Print this page
Saturday, 05 November 2022 11:10

ለአጣዳፊ አደጋ ተዓምረኛ መፍትሄ ያስፈልጋል። ግን ጊዜያዊ ነው።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

    • በተዓምረኛ መፍትሄ የምናገኘውን እፎይታ በመጠቀም፣ ለወደፊት የሚያዛልቁ ትክክለኛ መርሆችንና ፍሬያማ መንገዶችን ከፈጠርን፣ ያማረ  ታሪክ መስራት እንችላለን።
    • በእሮሮ ብቻ ሕመሞችን መፈወስ የምንችል ከመሰለንስ?
    • ለአጣዳፊ አደጋዎች ሁልጊዜ ተዓምረኛ መፍትሔዎችን ለማግኘት የምንጠብቅ ከሆነስ?
    • “የችግርና የተዓምር ዑደት”፣ መጨረሻው እንደማያምር የሚያስተምር ነው- የሙሴና የተከታዮቹ ትረካ።
          

      ከብዙ ምስቅልቅና መከራ፣ ከእልፍ ውድመትና እልቂት በኋላ፣ ሰላም ወረደ። የሙሴ ተከታዮች፣ ከባርነት እንዲላቀቁ፣ ከግብፅ እንዲወጡ ፈርዖን ፈቅዷል። ከዚህ በኋላ ምን ዓይነት ችግር ሊፈጠር ይችላል? ችግርማ ሞልቶ ተርፎ። ለዚያውም እየተደራረበደ፣ ለዚያውም በየዓይነቱ!
ከባርነት ማምለጥ ሌላ፤ ወደ ነፃነት ሕይወት መድረስ ሌላ! ከክፉ የባርነት መከራ መላቀቅ ቀላል ጉዳይ ባይሆንም፣ ወደ ነፃነት ሕይወት መሸጋገር ግን፣ እጥፍ ድርብ ብቃትን ይጠይቃል (ማለትም፣… የአእምሮ፣ የአካልና የባሕርይ ብቃት!)።
ስደተኞቹ የሙሴ ተከታዮች ግን፣ ወደ ምኞታቸው ለመድረስ ይቅርና፣… በወጉ ለማምለጥም አስተማማኝ አቅም አልነበራቸውም። የሃሳብ፣ የተግባርና የመንፈስ ስንቅ አላዘጋጁም።
ከሁለት ከሦስት ቀን፣ ቢበዛ ከሳምንት ከሁለት ሳምንት በላይ የሚያስኬድ ስንቅ የላቸውም። ቦሃቃ በጨርቅ ሸክፈው፣ በጫንቃ የተሸከሙት ሊጥ ገና ሳይቦካ መንገድ ላይ ጋግረው ይበላሉ። ግን የጋገሩትን ቂጣ በልተው ከጨረሱ በኋላ፣ አውላላ በረሃ ውስጥ ምን ይውጣቸዋል? ደረቅ በረሃ ላይ ምን ይጠጣሉ?
