Saturday, 05 November 2022 11:05

ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ተስፋ የተጣለበት ታሪካዊ ስምምነት

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(3 votes)

   - መንግስትና የህውሓት ታጣቂ ኃይሎች በ12 ነጥቦች ላይ ከስምምነት ደርሰዋል
       - በስምምነቱ መሰረት ህወሓት በ30 ቀናት ውስጥ ትጥቁን ሙሉ በሙሉ ይፈታል
       - ሁሉን አቀፍ ስምምነት ካልተደረገ የታሰበው ሰላም አይመጣም - ፕ/ር መረራ ጉዲና
       - በሰላም ስምምነቱ መካተት ያለባቸው ወገኖች ሁሉ አልተካተቱም - የፖለቲካ ምሁር
        

      በፌደራል መንግስትና በህውሓት ታጣቂ ሃይሎች መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ፣ ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የቆየው የሰላም ንግግር በስምምነት ተቋጭቷል። ሁለቱ ወገኖች ተኩስ ማቆምንና ህውሓትን ትጥቅ ማስፈታትን ጨምሮ በ12 ነጥቦች ላይ ከስምምነት ደርሰዋል።
ሁለቱ ወገኖች ከስምምነት ላይ የደረሱት ደም አፋሳሹ የሰሜኑ ጦርነት ከተጀመረ ድፍን ሁለት ዓመት ሊሞላው አንድ ቀን ብቻ ሲቀረው ነበር፤ባለፈው ረቡዕ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም፡፡ ታጣቂው ቡድን ህወኃት በትግራይ በነበረው የሰሜን እዝ ላይ አሰቃቂ ግድያና ጥቃት በመፈጸም ነበር የጦርነቱን እሳት የጫረው፡፡ በጦርነቱ ብዙ እልቂት፣ውድመትና መፈናቀል ደርሷል፡፡
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል የተባለውና በሁለቱ ወገኖች የተፈረመው ይኸው የሰላም ስምምነት፤አሥራ ሁለት ነጥቦችን የያዘ ሲሆን ኢትዮጵያን አሸናፊ በማድረግ የተቋጨ ነው  ተብሏል፡፡
ጠ/ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ  ባለፈው ረቡዕ  ምሽት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መግለጫ፤ የሰላም ስምምነቱ “ከአራት ዓመት ተኩል በፊት የተጀመረውን ለውጥ ወደፊት ለማራመድ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው” ብለዋል።
የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግና ለሰላም ቁርጠኛ መሆናቸውንም ጠ/ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ወዳጆች በጦርነቱ የተጎዱ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባትና በአጠቃላይ ላለው ልማት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠ/ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ጠይቀዋል።
የፖለቲካ ምሁሩ ዶ/ር አንተነህ ተስፋዬ በደቡብ አፍሪካ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፤ሁለቱ ወገኖች የደረሱበት የሰላም ስምምነት ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማስቆም የሚያስችልና የትግራይን ህዝብ መሰረታዊ ችግር የሚፈታ እንደሆነ ቢታመንም፣ ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላም በማስፈኑና በዜጎች መካከል የተፈጠረውን ቂምና ቁርሾ በማስቀረቱ ረገድ ብዙም ተስፋ የሚጣልበት አይደለም ይላሉ፡፡
እርቅ ዘላቂነት የሚኖረው በመንግስታት መካከል ብቻ ሲካሄድ እንዳልሆነ የሚገልጹት ምሁሩ፤ዜጎች በሚፈጠረው እርቅ ውስጥ ተሳታፊ ሊሆኑና በአግባቡ ይቅር ሊባባሉ ይገባል ብለዋል። በጦርነቱ ቀጥተኛ ተጎጂ የሆኑት የአማራና አፋር ክልል ህዝቦችን ያገለለና እነሱ እንዲመክሩበት ያልተደረገ እርቅ፣ ከቂም በቀልና ቁርሾ የፀዳ ሊሆን አይችልም ሲሉም ይሞግታሉ፡፡
የፌደራል መንግስት ከተለያዩ አገራትና ተቋማት የሚደርስበትን ጫናና እጅ ጥምዘዛ ተቋቁሞ ቡድኑን በትጥቅ ትግል ካሸነፈና ድል ማግኘቱን ካረጋገጠ በኋላ ከህወሓት ጋር ለድርድር መቀመጡ ለዲፕሎማሲያዊ አካሄዱ የሚያስቆጥርለት ነጥብ እንዳለ ባይካድም፣ ከዜጎቹ ጋር ስለሚኖረው ሁኔታ ሊያስብበትና የጦርነቱ ሰለባ የሆኑ ዜጎቹን የድርድሩ አካል ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፤አሁንም መንግስት ከዜጎቹ ጋር በተለይም ከአማራና አፋር ክልል ህዝቦች ጋር ሊወያይና ሊመካከር እንደሚገባ በማሳሰብ፡፡
