Saturday, 05 November 2022 11:27

“የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ገና ያልተነካ ገበያ ነው”

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

   • የብሮከር ሥራ እጅግ ከባድ፣ ጥንቃቄ የሚፈለግ፣ የደንበኞችን ስጋት የሚያቃልል፣ በሙያተኞች የሚሰራ ትልቅ ዘርፍ ነው…
       • በምንም መልኩ የሚመጣን አደጋ ወደ ኢንሹራንስ መውሰድ የአዕምሮ ሰላምን ይሰጣል

       ወ/ሮ ጌጤነሽ ሃይለማሪያም “የጌጤነሽ ሀይለማሪያምና ብርሃን ተስፋዬ ጀነራል ኢንሹራንስ ብሮከርስ” ኩባንያ መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ ሲሆኑ ኩባንያቸው የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል  ምክንያት በማድረግ ፤ ከጥቅምት 5 ቀን 2015 እስከ ጥቅምት 26( ዛሬ ማለት ነው) የዘለቀ የ“ኢንሹራንስ ወር” ንቅናቄን አዘጋጅተው በርካታ ፋይዳ ያላቸው ስራዎችን ሰርተዋል፡፡ ለማህበረሰቡም ግንዛቤ ፈጥረዋል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በታዳጊ እድሜያቸው እንዴት ወደ ኢንሹራንስ ዘርፍ እንደገቡ ፤ በኢንሹራንስ ዘርፉ ስላሉ ተግዳሮቶች፤ የብሮከርስ ኩባንያቸውን እንዴት እንደመሰረቱና በተያያዥ የኢንሹራንስ ጉዳዮች ዙሪያ ከወ/ሮ ጌጤነሽ ጋር ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ እነሆ፤



           የዩኒቨርሲቲ ትምህርት አቋርጠው በኢትዮጵያ መድህን ድርጅት ሥራ መቀጠርዎን  ሰምቻለሁ፡፡ እንዴት ነበር የኢንሹራንስ ዘርፉን መርጠው በኢትዮጵያ መድህን ድርጅት የተቀጠሩት?
ኢትዮጵያ መድህን ድርጅት በጣም በሚገርም ሁኔታ፤በአጋጣሚው ነው የገባሁት፡፡ በወቅቱ ከፍተኛ የፖለቲካ ሽኩቻ የሚካሄድበት ነበር፡፡ እኛ ተማሪዎች ሥለነበርንና የተለያዩ ፓርቲዎች ስለነበሩ የግድ አንዱ ፓርቲ ውስጥ ገብተሸ መሳተፍ አለብሽ፡፡ በወቅቱ ገለልተኛና ነፃ ሆነሽ ለመንቀሳቀስ የሚፈቅድ ሁኔታ አልነበረም፡፡ በወቅቱ ማለትም በ1969 ዓ.ም ነው ወጣትነቱም የሁኔታዎችም ግፊት ሥለነበር ወደ ፖለቲካው አዳላሁ መሰለኝ፡፡ በዚህ ጊዜ ይከታተሉሻል- ምን እንደምትሰሪ ምን እንደምታደርጊ በተለይ እኛ ተማሪዎች ላይ ይደረግ የነበረው ክትትል በጣም ከፍተኛ ነበር፡፡ ይህ ክትትል ሲበዛ የግድ የመታወቂያ ወረቀት ማግኘት ነበረብኝ። መታወቂያ ወረቀት ለማግኘት ደግሞ ሥራ መፈለግ ነበረብኝ፡፡ በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያ አውጥቶ ስለነበር ሄጄ አመለከትኩ፡፡ ፈተናውን በጥሩ ሁኔታ አለፍኩ፡፡ በጣም በአጋጣሚ ነው ሥራ የጀመርኩት፡፡ አስቤ ይህን ልሥራ ብዬ ወስኜ አይደለም ስራ የጀመርኩት እንዲያውም ኢንሹራንስ የሚባል ነገር ስለመኖሩም አላውቅም ነበር፡፡
በምን የስራ ዘርፍ ተቀጠሩ?
