Saturday, 22 October 2022 17:21

ከ110 ሚሊዮን ህዝብ የተጣራ ውሃ የሚጠጣው 15 ሚሊዮን አይሞላም

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 መንግስት በውሃ ላይ 30 በመቶ ታክስ መጣሉ ህዝቡ የተጣራ ውሃ እንዳያገኝ አድርጎታል
- የጥሬ ዕቃ በብዙ እጥፍ መጨመር ፋብሪካዎች እንዲዘጉ አድርጓል (ጌትነት በላይ (ኢ/ር)

ሰሞኑን  ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የውሃ ማሸጊያ ፕላስቲክ ማቅለሚያ የሆነውን “ማስተርባች” የተሰኘ ግብአት ወደ ሀገር እንዳይገባ በማገዱ ምክንያት የታሸጉ ውሃዎች በተፈጥሮውና ነጭ ቀለም ባለው የውሃ ማሸጊያ ፕላስቲክ ለገበያ እየቀረቡ ይገኛሉ።
ታዲያ ይህ “ማስተርባች” የሚባለው ግብአት መቅረቱ ለዘርፉ ምን አስተዋጽኦ አለው? ምንስ ያህል የውጪ ምንዛሬ ያድናል፣ የመጠጥ አምራቾች ዋነኛ ተግዳሮቶችስ ምን ምን ናቸው ስትል የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ የኢትዮጵያ ቢቬሬጅ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማህበር የቦርድ ፕሬዚዳንት ከሆኑት ጌትነት በላይ (ኢ/ር) ጋር ተከታዩን ሰፋ ያለ ቃለ-ምልልስ አድርጋለች- እንድታነቡት ጋብዘናል።


የውሃ ማሸጊያ ፕላስቲኮችን ሰማያዊ ቀለም የሚያላብሰውን ማቅለሚያ (ማስተር ባች)ን ለማስቀረት ምን አነሳሳችሁ?
ከማስተር ባች በፊት አንድ ነገር መግለፅ እፈልጋለሁ። ቀደም ሲል የታሸጉ ውሃዎች የአንገት ላይ ሽፋን (ኔክሲል) ነበራቸው። እሱ በተለምዶ የነበረና አካባቢን ከማቆሸሽ ውጪ ሌላ ጥቅም የሌለው፣ ሰው ውሃ ለመጠጣት ፕላስቲኩን ሲከፍት የአንገት ሽፋኑን የትም እየጣለ አካባቢን በጣም የሚያቆሽሽ ነበር። ይህንን ነገር እኛ በግላችን ወደ ውጭ ሀገር ስንሄድ ስናየው የውጪዎቹ በውሃ ፕላስቲካቸው ላይ አይጠቀሙም። እኛም ይህንን ተሞክሮ አይተንም ጠይቀንም ጥቅም እንደሌለው ከተረዳን በኋላ የውሃ ማሸጊያ ፕላስቲክ ላይ ሽፋን እንዳይኖር አድርገን አስቀርተናል። የውሃ ማሸጊያ ፕላስቲክ የአንገት ላይ ሽፋን ከቀረ ከሁለት ዓመት በላይ ሆኖታል።
እስኪ ማስተር ባቹ እንዴት እንደቀረ ያብራሩልኝ?