የወልቃይትና ራያ ጉዳይም በአገሪቱ ህግ መሰረት ይፈታል የሚለው ደግሞ ወደ ከፋ ችግር ሊያስገባ የሚችል በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል ብለዋል፤የፖለቲካ ምሁሩ፡፡
የሰላም ስምምነቱ የወገን እልቂትን የሚያስቆም በመሆኑ የሚደገፍ ነው ያሉት የኦፌኮ ሊቀመንበሩ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤በአገሪቱ ያለው ቀውስ እንዲቆም ግን ሁሉን አቀፍ የሆነ የሰላም ስምምነት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። የፌደራል መንግስቱ ከሁሉም ኃይሎች ጋር ሁሉን አቀፍ የሰላም ስምምነት ካላደረገ ወዴት እንደምንሄድ መተንበዩ አስቸጋሪ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ይህ በማይሆንበት ሁኔታ የተጠበቀው ሰላም ሊመጣ እንደማይችል ተናግረዋል።
መንግሥትና ህወኃት የተስማሙባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች፡-
የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት ማረጋገጥና የኢፌዲሪ ህገ-መንግስትን ማስከበር፤
ህወሓት ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈታ ስምምነት ላይ ተደርሷል። በዚህ መሰረትም ስምምነቱ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ ባሉ 30 ቀናት ውስጥ ቡድኑ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈታ የሚደረግ ሲሆን፤ ይህንን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግም የሁለቱ ወገን ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች አመቺ ቦታ መርጠው እንዲነጋገሩ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ስምምነቱ በተፈረመ አምስት ቀናት ውስጥ የሁለቱ ወገን ወታደራዊ አመራሮች የትጥቅ ማስፈታት ሂደት የሚመራበትን ዝርዝር አፈጻጸም በጋራ በማውጣት ተግባራዊ ስራዎች መስራት ይጀምራሉ።
የሁለቱ ወገን ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች በተገናኙ አስር ቀናት ውስጥ ህወሓት ያሉትን ሁሉንም የቡድንና ከባድ መሳሪያዎችን ለመከላከያ ሰራዊት ያስረክባል።
ስምምነቱ በተፈረመ በ7 ቀናት ውስጥ የፌደራል መንግስት መቀሌን ተረክቦ በከተማው ውስጥ እና ዙሪያ ሁሉንም አይነት የጦር መሳሪያ ያስፈታል።
በመሬት ላይ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የሕወሓት ተዋጊዎችን ከሰራዊቱ እንዲወጡ ለማድረግና መልሶ ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀል የሚያስችል ስራ ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል።
የጥይት ድምጽ በዘላቂነት እንዳይሰማ እና ጦርነቱ እንዲያበቃ የሚያስችል ዘላቂ የግጭት ማስወገድና የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በትግራይ ክልል ህገ-መንግስታዊ ስርዓትን ወደነበረበት ለመመለስ የሽግግር እርምጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ከስምምነት ተደርሷል። በአጭር ቀናት ውስጥ በትግራይ አሁን ያለው የህወሓት መዋቅር ፈርሶ የፌደራል  መንግስት የሚመራው የጊዜያዊ አስተዳደር ይቋቋማል። በሚዋቀረው ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥም የትግራይን ህዝብ የሚወክል አካል ይሳተፋል፡፡ የሚመሰረተው ጊዜያዊ አስተዳደር በሁሉም የትግራይ አካባቢዎች የማህበራዊ አገልግሎቶች በፍጥነት እንዲጀመሩ ሁኔታዎችን ያመቻቻል። ተግባራዊነታቸውንም ያረጋግጣል።
በሁለቱም ወገኖች በኩል የጥላቻ ፕሮፓጋንዳን ለማስቆም ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ህወሓት ያለ ፌደራል መንግስቱ እውቅና ከማንኛውም የውጪ አካል ጋር ግንኙነት ማድረግ ያቆማል። እንዲህ አይነት ተግባር የሚፈጽሙ ግለሰቦች ካሉ በሀገሪቱ ህግ መሰረት የሚጠየቁ ይሆናል።
የፌደራል መንግስት ህወሓትን ከአሸባሪነት መዝገብ ለማስወጣት የሚያስችል ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ስምምነት ላይ ተደርሷል።
አጨቃጫቂዎቹ የወልቃይትና የራያ ጉዳዮችም በአገሪቱ ህግ መሰረት የሚዳኙ መሆኑም በስምምነቱ ላይ ተጠቅሷል።
Read 11958 times