ምን መሰለሽ… ጥሩ የትምህርት ዝግጅት ስለነበረኝ ፈተናውንም በጥሩ ሁኔታ ሥላለፍኩ ቀጥታ “አንደር ራይተር” ሆኜ ነው የተቀጠርኩት፡፡ ይህ ማለት ሰዎች ያቋቋሙት ድርጅት ቢጎዳብኝስ ብለው፤ በባህር ላይ የሚጓጓዝ ንብረት ያላቸው ወይም መኖሪያ ቤቴ ቢቃጠልስ ብለው፤ ፋብሪካዬ ቢወድምስ ብለው ስጋት ሲገባቸው መጥተው ኢንሹራንስ የሚገዙበት ክፍል ነው “አንደር ራይተር የሚባለው”፡፡ እኔም ስራዬ በቀጥታ ከደንበኞች ጋር ነው የሚያገናኘኝ። እርግጥ ስራውን ስንጀምር ስልጠና ወስደን በደንብ ተቀርፀን ነው። ረዘም ያለ ጊዜ ሥልጠና ያሰለጠኑንም ከውጪ የመጡ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከዚያ በኋላ ሥራውንም ወደድኩት፡፡ በዚህ ሁኔታ ከሰዎች ጋር ስገናኝ ሁልጊዜ አዳዲስ ነገሮችን ሳውቅና ሲገባኝ ይበልጥ ሥራውን እየወደድኩት ሄድኩኝ፡፡
ወደ አቋረጡት ትምህርት አልተመለሱም?
ወደ ትምህርት ከመመለሴ በፊት ወደ አስመራ ሄድኩኝ፡፡ እንዴት ሄድሽ ካልሽኝ ፤ በትዳር ምክንያት ነው የሄድኩት፡፡ ቶሎ ነው ወደ ትዳር የገባሁት፡፡ ባለቤቴ አስመራ ይሰራ ስለነበር ወደ አስመራ ከሄድኩ በኋላ ቀጥታ ወደ ትምህርት ተመለስኩና አስመራ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ ቢዝነስ አድሚንስትሬሽን ተምሬ ዲግሪዬን ካገኘሁ በኋላ ወደ መድህን ድርጅት ሥራዬ ተመለስኩኝ፡፡ ሥራዬን የቀጠልኩት አስመራ ባለው የመድህን ድርጅት ነው፡፡ ስራዬን እየሰራሁ እያለሁ በአጋጣሚ ባለቤቴን በአውሮፕላን አደጋ አጣሁ፡፡ ይህ አደጋ የደረሰው በተጋባን በጥቂት ጊዜ ውስጥ ቢሆንም ሁለት ሴት ልጆች ነበሩን። በጣም ትንንሽ ነበሩ፡፡ ልጆቼን ይዤ መመለስ ስለነበረብኝ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡
ከዚያ በኋላ በኢትዮጵያ መድህን ድርጅት በተለያዩ የስራ ክፍሎች ለምሳሌ በካሳ ክፍያ፤ በሀላፊነትም በበታች ሰራተኝነትም ሰርቻለሁ። ይህ ክፍል ሰዎች በንብረታቸው ላይ አደጋ ሲደርስ የገዙት ኢንሹራንስ ጉዳቱን እንዲሸፍን ፖሊሲው ይፈቅዳል አይፈቅድም የሚለውን ከኢንሹራንስ ህጉ በመነሳት የሚተረጎምበት ክፍል ነው፡፡ በቅንነትና በታማኝነት ደንበኞችንም መስሪያ ቤትሽንም የምታገለግይበት ፤ ራስሽንም በእውቀት የምታበለፅጊበት ክፍል ነው፡፡
እነዚህን እውቀቶች ውጪ ሄደሽም እንድትሰለጥኚ መድህን ድርጅት እድል ይሰጣል፡፡ በዚህ ድርጅት እየሰራሽ ለመሰልጠን፤ ለማወቅና ለመለወጥ ካልተጋሽ ተቀባይነት የለሽም፡፡ ለዚህ መድህን ድርጅትን አሁንም አመሰግነዋለሁ፡፡
ብቻ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ መድህን ድርጅት በተለያዩ ሀላፊነቶች ላይ ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡
“ጌጤነሽ ሀይለማሪያም እና ብርሃን ተስፋዬ ጀነራል ኢንሹራንስ ብሮከርስ” የተሰኘውን  የራስዎን ኩባንያ እንዴት ነበር ያቋቋሙት?