እንግዲህ የውሃ ማሸጊያ ፕላስቲክ የሚሰራው ከፔትሮሊየም (የነዳጅ ድፍድፍ) ነው። በዚህ ምክንያት የፔትሮሊየም ድፍድፍ ዋጋ በጨመረ ቁጥር የውሃ ዋጋም ይጨምራል። የውሃ ማሸጊያ ፕላስቲክ ዋጋ በጨመረ ቁጥር ደግሞ ህብረተሰቡ ውሃ በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝቶ ለመጠጣት ይቸገራል። ያችን የአንገት ላይ ሽፋን በማስቀረታችን እንኳን ውሃን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸጥ ችለናል ማለት ነው።
በዚህ የአንገት ላይ ሽፋን ማስቀረት መነሻነት ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኔክሲልን (የአንገት ላይ ሽፋን) ብቻ ሳይሆን ማስተር ባችስ ምን ይጠቅማችኋል? ዋጋው ውድ ስለሆነ ቢቀርስ ምንድን ነው ችግሩ ብለው ጠየቁን እኛም እንደ ማህበር ካጠናን በኋላ አይ ግዴለም አያስፈልግም መቅረት ይችላል አልናቸው፡፤ ከዚህ በኋላ ኢንዱስተትሪ ሚኒስቴር ኢኒስቲትዩት ለአንድ ዓመት አጠኑት። በጥናታቸው እኛንም እያማከሩ ከቀጠሉ በኋላ ያገኙት ግኝት ማስተር ባች ምንም ጥቅም እንደሌለው ነው። እንዲያውም ጥናቱ የሚያመለክተው በማስተርባች የቀለመው የውሃ ማሸጊያ ፕላስቲክ መሬት ላይ ሲጣል ከተፈጥሮው ነጭ ፕላስቲክ ይልቅ ያለመበስበስ ዕድሉ በጣም ከፍተኛና ከተፈጥሮው በእጥፍ ይበልጣል። ስለሆነም በማስተርባች የቀለመ የውሃ ፕላስቲክ የሚበሰብስበት ጊዜ በጣም ረጅም ስለሆነ ለአፈርም ሆነ ለአካባቢ ብክለት ያለው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ነው የተደረሰበት። ስለዚህ ማስተርባች ከአካባቢ ጥበቃም ሆነ ከውጭ ምንዛሪ ብክነት አንጻር ጉዳቱ ከፍተኛ ነው ብለው ጥናታቸውን አሳዩን እኛም ተሞክሯችንን ገለጽን በጋራ ሆነን ይህንን ኬሚካል ማስቀረት ችለናል።
ይህ ማስተር ባች በተለምዶ የመጣ ስለሆነ ዝም ብሎ ከማስቀረት በጥናት ተደግፎ ተጠቃሚውም አምራቹም እንዲቀበለው ተደርጎ ነው እንዲቀር የተደረገው። አምራቹንም ይህ ነገር አይጠቅምም ወጪ በመቆጠብ ላይ ትኩረት አድርጉ አልን ምክንያም በዚህ ዘርፍ ከ100 በላይ አምራች አለ። ማህረሰቡም ይህን እንዲገነዘበው ነው እናንተም ማብራሪያ እየጠየቃችሁን ያላችሁት በዚህ መልኩ ግንዛቤ ይፈጠራል ብለን እናምናለን።
ማስተር ባች ለውሃ ማሸጊዎቹ ፕላስኮች ውበት ከማላበስ ውጪ ሌላ ምንም ጥቅም የለውም ማለት ነው?
አዎ ጥቅም የለውም። ምን መሰለሽ የጁስ እና መሰል ምርቶችን ብንወስድ ፕላስቲኮቹ የገባባቸውን ፈሳሽ መልክ ይዘው ይወጣሉ። እቃው ነጭ ቢሆንም ማለቴ ነው። የውሃው ግን ነጭ ሲሆን ውሃ ከለር ስለሌለው እቃውን ለማሳመር ተብሎ ብቻ ነው የሚቀልመው።
ማስተር ባች አካባቢንና አየርን ከመበከል ባለፈ ውሃው ላይ የሚፈጥረው ችግር  ወይም ውሃውን ስንጠጣው በሰውነታችን ላይ የሚያደርሰው የጤና ጉዳት በጥናቱ አልተገኘም?
በጥናቱ ከአየርና ከአፈር ብክለት ውጪ ውሃው ላይ የሚያስከትለው ብክለት የለም ስዚህ ጤናን ይጎዳል የሚል የጥናት ግኝት የለም። ማስተርባችን በማስቀረታችን ግን መቶ በመቶ ጤንነታችን የተጠበቀና የተሻለ ይሆናል።
እንደሰማሁት ማስተር ባች በውጭ ምንዛሬ ወደ አገር ከገባ በኋላ እንደ “ፖሊስተር” እና “ያር” የሚባሉ ሌሎች ግብአቶችን በመጠቀም ነው ማቅለሚያው ፕሮሰስ የሚደረገው። ግብአቶችን ጨምሮ ማስተር ባችን በማስቀረታችን በዓመት ምን ያህል የውጭ ምንዛ እናድን ይሆን?
