Saturday, 22 October 2022 17:16

አጥራቸውን አልገፋን፣ ከብታቸውን አልነዳን...

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ!
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ እንዴት ሰነበትክ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምንም አልል አንድዬ፤፣ ምንም አልል።
አንድዬ፡- ምን እንደሚናፍቀኝ ታውቃለህ?...
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እንዴ አንድዬ፣ አንተም የሚናፍቅህ ነገር አለ!
አንድዬ፡- ምርመራውን ተወኝና፤ ምን ይናፍቀኛል መሰለህ? ሙሉ ለሙሉ “ደህና ነኝ” ብለህ የምትመልስበት ጊዜ።
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ደህና ነኝ እኮ... ግን ምን መሰለህ...
አንድዬ፡- ይበቃኛል ምስኪኑ ሀበሻ፣ ይበቃኛል። መልሴን አግኝቻለሁ። “ግን”... የሚሏትን ቃል ከጨመራችሁ፣ ነገር አለ ማለት ነው። ግን፣ ዛሬ ምን እግር ጣለህ? ወይስ ናፍቄህ ነው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ... ምን መሰለህ... በጣም ግራ የገባን ነገር አለ። ምን መሰለህ አንድዬ...
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ ወደ ጉዳይህ። ጊዜ የተትረፈረፈው እናንተ ዘንድ ነው እንጂ እኔ ዘንድ አይደለም።
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እሺ አንድዬ። የእነዚህ የፈረንጆች ነገር ግራ ገባን እኮ!
አንድዬ፡- ይህን ነገር ከዚህ በፊት ነግረኸኝ ነበር እኮ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አሁን አሁን፣ ነገረ ሥራቸው በዛብን አንድዬ... በጣም በዛብን!
አንድዬ፡- እኮ አንድ፣ ሁለት እያልክ አስረዳኛ። ቆይ፤ ቆየኝማ... ፈረንጅ ስትል፣ ፈረንጅ እኮ ብዙ አይነት ነው። ትኞቹን እያልከኝ ነው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እነኚህ ምዕራባውያኑን ነዋ አንድዬ! እነዚህ ሰዎች የእኛን ደግ የማይፈልጉት፣ እንደው ይህን ያህል ምን አድርገናቸው ነው? እየተጠራሩ ነው እኮ እየተረባረቡብን ያሉት!
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ... ከፈቀድክልኝ ማለት ነው።
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ!...
አንድዬ፡- እሺ እንደፈቀድክልኝ እቆጥረዋለሁ። የእነሱን ርብርብ አቆይልኝና ስለእናንተ እናውራ።
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ስለእኛ ምን፣ አንድዬ?
አንድዬ፡- መጀመሪያ እኮ... እናንተ እርስ በእርስ ገሚሳችሁ በገሚሳችሁ ላይ እየተረባረባችሁ አይደል እንዴ! ንገረኛ... የራሳችሁ ዋነኛ ጠላታችሁ እኮ ራሳችሁ ሆናችኋል። አይደለም እንዴ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እሱማ አንድዬ... እሱማ ምን ይካዳል!
አንድዬ፡- እኔ እኮ አሁን፣… ግርም እያለኝ ነው። እንደው የማትወዛገቡበት ነገር የለም ማለት ነው? በቃ፣ የመናቆሪያ ሰበብ ነው የምፈልጉት ማለት ነው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ... እሱ ነገር እኮ እኛም ግራ ገብቶናል።
አንድዬ፡- በጥቅም እየተባላችሁ፣ በዘር እየተባላችሁ፣ በጎጥ እየተባለችሁ፣ በአልከኝ/ በአልሽኝ እየተባላችሁ፣ የእናንተ በሆነውም ባልሆነውም እየተባላችሁ፣… እግዚአብሔር ያሳይህ፣… ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በእኔ ጉዳይ እየተባላችሁ... ግራ የገባው ካለማ እኔ ነኝ ግራ የገባኝ። ፈረንጅ ፈረንጅ ከማለት በፊት የራስን ቤት ማጥራት አይሻልም?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እሱ ነው እኮ ያቃተን፣ አንድዬ! እሱ ነው እኮ ያቃተን!
አንድዬ፡- መጀመሪያ ሲሞከር እኮ ነው አቃተን ማለት የሚቻለው። አይመስልህም ምስኪኑ ሀበሻ? አትስማማም?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እስማማለሁ አንድዬ።
አንድዬ፡- እሺ። እንግዲህ ልጠይቅህ። እናንተ ቤታችሁን ለማጥራት ከልባችሁ ሞክራችኋል?... ዝም አልክ እኮ ምስኪኑ ሀበሻ። ጥያቄውን ልድገምልህ እንዴ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ሰምቻለሁ አንድዬ፣ ሰምቻለሁ።
አንድዬ፡- እና...
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ... እውነት ለመናገር፣ ሞክረናል ብዬ ለማለት አልችልም።
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ የምጠላውን ነገር ነው ያመጣህብኝ።
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምን አጠፋሁ አንድዬ?
