Saturday, 05 November 2022 11:37

ጥቅምት 24፡ መቼም አንረሳውም! መስዋዕትነታችሁ አገርን አቁሟል!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሀገር እንጠብቅ ህዝብን እናገልግል ያሉ፣ ቀን ገበሬ ማታ ደግሞ ጠባቂ ሆነው ለሃያ አመታት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የኖሩ፣ ሃሩሩ አቃጠለኝ በቃኝ፣ ብርዱ አቆረፈደኝ ይቅርብኝ ሳይሉ፣ ሌትና ቀን፣ በጋና ክረምት፣ ቆላና ደጋ እያሉ ስለሀገር መስዋዕትነት የከፈሉ፣ ስለህዝብ የተንገላቱ፣ ስለኢትዮጵያ የደከሙ የሰሜን እዝ አባላት በሰው ልጅ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ባልጠበቁት አካል፣ ባልጠረጠሩት መንገድ፣ ባልገመቱት ሰዓት እንኳን ለወንድም፣ እንኳን ለአንድ ሀገር ልጅ ለጠላት እንኳን በሚሰቀጥጥ መልኩ የተጨፈጨፉበት ሁለተኛ አመት ነው!
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ ጥቁር ቀን ነው፤ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ያነቡበት ቀን፡፡ ይህ ቀን ምስኪን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን በተኙበት የታረዱበት ቀን ነው፣ ይህ ቀን የታሪክ ጠባሳው ለዘላለም የሚኖር ቀን ነው። ይህንን ቀን ስናስታውስ በተኙበት የታረዱት ሀገር ጠባቂዎች፣ አስክሬናቸው ላይ በሲኖትራክ በጭካኔ የተነዳባቸው ወታደሮች፣ የሀገሬ ልጅ ያሉት ሲጨክንባቸው እራቁታቸውን ወደ ጎረቤት ሀገር ያመለጡ የሰራዊቱ አባላት የሚታወሱበት ቀን ነው።
ዛሬ ላይ የእነርሱ መስዋዕትነት ሀገርን አቅንቷል፣ የከፈሉት ዋጋ ለተቀረነው ለኛ የታሪክ ባላደራ እንድንሆን አድርጎናል። ሀገር እንድትቀጥል እነሱ ምክንያት ሆነዋል።
ዛሬ መላ ኢትዮጵያዊ ወገኖቼን ቆሜ አንድ ነገር እጠይቃችኋለሁ። ከዛሬ በኋላ እስከ ጥቅምት 24 ያሉትን ቀናት በዛ ጥቁር ጭለማ ቀን ሰብል ሲሰበስቡ ውለው በውድቅት ሌሊት የተጨፈጨፉትን ውድ ልጆቻችንን እንድናስታውስ አደራ እላለሁ።
ውድ ኢትዮጵያውያን፤ የነርሱ መስዋዕትነት ዛሬ ለኛ የመኖር ዋስትና መቀጠል ምክንያት ሆኗልና፡፡
ጥቅምት 24፡ መቼም አንረሳውም!
መስዋዕትነታችሁ አገርን አቁሟል!
(ሰለሞን አሰፋ)

Read 1327 times