Print this page
Saturday, 22 October 2022 17:27

በሲቃ መሐል ያለች ሳቅ

Written by  በድረስ ጋሹ
Rate this item
(2 votes)

በትዝታ የነበዘ፣ በብርድ የፈዘዘ ፊት፣ ሐሳብ የራቃት ልብ፣ ለአፍ ያጠረ እጅ ይዞ ተጋድሟል። አተኛኘቱ ዘመንን የሚሸኝ ይመስላል። አጀኒ! የወይኒ ልጅ።
ድንጋይ ተንተርሶ፣ ጤዛ ልሶ መኖር ከጀመረ ዋለ አደረ። “አሥራት በኩራት፣ ሲሶና እርቦ ይከፍል የነበረ ሰው ምጽዋት አምሮት ባልሆነ?” ይላሉ መንገደኞች። ተመጥጦ በማያልቅ ምራቃቸው “ምጽ” የሚሉለትም አልታጡም። “ዕድሜ” ለሞት እና ለሕይወት ድልድይ ሆኖ ይታዘበዋል።
እንደ ስንዴ የተለቀመ፣ እንደ ወተት የጠራ ማንነት መስራት እንዴት ተሳነኝ? ኀዘን ካልተዉት ላይተው፣ ኗሪም ሁሉ ከሞት ላይቀር፣ እስከመቼ ነው እህህ?
ለተሸሸገ ፈቃድ፣ ለተደበቀ ፍላጎት፣ ኑሮ መላ ካላበጀ... መፈትሔ ይሆን እንዴ ሞት? እልባት ያጡ የሃሳብ ውዝግቦች፣ በውስጡ ግብግብ ገጥመዋል።
[ኮሽታ፣ ተነስ የሚል፣ የሚጎነትል ስሜት።
ዝምታ፣ እምቢታ፣ አልነሳም የሚል አመጽ።
ህመም፣ ሲቃ፣ እህህ።]
በእጆቹ መሐል የተቀበረ ጭንቅላቱ፣ አቧራማ ነው። አመድ ላይ እንደ አህያ  ሲንከባለል የዋለ ያደረ አስመስሎታል። የተጋደመባት ሸራ፣ ከወርዷ የሰፋች፣ ከቁመቷ ያጠረች ናት። ካርቶን ትራሱ ኮባ ልብሱ ነው። የልብሱ ማጠር ጀርባውን ለዓይን አጋልጦታል። በትልቅ ጥፍር ያከከው (ያረሰው ማለት ይቀላል) አፈር የለበሰ ጀርባው ይታያል። ደም ቲፍ ቲፍ ያለበት... መስመር የሰራ ገላው!።
“አጀኒ”
“ወይዬ”
“እንቆቅልህ”
“ምን አውቅልሽ ሚጡዬ”
“ላይዘሩበት የሚያርሱት...”
“የእኔ ገላ ነዋ እሙዬ... የእኔው የከንቱው... የአጀኒ ገላ!”
ትስቃለች። ሳቋ ፍስኀ ነው። አእምሮውን በሳቋ እንደማደስ... ፈገግ-ፈገግ ትላለች። ከወደቀበት ትቢያ ቀና አለ - እንደ እባብ አፈር ልሶ።
“እሙዬ...ካላጣሽው ቦታ ግን ለምን ገላዬን አየሽ? የተራቆተውን?”
“ለዓይኔ የቀደመ እሱ ስለሆነ ነዋ አጀኒዬ”
ለሰው ዓይን የሚቀድመው ምን እንደሆነ ያውቃል። ከንጽሕና ይልቅ ዕድፍ፣ ከለበሰ የተራቆተ፣ ከጨመተ የለፈለፈ፣ ከነጭ ነጠላ ኩታ ጥቁር ነጥብ ይቀድማል!