ቀድመው አላሰቡበትም። አልተዘጋጁበትም። ከመዘዙ አላመለጡም። ቁራሽ እንጀራ አጥተው፣ አሳራቸውን በልተዋል። ጠብታ ውሃ ጠፍቶ፣ በመከራ ጽዋ ተቃጥለዋል።  
እንዲህም ሆኖ፣ ስህተታቸውን ተገንዝበው፣ ጉድለታቸውንም አስተውለው፣… ለወደፊት በቅጡ ለማሰብና ለማሰላሰል፣ መፍትሔ ለመሻትና መላ ለመዘየድ አልሞከሩም። ለረዥሙ የነፃነት ጉዞ የሚመጥን የአእምሮ ብቃትና የሃሳብ ስንቅ ለማሰናዳት አልጣሩም። በአካልና በመንፈስም ጭምር ለመዘጋጀት፣ “ቢያንስ ቢያንስ ከዛሬ ጀምረን በብርቱ መትጋት አለብን” ብለው አልወሰኑም።
ችግር በገጠማቸው ቁጥር መነጫነጭና ማጉረምረም ይጀምራሉ። የጥቃት ዘመቻ አፍጥጦ ሲመጣባቸው፣ ረሃብና ጥም ሲጠናባቸው፣… በእሮሮ ይጮኻሉ። “ምን ይሻላል?” ብሎ ማሰብ ግን የለም። እሮሮ በቂ አይደለም። መፍትሔ አያመጣም። እህስ? ሙሴ ላይ ቅሬታቸውን ያዘንቡበታል። ምሬታቸውን ያወርዱበታል። የሙሴ ወንድምና ረዳት የሆነው አሮን ላይም ያጉረመርማሉ።
ይሁን። መልካም። ስቃይ ቢበዛባቸው ነው ማልቀሳቸው። ቢጨንቃቸው ነው መጮኻቸው።
በፈረሶችና በሰረገሎች እየገሰገሰ የሚመጣ የፈርዖን ጦር፣ በጣም ያስፈራል። መሄጃ ያሳጣል። በተለይ ከወዲህ በኩል መደበቂያ የሌለው በረሃ፣ ከወዲያ በኩል መሻገሪያ የሌለው ሰፊ ባሕር የሆነባቸው ስደተኞች፣ ኃይለኛ ጦር ሲመጣባቸው፣ እጅግ ቢጨነቁ አይገርምም።
ምናለ እግራችንን በሰበረው ቢሉ አይደንቅም።
ረሃብና ጥምም ያማርራል፤ ተስፋ ያስቆርጣል። በተለይ ጭው ያለ አሸዋማ በረሃ ላይ፣ የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ ቀልጦ መቅረት፣ ከሞትም የስቃይ ሞት ነው።
በዚህ ሁሉ ጭንቀትና ስቃይ የተነሳ፣ ስደተኞቹ የሙሴ ተከታዮች እጅግ ቢማረሩ፣ አበዙት አያስብልም። ሙሴ ላይ እየተነጫነጩ የወቀሳ መዓት ቢጭኑበትም አይገርምም። ነገር ግን፣ ምሬትና ቅሬታ ብቻ መፍትሔ ይሆናል? እንደማይሆን በተደጋጋሚ በተግባር አይተዋል። አሁንም ግን እውነታውን አልተገነዘቡም። የየግላቸውን ሃላፊነት ለመውሰድ አልሞከሩም። በቃ፣ ሙሴን ካማረሩ በቂ መፍትሔ የሚሆን ይመስላቸዋል። ወይም ያስመስላሉ።
በግብፅ የባርነት ኑሮ ላይና በፈርዖን ግፍ ላይ ክፉኛ መማረራቸው፣ የተሟላ መፍትሔ ካልሆነላቸው፣ ሙሴና አሮን ላይ ማጉረምረምስ፣… እንዴት ያለ ተጨማሪ ጥረት፣ ምን ዓይነት ውጤት እንዲያመጣላቸው ፈልገው ይሆን?
