Saturday, 29 October 2022 12:33

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሴት ልብወለድ ጸሐፍት ቤዛዊት ዘርይሁን፤ “የመሐል ልጅ”

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(1 Vote)

የመሐል ልጅ (2013) ከጊዜያችን ድህረ ዘመናዊ ልብወለድ ጸሐፍት መካከል አንዷ በሆነችዉ ቤዛዊት ዘርይሁን (Bez Brown) ለህትመት የበቃ የአጫጭር ልብወለዶች መድበል ነዉ፡፡ በዚህ መድበል ዉስጥ የቀረቡት ልብወለድ ሥራዎች የተጻፉበት ቋንቋ (literaery diction) ዉብ ነዉ፡፡ የአንድ ድርሰት ታላቅነት አንዱ ሚዛን የተሰነደበት ቋንቋ ደረጃ ነዉ፡፡
በዚህ ጽሑፍ አትኩሮቴን ያደረኩት በቤዛዊት ሦስት የልብወለድ ሥራዎች ላይ ነዉ። እነዚህ ሦስት የልብወለድ ሥራዎች ክሽ ክሽ፣ መጫወቻዉ እና የዝ’ጌር ስኪኒ ሱሪ ናቸዉ፡፡        
፩. የተጋረደዉ ማንነታችን ዉስጠ መልክ (ክሽ ክሽ)
ክሽ ክሽ የተሰኘዉ የአጭር አጭር ልብወለድ (flash fiction) የመሐል ልጅ በተሰኘዉ መድበል ዉስጥ ከቀረቡት የቤዛዊት እጅግ ግሩም ሥራዎች መካከል አንዱ ነዉ፡፡ የልብወለዱ ስሜት (tone) መንፈስን የሚረብሽ (disturbing) ነዉ፡፡ የዚህ ትረካ ማዕከላዊ ጭብጥ (literary theme) ጥልቅ ጥላቻ (hatred) ነዉ፡፡ ጥላቻ በግለሰቦች ልብ ዉስጥ በቅሎ ስር የሚሰደዉ ሌሎች በአግቦ ወይም በገሀድ የሚወረዉሩትን ቅስም ሰባሪና አጥንት ሰርሳሪ ቃል ወይም ልብን የሚያደማ አሉታዊ ድርጊትን ተከትሎ ነዉ፡፡ ቤዛዊት በዚህ ድንክ ትረካ ዉስጥ የሳለችዉ ዋና ገጸባሕሪ የአእምሮ እድገቱ ዉስን የሆነ ሞሳ (autistic child) ነዉ። ይህ ሞሳ የአበባነት ዕድሜዉን እንደ እኩዮቹ ሐመልማል መስክ ላይ ካፊያ እየመታዉ ያልዘለለ፣ አቧራማ ሜዳ ላይ ፀሐይ እያነደደዉ ኳስ ያልተጫወተ፣ ጥላቻና መገለል በፈጠሩበት የሥነ ልቦና ህመም ይሰቃይ የነበረ ዕድለ ቢስ ነዉ፡፡ ገጸባሕሪዉ እኔ እያለ በአንደኛ መደብ አንፃር ግለ ታሪኩን የሚተርክልን መቃብር ሆድ ሆኖ ነዉ፣ በምልሰት (flashback)፡፡ የገደለችዉ ወላጅ እናቱ ናት፣ ጥገኝነቱ የፈጠረዉ ምሬትና ጥላቻ ልቧን አጨክኖት፡፡ ዋና ገጸባሕሪዉ ታሪኩን እንዲህ ይነግረናል፡
