Saturday, 29 October 2022 12:10

የሰይጣን መኪና

Written by  ትዕግስት ታፈረ ሞላ
Rate this item
(6 votes)

በእንቅልፌ ውስጥ ነቅቼ ነበር፡፡ የተኛሁበትን አልጋም ቤቱንም አላውቀውም፡፡ አንዲት ሴት በሩ አጠገብ ሳጥን ላይ ቁጭ ብላ ጥጥ ታሳሳለች። እሷንም አላውቃትም፡፡ ድንገት በሩ ተከፈተና አንድ ሰው ገባ፡፡ ቢንያም ነው፤ የመሥሪያ ቤት ባልደረባዬ፡፡ ሴትየዋን አንዴ በአይኑ ገረፍ አርጐ ወደ እኔ መጣ፡፡ ወደ እኔ ስለመጣ ደስ አለኝ፡፡ በሙሉ ፈገግታ አየሁት፡፡ የእሱ ፊት ላይ የሠላምታ ፈገግታ አይታይም፡፡ ደግሞ አልተኮሳተረም፡፡ አልጋው ላይ ተቀመጠና በሁለት እጆቹ የተጋደመ አካሌን አጠረ፡፡ እጆቹ መሀል ገባሁ፡፡ ፊቱ ለፊቴ እጅግ ቅርብ ነበር። ዓይኖቼ መድረሻ አጡ፡፡ ሳልወድ ከንፈሮቹን አየሁ፡፡ ብስል ያለ ቀይ፤ የወዛ ከንፈር፡፡ ድንገት ሳላስበው ከንፈሩ የእኔ ከንፈር ላይ አረፉ፡፡ ለአፍታ ያህል፡፡ በጣም የገረመኝ ነገር፣ ፊቴ ያለ መስታወት ይታየኛል፡፡ ቅልጥ፤ ድንግጥ ብሎ፡፡
እነኛ ውብ ከንፈሮች እንደገና ወደ እኔ ተሳቡ። አጥር የሆኑኝን ክንዶቹን ተመርኩዤ ሸሸሁት፡፡ በጥያቄ አየኝ፡፡ በር ላይ የተቀመጠችዋን ባለ ጥጥ አሮጊት አሳየሁት፡፡ ሃሳቤ ወዲያው ገባው፡፡ ከአልጋው ተነስቶ እጁን ዘረጋልኝ፡፡ ለዳንስ እንደተጋበዘች አይን አፋር ልጃገረድ እየተሽኮረመምኩ ከአልጋው ወርጄ ተከተልኩት፡፡
የሁለታችንም ልብ እጅግ ቸኩሏል፡፡ አንዳች ገለልተኛ ቦታ ፍለጋ እየተቅበዘበዝን እያለ ቢኒያም ታክሲ አስቆመ፡፡
እንደተያያዝን መኪናው ውስጥ ድርግም አልን፡፡ አሮጊቷ በእግሯ ትከተለናለች፡፡
እዚህ ላይ ነቃሁ፡፡ ነቅቼ እንኳን ፊቴ እንደቀለጠ፣ ልቤ እንደደነገጠ ብዙ ቆየ፡፡ ከደቂቃዎች በፊት ማር ልሼ ጣዕሙ ከአፌ እንደማይጠፋ አይነት የከንፈሮቹ ለዛ ሙሉ ቀን ከእኔ ጋር ነበረ፡፡
ህልሜ ታማኝ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ስነቃ ሙሉ ሃሳቡን ከምረሳው ቅጥቃጤ በቀር ያስታወስኩትን በተጨባጭ አይቼዋለሁ። አያቴ በሰፈራችን ዝነኛ ህልም ፈቺ ናት። ከልጆቿም ከልጅ ልጆቿም የእሷን ተሰጥኦ ትወርሳለች ተብዬ የምጠበቀው እኔ ነኝ፡፡
የዛሬው ሕልሜ ግን ከበደኝ፡፡ አያቴ በጠዋት ለቅሶ ልድረስ ብላ ስለሄደች አልተገናኘንም፡፡ ራሴ ለመተንተን ሞከርኩ፡፡ መሳሳም መራራቅ እንደሆን አውቃለሁ፡፡ ታዲያ ከቢንያም ጋር መቼ ተቀራርበን እንራራቃለን፡፡ ባለጥጧ አሮጊትስ ማናት? አልጋ ምንድን ነው? አልጋ እንኳን ማዕረግ ነው፡፡ ግን ወረድኳ! መኪና ተሳፍሮ መሄድስ? ሐይቅና ባህር በታንኳም በዋናም ማቋረጥ ውጭ ሀገር መሄድ ነው፡፡ መኪናስ ወዴት ይወስዳል?