እኔ የራሴን ኩባንያ እንዳቋቁም መንገድ የሆነኝ ከደርግ ወድቀት በኋላ በተለይ በ1986 እና 1987 ዓ.ም አካባቢ ማሪንና አቪዮሽን ኢንሹራንስ የሚባል መጣ፡፡ ይህ እንግዲህ የባህርና የአየር ላይ ኢንሹራንስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የኢትዮጵያ መርከቦች ኢንሹራንስ የሚሰጥበት ክፍል ነው፡፡ እኔም ወደ እዚህ ክፍል ወደ ሀላፊነት መጣሁ፡፡ ወደዚህ ክፍል ስመጣ ታዲያ ቀጥታ ግንኙነታችን ውጪ ካሉ የጠለፋ ዋስትና ሰጪ ኩባንያዎች ጋር ሆነ፡፡ የጠለፋ ዋስትና ሰጪ ማለት እዚህ ያለው የኢንሹራንስ ኩባንያ የሚያስተዳድረው በጣም ብዙና ትልልቅ ነው፡፡ የሚሰበስበውም ገንዘብ በጣም ብዙ ነው፡፡ ለምሳሌ ለ1 ሚሊዮን ብር የህይወት ዋስትና ምናልባት በዓመት የሚሰበሰበው አምስት ወይም ስድስት ሺህ ብር ነው፡፡ ብዙዎች መድህን ሲገቡ ደግሞ ፕሪምየሙ እያነሳ ይሄዳል፡፡ ለምን በአንድ ጊዜ ብዙ ሰው አይሞትም ብዙ ጉዳት አይደርስም። ስለዚህ ኢንሹራንስ ሰጪው ብዙ የህዝብ ገንዘብ እጁ ላይ ሲኖር ራሱም ይሰጋል፡፡ በዚህ የተነሳ ወደ ጠለፋ ዋስትና ሰጪዎች ይልከዋል፡፡ የጠለፋ ዋስትና ሰጪዎች ማለትም ለአገር በቀል የኢንሹራንስ ኩባንያ ዋስ የሚሆኑበት ነው፡፡
ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መድህን ከውጪ እንደሚገባው ማለት ነው?
ትክክል! የኢትዮጵያ አየር መንገድ እዚህ ብዙ መድህን ይገባል፤ ግን ብዙ ንብረት ስላለው በውጭ የጠለፋ ዋስትና ሰጪዎች ኢንሹራንስ ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥም የጠለፋ ዋስትና ሰጪ ኩባንያ ያለ መስሎኝ ነበር፡፡ የለም እንዴ?