ስነቃ በጣም ጠኧኧባብ አየር እና ድቅድቅ ጨለማ ነዉ፡፡ በአንድ ጊዜ እንደ በረዶ ቀዝቅዞ የነበረዉን ሰዉነቴን ድንጋጤ የወለደዉ ትኩስ ላብ ሲያያያ’ቀልጠዉ ይሰማኛል፡፡ ልቤን በድጋሚ ቀጥ ሊያደርግ የሚችል ፍርሀት ወረሰኝ፤ መተንፈስ አልቻልኩም፡፡ አፌና አአአ’ፍንጫዬ ዉስጥ የታጎረብኝ ነገር ትንፋሼን በኃይል ወደ ዉስጥ ይገፋዋል፡፡ እእእ’ጆቼና እግሮቼ ተጠፍረዋል፤ መነቃነቅ አልችልም ድምፅ ማዉጣትም እንደዛዉ፤ ጆሮሮሮ’ዎቼ በተከተተባቸዉ ነገር ተዘግተዉ፣ ጭልጭልታ የለቅሶ ጩኸት እየመጣ እየሄደ ይሰማኛል …
ለቅሷቸዉ መናኛ ነዉ፤ ከልባቸዉ አይመስልም፤ አይደለምም አዉቃለሁ። “በተገላገለችዉ” ይሉ የነበሩት ሁሉ “ተገላገለችዉ” እያሉ እንደሆነ፡፡ እርስ በእርሳቸዉ መጥፎነታቸዉን ሊደባበቁ የፈተሏት የዉሸት ግር ግር ነች አዉቃለሁ፡፡
እወዳታለሁ እናት አይደለች መቸስ …
እወዳት ነበር፤ ግን ሸክሟ ነበርኩ፤ የዘላለም ሸክሟ! የወለደችኝ በልጅነቷ ነዉ። የሰፈራችን ትላልቅ ሴቶች የእድሜዋንም፣ የአካሏንም እንስንስ ማለት አይተዉ “እንሿ” ብለዉ ሲሉ ሰምቼ በሰባት ዓመቴ ለመጀመሪያ ጊዜ እእእ’ንደምንም የሷን ስም ተጣራሁ፡፡ እእእ’ንደዛ ቆይቼ ነዉ አፍ የፈታሁት፤ ብጠብቅ ብጠብቅ ከእእ’እንሿ በስተቀር ምንም ጭማሪ ሳልናገር ሌላ ብዙ ጊዜ ፈጀሁ፡፡ ቢያዩኝ ቢያዩኝ ቶሎ አልተራመድኩም፤ ሌሎች ልጆች ሲሮጡ ሳይ እቀና ነበር፤ ቅናቴንም ለመናገር አፍ አልነበረኝም፣ መልኬም ከሌሎች ልጆች የተለየ ነበር፡፡ ሽንቴን ተቆጣጥሬ ራሴ መሽናት እስክችል ብዙ ቆየሁ፤ በየቀኑ እኔን ማጠብና ልብሴን ማፅዳት ያሰለቻት ነበር፡፡ ምን ላርግ? ፈልጌዉ ነዉ? አልፎ አልፎ ሌሊት ሌሊት አእምሮዬ ይረበሽና ስጮህ ሳድር አበሳጫታለሁ፤ ቀን ቀን እኔን ለማኖር፣ ነፍሷን ለማበርከት፣ ኪራይ ለመክፈል ስትሮጥ ትዉላለች (ቤዛዊት፣ 2013፡ ገጽ 182-183)፡፡
በዚህ ትረካ ቤዛዊት በአደባባይ ገልጣ የምታሳየን እኩዩንና ድብቁን የሰዉ ልጅ ሥነ ልቡና ወይም ነፍስ መልክ ነዉ፡፡ እንደ ቤዛዊት እሳቤ፣ የሰዉ ልጅ ከአዉሬም የከፋ እጅግ ራስ ወዳድ ፍጡር ነዉ፣ ለደስታዉ ሲል ሌሎችን ከመሰዋት ወደ ኋላ የማይል፡፡ የዋና ገፀባሕሪዉ ወላጅ እናት ለረዥም ዘመን ተሸክማዉ የኖረችዉን የአብራኳን ክፋይ በመርዝ የገደለችዉ አዲስ ከተዋወቀችዉ የፍቅር ወዳጇ ጋር እንደ ልብ ደስታን ለመቅጨት በመመኘት (sensual indulgence) ነዉ፡፡ በዚህ ሥራዋ ቤዛዊት ወሲብ የእናትነትን እንስፍስፍ ልብ አለት እስከ ማድረግ የሚደርስ ታላቅ ሚስጥራዊ ኃይል አለዉ ትለናለች፡፡ እንደ ቤዛዊት እሳቤ፣ ርህራሄ (compassion)፣ እንክብካቤ (caring) እና ፍቅር (love)፣ መተባበር (solidarity) …ወዘተ ማኅበረሰብ ሰርክ የሚሰብካቸዉ የወል የሞራል እሴቶች የይስሙላ ናቸዉ፡፡ ይህ የቤዛዊት እሳቤ ከኤቲካል ኢጎይስቷ አየን ራንድ ሐሳብ ጋር የሚመሳሰል ነዉ፡፡ ቤዛዊት የሚከተለዉን ጽፋለች፡
ጎረቤት እና ዘመዶቿ እኔን መሰሎች ለሚያሳድጉ ድርጅቶች እእእ’እንድትሰጠኝ ሁሌም ይወተዉቷታል፤ “እእእሺ” ትላቸዋለች። ለዛ ሰሞን ስትፈልግ ስታፈላልግ ከርማ ትመጣለች፡፡ እእእድሜዬ በመግፋቱ የሚቀበላት እያጣች ትመለሳለች፤ በእንደዛ አይነት ጊዜ ዉስጥ አታቅፈኝም፣ ስተኛ ራሴን አትዳብሰኝም፡፡ ጭንቀት ቢያወራጨኝም አታባብለኝም፡፡ ጀርባዋን ሰታኝ ዝም ትለኛለች፣ ሲብስባት በለቅሶ በተኛችበት ትፈርሳለች። አንድ ሦስት ቀን ቀና ብላ ልታየኝ ትጠየፈኝ ትቆይና የተባለችዉ እና ያደረገችዉ ዉሎ በማደር ሲረሳሳ፤ እንደዛ ያሏት ሰዎች ሲልኳት፤ እናትነቷ ቦታዉ ሲመለስ ዐይኔን፣ ጆሮዬን፣ እጄን እየሳመች በለቅሶ ይቅርታ ትጠይቀኛለች፡፡
አዝናለሁ፡፡ እእእእየፈለኩ የሷን ያህል አአአጥብቄ ላቅፋት ባለመቻሌ፡፡ ስሜቴን ልነግራት፣ ስሜቷን ልጋራት ባለመቻሌ፡፡ ችግሯ እኔ እንደሆንኩ እያወኩ፣ ያንን ያንን እያወኩ እንደማዉቅ እንድታዉቅ ማድረግ እንኳን ባለመቻሌ በጣም አአአአ’ዝናለሁ፡፡ ሌሎች ልጆች እእእ’ናታቸዉን እእእ’ንደሚያግዙት ሱቅ እንኳን አምና ልትልከኝ የማትችለኝ አይነት ልጅ በመሆኔ ይበልጥ አዝናለሁ፡፡ ዉጭ ከሌሎች ልጆች ጋር መጫወት እየፈለኩ ልጆቹ ስለማያስቀርቡኝ ብላ ብዙ አታስወጣኝም፡፡ ብርሃን እና አየር የቅርብ ሩቅ ዘመዶቼ ናቸዉ። ቡና ልጠጣ ስትሄድ አአአ’ታስከትለኝም፣ ቤታችንም ቡና አፍልታ ሰዉ አትጠራም፣ ብትጠራም አይመጡላትም፣ ቢመጡም የሚዋጋ ዐይናቸዉን ከኔ ላይ አአአ’ይነቅሉም፣ ከነቀሉም ሲሄዱ ደጁ ጋር እያማተቡ ሲወጡ ነዉ፡፡
