Sunday, 23 October 2022 00:00

ፍልስፍና ከራስህ የሚያርቅህ ሳይሆን ወደ ሰውነትህ የሚመልስህ ነው!

Written by  እ.ብ.ይ.
Rate this item
(0 votes)

ትርጉም ያለው ሕይወት፣… እውነትን መሰረት በማድረግና ጥበብን ፈልጎ በመጨበጥ እውን የሚሆን ነው።
ብዙዎች ፍልስፍናን የቃላት ማሳመሪያ የአፋቸው መዋያ ያደርጓታል። ጥቂቶች ግን ድምጻቸውን አጥፍተው በብልሃት ይኖሩባታል።
ትምህርታቸውን በፍልስፍና ጀምረው ሕይወታቸውን ከፍልስፍና ያቋረጡ ጥቂት አይደሉም። በየመድረኩ የሚፈላሰፉ በኑሯቸው ግን ከራሳቸው የተላለፉና የተኳረፉ መዓት ናቸው። ፍልስፍናን የሆዳቸውን ከርስ መሙያ ያደረጉ በአኗኗራቸው ግን ከፍልስፍና ሃሳብ የራቁ፣… እልፍ ናቸው።
ፍልስፍናን ሌላውን ማንጓጠጫ፣ በሰው እምነት ላይ ማላገጫ አድርገው ተገብዘው ያለቦታዋ ያውሏታል። እናውቅልሃለን የሚሉ ለራሳቸው የማያውቁ ፈላስፋ ተብየዎች በየመድረኩ፣ በየሰፈሩ፣ በየዩንቨርስቲው፣ በየስልጣን ወንበሩ ሞልተው ፈስሰዋል።
ጥቂት ብልሆቹ ግን ሌሎችን ያከብሩባትና ይረዱባት ዘንድ ፍልስፍናን የትህትናቸው መሰረት ያደርጓታል።
የጥንት ፈላስፎች ዛሬም ድረስ የመልካም አስተሳሰብና አኗኗር ተምሳሌቶች ሆነው ይቀርባሉ። የሮማውያኑ ፀሐፊያን እነ ሲስሮ፣ ሴኔካ እና ማርከስ ኦሪሊየስ፣ የአንድን ሰው ማንነትና የመንፈሳዊነት ዕድገቱት የሚለኩት ከሶቅራጥስ ህይወት ጋር በማነፃፀር ነበር ሲል ጀምስ ሚለር ይነገራል - “Examined lives from Socrates to Nietzsche” በሚባል መፅሐፉ።
በእርግጥም፣… ሶቅራጥስ ለእውነት ኖሮ እውነትን ሳይለውጣት እስከሞቱ ድረስ ጠብቋታል።
ፍልስፍናን በጥሩ ጊዜ ጀምሯት በክፉ ጊዜ አልጣላትም። በደስታው ዘመን ወድዶና ፈቅዶ የተከተላትን ፍልስፍና በአስከፊ ሁኔታውና በፈታኝ ጊዜው ፊቱን አላዞረባትም።
ለገባውና ፍልስፍናን በሕይወቱ መግለጥ ለሚሻ የጥንታዊያኑን ፈላስፎች ሕይወት ምሳሌ አድርጎ እውነትን ይከተላል።
ጥበብን ያስቀድማል።
እውቀትን ይዞ አስተሳሰቡን ያስተካክላል።
ስሜቱን ይገራል።
ሃሳቡን ያበስላል።
ግብሩን መልካም ያደርጋል።
ፍልስፍናን ከልቡ የሚያውቃት ሊኖርባት እንጂ በአፉ ሊያስመስልባት አይደለም።
እንደዘመኑ አንዳንድ አዋቂ ተብዬዎች ዕውቀቱን ሌሎች ላይ መንቀባረሪያ ሳይሆን ለሌሎችም መብራት የሚሆን ብርሃን ፈጥሮ ወደማይቀረው ይሄዳል።
ለብልህ ሰው ፍልስፍናን አፉ ላይ ብቻ ይሰለጥንባት ዘንድ አልተሰጠችውም።
ይልቁንስ ፍልስፍናን ከሃሳቡ ጋር አወራርዶ፣ በአዕምሮው አመላልሶ፤ ሃሳቡን አፋጭቶ፤ በሕሊናው ሰልቅጦ፤ በልቡ ሚዛን መዝኖ፤ ወደውስጡ አጣጥሞ ውጦ፤ ስሜቱን ገርቶ፤ ደካማ ሕይወቱን ለውጦ፤ በእጆቹ ስራ ገልጦ በዕድሜ ዘመኑ ሁሉ ይኖርባት ዘንድ የተሰጠችው ድንቅ ጥበቡ መሆኗን ያስመሰክራል።
በዚህ ዘመን ግን ፍልስፍና በአፍ የሚራቀቁባት፣ በቃላት የሚመጠቁባት እንጂ በተግባርና በባህርያቸው የሚገልጧት፤ በኑሯቸው የሚመስሏት አይደለችም። የዘንድሮ ፍልስፍና በጥበብ የሚጠልቁባት ሳትሆን በለብለብ ዕውቀት ከላይ ከላይ የሚንሳፈፉባት ሆናለች።
ፍልስፍና ከንግግር ማሳመር ጋር መያያዟ ለጥንታዊ ፈላስፎች የሚዋጥላቸው አይደለም። ሶቅራጥስ፡- “ምልከታዬን በመደበኛ ንግግር ባይሆን በምግባሬ እገልጣለሁ። ተግባራት ከቃላት በላይ ተዓማኒነት ያላቸው ማስረጃ አይደሉምን?” (“If I don’t reveal my views in a formal account, I do so by my conduct. Don’t you think that actions are more reliable evidence than words?”) በማለት ያሳስበናል።
ወዳጆች ሆይ.. ፍልስፍና አፋቸውን ለሚያራቅቁ ሳይሆን ሕይወታቸውን ለሚያሰለጥኑ ነው! ተፈላሰፍክ ማለት ከእውነታው መራቅ ማለት አይደለም። ይልቁንስ እውነቱንና እውነታውን መረዳህ ማለት ነው።
የፍልስፍና ከፍታ ላይ ደረስክ ማለት የሰውነትን ጣራ ተቆናጠጥክ ማለት ነው። ፍልስፍና ከወገንህና ከአንተነትህ የሚያርቅህ ሳይሆን ወደ ሰውነትህና ወደ ህዝብህ የሚመልስህ ነው። ከረሳኸው ማንነትህ ጋር መልሶ የሚያገናኝህ፣ ከተኳረፍከው አንተነትህ ጋር የሚያስታርቅህ፣ አንተ ፍልስፍና ነው። ፍልስፍና የሚያስፈልግህ ሰው እንድትሆን ነው።
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
ሠኞ ጥቅምት ፯ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም

Read 3103 times