Saturday, 29 October 2022 12:40

“ሰው የተፈጠረው እንደ ሳዲዮ ማኔ በማህበረሰቡ ውስጥ ለመመላለስ ነው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“...ዛሬ ግን በእግር ኳስ ባገኘሁት ገቢ ህዝቤን መርዳት እችላለሁ። ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን ገንብቻለሁ ፣ በከፋ ድህነት ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ልብስ፣ ጫማ፣ ምግብ አቀርባለሁ ። በተጨማሪም፣ በጣም ድሃ በሆነ የሴኔጋል ክልል ውስጥ ላሉ ሰዎች ሁሉ በወር 70 ዩሮ እሰጣለሁ። “
ከወደ ጥቁሮቹ መንደር ከወደ አፍሪካ ምድር፣ የእኛው ማንነት ያለው ታላቁ “ሳዲዮ ማኔ”፤ ሴኔጋል ከምትባል አፍሪካዊት እህታችን የተወለደ ነው። ሰው የተፈጠረው እንደ ሳዲዮ ማኔ በማህበረሰቡ ውስጥ ለመመላለስ ነው። ተቸግሮ ያሳደገህን ሲያልፍልህ ልታሳልፍለት። ሲርበው ልናጎርሰው፣ ሲታረዝ ልናለብሰው ነበር የተፈጠርነው። እንዴት እንደምቀናበት። እሱ ያደረገውን ሳስብ እኔ የተወለድኩበት አካባቢ ችግር አይኔ ላይ ይመጣብኛል። አልፎልኝ ባሳልፍላት ብዬ እመኛለሁ። መጀመሪያ ግን እንደዚህ አይነት ቅን ልብ ፈጣሪ ቢሰጠኝ ምኞቴ ነው።
ሳዲዮ ማኔ አንድ ቀን ዳርክስበርግ ለተባለ ክለብ ለመመልመል ወደ ሜዳ ገባ። እናም መልማዩ የማኔን አሮጌ ልብስና ባዶ እግር መሆኑን ተመልክቶ  እንዲህ አለው፤ "አንተ እዚህ የመጣኸው ለመመልመል ነው?”  ማኔም አንገቱን ደፍቶ፤ “አዎ“ ብሎ መለሰለት። መልማዩ፤" አንተ እኮ ለመጫወት የሚሆን በቂ ጫማ እንኳን የለህም” ታምረኛው ጫማው ሳይሆን እግሩና አዕምሮው እንደሆኑ ረስቶት ይሆን? ማኔ ግን “እኔ እዚህ ውስጥ ካሉ ተጫዋቾች በሙሉ የተሻልኩ ነኝ፤ ብቻ አንድ እድል ስጠኝ እና ችሎታዬን ላሳይህ” መልማዩም የማኔን የራስ መተማመን ጥግ ተመልክቶ እድሉን ሰጠው። ሜዳ ውስጥ ካሉት ተጫዋቾች በቂ የመጫወቻ ጫማ የሌለው ሳዲዮ፣ የመልማዩን ቀልብ ገዛ። ምልመላውን ከውጪ ሆነው እየታደሙ የነበሩት ተመልካቾች፣ ለማኔ ድጋፋቸውን አሰሙ። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ መልማዩ፣ ማኔ ምልመላውን እንዳለፈ ነገረው፣ ማኔም በዚህ ደስተኛ ሆነ። ወደ ፈረንሳይ አቀና። ስኬቱ ቀጠለ፡፡ የእንግሊዙ ሳውዝሀምፕተን ክለብ አስፈረመው። በክለቡ የሚያሳየውን ድንቅ ብቃት የተመለከቱት ሊቨርፑሎች የግላቸው አደረጉት። ሊቨርፑልን ወደ ታሪኩ ቀና ካደረጉት ዋነኛው ምሰሶ ይህ ተጨዋች ነው። አሁን በያዝነው የውድድር አመት ፣በእጥፍ ሳምንታዊ ደመወዝ የጀርመኑ ክለብ ባየርን ሙኒክ አስፈረመው። ኃያሉ ተጫዋች እዚህ ይገኛል። ሲበዛ የደግ ልብ፣ የአይበገሬነት፣ የድንቅ ብቃት ተሰጥኦ ባለቤት። ጥቁር ሰው ነው። እንደ አጼ ምኒልክ።