እእእ’ንደምትወደኝ አዉቃለሁ፡፡ ግን ልጅነቷን የበላሁ፣ ጉልበቷን ያደከምኩ፣ በሰዉ እንዳትፈለግ፣ ከሰዉ በታች ያደረኳት የገዛ ልጇ ነኝ፡፡ አልመረጥኩትም፣ እሷም አልመረጠችኝም፡፡ እእእ’ንደምትወደኝ አዉቃለሁ ግን ደሞ ትንሽ ትንሽ ትጠላኛለች፡፡ መሆን ከነበረባት ወይ ከምትችለዉ ላይ በየቀኑ ትንሽ ትንሽ ወደ ኋላ ጎትቼ አስቀርቻታለሁና፡፡
ቁመቴ ከቁመቷ እየበለጠ አገጨና ሽንት መሽኚያዬ ጋር ፀጉር ካወጣሁ በኋላ ፖፖ አቀብላኝ ፊቷን ማዞር ከጀመረች ወዲህ፤ ይዣት ሳንቀጫቅጭላት ያደጉትን መአት አይነት አረንጓዴ ክሮች፣ የእሷን ፀጉሮች እና የላስቲክ ብጥስጣሾች የተበተብኩባትን ክሽ ክሽ ቁልፌን “ጎረመስክ እኮ ባክህ” እያለች ከእጄ መንጠቅ ከጀመረች ጀምሮ፤ ስተኛ ማልበስ፣ እንደ ድሮዉ መደባበስ ከተወች ወዲህ፤ ከዚህ በፊት አይቼዉ ከማላዉቀዉ ሰዉ ጋር ወደ ቤት መምጣት ከጀመረችና እሱን ሳይ የሰዉዬዉ መንፈስ እየረበሸኝ ከቁጥጥሬ ዉጪ በሆነ ጩኸት እየጮህኩ እረብሻት ከጀመርኩ በኋላ በጣም እንደጠላችኝ አዉቄያለሁ፡፡
ብላ የማታዉቀዉን አፍ አዉጥታ “አንተስ ባትወለድ” እስክትል ድረስ …
ለመጨረሻ ጊዜ እእእ’እናቴ እንደበፊቱ ከፊቴ ቁጭ ብላ የሳመችኝ፤ ራሴን እንደልጅነቴ የደባበሰችኝ እና እእእ’ንግዳ የሆነ የማላዉቀዉ አይነት ሽታ የተቀባዉን አብሮ አደግ ክሽ ክሼን ከደበቀችብኝ ቦታ አዉጥታ የመለሰችልኝ ጊዜ እእእ’እዚህ መቃብር ሳጥን ዉስጥ ከመገኘቴ በፊት ነበር፡፡
በጠላችዉ ብዙ ደደብነቴ መሀል እእቺቺ ትንሽ እዉቀት ገባቺኝ፡፡ እእእእናቴ ገላኛለች! እእእንሿ እማማ ቀብራኛለች!!
የዉሸት ለቅሷቸዉ ከጭላንጭል ወደ ፀጥታ ቀስስስ እያለ ሄደ፤ ወይስ ደከመኝ? (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 184-185) ዝታጥንፈዉ  ናነንተት
፪. ሽንገላ እና ፀፀት (መጫወቻዉ)
የመሐል ልጅ በተሰኘዉ የቤዛዊት ሥራ ዉስጥ ከቀረቡት ሥራዎች አንዱ መጫወቻዉ የተሰኘዉ ትረካ ነዉ፡፡ መጫወቻዉ እንደ ክሽ ክሽ ሁሉ ድንክ ልብወለድ ነዉ፡፡ ይህ የቤዛዊት ሥራ ድንክ ቢሆንም ጐደሎነት የሌለዉ ግሩም ሥራ፡፡ ድንክ ልብወለድ ከማጠሩ በስተቀር ተለምዶአዊዉን የልብወለድ መሠረታዊያን (fundmentals of fiction) ያሟላ ልብወለድ ነዉ (ሀቺት እና ሀይስ፣ 2009፡ ገጽ xxix)። ቤዛዊት ይህን ድንክ ትረካ ምልዑ እንዲሆን አድርጋ የሠራችበት ቴክኒክ የጸሐፊነት ክህሎቷን በግልፅ የሚመሰክር ነዉ፡፡ በድንክ ትረካ ትልቅ ሜታፊዚካዊ ርእሰ ጉዳይን መፈከር ልዩ ተሰጥኦ ነዉ፡፡ የሥነ ጽሑፍ ምሁራን እንደሚናገሩት፣ ድንክ ትረካ የጸሐፊነት ክህሎት የሚፈተንበት የልብወለድ አይነት ነዉ፡፡