አየር ጤና ቆሜ ከህልሜ ጋር እየተጫወትኩ የመሥሪያ ቤታችን ሰርቪስ ድንገት ፊቴ ገጭ አለና ገባሁ፡፡ እንደወትሮዬ ሞቅ ያለ ሰላምታ አልመጣልኝም፡፡ በጅምላ ደህና አደራችሁ አልኩና የጅምላ መልሳቸውን እየሰማሁ ቁጭ አልኩ፡፡
ሰርቪሳችን ዘነበወርቅ ሲደርስ እንደገና ቆመና ሌሎች ባልደረቦቻችን ገቡ፡፡ የቢንያም ሠፈር ዘነበ ወርቅ መሆኑን እስከዛሬ ልብ ብዬ አላውቅም። እንዳየሁት ህልሜ ትዝ አለኝ፡፡ ሌሊት ያየኋቸው ከንፈሮቹ ከእሱ ጋር መሆናቸውን ለማረጋገጥ ሳላስበው አፈጠጥኩበት፡፡
አጋጣሚ ይሁን ለማፍጠጤ መልስ ለመስጠት ይሁን እንጃ ብዙ ባዶ ቦታ እያለ እኔ አጠገብ መጥቶ ተቀመጠ፡፡
በሰላምታችን መሃል እየሰረቅሁ ከንፈሮቹን አያለሁ፡፡ የሌሊቱ በወዝ ይበልጣል እንጂ ከንፈሩን አሁንም ይዞታል፡፡
ስለቆጡ ስለባጡ ያወራልኛል፡፡ እኔ በህልሜ ከእሱ ጋር የተወንኩትን ድራማ በጭንቅላቴ ውስጥ በምልሰት እየተረኩ አየዋለሁ፡፡
ስንመለስም አንድ ላይ ተቀመጥን፡፡ ውስጤ ይገርማል፡፡ በእውን ሊሆን ያለውን ነገር በራዕይ አሳየኝ እንዴ እላለሁ፡፡
ማታ ቤቴ እንደገባሁ ህልሜን ሴት ጓደኛዬ ያየችው አስመስዬ ለአያቴ ነገርኳት፡፡ አያቴ ፊቷን ጥቁር አድርጋ “ሦስት ጊዜ ህልም እልም፣ ህልም እልም ትባል” አለችኝ፡፡ በጣም ደነገጥኩ፡፡
“ለምን?” አልኳት በእርጅና የደከሙ አይኖቿን በአይኖቼ ወጥሬ ይዤ፡፡
“ከአልጋ መውረዷ ከማዕረግ መውረድ ነው። መኪናም ሠይጣን ነው፡፡ ልጁ አይሆናትም፡፡” አለች ቁርጥ አድርጋ፡፡
“እሽ አሮጊቷስ ምንድን ናት?”
“ጠባቂ አድባሯ ናት፣ የእሷ መከተል ጥሩ ነው” አለችኝ፡፡
የአያቴን የህልም ፍቺ መጠራጠር አልችልም። ግን ሦስት ጊዜ ህልም እልም ህልም እልም ማለት አቃተን፡፡
ከቢንያም ጋር የመሥሪያ ቤታችን ሰርቪስ ላይ ተገናኝተን የቆጡን የባጡን እናወራለን፡፡ ከዚህ በፊት የማውቀው የቆጥና የባጥ ወሬ አዲስ ይሆንብኛል፡፡ ግን ግር ይለኛል፡፡
መኪናችንን ሠይጣን የሚነዳው የሚነዳው ይመስለኛል፡፡
አንዳንዴ ደግሞ ብዙ ሴቶች ለእሱ ስላላቸው ፍቅርና ክብር ያወራልኛል፡፡ አንዷ ጥርስህ ያምራል ካለችው ሌላዋ ጨዋታህ ትለዋለች፡፡ ሁሉም ሴቶች ደግሞ ቆንጆ መሆናቸውን ይነግረኛል፡፡
አንዳንድ ወንዶች እነሱ ፍቅር እንደያዛቸው ማመን ሲያቅታቸው ስለሚያፈቅሯቸው ሴቶች ለወደዷት በማውራት ማፍቀርን እንደሚከላከሉ በልማድ ደርሼበታለሁ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ እነሱ ፍቅር ባይዛቸውም መወደዱን ይፈልጉታል። ለመወደድ በሌሎች ሴቶች ያላቸውን ሞገስ አጋነው ያወጋሉ፡፡
ይኼን ተራ ነገሩን አልወደድኩለትም። ግን ልቤ ሦስት ጊዜ ህልም እልም ህልም እልም ማለት አልፈለገም፡፡
አንዳንዴ በጨዋታ መሀል ውስጤ ህልምሽን ንገሪው ንገሪው ይለኛል፡፡ ግን ጨዋታውን ጥያቄ እንዳያደርገው ፈራሁ፡፡ በዚህ ኮርቶ ደግሞ የሰርቪስ ውስጥ ጨዋታችን ቢቀርስ የሚል ስጋት ወጥሮኝ ነበር፡፡ ግን ሰው እንዴት አንድ ወንድ ኮራ አልኮራ እያለ በተዋረደ ሃሳብ ራሱን ለማስጨነቅ ይፈቅዳል?
