Saturday, 22 October 2022 17:29

ትንሽ ልዑል (ምኑ ላይ ነው ነጥቡ?)

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(4 votes)

ታሪኩን በዝርዝሩም በአጭሩም ማጋራት አይከብድም። ግን ምኑ ላይ ነው ነጥቡ? ታሪኩ እንዲህ ነው።
አንድ ወርቃማ ፀጉር ያለው ትንሽ ልዑል ነበር። ደግሞም የራሱ ዓለም ነበረው። የራሴ ውብ ዓለም ይለዋል። በተዋበው ዓለምም፣ በሚያምሩ ጓደኞቹና ቤተሰቦቹ  ተከቦ ይኖራል። ትልቅ ናቸው። በወርቃማ ኩሬዎች የተዋበው ዓለም፣  የብር ቀልሃ የመሳሰሉ ባህሮች፣ እጅግ የሚያምሩ አበባዎች፣… ሮዝ፣ ቀይ፣ ሰማያዊ፣ ቢጫ ፣ ነጭ ሁሉም አይነት ህብር ያላቸው  አበቦች አሉት።
በበጋው ሞቃታማ ምሽት ወደ ሰማይ ሲመለከት አንዲት ትንሽ ኮከብ አየ። ኮከብዋም ሰማያዊ ናት። የራሱን ትልቅ አለም  ከነአበቦቹ ሲመለከት፣ ከሩቅ ያለችው ትንሽዋ ኮከብ በጣም አሳዘነችው። አንዲት ትንሽ  አበባ ይዛ  ይሆናል ብሎ አሰበ።
የሱ ዓለም ውስጥ፣  ትልልቅ ቆንጆ አበቦች በወርቃማው ጅርት ዳርቻ እጅብ ብለው ፈክተዋል። ወርቃማ ውሃ እየጠጡ የደስ ደስ ባለው የሙዚቃ ስልት ይቦርቃሉ።  ያቺ ከትንሿ ኮከብ ጋር ያለችው ትንሽ አበባ ግን ማን ውሃ ያጠጣታል? በጣም ስላሳዘነችው ውሃ ሊያጠጣት ቆርጦ ተነሳ።
መንኮራኩሩን አስነስቶ ወደ ትንሿ ኮከብ አቀና። ግን ብዙ  ዓለማትን ማለፍ እና ማረፍ ነበረበት።
 መጀመሪያ ያረፈው  አንድ ትንሽ ፕላኔት ላይ ነው። ከአንድ ንጉስ በስተቀር ሌላ ማንም አልነበረም።
“አቶ ንጉስ  እንዴት ነዎ?”
“ይመስገን ትንሹ ልዑል። እንኳን ደህና መጣህ”
“ለምንድን ነው የነገሱት?”
“ንጉስ ስለሆንኩኝ ነዋ”
“ነው እንዴ? ታዲያ ማን ላይ ነው የነገስሱት? ሰው የለ”
ንጉሱ ደነገጡ። እስከ  ዛሬ ንጉስ ነኝ ብለው ያስቡ ነበር። ገልመጥ ገልመጥ ቢሉም አሁንም ሰው የለም።
“ታነግሳለህ ትሽራለህ ትንሹ ልዑል።  እስከዛሬ ንጉስ ነበርኩ። አሁን ሻርከኝ”
“አይ አንተስ መላ የለህ! መሄዴ ነው።”
“የት ነው የምትሄደው? እባክህ ትንሽ ልዑል አትሂድ”
“ምን አደርጋለሁ?”
“የፍርድ ሚኒስትር አደርግሃለሁ”
“ማን ላይ ልፈርድ?”
ንጉሱ ደስ አለው። ወደ ንግስናው ተመለሰ።
“ሚስጥር ነው። አንድ አይጥ አለች።…አለም ላይ ሁሉ ትፈርዳለህ። ነገር ግን ሞት  አትፈርድም።  ከሞተች የፍርድ ሚንስትር አይኖርም። ምክንቱም ሌላ አይጥ የለኝም።”
“ለሀገሩ የፍርድ ሚኒስትር ከሆንኩኝ ከአይጥዋ ይልቅ አንተ ላይ ሞት ብፈርድ ይሻለኛል።”
ንጉሱ ደንግጦ፣ “ልክ ለአይጥዋ የምታደርገው ምህረት ለእኔ አድርግልኝ” አለ።
“ደህና ምሬሃለሁ። ነገር ግን አንተና አይጥ እኩል ናችሁ ማለት ነው?”
“ ንጉሡ አይጥዋን በንቀት እያየ፣ “ከዚች የማትረባ ፍጡር እኩል ሆኜ ከምኖር ሞቴን እመርጣለሁ። ምህረት አልፈልግም። ሂድ ውሃ ወደ ጠማት አበባ።እዚህ ገድለህ እዚየ ውሃ አጠጣ”
“ጓደኛየን ታውቃታለህ፤”
“እንዴታ ሁሉም ሰው ያውቃታል”
ትንሹ ልዑል ተደሰተ።ንጉሱ በጣም እውነተኛ ንጉስ እንደሆነ ተረዳ። እንዲያውም ብዙ ሰራዊት ካለው ንጉስ በላይ የተከበረ ንጉስ እንደሆነ መሰከረ።
“እውነትህን ነው አያ ንጉስ። ተዋርዶ አጎብድዶ ከመኖር በክብር መሞት የንጉሶች ባህሪ ነው።”