ይህንን ማቅለሚያ ከውጭ ለማስባት ከሶስት ዓመት በፊት 30 ሚሊዮን ዶላር ይፈጅ ነበር። አሁን ላይ የአምራቹም ቁጥር ስለጨመረ እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር ቀጥታ ከግዥ ብቻ እናወጣ የነበረ ሲሆን አሁን ማስተር ባችን በማስቀረታን 50 ሚሊዮን ዶላር በዓመት እናድናለን። እንደ ፖሊስተር እና ያርን ያሉ ግብአቶች ደግሞ ሲጨመሩ የምናወጣው ከዚህ በላይ ሲሆን አሁን ላይ እነ ፖሊስተርና ያርን መጠነኛ ፕሮሰስ ተደርጎባቸው ለጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ስለሚውሉ በዓመት የምናድነውን የውጪ ምንዛሪ ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ያደርገዋል። ይሄ ቀላል አይደለም። በሌላ በኩል ማስተር ባች ፒቲ የሚባል አለ ነጩ ማለት ነው። ከዚያ ጋር ነው የሚቀላቀለው። ስለዚህ ማሽንን ስንወስድ በተለያየ ምክንያት ማስተር ባች የሚሄድበት መስመር ቢዘጋና መለዋወጫ ቢያስፈልግ ማሽን ሊቆምና ስራ ሲስተጓጎል ይችላል። አሁን ግን እይዳይሰራ ነው የሚደረገው ይህም አንዱ ጥቅም ነው። ምክንያቱም ማሽኑ ነጩን ብቻ ነው በቀላሉ ይዞ የሚሄደው ማለት ነው።
ውሃ ከጠጣን በኋላ የሚጣለው ወይም ሰዎች እየሰበሰቡ የሚወስዱት የውሃ ማሸጊያ ፕላስክ የት ነው የሚደርሰው?
ሌላ ጥሩ ነገር አስታወስሽኝ። ይህ የሚሰበሰበውን ፕላስቲክ ጨፍልቀን ነው ወደ ውጭ የምንልከው። ለምን እንልከዋለን ካልሽኝ ይሄ የማስተርባቹ ቀለም ስላለውና ቀለሙን ከፕላስቲኩ ለመለየት ከባድ በመሆኑ ነው ወደ ውጪ የምንልከው።
እዚህ አገር ቀለሙን መለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂ የለንም ማለት ነው?
አዎ በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ ነው ወደ ውጪ የሚላከው። አሁን የውሃ ማሸጊያዎቹ ፕላስቲኮች ቀለም ስለማይኖራቸውና ነጭ ብቻ ስለሚሆኑ ጨፍልቀን ወደ ውጪ መላክ እንተውና እዚሁ አገር በተወሰነ ደረጃ ሪሳይክል ተደርጎ ጥቅም ላይ የማዋል ስራ ይሰራል ማለት ነው። ይህም ጥሩ ጥቅም አለው።
ሌላ ፋብሪካ ሌላ የሥራ እድል ለመፍጠርም ጥሩ አጋጣሚ ሊሆን ይችላል ማለት ነው?
ትክክል ነው ፕላስቲኮቹን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋሉ (ሪሳክይል) የማድረጉ ጉዳይ ትልቅ የሥራ እድል ፈጥሯል እስከዛሬም። አንድ ሜዳ ላይ የሚወድቅ የለም እየሰበሰቡ ይወስዳሉ። ተጨፍልቆ ወደ ውጭ ለሚላከው እንኳን ማለቴ ነው። አሁን ነጭ በመሆኑ ወደ ውጭ መላክ ስንተው ደግሞ እዚሁ መስራት ስለሚቻል ተጨማሪ ፋብሪካ መከፈቱና ለተጨማሪ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩ አይቀርም። የሆነ ሆኖ ማስተርባችን በማስቀረታችን ብዙ ጥቅም ነው የምናገኘው። ሪሳይክል ስራ ላይ የተሰማሩ አሉ አሁንም ነገር ግን ተጨማሪ ፋብሪካዎች መከፈታቸው አይቀርም።
ይሄ ማለት አምራቾች ማስተርባች በመቅረቱ  ለተጠቃሚ የዋጋ ቅናሽ ያደርጋሉ?
ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ ዋናው ውሃውን ውድ የሚያደርገው ማሸጊያ ፕላስቲኩ ነው። ከፔትሮሊየም ድፍድፍ እንደመሰራቱ ነዳጅ ሲጨምር የውሃውም ዋጋ አብሮ ይጨምራል። እንደምታውቂው ሰሞኑን ነዳጅ በጣም በሚያስደነግጥ ሁኔታ ከ47 ብር ወደ 57 ብር አድጓል፡፡ ሌላ ግዜ ቢሆን የውሃውም ዋጋ ይጨምር ነበር። አሁን ግን በአጋጣሚ ማስተርባች በመቅረቱ የውሃ ዋጋ ባለበት ይቀጥላል፡፡ ይሄ ማለት የውሃ ዋጋ ላይ አምራቹ ቅናሽ አደረገ ማለት ነው። በነገራችን ላይ ውሃውን የበለጠ ውድ የሚያደርገው ታክስ ነው ውሃ እንደ ቅንጦት እቃ ተቆጥሮ 30 በመቶ ይቀረጣል፡፡ ቫት 15 ፐርሰንት ኤክሳይስ ታክስ 10 ፕርሰንት ጉምሩክ 5 ፕርሰንት በድምሩ 30 ፕርሰንት ታክስ ተጥሎበታል ፡
ውሃ ከዳቦ ተለይቶ መታየት ነበረበት? ዳቦ አይቀረጥም ብየ ነው?
ትክክል ነው! ህብረተሰቡ ንጹህ ውሃ የመጠጣት መብት አለው። ይሄን መብቱን ደግሞ መጠየቅ ይችላል፡፡ ህዝቡ የዘይት ዋጋ ሲጨምርና ከገበያ ሲጠፋ ይጮሀል ጥሩ ነው። ነገር ግን ውሃም ላይ እንዲህ ማድረግ አለበት። አይተሽው ከሆነ በቧንቧ የሚመጣውን ውሃ እንኳን አንጀታችን ብረቱም አልቻለውም፡፡ ስለዚህ የተጣራ ንፁህ ውሃ የመጠጣት መብት አለኝ ብሎ ቫቱና ኤክሳይስ ታክሱ እንዲነሳ ህብረተሰቡ ነው መንግስትነ መጠየቅ ያለበት እንጂ አምራቹ አይደለም፡፡ ምክንያቱም እኛ ከህብረተሰቡ ሰብስበን ነው ቫቱንም ኤከሳሰይስ ታክሱንም ለመንግስት ገቢ የምናደርገው። መንግስት ቫትና ኤክሳይስ ታክሱን ቢያነሳ ህብረተሰቡ ውሃ  25 በመቶ ዋጋ ይቀንስለታል። ማስተርባቹ መነሳቱ ለአምራቹ ብቻ ሳይሆን ለህብረተሰቡም ጥቅም አለው። ለህብረተሰቡ ከቀነሰ አምራቹ ምንድን ነው የሚጠቀመው የሚል ጥያቄ ልታነሺ ትችያለሽ። ህብረተሰቡ ዋጋ ቀነሰለት ማለት የተጣራ ውሃ የመጠጣት ፍላጎቱ ይጨምራል ያን ግዜ አምራቹ በስፋና በጥራት እያመረተ ሲሸጥ ከብዛት ያተርፋል ማለት ነው፡፡
እስኪ ለጠቅላላ እውቀት እንዲረዳን የውሃ ማሸጊያ ፕላስቲክ ከነዳጅ ድፍድፍ(ፔትሮሊየም) ነው የሚሰራው ካልን ወደ ሃገር ውስጥ የሚገባው በምን መልክ ነው?