አለ እንጂ! የኢትዮጵያ ጠለፋ ዋስትና ድርጅት (Ethiopian Reinsurance Cooperation) የሚባል አለ፡፡ የሆነ ሆኖ የጠለፋ ሰጪዎች ዋስትና ውስጥ በሀላፊነት መምጣቴ ኤክስፖዠሬን አሰፋልኝ፡፡ ይህ ማለት ስራዬ የሚያገናኘኝ ከውጪ ብሮከሮች ጋር ሆነ ማለት ነው፡፡ በውጪ አገር ውል ገቢውና ውል ሰጭው በብሮከር ካልሆነ በቀጥታ አይገናኙም፡፡ ይህ ህግም ነው፡፡ ይህ እንግዲህ የራሴን ኩባንያ እንድመሰርት አነሳሳኝ፡፡
ለምን ካልሽኝ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ኢንሹራን የገባ ሰው ጉዳት ሲደርስበት ክፍያ ላይ ብዙ ውዝግብ አለ፡፡ ዋስትና ሰጪውም ስለ ፖሊሲው ስላለው ሁኔታ በደንብ አያስረዳም፤ ዋስትና ገቢውም ጊዜ ስለሌለው ቶሎ ቶሎ ብሎ ፖሊሲውን ይዞ ይሄዳል እንጂ ተረጋግቶ፤ “እንዴት ነው ምንድነው?” አይልም፡፡ ችግርና ውዝግብ የሚመጣው አደጋ ሲከሰት ነው፡፡
ይሄ ነገር በውስጤ ስላለ፤ሁለተኛ ከሰዎች ጋር መስራቴ አድማሴን ስላሰፋልኝ ይህን ነገር እኔ ብሰራ- ብሮከር ብሆን ይህን ውዝግብ በመጠኑም ልቀርፍ እችላለሁ በማለት የአዕምሮ ዝግጅት ማድረግና በውጪ ሀገር ካሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ስፃፃፍ ጥሩ ግብአቶች ይሰጡኝ ጀመር-ከዚያ በኋላ ወሰንኩኝ ፡፡ ከዚህ በኋላ ተቀጥሬ መስራት አልችልም አልኩኝ፡፡
ይህንን ስወስን ምንም ኖሮኝ አይደለም፡፡ እኔ ብሮከር ድርጅት ብሆን አሁን ከማገኘው የወር ደመወዝ በታች አላገኝም ብዬ ወስኜ፤ በ1989 ዓ.ም መጨረሻ “ጀነራል ኢንሹራንስ ብሮከር” የተሰኘውን ድርጅቴን አቋቋምኩ፡፡ እነሆ 25 ዓመት ሞላው ማለት ነው፡፡ የዛን ጊዜ የብሮከር ፈቃድ ለማውጣት ከባድ ነበር፡፡ በቀላሉ አይገኝም፡፡ የስራ ልምድ የትምህርት ዝግጅት፤ በስራ ዘመንሽ የሰራሽባቸው ሀላፊነቶች ሁሉ ይፈተሻሉ፡፡ ያን ጊዜ ዘርፉ አዲስ ስለነበር ብሄራዊ ባንክ ነበር ፈቃድ የሚሰጠው፡፡ ሂደቱ ጠንካራ ነው፡፡ ጥቂት ጊዜ ቢወስድብኝም ፈቃዴን አግኝቼ በ1990 ዓ.ም ወደ ስራ ገባሁ፡፡
እስኪ ስለብሮከር የስራ ባህሪ ትንሽ ያጫውቱኝ አንዳንዶች ብሮከር የሚለውን ቃል ብቻ በማየት በቀጥታ ከድለላ ሥራ ጋር ያገናኙታል?
በጭራሽ፤ ከድለላ ጋር አይገናኝም፤ አይመሳሰልምም፡፡
ምን መሰለሽ … ብሮከር የሚለው ቃል በአማርኛ ድለላ የሚለው ትርጉም ስለተሰጠው ነው ሰዎች የድለላ ስራ ነው የሚሉት። አንደኛ ሥራው ትልቅ አቅም ባላቸው ሙያተኞች የሚሰራ ነው። ቢያንስ ስራውን ለመስራት ዲግሪ ሊኖርሽ ይገባል። ወይም ደግሞ በውጪ ያሉ ቻርተርድ የሆኑ ልክ ለንደን አገር እንዳለው አንድ ትልቅ ኩባንያ በዘርፉ ሰርቲፍኬት ልታገኚ ይገባል። ወይም አሜሪካን አገር ኖማ የሚባል በህይወት ኢንሹራንስ ላይ የሚሰጥ ዲፕሎማ አለ። እነዚህን ካላገኘሽ ብሮከር መሆን አትችይም። ወይም በስራ ዘመንሽ የካሳ ክፍያ ክፍል፤ ውል ክፍልና ከፍተኛ ሆኑ የሥራ ዘርፎች ላይ መስራት አለብሽ።
በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ብሮከር ሥራው ምንድን ነው?
