Saturday, 29 October 2022 11:58

“ድሮስ ቢሆን...”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ በግለሰብ ደረጃ ስናወራ እንኳን እኮ አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ አሀ...ከምንም ጋር ያልተያያዘ፣ “ከጀርባ የሆነ ሴራ አለበት፣” ምናምን ለማለት እንኳን ዕድል የማይሰጥ የራሳችሁን ሀሳብ መስጠት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ወይም እኮ የሆነ ነገር ሲነግሩን...አለ አይደል...“እዚህ ላይ የአንተን ሀሳብ መስማት አልፈልግም፣” ይበሉንና ቁርጣችንን እንወቅ!
“ስማ ትንግርቱ እውነት ሊሆን ነው አይደል!”
“ትንግርት! የምን ትንግርት?”
“አንተ ሰውዬ ጭርሱን ሁሉንም ነገር ተውከው አንዴ! የዓለም ፍጻሜ ትንግርት ነዋ! እስከዛሬ አልሰማሁም እንዳትለኝ!”
“የዓለም ፍጻሜ ነው ያልከኝ! ግን አንተ እንዲህ አይነት ነገር በምን አወቅህ? ማለቴ ከሰማይ ቤት ቴሌግራም ተላከልህ እንዴ!”
“ይልቅ ቀልዱን ተወውና እውነት አልሰማሁም እያልከኝ ነው!”
“አልሰማሁም እያልኩህ ነው፡፡ እሺ አሁን ለምን እንደዛ እንዳልክ ለእኔ ለቀሺሙ በሚገባኝ መንገድ ልትነግረኝ ትችላለህ?”
“በቃ ፑቲን በሁለት ወይ ሦስት ቀን ጊዜ ውስጥ  አሜሪካንን አውሮፓን በኑክሌር ሊያደባያቸው ነው አሉ፡፡ አይገርምም! አንተን ይመስልሀል?”
አስቸጋሪ ነው፣ የምር በጣም አስቸጋሪ ነው። አለ አይደል... የተረጋጋ ነው፤ ለዘንድሮ ወሬ ቶሎ ጆሮውን አይሰጥም የምትሉት ሰው፣ መቶ ሰማንያ ዲግሪ ተሽከርክሮ እዛኛው ሰፈር ሲገባ የሆነ ደስ የማይል ነገር አለው፡፡ አሀ..ልክ ነዋ! በኋላ “ወዳጅህ እንዲህ አዳልጦት ዘጭ ሲል ዝም ብለህ ያየኸው!” ቢባል ሼም አይሆንም!
“አንተ ግን ከመቼ ወዲህ ነው እንዲህ አይነት ተረት የሚመስሉ ነገሮች መስማት የጀመርከው? ኑክሌር መተኮስ ማለት የሰፈር ደብድብ መሰላችሁ እንዴ ዝም ብሎ ቃታ የሚሳበው!” እመኑኝ አያስጨርሳችሁም፡፡
“በቃ... እዚህ ሀገር ላይ ያላችሁት አዋቂዎች እናንተ ብቻ ናችሁ፡፡ እኛ ምንም የማናውቅ መሀይሞች ነን ማለት ነው፡፡”
“አንተ ምን ነካህ! አሁን እንዲህ አይነት ነገር ከአፌ ወጣ! እኔ አሁን የሚስኢንፎርሜሽን ዘመን ስለሆነ ላለመሳሳት ብንመካከር ምን ችግር አለው ብዬ ነው፡፡”
“ዲስኩርህን ተወኝ እባክህ!” (ሰውየው ምነ ነካው! በጠዋት ደረቋን ቀንድቦ ነው እንዴ የመጣው!) “አላስወራ አላችሁን እኮ!”
“ኸረ እሺ! እሺ! ይቅርታ!”
ልጄ ዋነኝየው ኑክሌይር እኮ ተኳሹንም፣ የተተኮሰበትንም የዳር ተመልካቹንም አንድ ላይ አነባብሮ እምሽክ ነው!