ጥሩ! ኢትዮጵያ ሰላም ሆና በኡጋዴን በኩል ያለው ድፍድፍ በአግባቡ ከተመረተ እሰየው ነው፡፡ እንደ ማስተርባቹ ጥሬ እቃውን ማስገባት ትተን እዚሁ ማምረት እንችላለን የሚል ተስፋ አለን። ወደ ጥያቄሽ ስመለስ ፔትሮሊየሙን ያጣሩና ተረፈ ምርቱን ስኳር ወደሚመስል ነጭ ነገር ይቀይሩታል፡፡  መጠኑ የስኳር 2 ወይም 3 እጥፍ መጠን ያለው ነጭ ሆኖ ነው ጥሬ እቃው ወደ ሀገር የሚገባው። ከዚያ በኋላ “ኢንጄክሽን ማሽን ”የሚባል አለ እዚያ ማሽን ውስጥ ይገባና ወደ ፕሪፎርም (ቅድመ ቅርፅ) ይለወጣል፡፡ ፕሪፎርም ትንሹ የውሃ ፕላስቲክ ማለት ናት፡፡ ድሮ ፕሪፎርም ከውጪ እናስመጣ ነበር አሁን ግን እዚሁ መስራት ችለናል፡፡ አሁን የምናስመጣው “ፖሊኢቲሊን” የተሰኘውን ጥሬ እቃ ነው፡፡ ይሄ ፕሪፎርም ደሞ ብሎወር ውስጥ ይገባና ወደ አምራች ከሄደ መኋላ የምንጠጣበትን የመጨረሻ ቅርፅ ይይዛል
እስኪ ውሃው ከጉድኋዳድ እስከ ማሸጊያ ፕላስቲክ ድረስ ያለውን የማጣራት ሂደት ያብራሩልኝ?
ብዙ ሂደት ነው ያለው። ሰዎች ቤት ውስጥ አጣርተው ሲጠጡ እናያለን፡፡ የሚያጣሩት ”sand fillter“ ወይም አሸዋውን ብቻ የሚያስቀር ማጣራት ነው። እንግዲህ የጉድጓድ ውሃ ንፁህ እና የተፈጥሮ ነው የሚባል ነገር አለ አይደል ግን አይደለም። በኛ አመራረት መጀመሪያ ውሃው ከጉድጓድ ሲወጣ ካርበን ይጨመርበታል፡፡ አሁን በቧንቧ እየመጣ አብዛኛው ህዝብ የምንጠጣው ካርበን እንኳን አይጨመርበትም  ያሸዋ ማጣሪያ እና ክሎሪን ብቻ ነው የሚጨመርበት
እሱንም ቢሆን በሳምንትና በአስራ አምስት ቀን ነው የምናገኘው እኮ ኢንጂነር…
እሱማ ትክክል ነሽ። የእኛን የማጣሪያ ሂደት ነው እየነገርኩሽ ያለሁት እንጂ። መጀመሪያ ከጉድጓድ ሲወጣ ክሎሪን ይጨመርበትና ወደ ሳንድፊልተር (ወደ አሸዋ ማጣራት) ይሄዳል። ከሳንድ ፊልተር ወደ ካርበን (ቻርኮል) ወደሚባለው ይሄድና ካርበን ፊልተር ይደረጋል። ጀርሙንም የሚገድለው ሁሉንም የሚያጣራው ካርበን ፊልተሩ ነው። ከዚያ በኋላ ወደ “Five Micro” ሄዶ ይጣራና ወደ “One Micro” ሄዶ በደንብ ይጣራል ማለት ነው። ከዚህ ቀጥሎ አልትራ ቫዮለንት (UV) ይገባና በጨረር ጀርሙን እንዲሞት ይደረጋል ወይ ኦዞኔሽን ውስጥ ይገባል ማለት ነው።
በነገራችን ላይ “ሪቨርስ ሶስሞሲስ” የሚባል አለ ይህ ሂደት ውሃውን እየመላለሰ እዲጣራ ካደረገ በኋላ ነው ወደ (UV) እና ኦዞኔሽን ሚሄደው። ከዚያ እንደገና ወደ መሙያው ሲሄድ ሌላ ማጣሪያ አለ። ይህን ሁሉ ስታይው 7 እና 8 የማጣራት ሂደት አልፎ ነው ለመጠጥ የሚቀርበው።
ሂደቱ በጣም ይገርማል። ግን አንድ በተለምዶ የሚባል ነገር አለ። ውሃ በዚህ ሁሉ ሂደት ሲያልፍ የተፈጥሮ ይዘቱን ማለትም እንደ ብረትና ሚኒራል ያሉ ውህዶቹን ያጣል የሚል። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
