Saturday, 05 November 2022 12:36

ነገረ ድልድይ

Written by  አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)
Rate this item
(0 votes)

 ፩
 ከምንጠጣበት ባር ፣ በፍጥነት እየተመናቀረች ስትወጣ ተከትያት ወጣሁ። ዞራ “ኤጭ” በሚል ስሜት ገላምጣኝ ጀርባዋን ሰጠችኝ። የፍቅር ታሪካችን ቢፃፍ እንኳን ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የቅጠል ቦታ የሚይዘው የጀርባ ታሪክ ነው።  ጀርባዋ ላይ ወዴት እንደሚወስድ የማይታወቅ ካርታ አለ። ምናልባት ያን ካርታ ተከትዬ እሷን ወደ ማላይበት ወይም እሷን ብቻ ወደ ማመልክበት ቅዱስ አገር እሰደድ ይሆናል። ያ ሃገር መካ ወይ እየሩሳሌም እንዳይሆን በፀሎት እተጋለሁ። ጀርባዋ ላይ እንደ ሲስፐስ እድሜ ዘመኑን ድንጋይ እስከ አንገቷ የሚያንከባልል ሰው አለ።  እኔ የምወዳትን ልጅ ሳቅ አይደለም  የማውቀው...እኔ የምወዳትን ልጅ መልክ አይደለም ያጠናሁት። እኔ የምወዳት ልጅ ፍቅሯ ሳይሆን ጀርባዋ ነበር የደረሰኝ። እኔ የምወዳትን ልጅ ፈገግታ የመመልከት ክብር ላይ ገና አልደረስኩም። እኔ በምወዳት ልጅ የመታቀፍን ብርሃን ያላየሁ የፍቅር እውር ነኝ። እኔ በምወዳት ሴት ልጅ ጀርባዋ ላይ የቆምኩ የጨው አምድ ብቻ ነበርኩ።
ፊቷ ቆምኩ። ጨረቃ ብርሃኗን በረቂቅ ቱቦ ፊቷ ላይ አፍሳለች። ሳያት ትልልቅ ዓይኖቿ ሸሹኝ። ሰማዩን መመልከት ጀመረች። ጉንጮቿ ለኩሪፊያ ሲሉ አበጡ። የአፍንጫዋ ቀዳዶች ሰፉ። ፊቷን በእጇ አበሰች። አኩርፋም ታምራለች... ምን ጉድ ነው?
“እ” ስትለኝ፣ በእናቴ ማህፀን ውስጥ የመደበቅ ፍላጎት ውስጤ ተሰራጨ። የልብ ምቴ ጨመረ። አየዃት... ታምራለች።
“ምነው ደበረሽ እንዴ? ቤቱን እንቀይር?”
“ስራ አለኝ... Bye” ብላኝ ጥላኝ ሄደች።
“ቆይ አንዴ...”
“ስሚኝማ”
ጆሮዋ ሰምቶኝ አንደበቷ መልስ ከለከለኝ። ተናግሮ  ምላሽ ማጣት ጨው የተነሰነሰበት ቁስል ነው መሰል  ጠዘጠዘኝ...
በአንዲት ሴት የዚህን ያህል  ዝቅ የመደረግን ሃፍረት የምንችለው እኔና እብድ ውሻ ብቻ ነን።  ጨረቃዋ ከቀድሞ ብርሃኗ ደብዝዛለች። በእርግጥ ይህቺ እንስት በሌለችበት ሁሉም ነገር የሚታየኝ ደብዝዞ ነው።
ንዴት አይሉት ሃፍረት ሆዴ ውስጥ የንዴት ችቦ ለኮሰና ብዙ ጠጣሁ። የቤቱ ብርሃን ደበዘዘብኝ። የሚያዩኝ ሰዎች በዙ። ሃፍረቴን ያወቁብኝ መስሎኝ ከዚያም ቤት ሸሸሁ። ኑሮዬ ከሽሽት እልፍኝ ወደ ሽሽት መቃብር መሰለኝ።  የሃፍረትን መፅሐፍ የሚገልጡት እኔን ላሉት ወዳጅ እንጂ ለማንም የቡና ቤት ሰው አይደለም።
ቤቴ ገብቼ አልጋዬ ላይ ተንጋለልኩ። ዞረብኝ..                            
ስነቃ በሬ  በሃይል ይንኳኳል። ከፈትኩ... እሷው ነች።
