Print this page
Saturday, 29 October 2022 12:46

ኪስ

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

“--ብቸኛው የራስን ፍርሃት ፀጥ የማድረጊያው ዘዴ ደግሞ ጭካኔ ነው፡፡ የሰው ልጅ በህልውና ለመቆየት በሰፋቸው ብዙ ግልፅ እና ሚስጢር ኪሶቹ ውስጥ ጠልቀን ብንቆፍር የምናገኘው ፍርሃት እና ጭካኔን ነው፡፡--”

አልፎ አልፎ ፀጥታን ፍለጋ ወደ (ቅርብ) ገጠር እሄዳለሁኝ፡፡
መጠንቀቅ ካለብን በዋነኛነት መጠንቀቅ ያለብን ምኞታችንን ነው፡፡ ብትፈልገው የማታገኘው፣ ብታገኘው ደግሞ የማትፈልገው ነገር እንቆቅልሽ ነው፡፡ እንቆቅልሹ ፍቺ የሚኖረው “ድሮውኑ ምን እንደምትፈልግ ሳታውቅ ነው የተመኘኸው” የሚለው ሃቅ ላይ ነው፡፡
ፀጥታ ምን ማለት አንደሆነ ሳላውቅ ስለሆነ የምፈልገው፣ ባገኘውም አላውቀውም፡፡ የሳንድሬላን አንድ እግር ጫማ ይዞ የሚወዳት የመሰለችውን ልጃገረድ ሲያፈላልግ የነበረው ልዑል፣ አመዳም የቤት ሰራተኛ የጫማው ልክ ሆና ስትመጣ “እሰይ ስለቴ ሰመረ” የሚል ይመስላችኋል? እኔ ግን ነብስ ካወቅሁበት ጊዜ ጀምሮ የዚህ ተረት አስተላለቅ አይዋጥልኝም፡፡
እና ከተለመደው የከተማ ጩኸት እና ወከባ ርቄ በዚህ ጭቃ ቤት ውስጥ ለመፃፍ ስሞክር፣ በእርግጥ ከአዲስ አበባ አንፃር ከታየ መቼም ፀጥታው የተሻለ መሆኑ በሆነ ረገድ አይቀርም በማለት እያሰብኩ ነበር፡፡ ግን በተጨባጩ ቀነስ ይላሉ ብዬ የገመትኳቸው ድምፆች ከመጣሁበት ከተማም ይጎላሉ፡፡ በዘመነኛው አስተሳሰብ በስልክ ወይንም በሜጋፎን ብቻ የሰው ልጅ ድምፅ ማቋረጥ ይችላል ተብሎ የሚታሰብ ርቀትን የዚህ አካባቢ ሰዎች በላንቃቸው ያደራርሱታል፡፡ በኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ብቻ የሚያጥረውን ርቀት እንጥል ያለ ካርድ እና የድምፅ ጥቅል ይሻገረዋል፡፡
ለነገሩ የሰዎቹ ድምፅ አያውከኝም፣ ዜማዊ ነው ብዬም ልቀበለው እችላለሁኝ፡፡
የዚህ የገጠር ቤት ፀጥታ የሚደፈርሰው በሰራዊት ሳይሆን በአራዊት ነው፡፡ አራዊቱ ደግሞ በቀንም በማታም ነው የሚመጡት፡፡ ለምሳሌ ቅድም በሩን ክፍት አድርጌ ደጅ ደጁን እየተመለከትኩ ስቆዝም አንድ ጥቁር ድመት መጣ፡፡