መጫወቻዉ የሥነ ጽሑፍ ምሁራን ሥነ ልቡናዊ ልብወለድ (psychological novel) የሚሉት ልብወለድ ነዉ፡፡ የትረካዉ ዐቢይ ጭብጥ (central theme) ኀሊናዊ ፀፀት (existential guilt) ነዉ፡፡ ይህ ዐቢይ ኀልዮአዊ ጭብጥ (existential theme) የሰዉ ልጅ በተፈጥሮዉ ከተጎናፀፈዉ ፍፁማዊ አርነት ጋር የተሰናሰለ ነዉ፡፡ ፀፀት ለአድራጎታችን ሙሉ ኃላፊዉ እኛዉ ራሳችን እንደሆን መገንዘባችን የሚወልደዉ የመንፈስ ህመም ነዉ፡፡ በዚህ አጭር ልብወለድ ዉስጥ የተሳለችዉ ዋና ገጸባሕርይ በትረካዉ ዉስጥ ባልተገለፀ (የገጸባሕርይዋ ልቡና ብቻ በሚያዉቀዉ) አስገዳጅ ገጠመኝ ገላዉ ያልጠና የአብራኳን ክፋይ ልቧን አደንድና ለማደጎ የሰጠች አሳዛኝ እናት ናት፡፡ ይቺ እናት አድራጎቷ የፈጠረባትን ፀፀት መሸሽ ያልቻለች ገደ ቢስ እናት ነች፣ ራስን መሸንገል አይሳካምና፡፡ ታዲያ የዚህ ፀፀቷ ምንጭ ያጣችዉን ልጇን ትዝታ የሚጎትትባት አንድ ተራ ቁስ ነዉ፤ ቤቷ ዉስጥ የቀረ የልጇ መጫወቻ፡፡ ቤዛዊት የሚከተለዉን ጽፋለች፡
ይሄ አምጬ ከመዉለዴ በላይ መርሳት ያልቻልኩት ቀጭን ትዝታዬ ነዉ፡፡ በደረቅ ዉድቀት ከእንቅልፌ የሚቀሰቅሰኝ ብሶቴ፣ መጫወቻዉ የሚያወጣዉ ድምፅ፤ ኖታ ስሎ፤ ዜማ አቀናብሮ ሁልጊዜ ጆሮዬ ላይ ይዘፍናል፤ በዚህ ምክንያት ዉስጤ የተረበሸ ከተማ ነዉ፡፡ ከዚህ በላይ ግን ትዉስታዬ እንዲሰፋ አልፈቅድለትም፤ የምወደዉን ባለማሰብ ራሴን የገደልኩ ነኝ (ቤዛዊት፣ 2013፡ ገጽ 196)፡፡
፫. የቤዛዊት የፍቅር ፍልስፍና (የዝ’ጌር ስኪኒ ሱሪ)
የዝ’ጌር ስኪኒ ሱሪ፣ የመሐል ልጅ የአጫጭር ትረካዎች መድበል ዉስጥ የቀረበ ሌላኛዉ የቤዛዊት ሥራ ነዉ፡፡ ይህ ትረካ ለግጥ (parody) የምንለዉ ድህረ ዘመናዊ ልብወለድ (postmodern novel) ነዉ፡፡ በዚህ አጭር ልብወለድ ቤዛዊት የፍቅርን ተፈጥሮና ተቃራኒ ፅንፉን ወረት በጥልቀት ፈክራለች፡፡ የዝ’ጌር ስኪኒ ሱሪ አስማተ ገሀድ (magical realism) ብለን የምንጠራዉ ድህረ ዘመናዊ ልብወለድ ነዉ፡፡
