Saturday, 29 October 2022 12:43

“ሐሳብ ቤት ሲመታ”

Written by  ዳሰሳ - በድረስ ጋሹ
Rate this item
(2 votes)

“--ይኼን ስል የተጻፈ መጽሐፍ ሁሉ ይስማማኛል ማለት አይደለም። ሐሳብ ካለው እሰየው፣ ውበት ካለው እሰየው ግን ደግሞ ሐሳብ ሲደመር ውበት ከሆነ ፍስኀ ነው ለእኔ።--”

ሀብታም እና ደሃ እኩል እጅ ይሰጣል_ለሞት። ሊቅ እና  ደቂቅ ፤አዋቂና አላዊቂ እኩል ይረታሉ_በሞት። ሞት፤ ዘር ፣ቀለም፣ልቀት እና ምጥቀት አይመርጥም። ይኼ ልዕለ ሃያል የሆነ  መቅሰፍት የሚሸነፍበት አጋጣሚ አለ _እሱም በሥራ ነው። ሞትን ሁሌም የሚገድለው ሥራ ነው። “ስም ትከሉ” ይላል፤ የአገሬ ሰው፡፡ ጥሩ ሥራ ሥሩ ለማለት እንደሆነ መቼም አርጂ አንሻም። ጥሩ ሥራ ያለው ሰው ሞተ መባል አይገባውም ፤ይልቅ ጽሞና ላይ ነው ይሻላል እንጅ። የ”ሐሳብ ቤት ሲመታ” የግጥም ስብስብ ፀሐፊ ወጣቱ ዘወልድ አክመን ዘወልድ ማለፉን ስሰማ አዘንኩ ። (ይኼ ወጣት ገጣሚ “የሞተው በቀኑ ነው” እንዳንል በአፀደ ሥጋው ሳለ የጻፋት  “ቀን እና ሞት” ግጥሙ እንዲህ ትላለች ...
[“ የጊዜ ሰሌዳ የብርኅን ድልድይ
ነው እንጅ መስፈሪያ፤ ቀን አይደለም ገዳይ”]
እኔም ቆም ብዬ “ሞት ግን ለምን ወደ እኛ ይመጣል?” ስለው አጀኒን...ሥራችንን ሊያገዝፍ፣ ጥረታችንን ይፋ ሊያወጣ ይቀርበናል ይለኝ ነበር። በቁሙ ሞትን ይስላል፣ በሥራው መግደል እንዲችል ያምናል፣ ትንሽ ጨምርለት ሲልም ይመርቃል _ እኔም ልመርቀዋ...
[“በአፍላው ብዙ ሰርቶ ፥ ለሚቀደም በሞት
 ከዚያኛው አጉድለህ ፥ ለዚህ ጨምርለት”]
በዓለማችን ላይ ያሉ ድንቅ ፀሐፊያን፣ ድንቅ ሰዓሊያን፣ ድንቅ ተዋናያን ዝናቸው እየጎላ የሚሄደው ከሞት በኋላ ነው። በተለያዩ የሙያ መስኮች ከሞት በኋላ መግዘፍ የተለመደ ነው። ፍራንዝ ካፍካ፣ ኤድጋርድ አለን ፖ፣ ኢሚሊ ዲክንሰን ..ሰዓሊ Vincent Van Gogh፣ የዘመናዊ ጀነቲክስ መስራች Gregor Johann Mendel ፣የፊዚክሱ ሊቅ Ludwig Boltzmann እና ሌሎችም እስከ እለተ ሞታቸው ድረስ በጨለማ ውስጥ የቆዩ ናቸው። ሞት ደግሞ በሰው ዘንድ ይጎሉ ዘንድ ሰበብ የሆናቸው። (በአገራችን ስንት አሉ ከሞቱ በኋላ “ውይ ሳንረዳቸው ቀርተን" ብለን የምንጸጸትባቸው።)
ዘወልድ አክመን ዘወልድ፣ ሞቱን የተነበየ ያህል ይገልጠዋል፤ በሐሳብ ቤት ሲመታ። ከሞት ማህጸን ስለሚወለድ ስም፤ስለ ሁለተኛ ልደቱም  ይለናል...