ሰዓቱ ይንቀራፈፋል። ህጻኗ፣ ጎስቋላ አካሉን እየጠቆመች የምትስቅበቱ ከአጠገቡ የለችም። በሰላምታ የምትላመድ፣ ከሳማት የምትዋደድ ነጭ ወረቀት ናት። አሁን የለችም። ካይኑ ሸሸች። ችግሩን ሊያዋያት ሊነግራት ነበር። ግን ራቀችው... እንደ ፀሓይ፣ እንደ ጨረቃ።
በአእምሮው ውስጥ ከሌላ ነገር ሁሉ እየገዘፈች፣ ከዓይኑ ደግሞ እያነሰች... እያነሰች… ሄዳ ጠፋች። ጨለማ በውስጡ ሆነ። አንገቱን በድጋሚ ደፋ፣ ወደ መሬት... በእንባ መሬቱን ሊያጠጣ፣ አትክልት ሊያበቅል... በኀዘኑ፣ በእሮሮው።
“ኀዘን፣ ሙሾ፣ ምሬት፣ ላይሻገር የሕይወትን
ጎርፍ። ላያቀል አንዱንም ችግር፣
እንባው የማርያም መንገድ ላይሰጠው!።”
በውስጡ ብዙ ሐሳቦች ሲሯሯጡ፣ በውጭ ገጽታው ሥሩ ሲወጣጠር፣ ዓይኑ ሲቀላ ይታያል። ሲጨንቀው የሚያወራው ከራሱ ጋር ነው። ህጻኗ፣ ቢቆጧት ቂም የማትይዘዋ፣ ገራገሯ፣ ከሁሉ ለማጇ... እሷማ ርቃለች። ለብቻው እጥፍ ኩርትም ብሎ ብቻውን በንዴት ያወራ ያዘ... ስለ ሞት ስንቅ!።
“ሰዎች ግን ሞትን ይፈራሉ? ኧረ በፍጹም። ቢፈሩትማ ባልወለዱ... ባላማጡ። ሞት ለዚች ዓለም ተራ ነው። ግን ደግሞ ሞት ሞቶ አያውቅም - ስንቁ ፍጡር ነውና። ሰው እንደሁ በዝቷል... ይኼን ሁሉ ስንቅ ሳይጨርስ ለምን ብሎ ሞት ይሞታል?
ከበደ ሚካኤል ጠቢቡ ሰለሞንን ቢሞግቱ ምን አመጡ?
ለሁሉም ጊዜ አለው ትላለህ ሰለሞን ...
ለመሆኑ የሞት መሞቻ ጊዜው መቼ ነው?...
ቢለው ከበደ ሚካኤል ቢጠይቁ መልስ አላገኙም። የሞት መሞቻው፣… ስንቁ ሲያልቅ ነው። ስንቁም ብዙ ፍጡር ነው። ሲያንስም ሰው ነው! ወይኔ አጀኒ! የምበሽቀው የሞት ስንቅ እንደሆንኩ እያሰብኩ መኖሬ ነው።”
[እንባው በጉንጩ ፈሰሰ፣ አማረረ፣
ዕጣ ክፍሉን ረገመ፣ መሬት ተከፍታ
ብትውጠው ወደደ - ዕደለ ቢሱ!።
“አጀኒ”
ሚጡ ነበረች። “ከየት እና እንዴት መጣች?” ለማለት በሚያስቸግር አመጣጥ መጣች።
ተከሰተች አይሏት መንፈስ አይደለች።
አካል ናት አይሏት እንዴት ከመንገድ አላያት?
“ወዬ ሚጡዬ” (ሁለት የእንባ ዘለላዎች ፊቱ ላይ ወረዱ)።
“አስመሳይ ነህ እንዴ?”
“አዎ! አዎ ነኝ”
“መቼ ነው ታዲያ ራስህን የምትሆን?”
በአንዳች ኃይል መኝታውን ለቀቀ። እጁን ማማተብ አይሉት ማወራጨት፣ በፊቱ በደረቱ አዟዟረው።
“...ባስመስልስ እ?፣ ሚጡዬ ለምን ነገረኛ ትሆኛለሽ? ቆ...ቆይ ልንገርሻ! ...በውጫዊ አካል ላይ ተደርቦ የሚውል ልብስ፣ ለመኝታ ስንተኛ የምናወልቀው፣… ሰዎችን ልናስታርቅ የምንጠቀመው ሰናይ ቃል፣ ስንጣላ የምናጣው፣… ለደስታ የተገለጠ የሚመስለው ጥርሳችን፣ ከውስጥ ኅዘን ያረገዘው፣… ለይስሙላ... ለይምሰል የምንፈገው... የምንደርበው... የምናቀማጥለው... አዎ! ይፋ የወጣው መምሰል አለብኝ”...
“አይ አጀኒ!... ውጭ ተጥለሃል እኮ”
“ልውደቃ! ብርቅ ነው መጣል?”
