Print this page
Saturday, 05 November 2022 11:31

“የእኔማ ዠርጋዳ...”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

  “--እሺ ቆይ አየርላንድ ምን አደረግናት! (ኸረ የሰው ስም አይደለም! ሀገር ነች፡፡) አማሪካን ምን አደረግናት!.... አውሮፓ ህብረት የሚባሉትን ምን አደረግናቸው! ይፈቀድልንና አንድ ነገር እንበል...ክፉ የሚያስቡብን ሁሉ ጦሳችንን ይዘው ጥርግ ይበሉ! (አሀ...በሆዳችን ይዘን እንፈንዳ እንዴ!)---”
        
        እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው... አሁንም ማታ፣ ማታ “ለአንቺም ጠጪ ለእኔም አምጪ፣” የምትሉ ወገኖች... ጥያቄ ቢጤ ነው፡፡ እነኛ እያሳሳቁ ልክ ልካችንን የሚያጠጡን አዝማሪዎች አሉ ወይስ ዲጂታላይዝድ ሆነዋል! ቂ...ቂ...ቂ... የምር ግን ይቺ ዲጂታላይዝድ የሚሏት ነገር ሁሉ ቦታ ብቅ እያለች...አለ አይደል...ጦጣ ልንሆን ምንም አልቀረን፡፡ ሀሳብ አለን...መላ ያጣ ባህሪያችን ዲጂታላይዝድ ይሁንልንማ!
ኮሚክ እኮ ነው፣ የአዝማሪ ግጥም እንደ ኦፊሺያል ባዮግራፊ የሚሉት አይነት የምናደርግ አንጠፋም፡፡ “ስማ ስለእኔ ምን፣ ምን አይነት ግጥሞች እንደሚገጠሙ ሂድና እንትን ውስኪ ቤት ጠይቅ...‘የእኔማ ዠርጋዳ’ ተብሎ የሚዘፈንልኝ እኮ ነኝ! እናላችሁ... ዘንድሮ መአት አይነት አዝማሪነት አለ አይደል...እና በአዝማሪ ሙገሳ እሱ ደረታችንን የምንነፋ አንጠፋም። ቆይማ፣ ቆይማ...“አንጠፋም” ሳይሆን እንክት አድርገን አለን ለማለት ነው፡፡
አዝማሪ ማለት እኮ የግድ ማሲንቆ አንግቦ በየመዝናኛ ቦታው የሚዘፍነው ብቻ አይደለም። አሀ...ነጭ ነጯን መነጋገር ነዋ! (ስሙኝማ...‘ነጭ ነጯን መነጋገር’ የሚሉት ነገር ይብራራልንማ! ‘እውነትን’ ለመግለጽ “ነጭ” ቀለም የተመረጠው ያው የፈረንጅ ‘ተንኮል’ ነው አይደል! አሀ..ልክ ነዋ! ስንት ቀለም እያለ ‘ነጭ’ እውነትን ለመግለጫነት የተመረጠው በተዘዋዋሪ የሆነ ነገር ሊሉን ነው! “ዳውን ዊዝ ተንኮሊዝም!” ቂ...ቂ..ቂ... ዘንድሮ እኮ ‘የሴራ ፖለቲካ’ ምናምን የሚባለውን ነገር ከምንም ነገር ውስጥ መምዘዝ ይቻላል ለማለት ያህል ነው፡፡)
እናላችሁ... ዘንድሮ ነገርዬውን ሁሉ አስቸጋሪ ካደረጉት መካከል አንዱ ማሲንቆ የማናነግብ አዝማሪዎች መብዛታችን ነው፡፡ ሀቅ፣ ሀቋን መነጋገር ነዋ! እንበልና በሆነ ስብሰባ ላይ አለቅየው መክፈቻ ምናምን ነገር ካወሩ በኋላ ሌላ አስር ሰው ያህል አስተያየት ሰጥቷል፡፡ እናማ... አስራ አንደኛው ሰው ሊናገር እድል ይሰጠዋል፡፡ ያው የተለመደውን መግቢያ፣ መቅድም ምናምን ከደረደረ በኋላ “በእውነቱ እስካሁን የተናገሩት ሰዎች ባሉት ላይ የምጨምረው ነገር የለኝም።” ታዲያ ማን እጅህን አውጣ አለው! እጁን ለማውጣቱማ ምክንያት አለው፡፡
“አሁን መናገር የምፈለገው በእውነቱ ዋና ሥራ አስኪያጁ ያደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ በእውነቱ ውስጤን ጠልቆ ነው የተሰማኝ፡፡” በህግ አምላክ! እሳቸውም ሊታዘቡህ ይችላሉ። “በእውነቱ አሁን ቤቱን የምጠይቀው አንድ ጊዜ ሞቅ ባለ ጭብጨባ ለሥራ አስኪያጃችን ያለንን አድናቆት ብንገልጽ!” እናላችሁ ገና ደረጃ ያልወጣለት አዝማሪነት ይሏችኋል ይሄ ነው። ክቡር እሳቸው እኮ ሠራተኞቹ በስብሰባው በመገኘታቸው አመስግነው፣ “መልካም ስብሰባ እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ፣” ብለው ነው ቁጭ ያሉት፡፡ ግን እመኑኝ አዳራሹ በጭብጨባ ይናጋል፡፡ የማሲንቆ-አልባ አዝማሪዎች ክፋት ማነካካታቸው! በማናምንበት ማጨብጨብ ማለት መነካካት ማለት አይደል!