የሦስት ቀን መንገድ ወደ በረሃማው ጠረፍ፣ ወደ ባሕር ዳርቻ ሄደው ሰፈሩ። ግን፣ ባሕሩን እንዴት እንደሚሻገሩ ማንም አያውቅም። አላሰቡበትም።
በዚህ መሃል፣ ነገሩ የከነከናቸው ግብፃውያን ፈርዖኑም ጭምር፣… “እስራኤላውያንን መልቀቅ አልነበረብንም” በሚል መንፈስ እንደገና ሃሳባቸው እየደፈረሰ፣ በስሜት መጦዝ ጀምረዋል።
“ልቀቀን” “አልለቅም” በሚለው የሙሴና የፈርዖን ውዝግብ የተነሳ፣ አገሪቱ በቅራኔና በቀውስ ተመሳቅላለች። በጦርነት የተተራመሰች አገር መስላለች። ኑሮ ተጎሳቁሏል። ረሃብና በሽታ በዝቷል። በየቤቱም ሞትና ሃዘን ገብቷል። ከዚህ ሁሉ አሳዛኝ ጥፋትና እልቂት በኋላ ነው፤ የእስራኤል ልጆች ከግብፅ እንዲወጡ ፈርዖን የፈቀደላቸው። እንዲያውም እንዲወጡ አጣድፏቸዋል። ብዙ ግብፃውያንም እንደዚያው። ሰላም ናፍቋቸዋልና።
በማግስቱ ግን፣ መፍቀድ አልነበረብንም በሚል ስሜት ተብሰለሰሉ። ብዙም ሳይቆይ ስሜታቸው ገነፈለ። ፈርዖን ወደ በርሃማው የባሕር ጠረፍ፣ በፈረሶችና በሰረገሎች ጦሩን አዘመተ።
የግብፅ ጦር በእልህና በቁጣ ገስግሶ እንደደረሰባቸው የእስራኤል ስደተኞች ከርቀት አይተዋል። ማምለጫ ግን አልታያቸውም። አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል። ከጀርባቸው ባሕር ነው። ከፊት ለፊት ደግሞ የማይገዳደሩት የፈርዖን ጦር እየመጣባቸው ነው።
ሙሴና አሮን ላይ አጉረመረሙ። “እጅግ ፈሩ። ወደ እግዚሄርም ጮሁ” ይላል ትረካው። ከዚያም ሙሴ ላይ ምሬታቸውን እንዳወረዱበት ትረካው ያስነብበናል - በጥበበኛ አገላለፅ። በሙሴ የተማረሩት ስደተኞች እንዲህ አሉ።
“በግብፅ ምድር መቃብር ጠፍቶ ነው በምድረ በዳ እንድንሞት ያወጣኸን?… ተወን፣… በምድረ በዳ ከምንሞት ለግብፃውያን ተገዢ ብንሆንላቸው ይሻለናል… ብለን በግብፅ ሳለን የነገርንህ ቃል ይህ አይደለምን?” አሉት።
አስገራሚ አገላለፅ ነው።
“ተናግረን ነበር! ብለን ነበር” በማለት ራሳቸውን ነፃ ለማውጣትና ሙሴን ለመውቀስ ፈልገዋል። እሺ። “በግብፅ ምድር መቃብር ጠፍቶ ነው?” የሚለው መራራ ስላቅስ?
ከመነሻውም ልታስገድለን ነው ሃሳብህ፤… ልታስጨርሰን ነው አላማህ። ታዲያ፣ እንደ ልብ ሰፋፊ መቃብር ልትሰጠን ለኛ ተቆርቁረህ ነው ወደ በረሃ ያመጣኸን? በግብፅ ምድር የመቃብር ቦታ ጠፍቶ ነው?...
ንግግራቸው፣… ወቀሳ ብቻ ሳይሆን ውንጀላም ነው። “ልታስፈጀን እንደፈለግህ መች ጠፋን!”… እያሉት ነውና። አዎ፣ አብዝተውታል። ከመስመር አልፈዋል።
ነገር ግን፣ አትርሱ። የፈርዖን ጦር ይጨፈጭፈናል ብለው ከምር ፈርተዋል፤ ተጨንቀዋል፤ ተስፋ ቆርጠዋል። “ከባርነት ኑሮ የሚያመልጡበት የነፃነት ጉዞ”፣… “በአጭር የመቀጨት ጉዞ” ሆኖ ታይቷቸዋል። ከድጡ ወደ ማጡ ለመውረድ፤ ከባርነት ወደ እልቂት ለመድረስ ነው ጥድፊያው?
