Monday, 31 October 2022 00:00

“ኢትዮጵያዊነትን መምረጥ ከሃዲነት”

Written by  በተስፋዬ ነጋ
Rate this item
(0 votes)

“ኢትዮጵያዊነትን መምረጥ ከሃዲነት”  የሚለውን ቃል (ሀረግ) የሰማሁት የጀነራል ሳእረ አስከሬን ሽኝት በሚሌኒየም አዳራሽ በተደረገበት ወቅት ነበር:: ይህ ቃል ሲተነተን ብዙ ነገሮችን ያመለክታል፤ ሀገራችን ለገባችበት ፈተና መሰረታዊ መንስዔውን ይጠቁማል፡፡ ከ1983 እስከ 2010 ዓ.ም. በነበሩት 27 ዓመታት፣ በሀገርና በህዝብ ላይ የተሰራውን ሴራ ያሳያል፡፡ ለአንድ ችግር መፍትሄ ለመፈለግ፤ መንስዔውን በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል ብዬ ስለማስብ፤ “ኢትዮጵያዊነትን መምረጥ ከሃዲነት”  የሚለውን ሀረግ መነሻና መሰረት በማድረግ ጥቂት ለማለት ወደድኩ፡፡
በአስከሬን ሽኝቱ ወቅት እንደሰማነው፤ ይህ ለውጥ ከተጀመረ በኋላ ጀነራል ሳእረ ኢትዮጵያዊነትን በመምረጡ በጥቂቶች ዘንድ እንደ ከሃዲ እንደተቆጠረ ነበር የተጠቀሰው:: እንግዲህ “ጥቂቶች” ተብለው የተጠቀሱት፤ የጀነራሉ የቀድሞ የስራ/የትግል ባልደረቦች የነበሩና ከ1983 እስከ 2010 ዓ.ም. በነበሩት 27 ዓመታት፣ የመንግስት ስልጣን ይዘው የቆዩ ሰዎች መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የተሰባሰቡበት ቡድን ነው ኢትዮጵያዊነትን መምረጥ  እንደ ከሃዲነት የቆጠረው፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ ይህ የመገንጠል ዓላማ ይዞ ትግል የጀመረ ቡድን ነው፣ በ1983 ዓ.ም. በተፈጠረለት አጋጣሚ የኢትዮጵያን መንግስት ስልጣን ይዞ፤ የሚጠላውን ሀገርና ህዝብ ለ27 ዓመታት በጠመንጃ ሀይል ሲገዛ የቆየውና፤ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱን ለገጠሟት ፈተናዎች መሰረት የሆኑ የጥፋት ዘሮችን የዘራው፡፡ ቡድኑ በሀገርና ህዝብ ላይ የፈጸመውና የዘራው የጥፋት  ሴራ ከብዙ በጥቂቱ እንደሚከተለው ሊገለጽ ይችላል፡፡
በየትኛውም የአለማችን ሀገር ታይቶ የማይታወቅ፤ ህዝብን በዘር ለመከፋፈል ወይም ለማለያየትና፤ ሀገርን ለመበታተን የሚያስችል፤ በዘር (በነገድ) ላይ የተመሰረተ የፌዴራሊዝም ስርአትን መስርቷል፤
ይህንኑ አጥፊ ስርአት የሚደግፍ ህገ-መንግስት አዘጋጅቶ፤ ዘርን (ነገድን) መሰረት አድርጎ የከለላቸውና አላግባብ “ብሄር” ወይም “Nation” ብሎ የሰየማቸው የህብረተሰብ ክፍሎች፤ ሲፈልጉ መገንጠል የሚያስችላቸውን አንቀጽ በህገመንግስቱ አስቀምጧል፤
ክልሎቹ ለማእከላዊው መንግስት ቁጥጥርና አስተዳደር አስቸጋሪ እንዲሆኑና፤ የርስ በርስ ጦርነትና የህዝብ መፈናቀል መፈጠር እንዲችል፤ የራሳቸው የሆነ የተደራጀና የታጠቀ የጦር ሀይል እንዲኖራቸው አድርጓል፤