እንደ መደበኛው ድመት፣ ከሰው ልጅ ጋር ፊት ለፊት ሲጋጭ አንገቱን ቀልሶ የሚሄድ አይነቱ ግን አይደለም፡፡ ወደ በሩ ወጣሁኝ፡፡ ስጠጋው ጀርባውን ሰጥቶኝ በቀስታ ተራመደ፡፡
ድመት እንዳይደለ እርግጠኛ ሆንኩኝ፡፡ ጭራው የድመት አይደለም፡፡ እንደ ሸለምጥማጥ የጭራው አወፋፈር እና የሽንጡ አገዛዘም ያመሳስለዋል፡፡ እለታዊው “ዋይልድ ኪንግደም” ጀመረ አልኩኝ ለራሴ፡፡ ድንጋይ አንስቼ እንደ ከተማ ልጅ፣ ሁሉን ቻይ፣ ሆደ ሰፊ የሆነ የእጅ አጣጣል ወረወርኩኝ፡፡ የከተማ ልጅ እና ድንጋይ ከተራራቁ ቆይተዋል፡፡ ለኢንስታግራም ፖስት በስልኩ ካሜራ ሲቀርፅ በሚረጨው መብራት ነው ድመቱን ክፍ ብሎ የሚያባርረው፡፡ ስጋ በል የሆነ እንስሳ ላይ እንደ ቬጂቴሪያን ነው የወረወርኩት፡፡
ምናልባት ድመት እና ሸለምጥማጥ ተዳቅለው የፈጠሩት የተሻሻለ ዝርያ ሊሆን ይችላል ብዬ አሰብኩኝ፡፡ ዶሮ እና አይጥን ሳያማርጥ የሚመገብ ሃይለኛ፡፡
እዚህ ቦታ ፀጥታን የማጣው በእንስሳት አማካኝነት ነው፡፡ ቬጂቴሪያን ማለት ግን የዋህ ማለት አይደለም፡፡ ወይንም ማለት እንዳይመስላችሁ፡፡ እዚህ የቦታው ነዋሪዎች “ኦሶሌ” (ጩሬ) እያሉ የሚጠሩት ፍጥረት አለ፡፡ እንደሱ ፍጥረት የገጠር ቆይታዬን የሚያውክ የለም፡፡ ቅጠል የሚበላ ግን ኮርኒስ ውስጥ የሚኖር አውሬ ነው፡፡ ድምፅ ይጠላል ይባልለታል፡፡ የውሻ ጩኸት ያለበት ስፍራ አይገኝም ይባላል፡፡ ድምፅ ይጠላል ግን እንደዚህ እንስሳ ኮርኒስ እና ጣራን ሲያንኳኳ ውሎ የሚያድር የለም፡፡ ጣራው ላይ ሲፈነጭ ለሰማው ህፃናት ለመጫወት ጣራው ላይ የወጡ ነው የሚመስለው፡፡ የሚያዘወትረው ጨዋታ ደግሞ አባሮሽ ነው፡፡ ሁሌ ሩጫ ላይ ነው፡፡ ራሱንም ሳያሳድድ አይቀርም፡፡ በትንሽነቱ እንደ ጠርሙስ ማጠቢያ ብሩሽ የመሰለ ጭራ አለው፡፡ እንዳለው ያወቅሁት አንድ ጊዜ ከጣራው ወድቆ ሶፋው ላይ ሞቶ ከአዲስ አበባ ስመጣ ስለጠበቀኝ ነው፡፡ ትልቅ ሲሆን ቅርፅ ይለውጣል፡፡ ትልቅ ሆኖ ሳገኘው ሌላ ፍጥረት ሁሉ መስሎኝ ነበር። ተለቅ ሲል አይጠ-ሞገጥ ነው የሚመስለው፡፡ ሲመቸው ጥንቸልም ያህላል፡፡ ችግሩ ጣራ ላይ መሆኑ ነው፡፡ ከጣራው ስር ደግሞ እኔ ፀጥታ መፈለጌ፡፡
