Saturday, 05 November 2022 11:58

‹‹በቴኳንዶ ጥበብ አገርን መቀየር ይቻላል›› - አቶ መንሱር ጀማል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

       (የኢትዮ ዩናይትድ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት          የአዲስ አበባ ከተማ ኢትዮ ዩናይትድ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ፌደሬሽን ከትናንት በስቲያ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን በጊዮን ሆቴል አካሂዷል። በጉባኤው ላይ በከተማ ሚንቀሳቀሱ 24 ክለቦች ከ14 በላይ የተገኙ ሲሆን ከ11 ክፍለ ከተማዎች ሰባቱ ተሳትፈዋል፡፡ የቴኳንዶ ፌደሬሽኑ የስራ ዘመን  ዘመን ሊገባደድ ከ1 ዓመት ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል። ባለፉት 3 ዓመታት በፌደሬሽኑ አስተዳደር ላይ የነበሩ ፕሬዝዳንትና አብዛኛዎቹ የስራ አስፈፃሚ አባላት በስራ ላይ አልነበሩም፡፡ ስለዚህም የመንግስት መመሪያ በሚፈቅደው መሰረት ዓመታዊው ጠቅላላ ጉባኤ ተካሄዷል፡፡ ምክትል ፕሬዝዳንቱ የፕሬዝዳንት ስልጣኑን ተክተው እንዲወስዱ እና በተጓደሉ ስራ አስፈፃሚዎች ላይ የማሟያ ምርጫውንም አከናውኗል፡፡
በጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ መሰረት ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ መንሱር ጀማል ለሚቀጥሉት ስምንት ወራት  የቴኳንዶ ፌደሬሽኑን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ በሙሉ ድምፅ ተመርጠዋል፡፡ የተጓደሉ የስራ አስፈፃሚ አባላትን ለመተካት በተካሄደው የማሟያ ምርጫ ላይ በዋና ፀሃፊው 6 እጩዎች ቀርበው ነበር፡፡ የጠቅላላ ጉባኤው አባላት በስፖርቱ ውስጥ ያለፈ ሙያተኛ ከስራ እስፈፃሚው ጋር ተጣምሮ እንዲሰራ ያቀረቡት ሃሳብ ተቀባይነት አግኝቶ ለሰባት ስራ አስፈፃሚ አባላት ማሟያ ምርጫ ተደርጎ አዲሱ የፌደሬሽን አስተዳደር ሙሉ ለሙሉ ሊመሰረት በቅቷል፡፡ ከ4 ዓመታት የስራ ዘመን በቀረው ጊዜ የፌደሬሽኑን ህልውና ለማስጠበቅ የሚሰራ ይሆናል። በዓመቱ መጨረሻ ላይ በሚካሄደው ዋናው ጠቅላላ ጉባኤ ሙሉ ምርጫ እንደሚከናወንም ታውቋል። የፌደሬሽኑ ዋና ፀሃፊ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ባቀረቧቸው ሪፖርቶች የአሰልጣኞችና የዳኞች ማህበራት መደራጀታቸውን አመልክተው፤ አዲስ የተሾመው ስራ አስፈፃሚ በቀሪው የስራ ዘመን፤ የፌደሬሽኑን የገቢ አቅም በማሳደግ፤ ውድድሮችን ለማካሄድና ለስፖርቱ የንግድ ስራ የሚሆን ግንባታ መሰረት ለመጣልና ስፖርቱንና ውድድሮቹን ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
የኢትዮ ዩናይትድ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ፌደሬሽን አዲስ ፕሬዝዳንት አቶ መንሱር ጀማል በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ስፖርቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ ቃል ገብተዋል፤ በስራ ዘመናቸው ቴኳንዶ ለወጣቱ ተደራሽ እንዲሆን፤ ልክ እንደአትሌቲክስ ዋንጫና ወርቅ የሚመጣበት ደረጃ እንዲደርስ እንሰራለንም ብለዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ከስፖርት አድማስ ጋር ያደረጉት አጭር ቃለምልልስ እንደሚከተለው ነው፡፡
መንሱርንና ቴኳንዶን ምን ያገናኛቸዋል?
እውነቱን ለመናገር እኔን ከቴኳንዶ ጋር ሊያገናኘኝ የሚችል ምንም ነገር የለም፡፡ ስለ ቴኳንዶም ብዙ አላውቅም፡፡ ነገር ግን ወጣቶች ላይ ከመስራት አኳያ፤ ወጣቱ ማህበረሰብ ወደ ስራ ከመግባቱና ራሱን ከመለወጡ ጋር በተያያዘ ለመስራት ተገናኝተናል፡፡ በጣም ብዙ ሚሊየነር ወጣቶችን መፍጠር አለብን በሚለው ዓላማ ላይ የምንሰራበት ነው፡፡ በወጣቶች አዕምሮ ላይ መሰራት ስላለበት ነው፡፡ በማህበር ደረጃ የነበረው ቴኳንዶ ስፖርት ወደ ፌደሬሽን ሲለወጥ ተቋሙን  ማገልገል አለብህ የሚል ምክር ደረሰኝ፡፡ ፌደሬሽኑን ለመምራት ዋንኛው መስፈርት ቴኳንዶን የግድ ማወቅ አይደለም፡፡ ወጣቱ ላይ መስራት መቻልና የፋይናንስ ድጋፍና ምንጮችን መፍጠር እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡ በጀትም የላቸውም፡፡ በአሁኑ ወቅት ፈደሬሽኑ ከመንግስት የሚያገኘው ዓመታዊ በጀት ከ100ሺ ብር አይበልጥም፡፡ ይህ ደግሞ አንድ ውድድር ለማዘጋጀት እንኳን በቂ አይደለም። ስለዚህም እኔ ባገኘሁት ሃላፊነት የገቢ ምንጮችን በመፍጠር እና ከራሴ ድርጅቶችና ኩባንያዎች የምችለውን የበጀት ድጋፍ በማድረግ ፌደሬሽኑን ለማቋቋም ነው ያቀድኩት፡፡ ወጣቱ ማህበረሰብ ወደቴኳንዶ ጥበብ እንዲመጣና እንዲያተኩር ለመንቀሳቀስ ነው፡፡ በተለይ ቤት ውስጥ ተቀምጦ ስራ ፈትቶ ያለው ትውልድ በስፖርቱ ላይ በመስራት አገርን ማስጠራት እንደሚችል አምናለሁ፡፡ አንድ ሰው ተወልዶ አድጎ መሞት የለበትም፡፡ የሆነ ታሪክ ሰርቶ ማለፍ አለበት የሚል አመለካከት ከሚያንፀባርቁ ሰዎች አንዱ ወጣቱ ወደ ስፖርቱ መጥቶ የቴኳንዶን ጥበብ አሳድጎ ቢያንስ አዕምሮውን ሰፋ ሊያደርግ ይችላል፡፡ እንደ መንግስትም በሚታይበት ሰዓት የግድ መሳርያ ታጥቀህ አገርን መጠበቅ የለብህም፤ በቴኳንዶ ስፖርት ወታደሩን የአገርን ደጀን መጠበቅ ስለሚቻል  በዚያ ላይ የራሴን ድርሻ መወጣት አለብኝ ብዬ አስባለሁ፡፡
በማህበራዊ ሚዲያውም ዝነኛ እንደሆንክ ይታወቃል፡፡ በዚህ በኩልስ ስፖርቱን ለማንቀሳቀስ አቅድሃል? ማህበራዊ ሚዲያውን ለበጎ ማዋል እንዴት ይቻላል?