የዘር ፖለቲካን በማራመድና የሃገሪቱ ህዝብ፤ በተለይም ወጣቱ የጋራ የሆነ ሀገራዊ ቋንቋ እንዳይናገር፤ የክልላዊ ወይም የዘረኝነት ስሜት እንጂ የአንድነትና የሀገር ፍቅር ስሜት እንዳይኖረው ለማድረግ ጥሯል፤
የሀገሪቱ ሀብት በተለያየ መንገድ እንዲመዘበርና ጥቂቶች በጣም በልጽገው፤ ሰፊው ህዝብ ግን በድህነትና ከልክ ባለፈ የኑሮ ውድነት እንዲሰቃይ አድርጓል፤
ሀገሪቱ ወደብ አልባ እንድትሆን አድርጓል፡፡
ይህ ቡድን እነዚህን አስከፊና አሳዛኝ ተግባሮች የፈጸመው፤ የራሱን እኩይ ፍላጎት ለማሳካት እንጂ፤ የየትኛውንም የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ወክሎ እንዳልሆነ አምናለሁ:: በጣም የሚያሳዝነው ነገር ደግሞ የቡድኑ አባላት ካለፈው ስህተታቸው ከመማር ይልቅ፤ በአሁኑም ወቅት ሴራቸውን ለጻፉበት ህገ መንግስት መከበር ሲጮሁና ህዝብን ከህዝብ ለማለያየት፤ መንግስትንና ህዝብን ለማራራቅ ሲጥሩ ይስተዋላል፡፡
ውድ አንባቢያን፤ እነዚህ ሰዎች ጥፋት ሲሰሩ የቆዩትና አሁንም የሚሰሩት ለምን ይመስላችኋል? ጥያቄው ብዙ መልስና ማብራሪያ ሊሰጥበት ይችል ይሆናል፡፡ እኔ ግን በአጭሩ - የአስተሳሰባቸው ድክመትና አርቀው ማሰብ አለመቻላቸው ነው - እላለሁ፤ ምክንያቱም በጥልቀትና በርቀት ማሰብ ቢችሉ ኖሮ፤ የፈጸሙትና የሚፈጽሙት ተግባር ራሳቸውንና ቤተሰባቸውንም እንደሚጎዳ ይገነዘቡ ነበርና፡፡  ብዙውን ጊዜ ክፉ ተግባርን የሚፈጽሙ ሰዎች በርቀትና በጥልቀት ማሰብ የማይችሉ ናቸው:: ምክንያቱም ክፉ ተግባራቸው ራሳቸውን እንደሚጎዳ መገንዘብ አይችሉም፤ ሰው የዘራውን እንደሚያጭድ አያስተውሉምና፡፡
ያለፈው አልፏል፤ አሁን የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ትልቁ ቀዳሚ ስራ ሊሆን የሚገባው፤ በሀገሪቱ ውስጥ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም የድርሻውን መወጣት ነው:: በተጨማሪም፣ ባለፉት 27 ዓመታት፣በሀገሪቱ ላይ የተሰሩትን የህገ መንግስት፤ የፖሊሲና የመዋቅር ስህተቶች ማረምና ሁኔታዎችን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል፤ የጥፋት ወሬና አሉባልታን የሚፈጥሩና የሚያሰራጩ ሰዎች፤ እኩይ ተግባራቸው ማንንም እንደማይጠቅም አርቀው በማሰብና በመገንዘብ፤ ከአጸያፊ ስራቸው  መቆጠብ ይገባቸዋል፡፡ ለጥረታችን መሳካት የፈጣሪ እርዳታ እንዳይለየን ሁላችንም መጸለይ ይገባናል ብዬ አምናለሁ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ!!!
ከአዘጋጁ፡- ከላይ የቀረበው ጽሁፍ  ምንም እንኳን ከሁለት ዓመት በፊት የወጣ ቢሆንም፣ አሁን ያለንበትን ሁኔታም ስለሚያንጸባርቅ በድጋሚ አትመነዋል፡፡

Read 830 times