[“ከሞቱ ማህፀን፥ ስሙን ወልዶ ሲሞት
በሌሉበት ዓለም፥ ሁለተኛ ልደት]
ደራሲ በቁሙ ልዕልናን ቢመኝ፣ በሠራው ልክ እንዲከፈለው ቢሻ ነገሮች ቀና ይሆኑለታል አልልም። ትክክለኛ የሥራቸውን ይዘት ለመረዳት ዘመን መሻገር ሊጠበቅብን ይችላል (ምናልባትም ሌላ ትውልድ መሆንን ያህል)። በዚህ መሐል ደራሲና ተደራሲ እንደዘበት ይተላለፋሉ። ባለመረዳዳት መሐል ሰበብ አለች። እሷ የንቀት ሁሉ ምንጭ ናት። አድናቆት የሌላቸው ፀሐፊያን  በዓለም  ውስጥ መጽናኛ ሊያገኙ ይችላሉ- እሱም ከሞት በኋላ ባለው ታዋቂነት። አንዳንድ በዓለም ላይ በጣም ተወዳጅ እና በስፋት የተነበቡ ደራሲዎች ከሞቱ በኋላ ለዓመታት፣ እንዲያውም ለአስርተ ዓመታት ያህል ትልቅ ቦታ ያልተሰጡ መሆኑ አያጠራጥርም። ምጸታዊ ስሜት፣ ጠማማ አድናቆት፣ ሲቸራቸው ዘመናቸውን ይገፉታል። ሲሞቱ ግን ውዳሴ ይቸራቸዋል (ለመተቃቀፍ ምሽት ይመጣል እንዳለው ገጣሚው፣ ለመደናነቅ ሞት ይመጣል ማለት አለብን እንዴ?)።
ስለመደናነቅ መጽሐፉ ይናገራል። ክፋትን እንድናስታውስ፤ፍቅርን እንዳንረሳ፤መልካም ላደረገ ሙገሳን ሳይቀር ይመክራል። ሞቱንም እያስታወሰ እንደኖረ እማኝ ስንኝ ላጣቅስላችሁ...
[“መልካም ላደረገ፥ አትንፈግ ሙገሳ
በሌት ተቀን ኑሮህ፥ ሞትህን አትርሳ"]
ዘወልድ ይህን መጽሐፍ በሕይወት ሳለ ለምን አላሳተመውም ስል ለራሴ ጥያቄ አቀረብኩ። መጽሐፉን ስዳስስ ስክነቱን አገኘሁ። ቀስ ብሎ ማደግን...
[“ከአረሙ ጋራ አብረህ፥በእጅ እንዳትነቀል
ረድፍህን ጠብቀህ ፥ ሰከን ብለህ ብቀል”]
ወደ ድግሱ...
በዚህ ሰዓት ዘወልድ አከመን ዘወልድ ጽሞና ላይ ነው (ይህችን ዓለም ተሰናብቷታል)። ስለ ኗሪ ሐሳቡ ላወራ ልቤ ፈቀደ። ደጅ አይቶ ቤት ይገቧል፤ እናቷን አይቶም ልጇን ያገቧል። የግጥሞቹን አደረጃጀት አየሁ። አጭር፣ መካከለኛ እና ዘለግ ያሉ ናቸው። ምናልባትም ውልደቱን፣ እድገቱን እና ዘለግ ያለውን የጽሞና ጊዜውን አሰብኩ። ስዕላዊ ምልከታ ፣የሐሳብ አንድምታ፣ የዜማው ሁኔታ ..ኪናዊ ለዛው ሌላው ሌላውም ተዳምሮ ግጥምን ግጥም ያሰኛታል። ቃል ከሐሳብ ጋር፣ ቃል እና ሐሳብም ከዜማ ጋር እየተጣመሩ ስሙር ለአእምሮ፣ ውብ ለጀሮ ይሆናሉ።
[ቡቃያ ሐሳቦች]
ኼደን ለማንቀረው ፣ለመግባት ለምንወጣው፣ ለምናገኘው፣ ለምንደጋግመው ..ሕይወትም በዛቢያዋ ለምታሾረን ኗሪዎች፣ ክቡን ለምንደጋግም ፍጥረቶች ኹሉ ይለናል...