እናላችሁ...“ቅርቤ ነው፣ የምለውንም ይረዳኛል፣” ያላችሁትን ሰው ሳይቀር ዘንድሮ የሆነ ነገር ለማሳመንም ሆነ ለመተማመን አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ኮሚኩ ነገር እኮ አንዳንዱ ደግሞ ሲፈጥረው ስትጠረጥር ኑር ያለው ነው የሚመስለው፡፡ አጠገቡ ብታስነጥሱ እንኳን...አለ አይደል... “ትን ብሎት ሳይሆን እኔ ላይ የሆነ በሽታ ሊያስተላልፍብኝ ነው፣” ለማለት ወደ ኋላ የማንል  እኮ ቁጥራችን የትና የት ነው፡፡
መቼም ከሰው ጋር መመካከሩ ሸጋ ነው፣ በንጹህ ልብ እስከሆነ ድረስ፡፡
“ይሄ የኑሮ መወደድ መች ነው የሚለቀን?” ትላለችሁ፤ ቢሆንም ባይሆንም የሆነ የማጽናኛ ነገር ለመስማት፡፡
“መቼም አይለቀንም፡፡ ምን አለ በለኝ እየባሰበት የሚሄድ ነው የሚመስለኝ፡፡ አንተ ምን ይመስልሀል?”
“የእኔን አስተያየት እናቆየውና የአንተን አመለካከት አስረዳኝ፡፡ ለምን? ማለቴ በምን ምክንያት ነው እየባሰበት የሚሄደው?”
“ለምን ብሎ ነገር አለ እንዴ! ይብስበታል በቃ ይብስበታል፡፡ ሰውዬው፤ ሀገሪቱ እኮ ኢትዮጵያ ነች፡፡”
“ለምን ያልኩህ እኮ ለጭቅጭቅ ሳይሆን ምክንያቶቹን ብናውቅ ለሁላችን ጥሩ ይሆናል ብዬ ነው፡፡”
“ጭቅጭቅ ነው እንጂ! እኔ የምለው... በቃ ሁሉንም ነገር የምታውቁት እናንተ ብቻ ናችሁ? ለወንድ በር ልቀቋ! ዘላለማችሁን...”
“እሺ ይቅር...ይቅር!”
ይሄኔ ቶሎ ብሎ ሽው ማለት ነው፡፡ መወያየት የሚባል ነገር አይኖርማ!
“ስማኝ እንትና እኮ አይደለም እዚህ ሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ አክቲቪስት ባይሆን ምን አለ በለኝ! እውቀቱ እውቀት መሰለህ አንዴ! እሱ ዘንድ ጭንቅላት አለች! ስማ አይደለም እኛን... አውቃለሁ የሚለውን ምድረ ፈረንጅ ሁሉ በእንትኑ ቁጭ ማድረግ የሚችል ነው፡፡ አንተም የምትስማማ ይመስለኛል፡፡”
“እኔ ግን እንደዛ አይመስለኝም፡፡”
“ምን ማለት ነው... እንደዛ አይመስለኝም ማለት?”
“አይ ብዙ ጊዜ በሚሰጣቸው ቃለ መጠይቆች ስሰማው የሆኑ ነገሮች ከዚህም፣ ከዛም እየቆራረጠ ለመስፋት ይሞክራል እንጂ ምንም ነገር ላይ ሙሉ ለሙሉ እንኳ ባይሆን ትንሽ ጠለቅ ያለ የሚባል እውቀት የለውም፡፡”
“አቤት! አቤት! የእኛ ሀገር ሰው! በቃ ዘለዓለም ምቀኝነት፡፡ በቃ ገና ለገና ብቅ አለ ብላችሁ አናት አናቱን ልትሉት ነው!”
“ኸረ ተረጋጋ የምን ምቀኝነት ነው የምታወራው፡፡”
“ለነገሩ እኔ ነኝ ጥፋተኛው፡፡ የሚረባ ሀሳብ አገኛለሁ ብዬ ከእናንተ ጋር ማውራቴ!”