ጥሩ ጥያቄ ነው። ውሀው የተፈጥሮ ማንነቱን አያጣም እንዲያውም በተፈጥሮ ያለው ሚኒራል ውሃው ውስጥ በዛ ብሎ ነው መንግስት የሚቆጣጠረን። ሚኒራሉ ውሃ ውስጥ መብዛትም ማነስም የለበትም። ለምሳሌ የኩላሊት ህመም ላለባቸው ሰዎች ሚኒራል የበዛበት ውሃ እንዲጠጡ አይመከርም ይቸገራሉ። እንዲያውም ይሄ የማጣራት ሂደት የውሃውን ይዘት የሚያስተካክል እንጂ ተፈጥሮውን የሚያሳጣ አይደለም። የማጣራቱ ሂደት ግን በዋናነት ቆሻሻን የማስወገድ ነው። ሆኖም አንዳንድ ራቅ ያሉ ቦታዎች ላይ ፍሎራይድ በብዛት ያለበት ውሃ  አለ። ፍሎራይድም ሚኒራልም ሲበዛ ለጤና ጎጂ ነው። ሁሉም በመጠኑ ነው መሆን  ያለበት። የምግብ የመድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባስልጣንም የሚቆጣጠረውኮ ይሄንኑ ነው። በላብራቶሪ ይፈትሽና ትክክል መሆኑን  ሲያውቅ ነው የሚያሳልፈው። ተቆጣጣሪ አካል ያስፈለገውም ለዚህ ነው። አንዳንድ ሰው ውሃ አፍልቶ ይጠጣል። ይሄ በ100 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሙቀት ጀርሙን መግደል ይቻላል። ነገር ግን ቆሻሻውን አያወጣውም።  ያ ብረት ያዝጋል እንኳን አንጀት ብረትም አልቻለውም ያልኩሽ ይህንን ነው።
ይህ አባባል ከቧንቧ ቀድቶ ቀጥታ የሚጠጣውን አብዛኛውን ህዝብ የሚያስደነግጥ ይመስለኛል ኢንጂነር?
ግን ህዝቡ ማወቅ አለበት። እኛ ማህበረሰቡ የተጣራ ውሃ እንዲጠጣ ማበረታታት አለብን። አሁን አብዛኛው ሰው ተወደደ በሚል የተጣራ ውሃ አይጠጣም። እዚህ ጎረቤት ኬንያም ሆነ ጅቡቲ የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል የተጣራ ውሃ ነው የሚጠጣው።
እሱማ የአቅም ጉዳይ ሆኖ እንጂ ማንም ንጹህ ውሃ መጠጣት ጠልቶ አይደለም። እርሶ የጠቀሷት ኬንያ የአንድ የመንግስት ሰራተኛ ደመወዝ ኢትዮጵያ ካለው አንድ የመንግስት ሰራተኛ ደመወዝ ጋር ሲነጻጸር በ3 እጅ እንደሚበልጥ ጥናቶች ያሳያሉ የእለት ጉርሱን ማሟላት ያልቻለን ማህበረሰብ የታሸገ ውሃ ጠጣ ማለት ቅንጦት አይሆንም?
ትክክል ነሽ  ይሄ ሊሆን ይችላል አሁን ያልሽውም  ትክክል ሊሆን ይችላል። ከዚህ ቀደም ባለው ጊዜ ለምሳሌ 10 ዓመት ወደኋላ ሄደሽ እኛን ከኬንያ ጋር ገቢያችንን ብታወዳድሪ እኩል ነው ቢባል እንኳን ያን ጊዜ  እንኳን ኬንያዎች የተጣራ ውሃ ይጠጣሉ። ለምን ካልሽ ህዝቡ የተጣራ ውሃ ባለመጠጣቱ ለሚደርስበት የጤና ችግር ለመድሃኒት ያወጣዋል። ይሄንን ነገር ነው የማናገናዝበው። እነ ኬንያም ሆኑ ሌሎች ሀገራት የሄዱበት እሳቤ አንድ ሰው ታሞ ከሚያወጣው ገንዘብ ለንጹህ ውሃ የሚያወጣበት ገንዘብ በእጅጉ ያንሳል የሚል ነው።  