[“መሰናበት የለ፥ ’ቻው’ አንባባልም
የማይኼድብን ሰው፥ ከቶ አይናፍቀንም” (ገጽ1]
የራሳችን አጥፊ ራሳችን እንጅ ሌላ አይደለም እምነቱ ነው። ከወዳጄ ጠብቀኝ ከጠላቴ እኔ እጠነቀቃለሁ፣ ለምን እንደምንል የገባኝ እዚህ ነው። በዘመኑ የምንወደው ራሳችንን ነው። ከምንወደው በላይ ሊጥለን የሚታገል እንደለሌ ደግሞ የታመነ ነው። ገጣሚው የመድረሻ መራቅን፣ የስጋት ማየልን፣ በራስ የመጠለፍ.. በራስ የመሳብና የመውደቅ ኹነቶች ይከነክኑታል። እግረ መንገዱን የዝመና ጥጉ በአወቁት መጥፋት፣ ሲሞቱም በኗሪ ቁልቁል መታየት እንደሆነም ያክልበታል።
ሰው ሞተ የሚባለው ማንነቱን የቀየረለት ነው ይላል አጀ። ወዘ -ጭምብል ውስጥ ስላሉ የሕይወት መልኮች ይገልጣል። ፅድቅ በሌለበት ሥራ መዋልን ፣ ማንነትን አውልቆ ሌላ ስለመደረብ ፣ጨለማን ሲሽሩት ብርኀን እንደሚነጋ ፣ብርኀንንም ሲሽሩት ጨለማን ለማንጋት ነው ይለናል...
[“ ነብስን አጎሳቁሎ፥ ስጋን ማንደላቀቅ
ጨለማን ማንጋት ነው፥ ብርኀን   መሐል መጥለቅ” (ገጽ 4)]
ሕመም ለሰው ልጅ እንደ ዕጣ ክፍል የተሰጠው እንደሆነ ይቀኛል፤መቻልም መዳኛው እንደሆነ ጭምር፣ ግርፋትን ገላው ሳይችል፣ የጅራፍ ሰምበር በገላው ሳይኖር፣ የጋሬጣ ጭረት ከእግሩ፣ መቻልን ከልቡ ሳያሰርፅ በደመ-ነፍስ የሚኖር እንስሳት ነው ይለናል። በሁለት እሳት መሐል ስለሚንከላወሱ ነፍሶች፣ ጊዜን እያከሰሉ ስለሚኖሩ ልቦች ፣ንስሃ ስለራቃቸውም ያትታል። አብዝቶ ስለሚያስጨንቀን፣ ቁልቁል ስለሚያሳድገን፣ መመለስ ስለማንችለው ጸጸት...
[“በትዝታ ሞገድ ፥ከሐሳብ ቢያጠልቅም
ፅፎት ያለፈውን፥ ሰርዞት አያውቅም ።ገጽ7)]
የጊዜ ደመናን ለምትፈራ ነፍስ የተስፋ ጮራ ያመላክታታል። ትንፋሿ ረመጥ የሆነችበቱን ሴት በብዕሩ ይጠራታል። ነገሮች ላይ ያለን ጥባቆት ከጊዜ ወደ ጊዜ መጎተቱን ሳይጠቁምም አያልፍም። በጊዜያዊ ክብር ስለሚያንበሸብሹ ፤ቆይተው  ማሩን በመርዝ ለሚያሟሹት ሳይቀር ቁጣው ብቅ ትላለች። ያመኑበትን ስለመኖር...ይለናል
[“መዳኑን በይፋ፥ ያመነ መነኩሴ
ጠላት ስለሌለው፥ አይዝም አንካሴ። (ገጽ11]
ሩጫ በበዛባት ዓለም አሸናፊ አሸናፊ የሚሰኘው ተሸናፊ ስላለ ነው። ሞትም ሟች ስላለት እንደገነነ ሁሉ። ስለ ማረመም ፣ጸጥ ስለማለትም፣ የዝምታን ኃያልነት፣ የመንፈስ መዋዋስን ጥልቀት ይመረምራል። ሰው የሚወደውን ይስማል፤ ሰው ግን ደግሞ ራሱን አብልጦ ይወዳል፤ ይሁን እንጅ ሰው ራሱን ቢወድም ራሱን ሲስም አይታይም እያለ ይገራረማል። ምናልባትም በአካል ኖሮ ቢሆን የፀጋዬ ተ/ማርያም ሚስት ሮማን ከንፈሯን ስትነክስ፣ በራሷ ስትቅበጠበጥ እንደነበር ሹክ ባልኩት። ከኋላችን ስላለው እውር ነን ሊለን ይቃጠዋል...