ማማረራቸውና ሙሴን በወቀሳ መሸንቆልጣቸው አይደለም ስህተታቸው።
“አሁን ምን ይሻላል?” ብለው ለማሰብ አለመሞከራቸው ነው ጥፋታቸው።
ችግሮችን ሁሉ በሙሴ ላይ መጫንና መውቀስ፤ በአንዳች ተዓምር መፍትሔ አይሆንላቸውም። ከመዓት አያድናቸውም። ወይስ ያድናቸዋል?
አስገራሚው ነገር፣ ከፈርዖን ጦርና ሰይፍ ማምለጣቸው ነው። ለጊዜውም ቢሆን፤ መፍትሔ ለመሻትና መላ ለማበጀት ቅንጣት ታህል ሳይጥሩ፣… በተዓምር ከእልቂት ተረፉ።
ምናልባት ወደፊት፣ ስህተታቸውን ለማረምና ጉድለታቸውን ለማሟላት ይተጉ ይሆናል። አሁን ከመዓት ድነዋል። የንሥሐ “እድል” አግኝተዋል።
ወይስ፣…
“ይሄውና ያለ ሃሳብና ያለ ጥረት፣ በተዓምር ከእልቂት አምልጠናል። ወደፊትም፣ ማንኛውም ችግር ሲገጥመን፣ ወቀሳና ምሬት በቂ ነው” የሚል ስሜት ይለምድባቸው ይሆን?
ከትረካው እናያለን።
ከግል ወቀሳ፣ ወደ “ሕዝባዊ ጥያቄ”፣ ወደ አድማ!
እየገሰገሰ ከነበረው የፈርዖን ጦር ለትንሽ አምልጠዋል - በተዓምር። ባሕሩን ተሻግረዋል። ጭንቀታቸው ወደ ደስታ፣ እሮሯቸው ወደ እልልታ ተለወጠ። አብረው ዘመሩ።
“የአሮን እህት፣ ነብይ የሆነችው ማርያም፤ ከበሮ በእጇ አነሳች። ሴቶችም ሁሉ በከበሮና በዘፈን ከኋላዋ ተከተሏት”… ይላል ትረካው።
አሮን የሙሴ ወንድም ነው። ማሪያም የአሮን እህት ከሆነች፣ ለሙሴም እህቱ ናት። ይህም በሌላ ቦታ በትረካው ውስጥ ተጠቅሷል። ታዲያ፣ ለምን የአሮን እህት ተባለች? ዋናው ባለ ታሪክ ሙሴ ነው። ለምን “የሙሴ እህት” አልተባለችም? ለምን እንደሆነ ባይታወቅም እንኳ፤… ዋናው የትረካ ጅረት ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። ሙሴን ተከትለው ከግብፅ የወጡ እስራኤላውያን አሁን ተደስተዋል፤ ዘምረዋል፤ ዘፍነዋል።
ከዚያስ? ከዚህ በኋላ የሚመጣው የትረካ ቁምነገር፤ ሌላ ሳይሆን፤… አሁንም ተጨማሪ ቅሬታና ምሬት ነው።
ስደተኞቹ የሙሴ ተከታዮች፣ ምድረ በዳ ላይ የሚጠጡት ውሃ አጡ። “ሕዝቡም፤ ምን እንጠጣለን?” ብለው ሙሴ ላይ አጉረመረሙ ይላል ትረካው።
ይህን ተከትሎ የሚመጣው ቀጣዩ የትረካ ቁም ነገርም ሌላ አይደለም። እንደገና አሁንም ቅሬታና እሮሮ ነው - በረሃብ ሳቢያ።
እንዲያውም፣ በየፊናቸው ሲያማርሩና ሲያጉተመትሙ የነበሩ ቅሬታ አቅራቢዎች፣ አሁን ብዙ ሆነው ተሰባስበዋል። አባሪ ተባባሪ ሆነው፤ ለአድማ ተቧድነዋል። በሙሴና በአሮን ላይ ጣታቸውን ቀስረዋል።
አነጋገራቸው ሁሉ ተቀይሯል። ራሳቸውን እንደ ተወካይ መቁጠር ጀምረዋል።