ኩራቱ ንቀት ቢፈጥርብኝስ እላለሁ፡፡
ትልቁ ፍርሃቴ ግን ህልሜን ስነግረው ሰይጣን ያለ እኔ ፈቃድ በሌሊት ጭንቅላቴ ውስጥ ደርሶ ስላዘጋጀው ድራማ በነፃነት የሚያወራ ዓይነት ሰው ሆኖ ቢገኝስ … የሚለው ነው፡፡ ማለቴ ድራማውን እያደነቅን ወይ እየተቸን ብንስቅስ? ይኼን የእውነት እፈራለሁ፡፡ እንዲህ ያለን ጨዋታ የሚቋቋምን ሰው አለማክበር ከባድ ነው፡፡ ብዙ የተናቀ ሰው በሞላው ጭንቅላት ውስጥ ደግሞ የተከበረ ሰው ሲገን ንጉስ ይሆናል። ዙፋኔ ግን ረግቧል፤ ሸክም አይችልም፡፡
የቱንም ያህል ብፈራም ሦስት ጊዜ ህልም እልም፣ ህልም እልም ማለት አልቻልኩም፡፡
የእኔንና የቢንያምን አፍላ ቅርርብ የመሥሪያ ቤት ጓደኛዬ ልብ ብላ ካስተዋለች በኋላ አንድ ቀን በቁም ነገር ጠራችኝ፡፡
“ሰዎች ከቢንያም ጋር ሌላ ነገር የጀመራችሁ መስሏቸዋል፡፡” አለችኝ፡፡
ሳቄ መጣ፡፡ “ታዲያ ምን ይሁን” ብላት ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ግን የአንዳንድ ሰዎች ክብር በእውነተኛ መልስ ክፉኛ ስለሚነካ ዝም አልኳት፡፡
“ሚስቱ እኮ አንዴ መሥሪያ ቤት መጥታ ነበር፡፡” አከለችልኝ፡፡
ውስጤ አሁንም ለጨዋታዋ በረዶ ሆነ፡፡ ምንም የሚሞቀኝ ነገር አጣሁ፡፡ ሚስት ቢኖረው ባይኖረው እኔ ማግባት አልፈለግኩ፤ ምን ማለቷ ነው? የቆጥና ባጥ ወሬውን ወድጄለታለሁ። በእርግጥ ሁሌ ሳገኘው ህልሜ ትዝ ይለኛል። ህልሜ ትዝ ሲለኝ ከንፈሮቹን አያለሁ፡፡ ከንፈሮቹ ለሰይጣን መኪና የመሳፈሪያ ትኬት ይመስሉኛል፡፡ ትኬቱን መቁረጥ አልፈልግም፡፡
አንድ ቀን ከሥራ ወጥተን እንደተለመደው ሰርቪስ ውስጥ ተገናኘን፡፡ ዘነበወርቅ ስንደርስ ይወርዳል ብዬ አየሁት፡፡ አልወረደም፡፡ አየር ጤና ከእኔ ጋር ወረድን፡፡ ልክ በህልሜ እንዳየሁት እጄን ይዞ፣ እሱ እየመራ ካራ ካራ የሚል ታክሲ ውስጥ ገባን፡፡ ሚስቱ ብታየንስ? ውስጤ የሰይጣን መኪና ውስጥ እንደገባን ይነግረኛል፡፡ ወራጅ ማለት ወይም ህልም እልም፤ ህልም እልም ማለት ደግሞ አልቻልኩም፡፡ ባለ ጥጧ አሮጊት ትዝ አለችኝ፡፡ ሹፌሩ ፈጣን ጋላቢ ነው፡፡ መቼ እንደምንወርድ አላውቅም፡፡
(ምንጭ፡- አዲስ አድማስ ድረ-ገጽ፤ 19 ኖቬምበር 2011)

Read 1162 times