[“ቀድሞ በመፈጠር ፥ማንም ይቅደም ማንም
  ከፊት የምናየው ፥ ከኋላ አይመስለንም"]
“በምንሞች መሐል ምንም ስላልነበር፤ የዚያ ሰው ሽልማት መሰቀሉ ነበር “ይለዋል ጌታውን። ይመክራል ከልቡ። ስታስነጥስ ይማርህ እያሉ ባላስነጠስክበት ስለሚገድሉት ሰዎች ይናገራል። ለማስነጠስ ብቻህን ሁን ፣ከምትወዳቸውም ይማርህን ተዋስ ይለናል። እንቅፋትን የመፋለም ወኔ ይታይበታል ...
[“ከእንቅፋት የጸዳ፥ ዛሬህን አትሰራም
በዘመኑ ሙሉ፥ ጨለማን ያላየ፥ መብራት አያበራም" (ገጽ 28]
ብሶት ሽሽት ስንጓዝ ፣በደላው እቅፍ ስንያዝ ደስ አይበለን። የደላው የቸገረው’ለት አያድርስ ነው። በኑሮ በችግር እንዳናማርር ፣ በችግር በኑሮ ከሞተ እንድንማር ያጽናናል። መለያየትን በተለየ ያያታል። መለያየት ሞት ነው ይላል፤ ክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ። የለም የለም መለየት ሞት አይደለም ፤ሞት መለየትን አያክለውም መለየትም ሞትን አይመስለውም ይላል ገጣሚው። ዘወልድ በፋንተው መለያየትን እረስቶ አለመርሳት ወደሚል ፍች ያቀርባታል።
[“በአካል አለመኖር፥ ከመንፈስም መጥፋት
ከራስ እኩሌታ፥ ’ሚወዱትን ማጣት (ገጽ32]
[ጎልማሳ ሐሳቦች]
ከስኬት ዳርቻ የሚደ’ረስ በዕድሜ ሳይሆን በሐሳብ (በአስተሳሰብ) ነው። ፀጉራቸውን ሽበት ወሯቸው ከህጻን ያልተሻለ ተግባር የሚፈጽሙ መኖራቸው ግድ ሰጥቶታል። በጭንቅ ስለሚሞረደው፣ በሀሳብ ስለሚሳለው፣ በምናብ ስለሚነግሰው፣ ስለ ልብ ስር እረመጥ ትዝታም ስለሆነው ይጨነቃል። ህግ ስናወጣ ከራስ ጋር ቅራኔ የለም። ህጉ ከሌላ ሲቃረን ግን እንሽረዋለን። ለምን? ፍንጉጥ ላለመባል፣ ብቻችንን ላለመቅረት ሲል ስለ አቋም ይናገራል። በጌታው የተማመነ ሙክት ላቱን ከውጭ ያሳድራል እንዲሉ...ስለ ሐቅ ይገደዋል።
[“ታዝለህ ላለመኖር፥ በዕድሜ አንቀልባ
ቀድመህ እግር አውጣ፣ ከአንተነትህ ግባ”(ገጽ48]
ጋን ሲሞላ ውኃው እንደሚፈስ ሁሉ እናንተም ባዶነታችሁን ሙሉ፣ ለምን? በሉ ይለናል። መቃብር ቆፋሪ ለሞተ ሁሉ ሲለፋ ኖሮ እርሱ የሞተለት መቃብር ቆፋሪ (ቀባሪ) እንዳያጣ ይሰጋል። በዚህም በየመሐሉ ለራሳችንም እንድናስታውስ ሃሳብ  ይሰነዝራል። ወሬኞችን ደጋግሞ ሲሸነቁጣቸው ይታያል።
[“መንፈስ የሚወጉ፥ የሚያስፈሩ ቀንዶች
ባይታዩም አሉ፥ ከሰዎች ምላሶች” (ገጽ 53]
ደጋግሞ ስለ ሩቅ ሴት ይገለጻል። መጥቶ አጥቶሽ ነበረ ሲል ጥባቆቱን ይገልጽላታል። ሰዎች “ተዋት” ያላላሉኝ እንደማልተውሽ ገብቷቸው ነው... በፀሐይ አየሁሽ በጨረቃ ሰርፅሽኝ ይላታል (የናፍቆቱን መፈራረቅ ሲያወሳ)። ስለ መልካም ሰዎች (ማዕዘረ ብርኀን) ውለታ፣ ስለ ክፉዎችም (አፍቃሬ ጽልመቶች) ይገደዋል። ጨለማ ውስጥ ስንሆን ብርኀኑ ውስጥ ስለሚላወሱት ማየት እንደምንችል፤ በተቃራኒው ግን እንደሚከብድ ይለፍፋል። ውበቷ የገዘፈበትን ሴት ይላታል...