“አሃሃ- እኔ ስሞት ንግስናየ ላንተ ነው የማወርሰው። ከእውነተኛ ልጄ በላይ አንተ እውነተኛ ልዑል ነህ።”
“የታለ እውነተኛ ልጅህ?”
ከአይጥ በቀር ሌላ የለም። ንጉሡ አዘነ።
“ረጅም ዘመናት አለፉ እኮ። አይ ህይወት! “ አለ። አይጧን በጎሪጥ አያት።  “ከዚች ተገብስ ጋር ብቻየን ቀረሁ” ብሎ ተከዘና በወርቅ ዋንጫ ቀይ የወይን መጠጥ ቀድቶ ጭልጥ አድርጎ ጠጣ።  “በል ለመንገድ ከዚህ ተጎንጭ” ብሎ በሌላ የወርቅ ዋንጫ  ቀዳለት።”
“ጠጣ ያዝ። ደስታ የሚያመጣና ሃዘን የሚያስረሳ መጠጥ ነው። እርግጥ ህጉን አውቀዋለሁ። ለዚያ ነው ደብቄ የማስቀምጠው” ብሎ ጠርሙሱን ከዙፋኑ ጀርባ አስቀመጠው።
“ህጉ ምንድን ነው?” አለው ትንሹ ልዑል። ደስታ የሚሰጥ መጠጥ በጣም ጥሩ ነገር መሆን አለበት ሲል አሰበ።
“ነገስታትና ሃብታሞች አይጠጡ ህዝብ እንዳይበድሉ። ደሃ ይጠጣ፤ ድህነቱን ይርሳ ተብሏል። እኔ በድብቅ ነው የምጠጣው።”
“የማይረባ ህግ ነው። ከአሁን በኋላ በግልጽ መጠጣት ይችላሉ። ምን ሰው አለና ነው?”
“አ..አ..አ.. ሰው የለም እንዴ? ረስቼው። በግልፅ መጠጣት እችላለሁ ማለት ነዋ።”
“ለኔም አንድ ጨምሩልኝ”
“ አንድ ለመንገድ ነው የሚባለው። ደግሞም አይቻልም። መንገደኛ መስከር የለበትም። መጠጡ ደስታ ቢሰጥም አእምሮንም ያዛባል።”
“ታዲያ ከዚህ ስሄድ ይህን መጠጥ የት አገኘዋለሁ?”
“አትዘን ትንሽ ልዑል። መንኮራኩሩን ይዘህ በዚህ አቅጣጫ  ስትበር አንድ ጥሩ ሰካራም ብቻ የሚኖርበት አለም ታገኛለህ” አለ።
ትንሽ ልዑል አንድ ሰካራም ብቻ  ወደ ሚኖርባት ፕኔት ሄደ። ደርሶም አየ።  በምሽት ጨረቃ ሰካራሙ እየተከዘ ብቻውን ይጠጣል።
“አያ ሰካራም፣ ለምንድን  ነው ብቻዎን የሚጠጡት?”
“ለመርሳት”
“ምን ለመርሳት”
እያፈረ፣ “ማፈሬን ለመርሳት”
“ምን የሚያሳርፍ ነግር ተገኘ?
“መጠጣቴ?”
“ እርስዎ ከዚያ እብድ ንጉስ የባሰብዎ ሆኑ…”
ትንሹ ልዑል ወደ ሌላ ዓለም ቀጠለ ጉዞውን። አንድ ራሰ በራ ብቻውን ጠረጴዛ ላይ ተቀምጦ ቁጥር ይቆጥራል።
“ዘጠኝ መቶ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ ስድስት መቶ አርባ ሰባት ከ-”
“ምን እያረጉ ነው?”
“አቋረጥከኝ። ሂሳቡ ጠፋብኝ። ትንሽ ልዑል. እንኳን ደህና መጣህ። ዘጠኝ መቶ ሚሊዮን”
“ምን እያደረጉ ነው”
“ከዋክብት እየቆጠርኩኝ ነው- ተመራማሪ ነኝ”
“ቆጥረው ምን ያደርጓቸዋል?”
“እመዘግባቸዋለሁ”
“ከዚያስ?”
“አሃ ትዝ አለኝ። የኔ ናቸው”
“ለምን?”
“መጀመሪያ የቆጠርኳቸው እኔ ነኛ”
“እርሶ ደግሞ ከንጉሱም ከሰካራሙም የባሱ ሆኑ።”
መንኮራኩሩን አስነስቶ ጉዞውን ቀጠለ።
ወደ ሌላ ዓለም ደረሰ። አንድ ፋና ወጊ ሰው መብራቱን ያበራል ያጠፋል።
“ነጋ መሸ ነጋ መሸ እያለ  ይደጋግማል።”
“ምን እየሰሩ ነው?” አለ ትንሹ ልዑል።
“እያስጠነቀቅኩና እያበሰርኩ ነው”
“ምኑን”
“መንጋትና መምሸቱን”
“ለማን? ማንም የለምኮ”
“ቢሆንም፣ መብራት ማጥፋት ማብራቴን እቀጥላለሁ። ለጀግኖቹ መርከበኞች ፋና ወጊ  አሳሾች
“የእርስዎ ደግሞ ይብሳል።” መንኮራኩሩን አሰነስቶ ጉዞውን ቀጠለ።
ወደ ትንሿ ኮከብ ደረሰ።
ይህቺ ትንሿ ኮከብ ምድር ትባላለች።
ብዙ  ነገስታት፣ ብዙ አሳሾች፣ ብዙ ተመራማሪዎች ያሉባት ሃይለኛ ኮከብ ናት ባካችሁ! እሷ ራስዋም ውሃ አጠጣችው።

Read 842 times