እንደ ቤዛዊት እሳቤ፣ ፍቅር ጠማማዉን የማቅናት፣ ቁጡዉን የማለዘብ፣ ጎዶሎዉን የመሙላት፣ መናኛዉን የማስዋብ፣ ንፉጉን ቸር የማድረግ፣ አለቱን የማቅለጥ፣ ጨካኙን የማባባት ኃይሉ ታላቅ ነዉ፡፡ የቤዛዊት የፍቅር ፍልስፍና እንደሚነግረን፣ ልባችን በሌሎች ፍቅር ሲረታ የግለ አምልኮ ባቢሎናችን ይናዳል፡፡ ቤዛዊት እንዲህ ጽፋለች፡
ቀጠሮዬ ቦታ እስክደርስ ልቤ ተንሸራታ ሆዴ ዉስጥ ጥገኝነት ልትጠይቅ ምንም አልቀራት፤ አየሩ ትኩስ ሆኖ እንፋሎት በሀገሩ ላይ ይጤሳል፡፡ ሰንበትን አስመልክቶ ሰዉ ቤቱ ከቷል፤ አካባቢዉ ላይ ላመል የሚያልፍ ታክሲ ባለመኖሩ እጄን ግንባሬ ላይ ከልዬ እግሬ ዙሪያ ጀል ጀል የሚል ሰፊ ሱሪዬን እያየሁ በፍጥነት እራመዳለሁ፡፡ ሰዉ ሁሉ ከዘመኑ ጋር ለምን አትሄድም፣ ለምን ከእግሩ ስር የተንሽዋጠጠ “ስኪኒ” ሱሪ አትለብስም? ይለኛል፡፡ የማወራዉ ከጣማቸዉ ስለ ሽፋኔ ለምን ይጨነቃሉ? ዘመነኛ ሰዉ አይደለሁም፤ ከጊዜ ጋር ሄደዉ ለሚመጡ ነገሮች ልቤ መትቶ አያዉቅም፡፡ የድሮ ፎቶዬ እና የአሁኑ ቢተያይ ከእድገቴ በቀር አለባበሴ ላይ የተለየ ነገር የለዉም፡፡ በዘመን ዉጥን ዉስጥ መስመር መያዝ፤ ብልጭ ብሎ ለሚሄድ ነገር ቦታ መስጠት አልፈልግም፡፡ በዚህ በዚህ ጊዜን ማሸነፍ እፈልጋለሁ፡፡ ሰጥቶ የሚነጥቀኝ እንደሌለ እንዲገባዉ፣ እንደለመደዉ እየበረረ ሲያልፈኝ ሁለት ሺህ ዘመን ላይ የአባቴን የዘመን ገፅታ ተላብሼ ሲያየኝ፣ ጊዜ ራሱ ጊዜዉ እንዲምታታበት እፈልጋለሁ፡፡ ሃሃ! ቢሆንም ግን ለምወዳት ልጅ ስል ይሄን ዘመነኛ ሱሪ ለመሞከር አስባለሁ፡፡ ፍቅር ደስታዉ ይህ አይደል? መሸነፍ ግትርን ማጠፍ፣ ችካልን ማነቃነቅ? እንኳንስ አፍ አዉጥታ ጠይቃኝ ፊቷን ቅፍፍ አድርጋ ሰፊ እግሬታዬን ብትመለከት እቀይርላታለሁ፡፡ ለእሷ ስል! (ቤዛዊት፣ 2013፡ ገጽ 187)
እንደ ቤዛዊት እሳቤ፣ በፍቅር ስንወድቅ የምናፈቅረዉ ሌሎችን ሳይሆን በዉስጣችን ያነፅነዉን ተምኔታዊ ጣዖታችንን ነዉ፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ፍቅር ዉጫዊ ነገሮች በራሳቸዉ የሚከስቱት ቅፀበታዊ ምርኮ አይደለም፣ ከሥነ ልቡናችን ጋር የተቆራኘ፣ ለዉጫዊ ነገሮች ያለን ዉስብስብ ግብረ መልስ እንጂ፡፡