“የሕዝብ ጥያቄዎችንና ቅሬታዎችን” ተሸክመው የሚያመጡ፣ “የብዙሃን ተቆርቋሪ” ሆነዋል።
“ይህን ማህበረሰብ ሁሉ በረሃብ ልትገድሉ፣ እኛን ወደዚህ ምድረ በዳ አውጥታችኋል” ብለው ሙሴንና አሮንን ወነጀሉ።
“በግብፅ ምድር ሳለን፤ በሥጋ ምንቸት አጠገብ ተቀምጠን እንጀራ ስንበላ ስንጠግብ ሳለን፤ በእግዚሄር እጅ ምነው በሞትን!” ብለው አማረሩ። ሙሴንና አሮንን ነቀፉ።
ወቀሳው በአምላክ ላይም ነው።
ሊገድለን ከፈለገ ከኖርንበት አገር ከግብፅ አውጥቶ፣ በረሃ ላይ አቧራ እየቃምን በረሃብ አሰቃይቶ ከሚገድለን፤… እዚያው የሥጋ ወጥ ሳይናፍቀን፣ የእንጀራ ጉርሻ ሳይርቀን፣… ያኔ በሞቀ ቤታችን ውስጥ ቢገድለን ይሻል ነበር እንደ ማለት ነው።
ያው እንደተለመደው፤ በጥበበኛ አገላለፅ፣ የቅኔ ዘይቤም ጨምረውበት፣ ምሬታቸውን ተናግረዋል። መፍትሔ ለማግኘትና መላ ለመፍጠር ግን አልሞከሩም። ጨርሶ በሃሳባቸው አልመጣም። በተዓምር መፍትሔ እንዲመጣላቸው ነው የሚጠብቁት? የሰማይ እንጀራ እንዲወርድላቸው፤ ከደመናው ክምር ውስጥ የሥጋ ወጥ እንዲጨለፍላቸው ነው የፈለጉት?
ቢሆን ነው። “እንጀራ ከሰማይ አዘንብላችኋለሁ” ይላል ትረካው። ለእለት ጉርስ የሚበቃቸውን እንጀራ እንዲለቅሙ፤… በስድስተኛው ቀን ግን፤ እጥፍ ያህል እንዲሰበስቡና ግማሹን ለነጋታው እንዲያስቀምጡ ተነገራቸው። በሰባተኛው ቀን እረፍት ይሆናል ተብለዋል። የዘነበውን እንጀራ መሰብሰብ፤ እንደስራ ተቆጥሯል።
ለማንኛውም፤ በተዓምር ከረሃብ የተረፉት በዚህ መንገድ እንደሆነ ትረካው ይገልፃል። ከሰማይ የሚዘንበው እንጀራ፣… እንደ ደቃቃ በረዶ፤ እንደ ቅርፊት፤ እንደ ጥራጥሬ ይመስላል ተብሏል። የማር ጣዕም እንዳለውም በትረካው ተጠቅሷል።
በእርግጥ፤ በዚህ ትረካ መሃል፤ በጨረፍታ የተጠቀሰ ሌላ መረጃ አለ። አመሻሽ ላይ የሥጋ ምግብ፤ ጠዋት ደግሞ እንጀራ ከሰማይ እንደሚመጣላቸው የሚገልፅ ዓረፍተ ነገር አለ (ምዕ 16፡8)። የዚሁ ምዕራፍ ጠቅላላ ትረካ ሲታይ ግን፤ ጠዋት የሚለቅሙት እንጀራ (መና) ላይ ብቻ ያተኮረ ነው። ስጋ አልመጣላቸውም።
የሆነ ሆኖ፣ “ሕዝቡን በረሃብ ልትገድሉ ወደ በረሀ አመጣችሁን” በሚል እሮሮ ተጀምሮ፤ ከሰማይ በሚዘንብ መና ነው የምዕራፉ ትረካ የሚገባደደው። እፎይ የሚያስብል ይመስላል።
ግን የእፎይታ ጊዜ የለም። እዚያው በዚያው፤ በሌላ ምሬት ወደ ሌላ የትረካ ምዕራፍ ይገባል። ስደተኞቹ በውሃ እጦት ደርቀዋል። ጉሮሯቸው ቢንቃቃም፣ ምሬታቸውን ከመግለፅ ግን አላገዳቸውም። ከዚያም በላይ እንጂ።
ከአድማ ወደ አመፅ ለመዝለል አፋፍ ላይ!