ሳዲዮ ማኔ ይናገራል... ደግሞም ይናገር።
“ረሃብን ተቋቁሜ ሜዳ ላይ ሠርቻለሁ፣ ከጦርነት ተርፌያለሁ፣ በባዶ እግሬ እግር ኳስ ተጫውቻለሁ ፣ ምንም ትምህርት አልነበረኝም እና ሌሎች ብዙ ነገሮች፣ ዛሬ ግን በእግር ኳስ ባገኘሁት ገቢ ህዝቤን መርዳት እችላለሁ። ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን ገንብቻለሁ፣ በከፋ ድህነት ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ልብስ፣ ጫማ፣ ምግብ አቀርባለሁ። በተጨማሪም፣ በጣም ድሃ በሆነ የሴኔጋል ክልል ውስጥ ላሉ ሰዎች ሁሉ በወር 70 ዩሮ እሰጣለሁ። የሚያማምሩ መኪኖችን፣ የተዋቡ ቪላዎችን፣ መጓዣ አውሮፕላን ይቅርብኝና፣ ለህዝቦቼ ሕይወት ከተሰጠኝ ነገር ትንሽ እንዲወስዱልኝ እመርጣለሁ።”
 «እኔ ራሴን ከማንም በላይ አድርጌ አላስብም፤ ስራዬን በደንብ እሰራለሁ፤ በሴኔጋል ውስጥ ላሉ የሰፈሬ ሰዎች ስለሚቀጥለው ምግባቸው አብዝቼ እጨነቃለሁ፤ ለዚህም ነው ሁልጊዜ ቦታዬን ላለማጣት በጥሩ አቋሜ ላይ ለመሆን የምለፋው፤ ምክንያቱም ኮንትራቴን ላጣ እችላለሁ፡፡ ይህ ከሆነ የሰፈሬ ሰው ሊራብብኝ ይችላል፤ ባሎንዶር በአእምሮዬ ውስጥ የለም ፤ምክንያቱም እሱን በማሸነፍ የተራበውን ሰው ማጥገብ አይቻልም። እኛ ደግሞ ሁላችንም በራሳችን መንገድ ምርጥ ነን።”
በዚህ የውድድር አመት እንኳን ቦቹም ከባየርን ሙኒክ ባደረጉት ጨዋታ ላይ ሳዲዮ ማኔ ሳያውቅ በእጅ ጎል አስቆጥሮ ነበር። ነገር ግን VAR ጎሉን ከመመልከቱ በፊት ሳዲዮ ማኔ በእጁ ኳሱን ነክቶት ጎል እንደሆነ ይነግራቸዋል። እናም ጎሉ ትክክል አለመሆኑን ለዳኛው በመንገር ጨዋታው በቅጣት ምት እንዲጀምር ሆኗል፤ ነገር ግን ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ማኔ በትክክል ንፁህ ጎል ማስቆጠር ችሏል ፤ፍትሃዊ ጨዋታ ሁሌም ይከፍላል፤ ሳዲዮን።
 (ከግሎባል ሶከር በከፊል የተወሰደ)
ይኸው ሰሞኑን  በተካሄደ የሽልማት መርሃግብር ሳዲዮ ማኔ የሶክራተስ አዋርድ አሸናፊ ሆነ። ደግነት ሲያሸንፍ ማየት ደስ ይላል። ምናልባትም የአምናውን ሻምፒዮንስሊግ ሊቨርፑል አሸንፎ ቢሆን የባለንዲዮር አሸናፊም ጭምር እርሱ ነበር።

Read 630 times