የቤዛዊት የፍቅር ፍልስፍና እንደሚነግረን፣ ፍቅር ጊዜ የሚፈጥራቸዉን ኩነቶች መሠረት ያደረገ ጊዜአዊት ስሜት (temporal feeling) ነዉ፡፡ በሌላ አነጋገር፣ እንደ ቤዛዊት እሳቤ፣ ፍቅር ቋሚ የሆነ ተፈጥሮ የለዉም፤ ፍቅር የጊዜን ለዉጥ ተከትሎ እንደ ደመና የሚተን፣ እንደ ሸማ የሚያልቅ ነገር ነዉ፡፡ ቤዛዊት እንዲህ ጽፋለች፡
ከቆመችበት ሆና አስር ግዜ የእጅ ሰአቷን ታያለች፤ እሱ በአካባቢዉ የለም፡፡ ያለፈ ያገደመ አንገቱ እስኪቆለመም ይቃኛታል፣ ዐይኑ እስኪጎለጎል ያያታል፤ ታምራለች! ይሄን ማማሯን እዚህ አዲስ አበባ ከመጣች በኋላ ነዉ ያወቀችዉ፡፡ ተወልዳ ያደገችበት ድሬደዋ ማንም ነበረች፡፡ ካለፈ ታሪኳ ይዛዉ የመጣችዉ ታታሪ ሠራተኝነቷን እና ቅፅል ስሟን ብቻ ነዉ። “ሰዉ ብቻ” እዚህ ስም ላይ ብዙ ትዉስታዎች አሏት፤ ልጅነቷ እና የምትወዳቸዉ ሰዎች የተያያዙት በስሟ ነዉ፤ ለዛም ብላ እዚህም በዚሁ ስሟ ትጠራለች፡፡ የአሁን ፍቅረኛዋን እግሯ አዲስ አበባ እንደነካ ነዉ የተዋወቀችዉ፤ ዕድል ጥሏት፡፡ ከአዉቶብስ ተራ ከርፋፋ ፌስታሏን ይዛ ስትወርድ አሮጌ አረንጓዴ ሂጃቧ ያደመቀዉ የቀይ ዳማ ፊቷ አሳዝኖት የአዉቶብስ ተራ ወሮበላ ጉድ እንዳይሰራት ብሎ ቀረባት፤ የምትሄድበትን አድራሻ በየዋህነት ነገረችዉ። ሊያሳያት እየሄዱ ስሟን ጠየቃት፤ “ሰዉ ብቻ” አለችዉ፡፡ ሳቀ፣ ገና ያልረጋላት የመለየት ስሜት በእንባ እያነፋረቃት ስለ ስሟ፣ ስለ እናቷ እና ስለ እትዬ ሃሊዴ የተባሉ ሴት እና ጥላት ስለመጣቻት ሀገሯ አጫወተችዉ፡፡ ቃል ሳያወጣ ጀርባዋን አሻሽቶ በጨዋነት አፅናናት፡፡ ከፈለገችዉ እንድትደዉልለት ቁጥሩን ሰጥቷት የምትፈልግበት ንግድ ቤት አደረሳት፡፡ አሰሪዋ አቶ በላይ በጣም ጥሩ ሰዉ ነዉ፡፡ በጣም ቀልጣፋ ስለነበረች ጥሩ የሥራ ህብረት ፈጥረዉ ይሠራሉ፡፡ ከፍቅረኛዋ ጋር በእረፍቷ ሰአት ተነፋፍቀዉ እየተገናኙ እንደቀልድ ፍቅራቸዉ ለትዳር አስተጫጫቸዉ፡፡ ያለማወዳደር ያለወረት ወደደችዉ፡፡ ጥሩ የሚለዉ ቃል ፊቱ እንደ እሱ ይመስላታል፡፡ ይሄን እያሰበች ዞር ዞር ስትል ዐይኗ አንድ ቦታ ተተክሎ ቀረ፤ ያየችዉን ማመን አልቻለችም፡፡ አዲስ አበባ ከመጣች ዉበት በየአይነቱ ተመልክታለች፤ እንዲህ አይነት የሚያምር ሰዉ ግን አይታ አታዉቅም፡፡ ጠይም አይናማ፤ ዠርጋጋ ፂማም ነበር፡፡ ረጅም የሀገሯ ሰዎች የሚለብሱት አይነት