[“ስለ አንቺ ውበት፥ ብዙ ቀን ጽፊያለሁ
አንችን የሞሉ ቀን፥ አነብልሻለሁ"]
[“ውዴ ገጥሚያለሁ፥ ብዙ ዓ.ነገር
 እንዳንቺ ዝንተ ዓለም፥ ስሙም ባይሻገር”]2
[ዘለግ ያሉ ሐሳቦች]
ዘግናኝ ሰዓትን ለገፉት ተበዳይ ሰዎች የምናወራውን እንድንመርጥ ይሻል። ልጇ ለሞተባት እናት የባሏን መሰወር ማርዳት ፣የተቸገረ ሰው ፊት ስለድሎት ማውራት፣ ፍቅር አልሰምርልህ ላለው የራስን ልዩ ሕይወት መተረክ በሰው ቁስል ላይ እንጨት ከመስደድ አይተናነስም። ሲከፋው አጽናኙ ከነበረችዋ ሴት፣ ለቅጽበት ሲያጣት ስለሚጨንቀው እንስት መስማት የማይፈልገው ነገር አለ...
[“ልተውህ ነው ብለሽ ፥ እንደቀልድ መንገር
መቀበሪያን መማስ ፥ ነው ጉድጓድ መቆፈር” (ገጽ65]
ወደ ራስ መጥለቅን፣ ዝም ብሎ ዝም ማለትን (ሎሬት ፀጋዬ)፣ ራስን ማድመጥን ይሰብካል። ግጥምን ከሳቅ ይልቅ ሲቃ እንዲወልዳት (በሚያምር ዓለም ውስጥ የሚያምር ቅኔ እንደሌለ ያወሳል)። “መቸገር ግጥም ነው”ብሎ እስከመደምደም ድረስ። በስም ታሪክ መስራት፣ ወድቆ ማንሰራራት፣ ንፁሕ ጥርጊያ መስራት፣ ከህሊና መፍረድ፣ ከልቦና ማዘን፣ ጣት አለመቀሰር፣ ነፍስን በጽኑ ማዋቀር ነው ለእሱ ማወቅ ማለት። ሰው ከቀን ጋር ስለመመሳሰሉ ይለናል...
[“በመገረም ለዛ ፥ አንዳንዴ ሳስበው
እኛ እኛን ሳይሆን ፥ ቀኑን ነው ምንመስለው” (ገጽ84]
ዕድሜን እንደ ዶሮ ብልት ገነጣጥሎ ያሳየናል። እልፍ ብሎም body present , mind absent የሚሉትን ፈረንጆች ዘወልድ ይነካካዋል። ቤት ተቀመጠን ስለ ተሰደደው ሐሳባችን ይጨነቃል።
[“እኛ ከቤት ሳለን ፥ ደጅ የምንተዋቸው
ደጅ አደር ሐሳቦች ፥ እጅግ ብዙ ናቸው”(ገጽ 88)]
ለመቋጨት...
