Saturday, 05 November 2022 12:06

የሰዓሊ ተሰማ ሥነጥበባዊ ዲፕሎማሲ በኳታር

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 በኳታር ዋና ከተማ ዶሃና ሌሎች  ከተሞች  በርካታ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው ይታወቃል፡፡ በስነጥበብ፤ በንግድ፤ በህክምና፤ በአቪዬሽን፤ በግንባታ መስኮች  እየሰሩ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያውያኑ አንዱ በስነጥበብ ሙያው አስደናቂ የዲፕሎማሲ ስራ በማከናወንና የኳታር የዓለም ዋንጫ መስተንግዶ  በማሟሟቅ የተሰካለት  ሰዓሊ ተሰማ አስራት ተምትሜ ይባላል፡፡ ላለፉት 14 ዓመታት በኳታር የኖረው  ሰዓሊ ተሰማ   ከስነጥበብ ሙያው  ባሻገር በኳታር ኤርዌይስ የቴክኒክ ዲፓርትመንት የሚሰራ ነው፡፡ በታዋቂው የኳታር ኢንተርናሽናል አርት ፌስቲቫል QIAF ላይ የአፍሪካ ብራንድ አምባሳደር ሲሆን ለ2022 የዓለም ዋንጫ ላይ በበጎ ፈቃደኝነት እንዲያገለግሉ ከተመረጡ ኢትዮጵያውያንም አንዱ ነው፡፡
ሰዓሊ ተሰማ ኳታር  22ኛው የዓለም ዋንጫን እንድታዘጋጅ በፊፋ  በ2010 እኤአ ላይ ከተመረጠችበት ጊዜ አንስቶ  በስነጥበብ ሙያው የበኩል ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን ይናገራል፡፡ ከሚኖርበት ኳታር ከስፖርት አድማስ ጋር ባደረገው አጭር ቃለምልልስ እንደገለፀው ኳታር ለዓለም ዋንጫው አጅግ አስደናቂና አስገራሚ ዝግጅት ማድረጓን፤ ዘመናዊ ስታድዬሞች መገንባቷንና ከውድድሩ በኋላ የየስታድዬሞቹንን የግንባታ ቁሶች ለአፍሪካ ለመለገስ መወሰኗን በአድናቆት በመጥቀስ ነው። በትራንስፖርት፤ በማረፊያ አገልግሎቶች፤ በፀጥታና ደህነንት ለዓለም ዋንጫው በቂ ዝግጅቶች መደረጉንም አብራርቷል፡፡
ሰዓሊ ተሰማ በኳታር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን  በየትኛውም የዓለም ክፍል ከሚገኙ ማህበረሰቦች በልዩ ተግባራቸው እንደሚጠቀሱ ያስረዳል፡፡ በተለይ ከአትሌቲክስ ስፖርት ጋር በተያያዘ በሚሰጡት ድጋፍ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አለማ ከፍ አድርገው የሚያውለበልቡ ናቸው፡፡ ለዚህ ምሳሌ እንዲሆን በዳይመንድ ሊግና በዶሃ በሚካሄዱ የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ የፈጠሯቸውን ደማቅ ድባቦችን ጠቅሷል፡፡ ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ በስነጥበብ ሙያው በሚያደርገው ልዩ እንቅስቃሴ  ኢትዮጵያን በሚያስጠራበት ደረጃ ላይ መድረሱንም በልበሙሉነት ይናገራል፡፡   
ሰዓሊው በአረቡ ዓለም በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ላይ በስነጥበብ ባለሙያነቱ የተጫወተውን አስደናቂ ሚና ከራሱ አንደበት ባሻገር በተለያዩ ሚዲያዎች በተሰሩ ዘገባዎች ማረጋገጥ ይቻላል። በኳታር የዓለም ዋንጫ ዝግጅትና በአገሪቱ የስነጥበብ እንቅስቃሴ ስለሚያደርገው ንቁ ተሳትፎ ካወሱ ሚዲያዎች መካከል ኳታር ትሪቡንና አል ራያ ጋዜጦች፤ አይላቭኳታር ድረገፅና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ በስነጥበብ ዲፕሎማሲ ያከናወናቸው ተግባራት ሚዲያዎቹ በዘገባዎቻቸው ተምሳሌት አድርገው በመጥቀስ አድንቀውታል፡፡