ደግሞላችሁ የሚዲያ አዝማሪ አለ፡፡ ልከ ነዋ...ባለስልጣንዬው የሆነ ትልቅ ፋብሪከ መርቀው ሲከፍቱ ሊሆን ይችላል፡፡ እናላችሁ የአምስት ደቂቃ ፊልም ቢለቀቅ አራት ተኩሉ እሳቸውን ነው የሚያሳየው፡፡ ፋብሪካውስ!? ‘ብሬኪንግ ኒውስ’ የሚሆነው ትልቅ ፋብሪካ መመረቁ ሳይሆን እሳቸው መመረቃቸው ነው፡፡ ማሲንቆ ኖረም አልኖርም የእኔ ቢጤውን ሁሉ...አለ አይደል... “የእኔማ ዠርጋዳ” ማለት ይቻላል ለማለት ነው፡፡
ስሙኝማ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... ጉልበተኛ በዛብን እኮ! ኸረ አንድዬ አንድ ነገር በለን፡፡ በየደረጃው ያለ ጉልበተኛ አላስተነፍስ አለና፡፡ ጉልበተኛ ሀገሮች፣ ጉልበተኛ ፖለቲከኞች፣ ጉልበተኛ ዩቲዩበሮች፣ ጉልበተኛ ሚዲያዎች፣ ጉልበተኛ ሚጢጢ የፈረንጅ ባለስልጣናትና እንደፈረንጅ የሚያደርጋቸው ሁሉ! (ወይም ‘ወዘተ.’ ማለት ይቻላል፡፡ ጊዜና ቀለም ለመቆጠብ ያህል፡፡)
ስሙኝማ...በቀደም ጄፍ ፒርስ ለካናዳ ፓርላማ አባላት ስለኢትዮጵያ እውነት እውነቷን ሲያስረዳ እንዴት አፍ አፉን ብለው እንዳስቆሙት አያችሁልኝማ! ጭራሽ እኮ “አቋርጠው! አቋርጠው!” ሲሉ ሁሉ ነበር፡፡ (አንድ ዘመን ላይ ፊልም አልጥም ሲለን “ቁረጠው! ቁረጠው!” እያልን እንጮህ እንደነበረው፡፡) የሚገርም ነገር እኮ ነው፡፡ በየቦታው “እንደዚህ ሁኑ! እንደዛ ሁኑ!” የሚሉን ምን አይነት ሰዎች እንደሆኑ አያችሁልኝማ! እነሱ እኮ በየግልና በየቡድን ምክንያታቸው እውነትን መፈለግ ሳይሆን አስቀድመው የወሰኑትን አስጨብጭበው... ምን እነኚህ..... ‘ላጠጣቸው’ ነበር ግን ተውኩት! አሁንማ ኤለን መሰክ ትዊተርን እንደልባችሁ ልትጠቀሙ ትችላላችሁ ይላል ስለሚባል፣ ያኔ የምይዘው ወገብ ባይኖረኝም ወገቡን በመያዝ የሚያግዘኝ ፈልጌ አጠጣቸዋለሁ! ፈረንጅ እንዲህ ነው፡፡ በነገራችን ላይ አንዳንድ ቀኖች አለ አይደል...ፈረንጅ የእንትን ሰፈር ነገረኛ ባልና ሚስት አይነት የሚያደርገው አሁን ዘግይቶ ያመጣው ባህሪይ ሳይሆን የነበረ ነው፡፡ ነገርዬው እኛ ላይ በግልጽና በአደባባይ ዘግይቶ ስለደረሰ ነው እንጂ ያው ናቸው፡፡
‘ሂስትሪ’ ምናምን እንባባልና ስሙልኝማ...የተባበሩት መንግሥታት ምናምን የሚሉትን ተዉት፡፡ ደጃዝማች ከበደ ተሰማ “የታሪክ ማስታወሻ” በምትል መጽሐፋቸው ላይ ያሏትን እዩልኝማ...  “ያለፈው የጄኔቭ ማህበርተኝነታችን የኃይለኛውን ሀሳብ ነው እንጂ የደገፈው ተጠቂውን እንደማህበሩ ውል ሊረዳው አልቻለም፡፡ ስለዚህ አሁን ማህበርተኛ ነን፡፡ ነገር ግን የተባበረ ኃይልና ስልጣኔ ኖሮን ራስን የመቻል መልክን ካላሳየን ማህበርተኛ በመሆናችን ብቻ ረዳት አናገኝም...” እናላችሁ፣ ነገርየው አሁንም ያው ነው ለማለት ነው። ከዋሽንግተን እስከ ብረስልስ ጉልበተኞቹ መከራችን ሲያሳዩን ከረሙሳ!