ሽንቱ አሲዳማ ነው፡፡ ኮርኒሱን በሽንቱ ቦዳድሶ ጭርንቁስ አድርጎታል፡፡ የግዛት ማካለያም ሳይሆን አይቀርም፡፡ አንዴ ሽንቱን መርጨት የጀመረበት ቦታ ጣራው ተደርምሶ ካልወደቀ አስተዋፅኦ ማድረጉን አይተውም፡፡
ዘወትር ወደዚህ የጭቃ ቤት በሄድኩኝ ቁጥር ከዚህ ፍጥረት ጋር የሃይል ሚዛን ፉክክር እናደርጋለን፡፡ እኔ ጠፋ ብዬ ስመለስ፣ ፍጡሩ እና መሰሎቹ በቤቱ ላይ ነግሰው ይጠብቁኛል፡፡ ገና ስመጣ ከኮርኒሳቸው ብቅ እያሉ ተኮልኩለው ያስተውሉኛል፡፡ እኔ ወደነሱ መኖሪያ ቀዬ የመጣሁ ቱሪስት ነው የምመስለው፡፡ እንደገባሁኝ እኔ ደግሞ የግዛት ማስከበር ስራዬን እጀምራለሁኝ፡፡ የበሱትን ጣራ ባለሞያ ቀጥሬ አስጠግናለሁኝ፡፡ አባቴም ይሄንኑ ያደርግ ነበር። እኔም ትግሉን አስቀጥያለሁኝ፡፡
ዋናው ነገር የቅጥቀጣ ድምፁ ነው፡፡ አናጢው በመዶሻ እና ሚስማር ቆርቆሮውን እና ኮርኒሱን ሲመታ ባላንጣዎቼ ቤቱን ጥለው ይጠፋሉ። ምቾታቸውን ያጣሉ፡፡ ከሰል ሲቀጣጠል፣ ፋኖስ ሲለኮስ፣ ሙዚቃ ሲከፈት፣ ቡና ሲወቀጥ እና ወይራው ሲታጠን ቅኝ ገዢዎቹ ስደተኛ ይሆናሉ፡፡
ገና ስመጣ፣ የመደበቅ ክህሎታቸው እንኳን ጠፍቷቸው፣ ጣራ ላይ ዘና ብለው እንዳላስተዋሉኝ፣ ድራሻቸውን ያጠፋሉ፡፡ እነሱ እንዲጠፉ ግን እኔ እዛው መቆየት አለብኝ፡፡ ጣራ ላይ ቁጭ ቁጭ ብለው፣ ራሳቸውን እንደ ወፍ ቆጥረው ግን መብረሩን ረስተው ሲመለከቱኝ በድንጋይ እሩምታ ሰላምታ እሰጣቸዋለሁኝ። ግራኝ በመሆኔ ስወረውር መሳት የለብኝም ብዬ ራሴን አሳምኛለሁኝ፡፡ እምነት ደግሞ ዛሬ ባይሳካም ነገ ይሳካ ይሆናል ብሎ የመፅኛ (መፅናኛ) አቅም ነው፡፡
ግራ ዘመሙ የፖለቲካ ጎራ ሁል ጊዜ እንደሳተ ነው፡፡ ሙከራው፣ ወይ አንድም ጊዜ ልክ አይመጣ፣ ወይ ሙከራውን አይተው… ዝም ብሎ ለመሳት ይወረውራል፡፡ ዋናው ጣራው መንጓጓቱ ላይ ነው፡፡ እንደው እንስሳት እንደ ሰው ስሜትን የሚገልፅ ፊት ቢኖራቸው ሀዘናቸው መልካቸው ላይ በተነበበ ነበር፡፡ እንደ ሞናሊዛ ያኮርፉ ነበር፡፡ እንስሳት ቅንድባቸውን እና የግንባር ቆዳቸውን እንደ ሰዎች የመጠቀም ደረጃ በዝግመተ ለውጥ ስላላደረሱት ሊሆን ይችላል ሁሌም አንድ አይነት መልክ ያላቸው። የዱር እንስሳት መልክ ሁልጊዜ ንቁ የሚመስል አይነቱ ነው፡፡ የቤት እንስሳት ደግሞ ከድመት በስተቀር ሁሌ የሞኝ መልክ ነው ያላቸው፡፡ ለእኔ እንደዛ ይመስለኛል፡፡