እኛ ደንበኛውን (አገልግሎት ፈላጊውን) ነው የምንወክለው። አገልግሎት የሚፈልግ አንድ ተቋም ይኖራል። ያ ተቋም ምን አይነት የመድህን ፍላጎት እንዳላው እናያለን። ለምሳሌ ፋብሪካ ቢሆን ያ ፋብሪካ በዋናነት ሊጋለጥ የሚችልባቸው አደጋዎች ምን ምን ናቸው? የእሳት አደጋ (ከውጪ የሚመጣ ወይም ከውስጥ የሚነሳ)፣ ማሽነሪዎች በጉዳት ሊሰበሩ ይችላል፤ የስርቆት፣ የመብረቅ አደጋ፣ በፖለቲካ አለመረጋጋ ወዘተ… የሚለውን እንለያለን። በነገራችን ላይ ሀገር ሰላም በነበረበት ጊዜ በፖለቲካ አለመረጋጋት፣ በህዝብ አመጽ የሚለው በፖሊሲው አይታቀፍም ነበር። አሁን አሁን ነው የተጀመረው። በውጪ አገር በተለይ በአልቃይዳ የኒውዮርክ መንታ የቢዝነስ ህንፃዎች በሽብር ሲወድሙና “ቴሬሪዝም” የሚለው ሲመጣ ነው መታሰብ የጀመረው፡፡ ብቻ እነዚህን ሁሉ ከደንበኛው ፍላጎት አንፃር እንቃኛለን፡፡ በምንም መልኩ የሚመጣን አደጋ ወደ ኢንሹራንስ መውሰድ ከምንም በላይ የአዕምሮ ሰላምን ይሰጣል፡፡ የሆነው ሆኖ ለዚህኛው ንብረትህ ይህን ኢንሹራንስ ብትገባ የተሻለ ነው። ይሄኛው የኢንሹራንስ ኩባንያ ይበልጥ የተሻለ ነው ብለን ከነምክንያታችን እናማክረዋለን። ንብረቱ ማለትም የፋብሪካው የማሽነሪዎቹ፣ የሰራተኛው ሁሉ ምን ያህል ያወጣል ብለን ገማች እንልካለን። በአጠቃላይ የዛን ፋብሪካ ባለቤት ሙሉ በሙሉ በማማከር “ስጋቶቼ እነዚህ ናቸው” ብሎ እንዲያውቅ ነው የምናደርገው። ይህን ካወቀ በኋላ ዋጋ ማውጣት ግድ ስለሆነ እንደ ድርጅቱ ጥንካሬና የሀብት መጠን ድርጅቱን ሊመጥኑ ከሚችሉ ኩባንያዎች ጋር እናወዳድራለን።
አገልግሎት ሰጪዎቹ (የኢንሹራንስ ተቋማቱን) የድርጅት አወቃቀር፣ የፋይናንስ አቅም፣  የጠለፋ ዋስትና መግባት አለመግባታቸውን ሁሉ እናወዳድራለን። የማኔጅነምቱን የተግባቦት አቅምና የሰራተኞቻቸውን ትጋት ሁሉ አይተን ነው፣ ለደንበኛችን ይህ የኢንሹራንስ ተቋም የተሻለ ነው ብለን የምናስገባው። እነዚህን ሁሉ እንደ ኢንሹራንስ ብሮከር ተጠንቅቀን ካልሰራን ተጠያቂ ነን። ይሄ ማለት በደንብ ባለማማከር፣ የውሸት መረጃ በመስጠት ጥንቃቄ ባለማድረጌ ይህን ያህል ጥፋት አደርሳለሁ ተጣያቂ ነኝ ብለን ነው የምንሰራው። ለፈቃድ ሰጪውም ክፍል የገበያችንን ሶስት እጥፍ ፖሊሲ ማቅረብ አለብን። የብሮከር ስራ ከዚህም በላይ እጅግ ከባድ ጥንቃቄ ሚፈልግ የደንበኞችን ስጋት የሚያቃልል በሙያተኞች የሚሰራ ትልቅ ዘርፍ ነው። እኛም ያለፉትን 25 ዓመታ በትንቃቄና በታማኝነት ነው ስንሰራ የኖርነው።