ከቅሬታ ወደ ውንጀላ የተሸጋገሩት የጀመሩት ቅሬታ አቅራቢዎች፣… ተቧድነው አልቀሩም። “ሕዝቡም ሙሴን ተጣሉት። የምንጠጣውን ውሃ ስጠን አሉት” ይላል ትረካው። ታዲያ እንዲሁ በደረቁ አይደለም የተተረከው። “ሕዝቡም በዚያ ስፍራ ውሃ ተጠሙ” ካለ በኋላ፣ እንዲህ ይላል።
“እኛንና ልጆቻችንን፤ ከብቶቻችንም በውሃ ጥም ልትገድል፤ ለምን ከግብፅ አወጣኸን?” በማለት ሙሴ ላይ አመረሩ።
እኛንስ ግደለን! እሺ። ግን፣ ልጆቻችንንም በውሃ ጥም ልትፈጅ ነው ያመጣኸን? ከብቶቻችንስ ምን በደሉ?
ነገሩ እየመረረ ነው። ቀደም ሲል፣ ቅሬታ አቅራቢዎች፣… ሙሴ ላይ ለአድማ ሲቧደኑ እንደነበሩ አይተናል። አሁን ደግሞ፣ “ሙሴን ተጣሉት” ተብሏል። ሙሴም ሁኔታቸው ገብቶታል።
“ሊገድሉኝ ተቃርበዋል” ብሎ ይናገራል። ወደ እግዚሄር ይጮሃል። እሱም በፊናው፣ የራሱን ቅሬታና አቤቱታ ያቀርባል።
ለጊዜው፣ አሁንም ተዓምረኛ መፍትሔ ይመጣ ይሆናል። ግን የነገሩ አዝማሚያ፣ የት ድረስ ያስኬዳል? እስከ መቼ ያዛልቃል? ነገሩ ተደጋገመ።
ቅሬታ አቅራቢዎች በጭንቀት እንደ ተበዳይ ምሬታቸውን ይደረድራሉ።
በአንዳች ተዓምር ከአጣዳፊ መከራ ይድናሉ።
ይሄ “የምሬትና የተዓምር ዑደት”፣ በዚህ ከቀጠለ እንጃ። መውጪያ የሌለው አዙሪት እንጂ፣… በጭራሽ የጤና አይመስልም።
በቅሬታ ከማማረር አልፈው፣ በቅኔ ወደ መወንጀል ተሸጋግረዋል። ለአድማ ከመቧደን አልፈው፣ በጥላቻ ስሜት ሙሴ ላይ ጥቃት ወደ መሰንዘር ተቃርበዋል።
አዎ፣… ሙሴ ከግብፅ እንዲወጡ አነሳስቶ መርቷቸዋል። ያለ ዝግጅት በተጀመረው ጉዞ  ብዙ መከራ ሲደርስባቸው፣ ሙሴ ላይ ማማረራቸውና ወቀሳ መሰንዘራቸው ተገቢ ነው።
ነገር ግን፣ ለነፃነት እንዲነሱ በጉልበት አላስገደዳቸውም።
በጉዞ ላይ፣ የመፍትሄ ሃሳብ እንዳያመጡና መላ እንዳይፈጥሩ በጊዜው አልከለከላቸውም።
እስካሁን ምንም ዓይነት ጥቃት አልፈፀመባቸውም።
ግን ሊገድሉት ተቃርበዋል።
የሆነስ ሆነና፣ በጥላቻ ስሜት ሙሴን ቢገድሉት፣ ምን የሚያገኙ መስሏቸው ይሆን? በዘፈቀ የጠሉትን ነገር ትተው ማምለጥ ማለት፣… ወደሚወዱት ነገር መድረስ ማለት እንዳልሆነኮ በተግባር አይተዋል። በጭፍን ስሜት የጠሉትን ነገር ማጥፋት ማለት፣ ለሚወዱት ነገር ሕይወት መዝራት ማለት እንዳልሆነ አሁንም አልገባቸውም? በጭፍን ጥላቻ ደም ማፍሰስ ማለት፣… እህል ውሃ እንደማይሆላቸው አልተገነዘቡም?