አንዘረዘረው። ጉልበቱ ተንቀጠቀጠ። አፈር የቃመ ልብሱ ገለባ ያዘንብ ጀመር። መቀመቅ የገባች ዓይኑ ተስለመለመች። ከጭንቁር ዓይኑ እንባው ሲያመጨምጭ ያሳዝናል። የመኝታው ጎባጣ ጎድጓዳው የወጋው አካሉ ሰምበር ሰርቷል። ጠጠሩ የጠጠር ቅርጽ፣ ድንጋዩም የፊናውን። ሰዎች በየአቅማቸው ችግር አዋጥተው እንደሰጡት ሁሉ፣ እንባ በሚያስተጓጉለው ቅላጼ አወራት።
“ሚጡዬ! ሰዎች አትኩረው አይዩኝ። ዓይን ፈራሁ። በመውደቄ ሊዝቱ ጣት አይቀስሩ። ወድቂያለሁ። ግን መሬት መያዜን ይረዱልኝ። አወዳደቃቸው መሬት ለመያዝ የማያበቃቸውስ? ይብላኝ ለእነሱ።…
ቆይ ግን... ምኑ ላይ ነው መበላለጣችን?... ዛሬ ሰው ነገ አፈር አይደለንም? ኀዘንን እንደ አጓጉል ሥጋ ማኘክ ልምዳችን አይደለም? እስኪ ሰው ሲሞት ስቆ የሸኘ አሳዪኝ ሚጡዬ። በ130 ዓመቱ ለሞተ አዛውንት ደረት መድቃቱ ማስመሰል አይደለም? ይኼንንስ አልተዋረስነውም?
...ፀሓይ ከአገር አገር ታዳላለች። ብርድ የሚከርምባቸው አገሮች፣ ፀሓይ የሚበዛባቸው ሃገሮች አሉ። የሰው ልጅ እኩል እንዲወርሰው የተሰጠ ሞት እና ኅዘን አይደለምን?... ከጊዜ ጋር ቂም አለኝ እንጅ፣ እሱም እኩል ተሰጥቶን ነበር ሚጡዬ!”
[ከልቡ፣ እንደ እናት፣ ሰቅ... ሰቅሰቅ
ብሎ አለቀሰ። እንባ በደሉን እንደሚያሽርለት።
ከስቃይ ነጻ እንደሚያወጣው ኹሉ]
ህጻኗ ልባዊ ስሜቱን ተረድታ ኖሮ አዘነች። ዕንባዋ ከዓይኗ ጋን ከብለል ፍስስ... አለ። ከንፈሯን ጣለች። አዬ ልጅ... አዬ ልብ!። ህጿኗን አያት፣ ከልቡ። እንባዋ ልውረድ ልቅር ሲታገል፣ ከንፈሯ ላይ ቃል ሲንከባለል ልብ አለ። አቀፋት። የምትወደውን የበቆሎ እሸት በእጇ ሰጣት። እንባዋን እሱ ወረሰ፤ ሊያለቅስ።
“ዛሬ አታልቅሽ።
ከዕድሜሽ እኩል የሚረዝም የኀዘን ጅረት ከፊትሽ አለ፤ አትቸኩይ!”
አቀፋት ከልቡ። አሳዘነችው በሁኔታዋ።
“እንባን፣… አሁን ባይሆን ነገ አታመልጠው። የደስታ አውታር በኀዘን መሰራቷን አውቃለሁ። የሁሉንም ቤት በፍትሐዊነት ያንኳኳል - ኀዘን። አንቺ እንቡጥ ልጅ ከሀዘን ልሸሽግሽ አልተቻለኝም። ዘመንሽ ላይ እንቅፋት ተኮልኩሎ ይታየኛል፤ ለማለፊያሽ ተጨነቅኩ። አይወድቁ ይመስል በመውደቄ፣ አያጡ ይመስል በማጣቴ፣ አይከፉቸው ይመስል በመከፋቴ የተዘባበቱት ብዙ ናቸው። በእድሜ አርጅተው በመንፈስ ከጨቅላ  ህጻናት ከማይበልጡ ሰዎች ይልቅ፣ የህጻን አዋቂ አንቺ ትሻያለሽ። ገር፣ ንጹሕ፣ የዋሕ ዕድሜሽ ላይ ነሽ። ብችል ከዕድሜዬ ቀንሼ ብሰጥሽ በወደድኩ። እንኪ ማስታወሻ ይኼንን”… የእጁን ሃብል ሰጣት። ሮጣ በምግብ ቀይራ አመጣችለት። አዘነ... አለቀሰ።
[ራሱን አየ፤ ታዘበው። የፈሰሱትን የእንባ
ዘለላዎች አነሳ። በስስት።
ህመሙን ልትጋራ መሻቷን
በደንብ አያት።]

Read 1045 times