Saturday, 22 October 2022 17:27

“ይድረስ ለወንድሜ ለማላውቅህ” - ከባለቅኔ ፀጋዬ ገብረመድኅን

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የህሊና ጥያቄና፣ የነፍስ ጥሪና ንስሐ ነው። ጥሪው ለራስ ቢሆንም፣ አድራሻው ለወንድም ነው።
ለቅርብ ሰው ነው። ደግሞም፣ ለሩቅ ሰው ነው - “ይድረስ፣ ለወንድሜ ለማላውቅህ!” ይላል። ማነህ ሲልም ይጠይቃል።
አዎ፣ መልዕክቱ ለወንድም ነው። “አንተ የማማ ኢትዮጵያ ልጅ” እያለ በስም ያናግራል። ግን፣ እንደተጠፋፉም ያውቃል። የቅርብ ሩቅ ሆነዋል።
ወንድም ወንድሙን አጥቷል። “አሳብ ለአሳብ ለተጣጣን” እያለ ብቻውን ቆሞ ይጣራል።
ምን አጣላን? ማን አጣላን? እያለም ይጠይቃል።
ይድረስ ለወንድሜ ለማላውቅህ
ይድረስ ላንተ ለማላውቅህ
ለወንድሜ ሩቅ ለማልፍህ
ለምታውቀኝ-ለማላውቅህ፣ ለምታየኝ-ለማላይህ…
ማነህ ባክህ?
ሳትወደኝም ሳታምነኝም፣ አጢነህ ለምትፈራኝ
ስናገርህ አጠንቅረህ፣ አተኩረህ ለምትሰማኝ…
ይድረስ ለክቡር ወንድሜ፣ ለአረህ ዟሪው ለገታሩ
ለሩቅ ገጠሬ ነባሩ
ለማላውቅህ ለዳርዳሩ፣…
ማነህ
ከሩቅ የምታስተውለኝ
የማልለይህ-የምትለየኝ
ተግተህ የምትገምተኝ፣ ያላየኸኝ አስመስለህ
አቀርቅረህ ተግ ብለህ
ባንደበትህ የእርግማን መርዝ፣ በልብህ ትእዝብት
ቋጥረህ…
የፀጥታው የዋሻው ሱቅ
ማነህ አንተ የቅርቤ-ሩቅ
ማነህ…
ከረን ነህ መለሎ ብሌን
ከአሰብ ወደብ እስከ ሰሜን
ስትሳብ ስትሰበሰብ
ሽንጠ ሰንበሌጠ-መርገብ
ከኡሙራ ነህ ከመረብ
አኑአክ ነህ ወይስ ገለብ
ከዘር ተገፍተህ ተሰደህ
በሐሩር ሰደድ ተጥለህ
በንዳድ መቀመቅ ታጥረህ
በእልቂት አፋፍ ፈፋ ያለህ
ማነህ
“አጋው” ነህ ወይስ ሺናሻ
ቅማንቴ ነህ ወይ ፈላሻ
ስምህ ሆነብን ግርሻ፣
ግራ ጎንደር ነህ መተከል
ባላዋቂ የምላስ ቅርስ፣ ዘር ንፍገት ስትቀበል
ያለዕዳህ ስምህ ሲበከል
እምትችል እምትቀበል፣ እማትሞት እማትነቀል
ማነህ
ቆለኛ ሸክላ ሰሪ ነህ
ያገር ዕድል ያገለለህ።
ለጥበብህ እንደመካስ
በደባትር ትንታግ ምላስ
ዘለዓለም ልብህ የሚላስ
ማነህ
ገባር ነህ የሙክት ሳቢ
እረኛ ነህ የከብት አርቢ
አራሽ ነህ ያገር ቀላቢ
አማል ነህ የግመል ሳቢ…
ባክህ ማነህ ወንድምዬ፣ አንድም ቀን የማንወያይ
በውል፣ በጣይ፣ ባደባባይ
በፎቶ ግራፍ ዓይን እንጂ፣ ዓይን ለዓይን የማንተያይ
እኔ ለወሬ አንተን መሳይ፣ አንተ ለጭንቅ እኔን መሳይ።
ማነህ እኮ የማላውቅህ
ማዶ ለማዶ ሩቅ ለሩቅ፣ በመኪና ዓይን የማይህ
የማትቀርበኝ የማልቀርብህ
ጠረንክን የምጠየፍህ
በጋዜጣ በመጽሔት፣ ወሬህን የምተርክህ
ሥዕልክን ፎቶግራፍክን፣ ላገር ጎብኚ የምሸጥህ፣
ማነህ አንተ ወንድምዬ፣ የማላውቅህ የምታውቀኝ
ሶዶሬ ማዶ እምታልፈኝ
በዝምታህ የምትከሰኝ
ባይንህ ጦር የምትገሥፀኝ
የሆድክን የማልጠይቅህ፣ የሆድክን የማትነግረኝ
ማነህ
ቦረን ነህ አባ ጋናሌ