የኢንሹራንስ ዘርፍ ረጅም ዓመት ያስቆጠረ ቢሆንም ማህበረሰቡ ስለ ኢንሹራንስ ያለው ግንዛቤ አናሳ ነው ይባላል። ለምንድን ነው በአገልግሎት ሰጪውና በህብረተሰቡ መካከል ያለው ግንኙነት የተራራቀው? ለምንስ ነው በዚህ ልክ ህብረተሰቡ ግንዛቤ ያልጨበጠው ይላሉ?
በመጀመሪያ ደረጃ ሃላፊነቱም ሆነ ተጠያቂነቱ የሚመጣው ከእኛ ነው ብዬ አምናሁ። አየሽ ይህን ኢንዱስትሪ ለማሳደግ ብዙውን የህብረተሰብ ክፍል ስለ ኢንሹራንስ እንዲያውቅና ኢንዲገነዘብ ማድረግ አለብን። ህዝቡ ስለ ኢንሹራስ እውቀት ታጥቆና አምኖ ሁሉም ኢንሹራንስ እዲገባ ቢደረግ፣ ትልቅ ገበያና ፋይናንስ ያለበት ዘርፍ ነው። ገና ያልተነካ ገበያ ነው። አዲስ አበባ ውስጥ በየጊዜው ግንባታ ይካሄዳል ግን አብዛኞቹ ቤቶች ኢንሹራንስ የላቸውም። በሪል እስት፣ በግለሰብ፣ በህንጻዎች ግንባታ ብዙ እየተሰራ ነው፤ ግን ስንቶቹ ኢንሹራንስ አላቸው ብትይ፣ አብዛኞቹ የላቸውም።
ባለንብረቶቹ ኢንሹራንስ እንዲገቡ የሚያስገድድ ህግ የለም?
የለም! አሁን ገና ጥሩ ነገር አስታወሽኝ። አየሽ ኢንዱስትሪው በጋራ ተባብሮ ጥናትና ምርምር ተደርጎ ወደ መንግስት ቢላክና ክትትል ቢደረግ፣ ትልቅ ውጤት ይመጣ ነበር። ለህይወት፣ ለቤት፣ ለንብረት ኢንሹራንስ ቢገባ ያለው ጥቅም ከመንግስት አንፃር፣ ከቤተሰብ አንፃር፣ ከባለንብረቱ አንጻርና ዘርፉን ከማሳደግ አኳያ ቢገመገም ትልቅ ለውጥ ያመጣ ነበር። ይህ ግን አልተሰራበትም። ይህንን መስራያ ለብን እንደ ኢንዱስትሪ እኛ ነን። አብሮ በጋራ ቆሞ ለመስራት ራዕይ ያስፈልጋል። ያንን አርቀን አልተመለከትነውም።
እናንተ 25ኛ ዓመታችሁን ምክንያት በማድረግ አንድ ኢኒሼቲቭ ወስዳችሁ ከትቅምት 5-26 የሚቆይ የ”ኢንሹራንስ ወር” በማዘጋጀት ወሩን ሙሉ ስለ ኢንሹራንስ እንዲወራ በማድረግ ማህበረሰቡም ሆነ እኛ ጋዜጠኞች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር እየሰራችሁ ነው። እስኪ በዚህ ወር ምን ምን ቁምነገሮች ተሰሩ?
