Saturday, 05 November 2022 11:24

“ስናሸንፍ አንደንፋ፤ ስንሸነፍ አንገት አንድፋ!”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 ከእለታት አንድ ቀን አንድ አዛውንት አባት  ለልጃቸው የሚከተለውን የቻይናዎች በሳል ምክር ለገሱት።
1. እቅድህ የዓመት ከሆነ እሩዝ ዝራ
2. እቅድህ የ5 ዓመት ከሆነ ባህርዛፍ ትከል
3. እቅድህ የዘለዓለም ከሆነ ልጅህን አስተምር
ያ ልጅ ይህን መሰረታዊ እውነት ይዞ አደገ። አዋቂ በሆነም ሰዓት  ለልጆቹ ሶስቱን ትምህርት አስተማረ። ልጆቹ ግን በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ጥያቄ ከማንሳት ወደ ኋላ አላሉም።
 አንደኛው ልጅ፤ “አባቴ ሆይ፤ ከሩዝ ይልቅ ጤፍ አይሻልምን?” ብሎ ጠየቀው።
አባትም፤ “ጤፍ የአገርህ፣ ሩዝ የሌላ ሀገር ነው፤ ሆኖም ወሳኙ ጉዳይህ ዘር መዝራት ነው።”
ልጅ፡- “አባቴ ሆይ፤ ባህርዛፍ ብዙ ሃብት ንብረት ነው ብዬ እቀበል ዘንድ ትመኝልኛለህን? ባህር ዛፍ የእኔ ነው ብዬ እንድወስደው እንደምን ወደድክ?”
አባት፡- “እውነት ነው ልጄ ባህር ዛፍንም ከውጪ አምጥተን ማጽደቅና መትከላችን ይታወቃል። ሆኖም የኛ ምድር እንዲፈቅደው አድርገን አላሳደግነውም፤ ዛሬ እንደ ሀብታችን አድርገን ኮርተንበታል” አሉት።
ልጅ፡- “አባቴ ሆይ፤ ሶስተኛው ምክርህ ከቀደሙት ሁለት ምክሮችህ በምን ይበልጣል?”
አባት፡- “ልጄ ሆይ፤ ምክር ተበላልጦ አያውቅም፤ ምክር ሁሉ እንደየ ወቅቱ ጠቃሚ ይሆናል። ዋናው ነገር የአንተ ወቅትንና ጊዜን ማወቅ ነው። ለማንኛውም ሶስተኛው ምክሬ ምንጊዜው እወቅ የሚል ነው፤ እወቅ ስልህ ተማር ማለቴ ነው። የማንኛውም ነገር ቁልፍ ትምህርት ነው። አንተ በተማርክ ቁጥር ሀገርህ በአንድ የተማረ ሰው ታድጋለች። ምኞትህ የበለጸገች ሀገር እንድትኖርህ ይሁን። አባቶቻችን ትምህርትህን ይግለጥልህ ብለው የሚመርቁህ ለዚህ ነበር። አሁንም የእኔ ምርቃት ትምህርትህን ይግለጥልህ የሚለው የሆነው ለዚህ ነው።”
ልጅ፡- “አባቴ ስለትምህርት የነገሩኝን ተረድቻለሁ። ትምህርቱን ተምሬ ግን ምን ጥቅም ላይ እንደማውለው ገና አልገባኝም” ሲል ጠየቃቸው።
አባት፡- “ልጄ ሆይ፤ አንዱ የትምህርት ጥቅም ከባላንጣህ ጋር መደራደሪያ ስልትን ማወቅ እንድትችል ዘዴ መፍጠሩ ነው። ስታሸንፍ አለመደንፋት፣ ስትሸነፍ አንገት አለመድፋት እንድትችል የሚያደርግህ ትምህርት ነው” ሲሉ አስረዱት ይባላል።
***
ድርድር ለአንድ ሀገር ያለው ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጠቀሜታ እጅግ ትልቅ ነው። ዋነኛው ቁምነገር ግን የሃይል ሚዛንን ማወቅ ነው። ድርድር ከኢኮኖሚዊ ጠቀሜታ ጋርም ውስጣዊ ትስስር አለው። ማንኛውም ከውጭ ሀገርም ሆነ ሀገር ውስጥ ካሉ ፖለቲካዊ ሃይሎች ጋር መንግስት የሚያደርገው ድርድር፤ ጥብቅ ጥናትና ግንዛቤ ማድረግ ያሻዋል የምንለው ለዚህ ነው!
በሀገራችን አያሌ ጦርነቶች ተደርገዋል፣ ብዙ ደም ፈሷል፣ ብዙ የህዝብ መስዋዕትነት ተከፍሏል። ለዚህ ውድ ዋጋ መንግስትም ከተጠያቂነት አያመልጥም። ከብዙ አገሮች ቀዳሚ የነበረችው አገራችን ኋላቀር እንድትሆን ካደረጓት ምክንያቶች አንዱ ጦርነት ነው። ጦርነት ከፖለቲካዊ ጠቀሜታው ይልቅ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ ያይላል። በትንሹ ለማየት ለጦርነት ዝግጅት እየተባለ “በእናት አገር ጥሪ” ስም የተከፈለው መስዋዕትነት ብቻ እንኳን ምን ያህል የአገሪቱን ህብለ ሰረሰር እንደሰበረው ለማየት የምንጃር ባላገር የተናገረውን ማውጠንጠን ይበቃል፡-
“እናትና አባቴን በጊዜ ቀብሬ
መንግስት እጦራለሁ አንጀቴን አስሬ!”
እዚህ ላይ የጥንቱን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን አነጋገር ዛሬ ለማስታወስ ስሞክር የበለጠ ሁኔታውን ለማየት ያድለናል። እንዲህ ነበር ያሉት፡
“የሰሜኑ ክፍለ ሀገራችን  ማንኳኳት የማይለየው በር ነው”
ዛሬም ላይ ቆመን ብናየው፤ የአባባሉ እውነታ ህያው መሆኑን መገንዘብ አያዳግተንም!
የሁልጊዜ ዜማችን፣ የሁልጊዜ ሙሾአችን “ጦርነት” ብቻ መሆኑ እጅግ ያሳዝናል። ከጦርነት ማግስት ስደት፣ ረሃብ፣ መፈናቀል፣ ድንኳንና መርዶ እንጂ የተረፈን ነገር አልነበረም። ያቃተን “ጦርነት ይውደም” ብለን መፈክር ማስገር ነው። አሁንስ “ጦርነት ይውደም” እንበል፤ መንግስትም ይህንን መፈክር ይስማ።
“ስናሸንፍ ከመደንፋት፣ ስንሸነፍ አንገት ከመድፋት” አባዜ ፈጣሪ ይጠብቀን!

Read 11803 times