛጊ ሚሳየል ያካሄዳቸው የዋዜማ ጥቃቶች ቀዳሚዎቹ ናቸው።
የታሰበውን ያህል ባይሆንም፣ የዩክሬን ራዳሮችና የአየር መከላከያ ጣቢያዎች የእሳት ዶፍ ወርዶባቸዋል። የመገናኛ ማዕከላት ተደብድበዋል። የስልክና የኢንተርኔት አውታሮችም የድርሻቸውን ተጋርተዋል። ግንኙነቶች ተበጣጥሰዋል።
ዩክሬን ሙሉ ለሙሉ ጨለማና ጭርታ ባይውጣትም፣ የመገናኛ አውታሮቿ ተቆራርጠዋል። በሚሳዬልና በጦር አውሮፕላን ድብደባ  ብዛት ስለወደሙ ብቻ አይደለም።
በኢንተርኔት አማካኝነት የሚካሄዱ የኤሌክትሮኒክስ አጥፊ ጥቃቶች፣ የስለላና  የጠለፋ ሴራዎች እንዲሁም ገመድ አልባ ግንኙነቶችን የሚረብሹ የሬዲዮ ሞገድ ማገጃ እርምጃዎችም ለዩክሬን ትልቅ ፈተና ሆነዋል። ትልቁን መፍትሄ ያገኙት፣ ከስፔስ ኤክስ መስራች ከስታር ሊንክ ፈጣሪ ከኢሎን ሞስክ ነው።
የዓለማችን ቁጥር 1 ቱጃር ነው። በኤሌክትሪክ መኪና ቴክኖሎጂዎች ዙሪያ የዓለማችን ቀዳሚ አምራች ሆኗል- ቴስላ በተሰኘ ኩባንያው።
ትዊተርን በ40 በ50 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት የጀመረውን ድርድር በእንጥልጥል በማቋረጡ ደግሞ የዓለማችን መነጋገሪያ ሆኖ ከርሟል።
ለልቡ የቀረበ የነፍስ ህልሙ ግን፣ የሕዋ ቴክኖሎጂና የጠፈር ጉዞ ነው። ወደ ሕዋ ወደ ጨረቃ ብቻ አይደለም። ከምድር ወደ ማርስ፣ መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት መጀመር ነው ሕልሙ። ምን ይህ ብቻ?
የሰው ልጅ፣ ከምድር በተጨማሪ ሌላ መጠባበቂያና አማራጭ መኖሪያ ዓለም ያስፈልገዋል ባይ ነው- ኤሎን ሞስክ።
ለዚህም፤ እስከ ዛሬ ያልተሰሩን ያልተሞከሩ ኃይለኛ ሮኬቶችን መፍጠር ይኖርበታል። እንዲሁም መንገደኞችን በብዛት ለማሳፈርና  ጓዝ ለመጫን የሚያገለግሉ ግዙፍ መንኮራኩሮችን መስራት እንዳለበት ያውቃል።
ችግሩ ምንድን ነው? የሮኬትና የመንኮራኩር ስራ በመንግስታት በጀት የታጠረ ነው። በግል ኢንቨስትመንት አልተለመደም።
ኢሎን ሞስክ ግን ገባበት። በሮኬትና በመንኮራኩር ስራ ውስጥ ሲገባ፣ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሃብት አፍስሷል። ግን በቀላሉ ከመሬት ፈቅ የሚል ስራ አይደለም። ወጪው ከባድ ነው። ምን ተሻለ?
ሮኬቶችን መስራቱ ካልቀረ፣ ወደ ጨረቃና ወደ ማርስ የሚደርሱ ሮኬቶችን ከመፈብረኩ በፊት፣ እዚህ ቅርብ ሳተላይቶችን ወደ ህዋ በማጓጓዝ መንቀሳቀሻ ገቢ ማግኘት እንዳለበት ገብቶታል። ይህም ግን በቂ አይደለም። ገበያው ትንሽ ነው። እናም ራሱ ለራሱ አዲስ ገበያ መፍጠር አለበት።
ግን ረዥም ጉዞው ወደ ማርስ ነው። እስከዚያው ግን እግረ መንገዱን፤ “ስታርሊንክ” የተሰኘ ኩባንያ አቋቋመ።
በሳተላይት የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ለመፍጠር ወሰነ። ለዚህም እልፍ ሳተላይቶችን ማምጠቅ ያስፈልጋል። አንድ ሺህ ሳተላይት? ሁለት ሺህ?
እስከ ዛሬ፣ ሕዋ ላይ የሚገኙ ሳተላይቶች ቢቆጠሩ ስንት ቢሆኑ ነው?  ስምንት ሺ? 10 ሺህ?...
የአሜሪካ፣ የአውሮፓ፣ የራሺያ፣ የቻይና፣ የጃፓን ሁሉ ተቆጥረው ማለት ነው። እና፣ አንድ ሰውዬ መጥቶ እልፍ ሳተላይችን አመጥቃለሁ ሲል ማን ያምነዋል? ብዙዎች አላመኑትም።
ኤሎን ምስክ ግን የተናገረውን ፈጽሟል። ለዩክሬን ደርሶላታል። የኢሎክ ሞስክ ሁለት ሺ ሳተላይች፣ በበርካታ አገራት ፈጣን የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል። ለዩክሬንም ጭምር። እንዲያውም፣ እስከ ዛሬ በነፃ ነበር የሚጠቀሙት።
አሁን ግን ወጪው በዛብኝ  እያለ ነው- ኤሎን ሞስክ። በየወሩ 20 ሚሊዮን ዶላር እየከሰርኩ ነው ብሏል- ቱጃሩ። እስካሁን ለዩክሬን ዜጎች፣ ለመንግስትና ለጦር ኃይል ተቋማት ነፃ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ለማቅረብ 100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አስከትሎብናል ሲልም ተናግሯል።


Read 841 times