ሲግፊልድ የተባለው ኮሜዲያን የቀለደው ቀልድ እዚህ ነጥብ ላይ ትዝ ሊለኝ ይችላል፡፡ እሱ በእንስሳት እና በሰው ልጆች መሃል ያለው ዋና ልዩነት “ኪስ” ነው ይላል፡፡ ውሻ አጥንት ለመቅበር መሬት ሲቆፍር የሚውለው የዚሁ የኪስ ናፍቆት ነው፡፡ ግን ካንጋሮ የተባለውን ፍጥረት ደግሞ ካስተዋልነው በተፈጥሮ የተሰጠው ኪስ ሆዱ አካባቢ አለው፡፡ ምን ዋጋ አለው ታዲያ… እጁ ደግሞ በጣም አጭር ስለሆነ ወደ ኪሱ መድረስ አይችልም… እያለ ይሄው ኮሜዲያን ያላግጣል፡፡
ልብስ የሰፋ ዕለት ነው የሰው ልጅ ኪስ የፈለሰፈው፡፡ ሰውነቱን በሰራው ልብስ ኪስ ውስጥ ከቶ ከብርድ አተረፈው፡፡ ልብስ የለበሰውን ሰውነቱን ደግሞ ቤት ሰርቶ ተጨማሪ ኪስ አበጀለት፡፡  በኪሱ እና በሰራው ቤት ውስጥ ያለውን የቤተሰቡን አባል አዋጥቶ ሀገር መሰረተ፡፡ ሃሳቡን የሚያከማችበት ኪስ ደግሞ በቋንቋው አዋቀረ፡፡ … ችግሩ የኪስ መኖር የሌብነትን ወንጀል መፈጠርንም ያስከትላል፡፡ ሀገር የሚያፈርሱ አክቲቪስቶች ከማህበረሰቡ ኪስ ነው ዝና እና ገንዘባቸውን የሚመነትፉት። ብዙውን ጊዜ መመንተፍ ሳያስፈልጋቸው ነው ማህበረሰቡ ራሱ የሚሸልማቸው፡፡
ይሄ ጣራዬ ላይ የሚሮጠው ፍጥረት በእኔ ኪስ ውስጥ ወይንም በቤቴ ኮርኒስ ውስጥ ኑሮውን ስለቀለሰ ነው ድንጋይ የወረወርኩበት። ተቻችለን እና ተከባብረን አንድ ላይ መኖር አንችልም፡፡ ወይ እሱ ቤቱን መኖሪያው ያደርጋል ወይንም እኔ፡፡ የእኔን በስፍራው አለመገኘት ተጠቅሞ ነው ህይሉን የሚያጠናክረው፡፡
ክፍት በሆነው በር ሳስተውል ደግሞ ሌላ ፍጡር በበሩ ለመግባት ሙከራ እያደረገ ነው። ይሄኛው ፍጡር እንኳን ሲቪል መሀንዲስ ነገር ነው፡፡ እንዲያውም ከገጠር የበለጠ ከተማ አካባቢ አይጠፋም፡፡ የሲሚንቶ እና የብሎኬት ወዳጅ ነው፡፡ የጭቃ ቤቱ ወለል ሊሾ ስለሆነ ነው የሲሚንቶ ናፍቆቱን ለመወጣት ወደ ውስጥ መግባት የፈለገው፡፡ የእንሽላሊት ነገር!