እሺ ቆይ አየርላንድ ምን አደረግናት! (ኸረ የሰው ስም አይደለም! ሀገር ነች፡፡)  አማሪካን ምን አደረግናት!....አውሮፓ ህብረት የሚባሉትን ምን አደረግናቸው! ይፈቀድልንና አንድ ነገር እንበል...ክፉ የሚያስቡብን ሁሉ ጦሳችንን ይዘው ጥርግ ይበሉ! (አሀ...በሆዳችን ይዘን እንፈንዳ እንዴ!) ደጃዝማች ከበደ ተሰማ እንዲህ ይላሉ...“እኛና ኢትጵያውያንን ወዶና አክብሮ ነው እንጂ መስማማት የሚገኘው ንቆና አዋርዶ አይደለም፡፡”
ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... ከእንግዲህ “እሱ እኮ ፈረንጅ ነው፣” ከተባላችሁ “እሱ እኮ ተንኮለኛ ነው!” ማለት ሊሆን ስለሚችል አስተያየቱን የሚሰጠውን ሰው “እንደእሱ ስትል ምን ማለትህ ነው!” ብላችሁ ጠይቁ፡፡ ቀላል ተንኮል ነው እንዴ! ‘ታዛቢ’ ሆነው ገብተው ‘ዋነኛ ባለጉዳይ’ መሆን እኮ፣ አለ አይደል...ሚዜ ሆኖ መጥቶ ሙሽሪትን መንጠቅ በሉት! እኔ የምለው... እኒህ ሊንዳ ምናምን የሚሉዋቸው ሴትዮ የግል ጉዳያቸውን በቦተሊካው አያምጡብና! አሀ...እኛ ስንት ጉዳይ እያለብን ስለሰው ‘ምራት’ ምን አገባን! ቂ...ቂ...ቂ....
እና ጉልበተኛ በዛብን፡፡ የጥበቃ ጉልበተኞች በዙብን፡፡ ልክ ነዋ! አሀ እኛ ዋናውን በር አልፈን ለመግባት በኮትና ሱሪ ለመሸለል አስር ሺዋን ከየት እናምጣ፡፡ አስር ሺህ! የሆነ ልቡ የወደደውን ጫማ ሲጠይቅ “አስር ሺህ ብር፣” የተባለው ወዳጃችን፣ አስር ሺህ ሉሲፈሮች የሰፈሩበት ያህል ነበር የደነገጠው፡፡ እናላችሁ... ዋነኛው ጉዳያችሁ ዋና ሥራ አስኪያጁ ዘንድ መሆኑ ቀርቶ ጥበቃው ዘንድ ሲሆን ቀላል ጉልበተኝነት ነው እንዴ የሚገጥማችሁ! ከፈለገ ያስገባችኋል፣ ካልፈለገ አያስገባችሁም፡፡ አለቀ...ምንም ጣጣ ፈንጣጣ ብሎ ነገር የለም፡፡ ለበላይም አቤት ለማለት እኮ መጀመሪያ ጉልበተኛውን ማለፍ ያስፈልጋል፡፡ ማን ቢያስገባችሁ!
ደግሞላችሁ...የእቃ አውራጆች ጉልበተኞች በብዙ ሰፈር አሉ ይባላል፡፡ ሠርቶ መኖርን የመሰለ ነገር የለም...ስንትና ስንት ሚሊዮን ሰው መሥራት እየቻለ ሥራ አጥ በሆነባት ሀገር ማንኛውንም ሥራ ማድነቅ አሪፍ ነው፡፡ ኮሚክ እኮ ነው! እቃ ለማውረድ የሚጠየቀው ገንዘብ አንዳንዴ “ቆይ በሂሳብ ማሸን ላስበው፣” ሊያሰኝ ምንም አይቀረው፡፡ እኔ የምለው...ከአምስት ሺሀ ብር የማይበልጥ ዋጋ ያለውን ዕቃ ለማውረድ “ሰባት ሺህ ብር...” መጠየቅ ምን የሚሉት ‘ሀገር በቀል ቢዙ’ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ነገሮች ለምን የሆነ ስርአት እንደማይበጅላቸው አይደንቃችሁም!
የታክሲ ረዳት ጉልበተኞች ነገርማ ተዉት። በቃ እነሱ ራሳቸውን የቻሉ ሀገር ናቸው። ይኸው አይደለም ከጨለመ፣ አይደለም አመሻሹ ላይ ቀን በቀን እንደልብ የሚጠየቀው ፍራንክ እኮ አስቸጋሪ ነው፡፡ ጠዋት በአስር ብር የሄዳችሁት መንገድ ረፋዱ ላይ አስር ብር ስትሰጡ “ያስጨምራል፣ አስራ አምስት ሆኗል፣” ይላችኋል፡፡ አትከራከሩት ነገር ‘ራምቦ ቁጥር ምናምን’ ነገር ይሆንባችኋል፡፡
እናማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል...ይሄ የአዝማሪነት ነገር “የእኔማ ዠርጋዳ...” ስለተባለ ሰማይ ለመጨበጥ መሞከር አሪፍ አይደለም፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1493 times