በተለያዩ የሶሻል ሚዲያ አውታሮች በቲክቶክ፤ በፌስቡክ፤ ፤ በሊንክደን፤ በትዊተር፤ በዩቲውብና በሌሎችም ከሚሊየን በላይ ተከታዮችን አፍርቻለሁ። ወጣቱን በንግግር ብቻ ሳይሆንም በተግባር ምን ልሰራለት እችላለሁ ብዬ በማስብበት ሰዓት ነው  በቴኳንዶ ፌደሬሽኑ የመስራቱ እድል የመጣው፤ ሃላፊነቱም ብዙ ለመስራት ያግዘኛል፡፡
 ሶሻል ሚዲያዎችን ለበጎ ነገር በመጠቀም እኔ ከፍተኛ ልምድ ነው ያለኝ፡፡ መንሱር ሶሻል ሚዲያን ለበጎ ተግባራት ይጠቀማል ቢባል ምንም ማስረጃ ማቅረብ አያስፈልገውም፡፡ በተለይ ቲክቶክ በተባለው ድረገፅ በእጅጉ ተሳክቶልኛል፡፡ ወደ ጉጉል ድረገፅ ሄደህ መንሱር ጀማል ሾርት ቪድዮስ Mensur Jemal Short videos ብለህ ብትፈልግ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምላሾች ነው የምታገኘው። በስሜ የተከፈቱ ፌክ አካውንቶች በብዛት አሉ። በዩቲውብና ፌስቡክ ላይ አመዝኖ የነበረውን የውሸት ፕሮፖጋንዳ፤ ፖለቲካን ሳያውቁ ፖለቲካን የመተንተኑ ነገር በቲክቶክ አጫጭር ቪድዮዎች ሚዛኑን እንዲጠብቅ ለማድረግ እንደቻልኩ ነው የማስበው፡፡ እንደምታውቀው ዛሬ ዩቲውብም ፌስቡክም ያን ያህል አይደለም፡፡ የአሁኑ ወጣትና ታዳጊ ትውልድ ያለው ቲክቶኩ ላይ ነው፡፡ በቲክቶኩ ላይ መንሱር ሁሌ ጠዋትና ማታ አዎንታዊ ሃሳቦችን፤ ኢትዮጵያ ተስፋ እንዳላት በመግለፅ ይታወቃል፡፡ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊ ወይም ተቃዋሚም አይደለሁም፡፡ የማንም አባልም አይደለሁም፡፡ በምጠቀምበት የሶሻል ሚዲያ አውታር አገራችን ተስፋ እንዳላት፤ መለወጥ እንደምንችል፤ ሰርቶ ማደግ እንደሚቻል፤ መንግስት የሚያወጣውን ህግ ጠብቀን ወንጀለኛ ሳንሆን መስራት እንዳለብን፤ ግብና ህልም ከያዝን መተግበር እንደሚቻል ሁሌም እየተናገርኩ እገኛለሁ፡፡ ብዙ ሰዎችን ወደ አዎንታዊውና ቅን አስተሳሰብ እንዲቀየሩ ተፅእኖ መፍጠር የቻልኩ ይመስለኛል፡፡
በፕሬዝዳንትነት በተሾምከበት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በተደጋጋሚ ከተነሱ ጉዳዮች አንዱ በቴኳንዶ ስፖርት የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተሳትፎ ማሳደግ የሚለው ይገኝበታል፡፡ ባንተ በኩል ለወጣት የቴኳንዶ ስፖርተኞች የውጭ አገር ውድድሮችን በመፍጠር ምን ለመስራትስ አቅድሃል?
ከአገር ውጭ በስደት ከሰባት ዓመታት በላይ ቆይታ ነበረኝ፡፡በተለይ በኤስያዋ አገር ኢንዶኔዦያ  አብዛኛዎቹን አመታት በኑሮ አሳልፊያለሁ፡፡ የቴኳንዶ ስፖርት በተለይ ከደቡብ ኮርያ ተነስቶ በመላው ዓለም እንደተስፋፋ ይታወቃል፡፡ በተለያዩ የንግድ ስራዎች የማውቃቸው ብዙ ኮርያውያን ጓደኞች ስላሉኝ ወደዚያው አገር ከኢትዮጵያ የተወሰኑ የቴኳንዶ ባለሙያዎች በመውሰድ የልምምድ ልውውጥ የሚያገኙባቸውን መድረኮች መፍጠር እፈልጋለሁ፡፡ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚና የቦርድ አባላት ጋር ባለኝ የቀረበ ግንኙነት በስፖንሰርሺፕ ድጋፍ የውጭ ጉዞዎችን ለማሳካትም እሰራለሁ፡፡ ከትልልቅ ባለሃብቶች ጋር ያለኝን  ግንኙነት በመጠቀም ለስፖርቱ የተለያዩ እገዛዎችን በመሰብሰብ በውጭ አር በሚካሄዱ ውድድሮች ወጣቱን ለማሳትፍም እቅድ አለኝ፡፡በአገር ውስጥ ያለውን የቴኳንዶ ስፖርት  እንቅስቃሴ በማጠናቀር ወጣቱ ከስፖርቱ የሚያገኘውን ጥቅም ለማስፋትም አስባለሁ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ብቻ ከ23 በላይ የቴኳንዶ ክለቦች እና በስራቸው ደግሞ ከ100ሺ በላይ ስፖርተኞችና ባለሙያዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ወጣቱ በቴኳንዶ ጥበብ አገርን መቀየር ይችላል በሚል አስተሳሰብ  ለመስራት ተዘጋጅቻለሁ፡፡  

Read 89 times