ጭራው በጣም ረጅም ነው፡፡ እንሽላሊት እርስ በራሱ ሲጣላ ጭራ ይቆራረጣል ይባላል። ይሄኛው የሚጣላው አጥቷል ማለት ነው፣ ጭራው እንደ ሴት ልጅ ጠጉር የተንዠረገገው። ለማንኛውም ይሄም እኔ ቤት ውስጥ (ኪስ ውስጥ) መግባት አይፈቀድለትም፡፡
አንዱ ሲሄድ ሌላኛው ደግሞ ይመጣል፡፡ በጣም ጥቁር የሆነ ተርብ ወደ ክፍሉ ዘው ብሎ ገብቶ ቀፎውን ማንጠልጠል የሚችልበትን ተስማሚ ቦታ ቅኝት ማድረግ ጀምሯል፡፡ ዝም ቢል ያን ያህል ቦታም ባልሰጠሁት ነበር፡፡ ግን እነዚህ ፍጥረታት ዝም አይሉም፡፡ ፀጥታን ፍለጋ ወደ ገጠር መሄድም የማይሆነው ለዚህ ነው፡፡ ድምፅ የማያወጡት ደግሞ ሹልክ ይላሉ።
አጎንብሼ እያነበብኩኝ በአንደኛው የዐይኔ ጫፍ አንዳች ነገር ውልብ ሲል አየሁኝ፡፡ ትንሽ ስጠብቅ ደገመው፡፡ ጥቁር አይጥ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ያስቀመጥኩላቸው መርዝ አልቆባቸዋል ማለት ነው፡፡ መርዙን በቡና ሲኒ ማቅረቢያ አድርጌ ነው በተለያየ የቤቱ ጥግ ያጠመድኩት። ወደ ቡና ማቅረቢያው አይጦቹን ማቅረብ እንዲቻል ከመርዙ ጋር ምግብም ደባልቄ ነው ያኖርኩላቸው፡፡ እኔ መኖር እንድችል እነሱ ደግሞ እንዲሞቱ ነው ያኖርኩላቸው። እኔም ኖሬ አልጠግብም፣ እነሱም ሞተው አያልቁም። መርዙን ያደረግሁበት ማቅረቢያ ላይ “ይሄ መርዝ ነው” የሚል የፅሁፍ ማስታወሻ ከትቤበታለሁኝ፡፡ ስፅፍ በግማሽ ሳቅ እና በግማሽ ኮስታራ መንፈስ ነበር፡፡ የሚያነብ አይጥ ከመጣ በህይወት ሊተርፍ ይችላል፡፡ የሚያነብ አይጥ ቢመጣማ ለእኔው ራሴ መርዝ ቀምሞ ይሰጠኝ ነበር፡፡ አይጥም ኪስ የለውም።
ከዚህ በፊት እዚሁ ቤት ውስጥ ሌላ ተሳቢ እንስሳ በውድቅት ሌሊት ሲንጎራደድ ማግኘቴን አጫውቻችኋለሁ? ያን ቀን ፀጥታውን ያጠፋው የራሴው ልብ ምት ነው፡፡ የልብ ምት ሲጨምር የራስን ጆሮ ይደፍናል፡፡ ፀጥታ ማለት ግን አይደለም፡፡ በህይወት ያለ እባብ በህይወቴ ያየሁት ያን ምሽት ነው፡፡
ብቸኛው እውነተኛ ፀጥታ እሱ ስሜት  ነው፡፡ የራስን ኪስ ከማስከበር የሚመጣ የልበ ሙሉነት ስሜት፡፡ ድሮውኑ ጩኸቱ የሚመነጨው  ከራስ ፍርሃት እና ስጉነት ነው፡፡ ብቸኛው የራስን ፍርሃት ፀጥ የማድረጊያው ዘዴ ደግሞ ጭካኔ ነው፡፡ የሰው ልጅ በህልውና ለመቆየት በሰፋቸው ብዙ ግልፅ እና ሚስጢር ኪሶቹ ውስጥ ጠልቀን ብንቆፍር የምናገኘው ፍርሃት እና ጭካኔን ነው፡፡

Read 1141 times