22ኛውን የዓለም ዋንጫ በስነጥበባዊ ዲፕሎማሲ በደገፈበት ምስጉን ተግባሩ ዙርያ ለስፖርት አድማስ ሲናገር የስዕል ስራዎቹ ይህን እንደሚያንፀባርቁ በማብራራት ነው።  ማፕ ኢንተርናሽናል የተባለ የስነጥበብ ተቋም በ2019 እኤአ ላይ ‹‹ከለር ኦፍ ዴዘርት›› በሚል ርእስ ባዘጋጀው ኤግዚብሽን  አስደናቂ ተሳትፎ ነበረው፡፡ የኳታርን የዓለም ዋንጫ መስተንግዶ ለመደገፍ በዶሃ የሚገኙ አፍሪካውያን ማህበረሰብን ባስተባበረበት ሚና ተንቀሳቅሷል፡፡ ከ51 በላይ የስነጥበብ ባለሙያዎች 102 የስዕል ስራዎችን ባቀረቡበት ኤግዚብሽን ላይ  የሱ ስዕል በልዩ ጭብጡ አነጋጋሪ ለመሆን ችሏል፡፡ በ2021ና በ2022 እኤአ ላይ በተካሄዱት የኳታር ኢንተርናሽናል የአርት ፌስቲቫሎች ዓለም ዋንጫውንና አዘጋጇን ኳታር በሚያስተሳስሩ ጭብጦች  የሰራቸው ስዕሎች በኳታር ንጉሳውያን ቤተሰቦች፤ መንግስታቸው፤ የስነጥበብ ተቋማት መሪዎችና የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ተደንቀውለታል፡፡
ከሰዓሊ ተሰማ የስነጥበብ ስራዎች መካከል አንደኛው የኳታር ንግስትን በልዩ አድናቆት የገለፀበት ነው። ንግስቲቱ በአገሪቱ የትምህርት ልማትና ሴቶችን የማብቃት ፖሊሲዎች ያከናወኑትን ተግባር ያደነቀበት፤ ከቤተሰባቸው ጀርባ ዓለም ዋንጫውን በማዘጋጀት ለነበራቸው አስተዋጽኦ መታሰቢያ ያደረገው ነው፡፡ ሌላኛው ስዕሉ ደግሞ የጨለማ ድባብ በተላበሰ የኳታር ካርታ ላይ ንጉሱን ተስፋና  ገፅታን ተላብሰው ኳታር ዓለም ዋንጫ በስኬት እንደምታዘጋጅ የሚያንፀባርቁበትን ስሜት ገልፆታል፡፡ ኳታርያውያንና በዚያው የሚኖሩ የውጭ አገር ዜጎች ለዓለም ዋንጫው ዝግጅት ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ለማንፀባረቅ ደግሞ በኳታር ባንዲራ የቀለመችን ኳስ በጥፍሩ የያዘ አሞራ ነው የሳለው፡፡ ሰዓሊ ተሰማ ለስፖርት አድማስ በሰጠው አስተያየት በኳታር ካርታ ላይ በሚሰራቸው  ስዕሎቹ ለማንፀባረቅ የፈለገው በጎረቤት አገሮቿ ማዕቀቦችና የተለያዩ እግዶች የተጣለባት አገር ዓለም ዋንጫውን በእልህና በቁርጠኝነት ለማስተናገድ መቻሏን በማድነቅ ነው፡፡  የዓለም ዋንጫ ለኳታርና ለህዝቧ ብዙ ፀጋ እንደሚያስገኝ የተናገረው ሰዓሊው አገሪቱ ዓለምን ለማስተናገድ ያደረገችው ዝግጅት በስነጥበብ ስራዎቹ መንፀባረቃቸውን በማስገንዘብ ነው። ስዕሎቹ ኳታር በቆዳ ስፋቷ ትንሽ  አገር ብትሆንም ግዙፍና ታላላቅ ሁኔታዎችን ለዓለም  ማበርከቷን ያሳያሉ፡፡  እንደ ሁለተኛ አገሩ ለሚመለከታት ኳታር ያለውን ፍቅር፤ ክብርና ድጋፍም ገልፆባቸዋል፡፡
ሰዓሊ ተሰማ ተምትሜ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አለ የስነጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ተመርቋል። በስነጥበብ ሙያው ከ30 ዓመታት በላይ የሰራ ሲሆን፤ በግሉና በቡድን በርካታ ዓለም አቀፍ የስዕል ኤግዚብሽኖች ለመሳተፍ የበቃና በርካታ ሽልማቶችንም  ያገኘ ነው፡፡ የስዕል ኤግዚብሽኖችን ካቀረበባቸው አገራት ኢትዮጲያ፤ ጅቡቲ፤ ፈረንሳይ፤ ስዊድን፤ ጣሊያን፤ ሆላንድ፤ እንግሊዝ፤ አየርላንድና ኳታር ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ ባለፉት 10 ዓመታት ኳታር ዶሃ ውስጥ በሚካሄዱ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የስነጥበብ ፌስቲቫሎችና እንቅስቃሴዎች ላይ በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል፡፡ በአረቡ ዓለም የኢትዮጵያና የአፍሪካ ስነጥበብ አምባሳደር ሆኖ  በማገልገልም ተዋጥቶለታል፡፡ በተለይ በኳታር ዓለም አቀፍ የአርት ፌስቲቫል ላይ በአፍሪካ ብራንድ አምባሳደርነት ለ4 ዓመታት እንዲያገለግል ከተመረጠ በኋላ ለአህጉሪቱ ሰዓሊዎች ዘርፈ ብዙ ድጋፍ በመስጠት ቀጥሏል፡፡ በ2021 እና በ2022 እኤአ ላይ በተካሄዱት QIAF ፌስቲቫሎች ላይ ሲሰራ የኢትዮጵያን የስነጥበብ ባለሙያዎች እንዲሳተፉና ተሸላሚ እንዲሆኑ በማድረግ ድንቅ ስራ አከናውኗል፡፡ ባለፉት 3 ዓመታት በተካሄዱ የዓለም ዋንጫውን መስተንግዶ በሚያሟሙቁ ዘመቻዎች ባደረገው  ንቁ ተሳትፎ ከበሬታን ከማትረፉም በላይ ከአትሌቲክስ ስፖርት ባሻገር በዓለም አቀፍ የስነጥበብ ፌስቲቫል ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ በማውለብለብ ታሪክ ሰርቷል፡፡


Read 11031 times Last modified on Saturday, 05 November 2022 12:44