የኛጳ ጠር አባ ጣሌ
ወይ “ሳፋር” ንጥረ ሶማሌ፣
ከረን ነህ ወይስ ዳንካሌ
አፋር ነህ አባ ቱማታ
ማታሐራ ወይ ከምባታ
ወይስ ኩናማ አባ ዱታ፣
ማነህ ጎበዝ ማነህ አያ
ኢማኑ ነህ አባ ራያ
ወይስ ኢቱ አባ ሎቲ
የአዳል ሞአ የአዳል ሞቲ፣
እኮ ማነህ ሩቅ ያለኸው
ማንነትክን የማላውቀው
እማልሰማ እማልጠይቅህ
እማትነግረኝ እማላውቅህ፣
ማነህ ጎበዝ ሳስተውልህ፣ አተኩረህ ጭጭ እምትል
እማትታጠፍ ቅምጥል
መሃል አገር ያልሸተተህ
ባሻገር ዙር ድንበር ያለህ
የእህል ደላላ እሚበላህ
ባለሚዛን እሚያዋካህ፣
ማነህ
የዝምታ መደብር ነህ?...
እኮ ማነህ ስምህ ማነው
የዘር ግንድህ የሰየመው
ተበጥሶ ያልተቀጠለው
ሥርህ ማነው?...
በልቦናህ የምታማኝ
ታዝበህ የምትሰማኝ
ባትወደኝም ባታምነኝም፣ አጢነህ የምትፈራኝ
ማክበር እንጂ እማታስጠጋኝ፣
ማንነትክን ምንነትክን፣ ላልሰማህ የምጠይቅህ
ለጉልበት ለላብህ በቀር፣ ላንተነትህ የማልቀርብህ
ከዓይነ-ጥላዬ አትሸሸኝ፣ ከዓይነ-ጥላህ እማልርቅህ
ላፌ እንጂ ለልቦናዬ፣ የማትመስለኝ የማልመስልህ
ከመንፈሴ እምገልልህ
ከሕሊናዬ እማሸሽህ
ቦታህን የማትረሳ፣ ቦታህን የማስታውስህ…
ማነህ
ይድረስ ለክቡር ወንድሜ፣ ሕመምክን ለማታዋየኝ
በጸጥታህ ለምትወቅሰኝ
ጎፈሬህን እንደአባትህ፣ እንደሞህ አጎፍረህ
በወለባ አንቆጥቁጠህ
ሎቲ አጥልቀህ ጦር አንግበህ
በመኪና እግር እማልፍህ
የማትጠራኝ የማላውቅህ፣
ማነህ
በየቱሪስቱ ካርድ ላይ
ከቦህ ሰማያዊ ሰማይ
አተኩረህ የምትታይ
ውሸትክን ፈጠህ ሳቅሁ ባይ፣
እንደቴክኖክራሲ አግቦ
ዙሪያህ በሀሰት ጌጥ ታጅቦ
እፎይታ ያቀፈህ መስለህ
ትእዝብት በዓይንህ ጦር አዝለህ
ርቀህ ተቀብረህ ሰንብተህ
የቱሪስት ካርድ የሳበህ
አንተ ማነህ?
እኮ ማነህ ወንድምዬ፣ ደራሲ የሚቀኝብህ
ሠዓሊ የሚነድፍብህ
ቀሲስ የሚቀስስብህ
የቱሪስት የጋዜጠኛ፣ ካሜራ እሚጋበዝብህ
የሚተች የሚተረጎም፣ የሚነድፍህ የማንም እጅ
የማነህ ደም የማነህ ቅጅ?...
አንተ የማማ ኢትዮጵያ ልጅ
እኔማ ሆኜብህ ፈረንጅ
አሳብ ለአሳብ ለተጣጣን
ምን አጣላን ማን አጣላን
ማን እንዳንወያይ ገራን
እንደባቢሎን ኬላ ግንብ፣ ለመተላለፍ የቀባን
አንተን የዘልማድ ዘላን፣ እኔን የመኪና ዘላን
እንድንሆን የገፋፋን?
ማነው ምንድነው ወንድሜ፣ ሆድ ለሆድ
የሚያናክሰን
ሳንርቅ የሚያራርቀን፣ ሳናኮርፍ የሚያኳርፈን!...
ይድረስ ለክቡር ወንድሜ፣ ለምትሳብ ናዳ ጥጉን
ፈፋ ዙሪያ ሸንተረሩን
ሸለቆውን ፈረፈሩን
ዳር ድንበሩን ሩቁን-ሩቁን፣
ከዘር ተገፍተህ ተሰደህ
በሐሩር ሰደድ ተጥለህ
በንዳድ መቀመቅ ታጥረህ
በእልቂት አፋፍ ፈፋ ላለህ…
እኛ መሀል ለሌለኸው
ታሪክህ ለተሸፈነው
ሁሉን ከሩቅ አብሰልስለህ፣ አጠንቅረህ ለምታየው…
ይድረስ ለክቡር ወንድ፣ ለምታየኝ ለማላይህ
ለምታውቀኝ ለማላውቅህ
ማነህ ባክህ…
ማነህ
ለበጌምድር ወይጦ ባላገር (፲፱፻፰፫-ደባርቅ)

Read 886 times