ለነገሩ፣ ባይገድሉትም እንኳ፣ ከምሬትና ከነቀፋ ባሻገር፣ የመፍትሔ ሃሳብ ለማመንጨትና የሚጨበጥ መላ ለመፍጠር አልጣሩም። የሙከራ ምልክት አልታየባቸውም። “የኛ ሃላፊነት አይደለም” ብለው ሃሳባቸውን እርግፍ አድርገው የጣሉት ይመስላል - በርቀት የወረወሩት።
ቅሬታና ወቀሳ ብቻ ደግሞ፣… በራሳቸው ጊዜ መልካም ለውጥን አያመጡም። መፍትሔ አይወልዱም። ፍሬ አይሰጡም።
የጠሉትን መሸሽ ማለት፣… መንገዳቸውን በትክክል ካልመረጡ በስተቀር፣ የሚወዱት ዘንድ መድረስ ማለት አይደለም።
የማምለጫ ፍጥነታቸው፣ የመድረሻ ግስጋሴ እንዲሆንላቸው፣ ገና ከመነሻው በውል ካላሰቡበት፣ ገና ከውጥኑ በጥንቃቄ ካልተዘጋጁበት፣… በረሃ ለበረሃ የመንከራተት አበሳ እንደሚያስከትልባቸው አልተገነዘቡም።
ለመሸሽ ሲሮጡ፣ ወደ ከፍታ ከመጓዝ ይልቅ፣ በዘፈቀደ እየተደናበሩ ቁልቁለቱን ከተንሸራተቱ፣… ከነባር ቦታቸው ቢያመልጡም እንኳ፣ ወደባሰ መከራ የመግባት ሩጫ ይሆንባቸዋል። ደግሞም በተግባር፣ መዘዙን በተደጋጋሚ አይተዋል። አሁንም ግን፣ ከስህተታቸው አልተማሩም። አዝማሚያቸው አያምርም። በጊዜ ሁነኛ መፍትሔ ካልተገኘ፣… አመፅና ትርምስ መፈጠሩ አይቀርም።
ሙሴ፣… ከአመፅና ከትርምስ የሚያድን መፍትሔ አላገኘም።
ፈርዖን ላይ ሲያማርሩ የነበሩ መከረኛ ስደተኞች፣ አሁን ሙሴ ላይ ያጉረመርማሉ። ማማረርን ሙያ አስመስለውታል።
እንዲህ ሲባል ግን፣ ሙሴና አሮን፣ ገና ከመነሻው በሃሳብና በተግባር የተሟላ የነፃነት ዝግጅት አድርገዋል ማለት አይደለም። የሃሳብ፣ የተግባርና የመንፈስ ስንቅ አሟልተዋል ወይም ለነፃነት ጉዞ በብቃት ተዘጋጅተዋል ማለት አይደለም። በጭራሽ። “ዮቶር” ሲመጣ፣ ለሙሴ ምን ዓይነት የመፍትሔ ሀሳቦችን እንደሚያቀርብ ለመመልከት እንሞክራለና።….

Read 3219 times