ይህ  ሐሳብ ቤት ይመታል የተሰኘ የዘወልድ አክመን ዘወልድ  መጽሐፍ፣ ትኩረቱ ወደ ሐሳብ ነው። ሐሳቡም መልዕክትና አጽንዖት ይበዘዋል። በብርሃኑ ገበየሁ የአማርኛ ስነግጥም ንድፈ_ሃሳብ ማብራሪያ እና ትንታኔ መፅሐፉ፤ wystan hugh Auden ገጣሚ ከቃላት ጋር መጫወት እንጅ ልገልፀው የምፈልገው መልዕክት /ጠቃሚ ምክር አለኝ እንዳይል ያስረዳል። እንግሊዛዊው ገጣሚ keat? በፊናው ግጥም፣ እውነትና ውበትን ይይዛል ይላል። ቅርጽን ተመርኩዘው የሚጻፉትን (ደመ ግቡ ግጥሞች ልበላቸው?) የሚደግፉ አሉ። ይዘትን ተመርኩዘው የሚጻፉትን (ስብከት አዘል ግጥሞች ልበላቸው?) የሚደግፉ አሉ። ሁለቱን አዋሕደው የያዙም የkeat መሰሎች አሉ። የቃላት ውበትን ተመርኩዘው የሚጻፉ ግጥሞችና መልዕክት ለማስተላለፍ ተብለው የሚጻፉ ግጥሞች አንዱ ሌላውን የሚጻረሩ (mutually exclusive) መሆን አይገባቸውም ባዮች አሉ። ምርጫው ለየግላችን የተተወ ነው::
ይህን መጽሐፍ እንዳነበው መጋበዜን ወደድኩት። የተለያዩ ደራሲዎችንና ገጣሚዎችን ሥራ ሳነብ በእነሱ ጫማ ሥር መሆንን እመርጣለሁ። እንጅማ እኔ ለግጥም ያለኝ አረዳድ  ዘወልድ አልያም ሌሎች በተረዱበት መልኩ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም። ለራሴ ስጽፍ በራሴ እሳቦት የሰዎችን ሳነብ እንደ’ነሱ እሳቦት መናጥ ይስማማኛል።
ይኼን ስል የተጻፈ መጽሐፍ ሁሉ ይስማማኛል ማለት አይደለም። ሐሳብ ካለው እሰየው፣ ውበት ካለው እሰየው ግን ደግሞ ሐሳብ ሲደመር ውበት ከሆነ ፍስኀ ነው ለእኔ። በዘወልድ አክመን ዘወልድ መጽሐፍ ውስጥ የምትደጋገም (በብዙ ገጣሚዎችም ጽሑፍ ውስጥ የማያት ነገር አለች፤ብትቀር የምላት)። እንዲህ ነው ቃናዋ...
[..እንን እንን፣ እንንን ዓለም
...እንን እንን፣ እንንን የለም።]
የዚህ ግጥም ስብስብ ጸሐፊ ልብ ይሙላ አይሙላ ማወቅ አንችልም (የሞት አድማስ ጋርዶናል)። በሕይወት ቢኖር ይኼ መጽሐፍ በዚህ  ደረጃ ይወጣ ነበር ወይ? መልስ የለኝም። ከወጣ ወዲያስ ረብ ያለው ነገር አበርክቷል ወይ? ለዚህ መልስ አለኝ።
ቆንጆ ቆንጆ ሐሳቦችን በተለይ በአጭር ግጥሞቹ ውስጥ ሰጥቶናል። በጎ አስተሳሰቦችን፣ ተስፈኝነትን፣ ወደ ራስ ማተኮርን፣ ቀስ ብሎ ማደግን፣ ጠንካራ እምነትን ...ብዙ ብዙ ነገሮችን ወደ እኛ ለመሰንዘር ችሏል።
[“አንዳንዴ...
በመውደድ ቆንጅቶ ፥ በመፋቀር ሲኳል
ግጥም ይመስልና ፥ ሐሳብ ቤት ይመታል (ገጽ25]
ዘወልድ ሐሳብ ላይ ይጫወታል። ገና ሃያዎቹ ውስጥ የነበረ ገጣሚ መሆኑ ደግሞ ያስቆጫል ።ከዕድሜ የሚገኙት ዕውቀቶችን ሲጨምር የት ሊደርስ እንደሚችል መገመት ቀላል ነው ።ይሁን እንጅ የዕድሜ ገፁ ተሸብሽቧል፣ እረፍም ብሎት አሸልቧል። ኗሪ ሐሳቦቹ ናቸው። ቀሪ ሥራዎቹም የኅትመት ብርኀን አይተው እንደምናነባቸው ተስፋ አደርጋለሁ።
[“በኑሮ በችግር ከምታማርሩ
በችግር በኑሮ ፥ከሞተ ተማሩ” (ገጽ 31]

Read 217 times