አንድዬ፡- በቀጥታ ሞክረናል ወይም አልሞከርንም እንደማለት፤ “ሞክረናል ብዬ ለማለት አልችልም” ብሎ ዙሪያ ጥምጥም መጠማዘዝ ምን ያስፈልጋል? ወይ ሞክራችኋል፣ ወይ አልሞከራችሁም።
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አልሞከርንም አንድዬ።
አንድዬ፡- ጎሽ፣ ምስኪኑ ሀበሻ! ምን መሰለህ? ሁሉም ነገር እንዲህ ፊት ለፊት በግልጽ ሲሆን፣ ነገሮች ቀላል ይሆናሉ። ምንድነው የምትሉት፣ ይሄ፣… ከከተማው አንድ ጫፍ ወደ ሌላ ጫፍ መኪኖች የሚሄዱበት እንኳን...
ምስኪኑ ሀበሻ፡- የቀለበት መንገድ?
አንድዬ፡- አዎ፣ የቀለበት መንገድ። እና የቀለበት መንገዶችን ለመኪኖቹ ተዉና ነገራችሁን ቀጥ ባለው መንገድ ውሰዱት ልልህ ፈልጌ ነው። አስቀየምኩህ እንዴ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- በጭራሽ አንድዬ፣ በጭራሽ!
አንድዬ፡- እንደው ፊትህ ኮምጨጭ ቢልብኝ እኮ ነው።
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ም... ምን መሰለህ? “አንድዬ ሳያውቅ ቀርቶ ነው እንዲህ አይነት ጥያቄ የሚጠይቀኝ” ብዬ እያሰብኩ ስለነበር ነው። አንድዬ፣ አንተ እኮ የማታውቀው ነገር የለም።
አንድዬ፡- እኔም የማላውቀው ነገር የለም እላለሁ። እናንተን በተመለከተ ግን፣ አሁን አሁን እየተጠራጠርኩ ነው።
ምስኪኑ ሀበሻ፡- የሚደብቁኝ ነገር አለ ብለህ ነው አንድዬ?
አንድዬ፡- አዎ፣ ምን ያህል ነገሮች ደብቀውኝ ይሆን እያልኩ። እንግዲህ ምስኪኑ ሀበሻ ከእኔ መደበቅ ከቻላችሁ፣ የምድሩን ደግሞ አንተ አስበው።
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ በእርግጥ ከአንተ የሚደብቁ እየመሰላቸው መከራቸውን የሚያዩ አሉ።
አንድዬ፡- አዳምጠኛ ምስኪኑ ሀበሻ! እህ ብለህ ስማኝ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ይቅርታ አንድዬ፣ አዳምጣለሁ።
አንድዬ፡- “ከአንተ የሚደብቁ እየመሰላቸው”… ትለኛለህ። እኔ እኮ የደበቁ እየመሰላቸው ሳይሆን ምንድነው የደበቁኝ እያልኩ ነው።
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ ከፈለግክ ተቆጣኝ እንጂ... በምንም መንገድ እንደእሱ የሚሆን ነገር አይደለም።
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ አንድ ቀን እነኚህን መልካም መልካም ቃላት አጠራቅሜ የሆነ ሽልማት ሳልሰጥህ አልቀርም።
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አመሰግናለሁ አንድዬ።
አንድዬ፡- ስማኝ... ስለቀለበት መንገድ ሳታውቅ ቀርተህ ነው ወይ ላልከኝ፤ አዎ አውቃለሁ። ግን ምስኪኑ ሀበሻ፣… ሁልጊዜ “አውቃለሁ አውቃለሁ” ማለት ጥሩ አይደለም። አልለቅ ያላችሁ አንዱ በሽታ እሱም አይደል!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እውነት ብለሀል አንድዬ።
አንድዬ፡- አየህ ብዙ አወቅሁ፣ አወቅሁ ሲበዛ፣… በሽታ ነው። ሻገር ሲሉ ከአንተ ብዙ እጥፍ የተሻለ የሚያውቁ መቶዎችና ሺዎች መኖራቸውን መርሳት ጥሩ አይሆንም።
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ልክ ነው አንድዬ።
አንድዬ፡- በነገራችን ላይ፣ እዚህ ሁሉ ውስጥ የገባነው ምን ማውራት ጀምረን ነበር?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ስለ ፈረንጆች ነበር አንድዬ።
አንድዬ፡- አዎ ስለ ፈረንጆች። ምን አድርገናቸው ነው የሚረባረቡብን ነው ያልከኝ፣ አይደል!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አዎ አንድዬ፣ ግራ ገባን እኮ! አሁን ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ ታውቃለህ። ደግሞ እኮ፣ የውስጥ ጉዳያችን፣ እኛንና እኛን ብቻ ነው የሚመለከተው።
አንድዬ፡- ልክ ነህ።
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እየተጠራሩ፣ እየተቀባባሉ በውስጥ ጉዳያችን እየገቡ በዛቻ ሊያስፈራሩን፣ በትዕዛዝ ሊያሯሩጡን የሚፈልጉት፣ ከእኛ ጋር ምን ቁርሾ ኖሯቸው ነው? አጥራቸውን አልገፋን፣ ከብታቸውን አልነዳን፣ ቤታቸውን አላፈረስን። እነሱ እዛ እኛ እዚህ። ምን እንሁን ብለው ነው የሚራበረቡብን?... አንድዬ ዝም አልከኝ።
አንድዬ፡- ጨርስ ብዬ ነው። ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ። በዚህ ነገር ላይ ሌላ ጊዜ ብናወራ ቅር ይልሀል?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምን ቆርጦኝ አንድዬ! ምን ቆርጦኝ ነው ቅር የሚለኝ።
አንድዬ፡- በል በሰላም ግባ።
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አሜን አንድዬ! አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1195 times