አረንጓዴ ቀሚስ ለብሷል፡፡ ፈርዶባት አረንጓዴ ትወዳለች፤ በየደሞዟ አንድ አንድ እያለች ሰባት ስስ አረንጓዴ ቀለም ያላቸዉ ሂጃቦች ገዝታለች፤ እንደሷ ሁሉ የእሱም ዐይን ተሰክቶባት ነበር፡፡ ወደ ቆመችበት ሄደ፤ የፊቱ ጥራት የእጁ ማማር አዲስ እንደ ተወለደ ልጅ ለዐይን ይለሰልስ ነበር፡፡ በፊቱ መቆም እስኪያቅታት የማታዉቀዉ ስሜት አርበደበዳት፤ በእጁ ደገፍ አድርጎ አቆማት። የሆነ ዉበት ፏፏቴ የሰራበት ደማቅ ፀጉራማ ሰዉ ነዉ (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 193-194)፡፡
እንደ ቤዛዊት እምነት፣ ወረት የፍቅር ተቃራኒዉ ፅንፍ ነዉ፡፡ እንደ እሷ እሳቤ፣ ሁሉም ነገር የለዉጥ (fluidity) ሕግ ተገዢ ነዉና ፍቅር በጊዜ ሂደት ቀዝቅዞ በወረት ይተካል፡፡   
ቤዛዊት እንደምትነግረን፣ ሰዎችን እስከ ዕለተ ሞታቸዉ በአብሮነት የሚዘልቁት ፍቅራቸዉ የማይነጥፍ ወይም ቋሚ ስለሆነ አይደለም፤ በአብሮነት ሳሉ የተጋሩት ክፉ ደግ ይሉኝታ እና ፀፀትን ፈጥሮ ኮብላይ ልባቸዉን ገስፆ ወደ አፍቃሪያቸዉ እቅፍ ስለሚመልሳቸዉ እንጂ፡፡ ስለሆነም፣ ለቤዛዊት ከሀዲ ግለሰቦች ይሉኝታ ቢሶች እንጂ ፍቅር ገፊ ወረተኞች አይደሉም። ቤዛዊት የሚከተለዉን ጽፋለች፡ታቸዉ፡940 feeling) nwu
የምትጠብቀዉ ዉዷ ከአስፓልት ማዶ እንዳያስቆማት ሮጥ ሮጥ ብሎ ሲመጣ አየችዉ። የሆነ ኮሳሳ ቢጤ እንደሆነ ለመጀመሪያ ግዜ አስተዋለች፡፡ ፍቅር አግዷት ልብ ያላለችዉ፣ ወፍራም ጭኗ መሐል አቃስቶ ብድግ ሲል የሚቆምባቸዉ ጭራሮ እግሮቹ ተከሰቱላት። “ለምንድን ነዉ በዛ እግሮቹ ስኪኒ ልበስ ብዬ ማስቸግረዉ?” ደነገጠች፤ አሳዘናት፤ የልቧን ምኞት ተፀየፈችዉ፡፡ እጇን ከዚህ ከተወለወለ መስታወት መሳይ ሰዉ መነጨቀች፤ ለአንዳፍታ ሀገሯ ጥላት የመጣቻትን ቁሌታም ጓደኛዋን የሆነች መሰላት፤ ትታዉ እንደ ፍቅሯ በሶም ሶማ ወደ እሱ ተሻገረች (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 194)፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊዉን በ Telegram Channal: መኮንን ደፍሮ ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 2042 times