በትንሽ ትልቁ ጦሽ የምትለው ነገር ካለችባችሁ በቃ ምን አለፋችሁ “የቀለጠው መንደር፣” ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ ይሰውረንማ!
እናላችሁ...ዘንድሮ ከብዙዎቻችን ጋር በሚደረግ ወሬ ከምንም ጋር ያልተነካካ የራሳችሁን አስተያየት መስጠት አስቸጋሪ ነው፡፡ ምንም በሉ ምንም የተናጋሪውን ሀሳብ “አሀ ገዳዎ፣” ብላችሁ ካልተቀበላችሁ እናንተን አያድርገኝ፡፡ “ድሮስ ቢሆን...” ብሎ ይጀምርላችኋል፡፡
እኔ የምለው ብዙዎቻችን እንዲህ ነገሮችን በአንድ ጊዜ ሦስት መቶ ዲግሪ መጠምዘዝ እንደምንችለው፣ ምነው  ክፉ ክፉውን ነገር ወደ ደግ፣ ደግ ነገር አናሽከረክረውምሳ!
እሱዬው የሆነ እሱ ‘የሚደነቅ ቤት’ የሚለው ‘ፉድ ቤት’ ይዟችሁ ይገባል፡፡ “የዛን ቤት ምግብ አንድ ጊዜ ከቀመስክ ምን አለ በለኝ ምሳ ሰዓት ቦታ እንዳይያዝብህ በሌሊት መጥተህ እስኪከፈት ካልጠበቅህ ከምላሴ አንድ፣ ሁለት እየተባለ ጸጉር ባይነቀል! (ዘንድሮ ከዚህ የባሰ መአት ማጋነን አለ በሚል የገባ መሆኑ እንዲታወቅ ነው፡፡)
አሪፍ የሚለውን ምግብ ለሁለታችሁም ያዛል፡፡ እና ሁለቴ እንደጎረሳችሁ “እህ ታዲያስ!” ይላችኋል! እናንተ እኮ ምን እንደጎረሳችሁ፣ ምን እያኘካችሁ እንደሆነ ለማወቅ አፋችሁ ውስጥ ወዲህ ወዲያ እያዘዋወራችሁ ምርመራ ላይ ናችሁ፡፡
“ምነው ዝም አልክ?”
“እኔ አስተያየት ከመስጠቴ በፊት የሆነ ነገር ብጠይቅህ ቅር ይልሀል?”
“ለምን ቅር ይለኛል! ደስ ነው የሚለኝ!”
“የቤቱ ምርጥ ምግብ ይሄ ነው አይደል?”
“ማስተካከያ፣ ምርጥ ሳይሆን የምርጦች ምርጥ ነው፡፡ እናስ...?” ዓረፍተ ነገሩ መጨረሻ ላይ የጥያቄ ምልክት ቢኖርበትም እየጠየቀ ሳይሆን እሱዬው “አሁን ያልኩትን ድገምልኝ፣” ማለቱ ነው፡፡ ልክ ነዋ...ለምሳሌ የሆነች ልጅ “ምናምኔ” ብሎ አምጥቶ “ስማ ታዲያ አረፍ አይደለች?” ሲል መልስ አሰጣጥ ላይ ብልጥ ካልተሆነ አስቸጋሪ ነው... ለእናንተ አሪፍ ላትሆን ትችላለቻ! እናላችሁ... የምርጦች ምርጥ የተባለውን ምግብ ለጋበዛችሁ ሰው እንዲህ ትሉታላችሁ...
“እውነቱን ልንገርህና አሁን እያሳሰበኝ ያለው ሌሊት ወደ መጸዳጃ ቤት እንዳያሯሩጠኝ ነው፡፡”
“ምን ለማለት.... ቆይ እናንተ የምታጨበጭቡላቸውን ቤቶች አናውቃቸውምና ነው!”
እና...“ድሮስ ቢሆን...” የሚሉት ነገር እንደልባችን እንዳንናገር ‘ጋሬጣ’ እየሆነብን ነው ለማለት ነው፡፡  
ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 1376 times