ቀድሞ በሽታን መከላከል ታሞ ህክምና ከመሄድና ጤናን ከመፈለግ እርካሽ ነው ማለት ነው። ታዲያ እኛ ይሄንን አካሄድ ለምንድን ነው የማንከተለው። አሁን እኮ በሀገራችን የኩላሊት በሽታ ተስፋፍቷል። የውሃ ወለድ በሽታና ሌሎች በሽታዎች አሉ። ህዝቡ ምግብ የፈለገ ቢወደድ አይተውም። ውሃም እኮ ምግብ ነው። ለምን አናስበውም? ይሄ የግንዛቤ ችግር ነው ብዬ ነው የማስበው። ምክንቱም ሚዲያውም መንግስትም ሆነ የጤና ባለሙያው  ህብረተሰቡ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር አልሰራም። ቢሰራ ኖሮ ብዙ የኢትዮጵያ ህዝብ ይጠጣ ነበር። ብዙ ፍላጎት ሲኖር አምራቹ በብዛት አምርቶ ከብዛት  ስለሚያተርፍ የውሃ ዋጋ እየቀነሰ ይሄድ ነበር። አሁን ላይ በኢትዮጵያ 110 ሚሊዮን ህዝብ ቢኖርም የተጣራ ውሃ የሚጠጣው 15 ሚሊዮን  አይሆንም።
ዝቅተኛ ኑሮ ላይ ያሉትን ብንተው እንኳን መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለው እንኳን እየጠጣ አይደለም ምክንቱም የግንዛቤ ችግር ስላለ ነው።
በውጭ ምንዛሬ ከሚገቡትና ወረፋ ከሚጠብቁት ውስጥ  “ማስተር ባች” አንዱ ነው። ይሄ ደግሞ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እንዳይሰሩ ያደርጋቸዋል ተብሏል። አሁን መቅረቱ ምን ያህል ለውጥ ያመጣላችኋል?
ፋብሪካዎች በሙሉ እንዳይሰሩ ያደረጋቸው የውሃ ማሸጊያ ፕላስቲክ መወደድ ነው። ከዚህ በፊት 50 ብር ይሸጥ የነበረው ይኸው እቃ አሁን እስከ 250 ብር ደርሷል። ይህ ማለት ጥሬ እቃው 4 እጥፍ ሲያድግ የውሃ መሸጫ ዋጋ ያደገው 2 እጥፍ ብቻ ነው። የውሃውን መሸጫ ልክ እንደ ጥሬ እቃው በሶስትና በአራት እጥፍ ላሳድግ ቢባል ህብረተሰቡ የመግዛት አቅም የለውም። አሁን አምራቹ እየከሰረ ነው የሚሸጠው። አሁን አምራቾች የሚቀጥሉት ማስተር ባቹ ስለተነሳ አይደለም። ማስተር ባች መነሳቱ በጣም ጥቂት አስተዋጽኦ ነው ያለው። በዚች ትንሽ አስተዋጽኦ እንኳን አምራቹ ነዳጅ ሲጨምር ዋጋውን ባለበት አስቀጥሏል። አሁን ዋነኛው ነገር ኤክሳይስ ታክስ፣ ቫትና የጉምሩክ ቀረጥ ተደምሮ 30 በመቶ ቀረጥ መጣሉ ነው። በዚህ ምክንት 21 ፋብሪካዎች ተገዝተው ነበር። ሰሞኑን አምስቱ በሙሉ አቅማቸውም ባይን ወደ ስራ ተመልሰዋል 16ቱ ግን እስካሁን እንደተዘጉ ናቸው። ህዝቡ ውሃ ላይ ቫትና ኤክሳይስ ታክስ ይነሳልኝ ቢልና መንግስት ቢያነሳ፣ አንደኛ የውሃ መሸጫ ዋጋ ይቀንሳል። ዋጋው ሲቀንስ ማህበረሰቡ በብዛት ይገዛል፣ ህብረተሰቡ በብዛት ሲገዛ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ይሰራሉ፣ ከብዛት ያተርፋሉ። በርካታ ሰራኞችም ይቀጥራሉ አየሽው ጠቀሜታው የጎላና የተሳሰረ ነው። ዋናው የዘርፉ ችግር ይሄ ነው። ጉምሩክ የሚቀርጠውን አምስት ፐርሰንት ለማስቀረት ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገርን ነው። በቅርቡ ይነሳል ብለን እናስባለን 25 በመቶው ግን ለአምራቹም ለህዝቡም ከባድ ነውና መንግስትም ህዝቡም ሊያስብበት ይገባል ስንል እንደማሀበር እናስስባለን።

Read 1521 times