ጄነራል ኢንሹራንስ ብሮከርስ 25 ዓመት እንደሞላው ሳስብ በጣም ነው የገረመኝ። እውነት ለመናገር ምንም እንኳን ስራው ከባድ ቢሆንም፣ የስራ ትንሽ ባይኖረውም፣ እንኳን 25 ዓመት 25 ወር የሆነው አይመስለኝም። ነገር ግን 25 ዓመት ደግሞ ሩብ ክፍለ ዘመን ማለት ነው። ለዚህ ጊዜ መብቃት በራሱ ትልቅ ነገር ነውና በቁም ነገር ብናሳልፈው ብለን አሰብንና፣ ይሄው ወሩን ሙሉ ስለ ኢንሹራንስ ብዙ ነገር አድርገናል። የዘርፉን ችግሮች በተመለከተ ጥናቶች ተሰርተው ለውይይት ቀርበዋል። የዘርፉ ተዋንያን እርስ በእርስ ለመቀራረብና ለመነጋገር ዕድል ተፈጥሯል። ፖሊሲዎቹና አሰራሮቹ በሚሻሻሉበት ሁኔታ ላይ ተነጋግረናል። በሬድዮ በቴሌቪዥን በኦንላይን ሚድያዎች እየቀረብን ስለ ኢንሹራንስ ብዙ ነገሮችን በመግለፅ ግንዛቤ ለመፍጠር ሞክረናል። ብቻ በርካታ ውጤታማ ስራዎች ሰርተናል ብዬ ነው የማስበው። አየሽ ኢንሹራንስ ትልቅ ኢንዱስትሪ ሆኖ ባንክ ላይ የተለጠፈ ነው። ነገር ግን የራሱ ኮሚሽን ተቋቁሞለት በዚያ ኮሚሽን ራሱን ችሎ የሚተዳደርበት መንገድ እንዲፈጠር ጥያቄ ቀርቦ ይህንንም በትልቅ አጀንዳነት ወስደን እየሰራንበት ነው። በአጠቃላይ ወሩ ብዙ ቁም ነገሮች ተሰርተውበታል። ዛሬ ምሽት በምስጋናና ለስራው አስተዋፅኦ ያደረጉትን እውቅና በመስጠት ይጠናቀቃል።
እንደፈጣሪ ፈቃድ  ብዙ ለመስራት እያሰብን ነው። አሁን በኢንሹራንስ ወሩ ምክንያት መቀራረቡም መነጋገሩም ስለተፈጠረ ተቋርጦ የነበረውንና ለ7 ዓመታት በሸገር ራዲዮ ስለ ኢንሹራንስ ግንዛቤ ለመፍጠር ሲተላለፍ የነበረውንና ደጋፊ በማጣት ትተነው የነበረውን “ተገን” የተሰኘውን የሬዲዮ ፕሮግራማችንንም እንጀምረዋለን።  የኢንሹራንስ ወሩም በጥሩ ሁኔታ የሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ እየተነጋገርን ነው፡፡ በአጠቃላይ የኢንሹራንስ ወሩ ትልቅ ንቅናቄ የተፈጠረበት፤ ትልቅ ግንዛቤ የተሰራበት፤ የዘርፉ ተግዳሮቶች ተለይተው የወጡበት፤ የዘርፉ ተዋንያን ተቀራርበው  የተወያዩበትና የመፍትሄ አቅጣጫዎች የተቀመጡበት ስለሆነ ኢኒሼቲቩን በመውሰዳችን በጣም ደስ ይለናል። ይህንን ስናስብ ይመለከተናል ብለው አብረውን የሰሩ ተቋማትንም ሆነ የሚዲያ አካላትን በእጅጉ እናመሰግናለን።


Read 11866 times