Saturday, 22 October 2022 17:35

ሥርዓት አቃቢ፣ ሥርዓት ቀያሪ፣ ነባርና አዲስ፣ ብሉይና መጤ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአገራትና የመንግሥት፣ የሃይማኖትና የባሕል፣ የፍልስፍናና የፖለቲካ ታሪኮች ውስጥ የማይጠፋ ነገር ቢኖር፣… ሥጋትና ቅሬታ የተቀላቀለበት ስሜት ነው።
ነባሩ እንዳይፈርስና የባሰ እንዳይመጣ መስጋት፣ መቼም ቢሆን ከሰው ታሪክና ከሰው ኑሮ ተለይቶ አያውቅም።
ከነባሩ የተሻለ አዲስ ነገር እንዲመጣ መመኘትም፣ ከሰው ተፈጥሮ የሚመነጭ ባሕርይ ነው።
ችግር እንዳይባባስ መስጋት ሕይወት እንዲሻሻል መመኘት፣… ተፈጥሯዊ ባሕርይ ብቻ ሳይሆኑ ጤናማ ዝንባሌም ናቸው።
ችግሩ ምንድነው?  እንደተለመደው፣… ከሰው ስህተት አይጠፋም። የሃሳብ መስመሩ ይሳሳታል። ሚዛኑ ይዛባል።
አንዳንዴ፣ ጥሩና መትፎ ይደበላለቁበታል። በዚህም ትክክለኛ ሃሳቦችን ይቃወማል። ጥሩ ለውጥ ሲመጣ፣ “የባሰ ነው” ብሎ ይሰጋል፤ ይከላከላል፤ ይጠላል፤ ያወግዛል።
ግን እንዳሰበው ላይሆን ይችላል።
“የተሻለ ነው” ብሎ ለብዙ ጊዜ የተመኘውና የዘመረለት፣ ለዓመታት የደከመለትና ከባድ ዋጋ ከፈለለት ነገር፣ በእውን ሲታይ የመከራ ተራራ ሊሆንበት ይችላል። የሲዖል ጉድጓድ ሲቆፍር ነበር ለካ እድሜውን የጨረሰው ያስብላል።
ጥሩና መጥፎ የዚህን ያህል ሙሉ ለሙሉ ባይምታቱበት እንኳ፣ የሃሳብ መስመሩ ተዛብቶ ሽቅብ ቁልቁል ባይገለበጥም እንኳ፣ ሚዛኑ ሊሳሳት ይችላል።
ለዓመታት ለፍቶ፣ ያለ የሌለውን ጥሪት ሁሉ አሟጥጦ፣ ከማላዊ ወደ ማሊ፣ ከቬንዝዌላ ወደ ጓቲማላ፣ ከሃይቲ ወደ በርማ በስደት መግባት ቢችል፤ እንዳሰበው የጥገኝነት ብቻ ሳይሆን የዜግነት ፈቃድ ቢያገኝ አስቡት። በከንቱ ነው የደከመው።
ያን ያህልም ለውጥ ላያመጣ ነገር፣ ትልቅ ልዩነት የሚያስገኝ መስሎት ነው። ማላዊ ከማሊ ትሻል ይሆናል። ግን ልዩነታቸው፣ ያን ያህልም ሚዛን የሚደፋ አይደለም። ሚዛናችን ካልተዛባ በቀር።
ፊንላንድ ወይም ስዊድን ውስጥ ሆኖ፣ እንደ ዴንማርክ የመሆን ህልም የያዘ የፍልስፍና ሃሳብ ወይም የፖለቲካ አላማም እንዲሁ፤ ሚዛኑ ተበላሽቷል። ለጥቃቅን ለውጦች ነው እድሜውን የሚጨርሰው። ኪሳራ ነው።
የሃሳብ ሚዛኑ እየተዛባ በከንቱ ልፋት የእዳ ተሸካሚ ይሆናል።
የሃሳብ መስመሩ ከተዛባና ከተበላሸ ደግሞ፤ በገዛ እጁ የለኮሰው እሳት ይለበልበዋል። ማገዶ ሆኖ አመድ ሆኖ ሊቀርም ይችላል። ለሌሎችም ጦስ ይንባቸዋል እንጂ።
 የሃሳብ መስመሩ ባይሳሳትና ሚዛኑ ባይዛባስ? ከብዙ መከራ የመዳን፣ ለትልልቅ ስኬት የማብቃት እድል ይኖረዋል። በቂ ነው ማለት ግን አይደለም። በጭራሽ።
የሃሳብ መስመሩ እጅግ የጠራና የተስተካከለ ቢሆንም እንኳ፤ ነባር ሥርዓቶችንና አዳዲስ ለውጦችን መርምሮ መዳኘት ቀላል ስራ አይደለም።
ነባር ሥርዓት ሁልጊዜ፣ ብዙ ፋይዳዎችንና ብዙ እዳዎችን አቀላቅሎ የያዘ ነው። ስንቱን መርምሮ፣ የስንቱን ገፅታ አነጻጽሮ መዳኘት ይችላል? በዚያ ላይ፣ ሁሉም ፋይዳና እዳ እኩል አይደለም። አንዳንዱ ጣፋጭ ጣዕም ወይም አጣዳፊ ህመም ነው።
አንዳንዱ ደግሞ፣ ለጊዜው ምንን ጣዕምና ምሬት ባይኖረውም፣ ውስጥ ለውስጥ እየፈወሰ የሚያንፅ፣ አልያም ቀስ በቀስ ከስር እየሸረሸረ የሚያመነምን ሊሆን ይችላል።
ለየትኛው ምን ያህል ትኩረትና ምን ያህል ቅድሚያ መስጠት እንደሚያስፈልግ ማስላትና ማመዛዘን ቀላል ነው? አይደለም።
አዳዲስ ለውጦችም እንደ ነባር ስርዓቶች፣ የፋይዳዎችና የእዳዎች፣ የጥፋቶችና የልማቶች ቅልቅል ናቸው። ከዚያ ላይ፣ በዓይነትና በመጠን፣ በስፋትና በፍጥነት  የሚለያዩ ናቸውና፤ ጥሩና መጥፎውን ለይቶ መዳኘት ክብደታቸውን መመዘን የዋዛ ስራ አይደለም።
Read 322 times