በዝምታ አንድ ወረቀት አቀበለችኝ። አየሁት፣ የመፅሐፍ ዝርዝር ነው። በዝምታ ተግባባን... ገዝተህ ና የሚል የባርነት ማህተም ፊቷ ላይ ከማንበቤ ጥላኝ ወጣች። ትንሽ ብታወራኝስ? አንዴ ብታቅፈኝስ? ደህና አደርክ? ብትለኝ ከእድሜዋ ይቀነሳል? ጉንጬን ብትስመኝ ከንፈሯ ይሟሟል? ለሰከንድ እንኳን ብታየኝ ዓይኗ ይጠፋል? የፍቅርን ሃፍረት ተሸክሜ የምጓዝ ሎሌ ነኝ። የእራሴን ሲኦል የሰራሁት በእራሴ እጅ ነው። የተሸከምኩት ክቡድ መስቀል የተሰራው ኮትኩቼ፣ ውሃ እያጠጣሁ  ካሳደግሁት ዛፍ ነበር። የተገረፍኩበትን ጅራፍ የገመድኩት እራሴ ነኝ። የጠፋሁት እራሴ በዘረጋሁት መንገድ ነው። ባይተዋር ሆኜ የምኖረው ባቀናሁት ከተማ ነበር።
ድፍን አዲስ አበባን ዞሬ፣ በየመፅሐፍት መደብሩ ተንከራትቼ ያለችኝን መፅሐፍት  ገዛሁ። ገንዘብ ስላልነበረኝ ከጓደኛዬ ሞገስ ተበድሬ ነው ታድያ። መፅሐፉን አስቀመጥኩላት። ምሽት ላይ መጣች። የገላዋ ርሔ ለአፍንጫዬ ደረሰኝ። አቀፍኳት። እንደ መሸሽ ቃጣት። ልስማት የነበረኝን ሃሞት የሃፍረት ጥይት ገደለውና ዓይኗን ማየት ጀመርኩ። ዓይኗ ለምን ይሸሸኛል? ይሄን ያህል ጠላችኝ እንዴ?
“አገኘህ?”
“አዎ” ሰጠዃት።
“ያንቺን ግጥም መች ነው የምታነቢልኝ?”
“ግጥም የት ይገባሃል አንተ፣ አርፈህ ብቀላ፣ ሴረኛው ምናምን የሚባሉ መፅሃፎችን አንብብ”
“የሳጥናዬል ጎል በኢትዮጵያንምእኮ አንብቤያለሁ”
“አልኩህ እኮ...”
“ታድያ ጥሩ አይደሉም እንዴ?”
“ላንተ ጭንቅላት ጥሩ ናቸው”
“ላንቺስ?”
“ቻው”
ሄደች። ጀርባዋን አየሁት። ያው የማውቀው ጀርባ ነው።  መጠጣት ፈለኩ። ሞገስ ጋ ደወልኩለት... ቤቱ እየቃመ ነው። ተነስቼ ወደ እሱ አዘገምኩ። ስገባ እጣን ይጨሳል። በቡና ሽታ ቤቱ ታውዷል። የአስቴር ሙዚቃ ተከፍቷል። አስቴር “ካቡ ተንዶብኝ” ትላለች...  የሆነ መፅሐፍ ገልጦ በእጁ  ይዟል። ቤቷ አንድ ክፍል ናት። የመፅሐፍ መደርደሪያው ብቻ የቤቱን ሲሶ ይዟል።  ቢያንስ መሸሸግያ እንዳጣች አይጥ ጠላቶቼ ፊት እየቆምኩ አልተመታሁምና ደስ አለኝ። ፍራሽ ላይ ተቀመጥኩ። ቃም አለኝ።
“ባክህ መጠጣት ነው የምፈልገው”
አረቄ ቀዳልኝ፡፡
ጉሮሮዬን እየሰነጠቀ ወረደ።
“ምነው?” አለኝ...
“ምንም” አልኩት...
አየኝና፤ “እሷው ነች ዛሬም?”
“ተወኝ እስኪ... “
“አንዳንድ ችግሮች መፍትሔአቸው ተመሳሳይ ነው። መተው  የሚባል ነገር አለ። አንድን ድንጋይ ታግለህ ልታንቀሳቅሰው ትችል ይሆናል፣ አንድን ልብ ግን ታግለህ እንዲወድህ ማድረግ አትችልም። ሴት ልጅ ካልፈለገችህ ለውሻ እንኳን የማትነፍገውን ክብር ትከለክልሃለች። ብዙ ንቀት እያሸከመችህ እራስህን እንድትጠላ፣ ከመሬት በታች እንድታንስ ታስገድድሃለች። አንተም የዚህ ገፈት ቀማሽ ነህ። ለመጨረሻ ጊዜ አናግራታለሁ። መልሷን እሰማለሁ። ምናልባት በእሷም ጫማ መቆም ይገባኝ ይሆናል። “
ይሄን ሲያወራ እኔ ሶስተኛ መልኬ ላይ ደርሼ ስለ አራተኛ መልኬ ነው የማስበው።
“ምናልባት ከእብድ ውሻም ወርጄባት ቢሆንስ የምትንቀኝ... ሃሳቦቿ እንደ ስሟ ረቂቅ ናቸው። ፊቷ ላይ ጥልቅ ነገር ነው የሚታየኝ። ግራ የገባኝ ነገር ካልፈለገችኝ ለምን እኔ ጋ ትመጣለች?"
“የረቂቅ ጭንቅላት ቢከፈት ከጥልቅ ሃሳብ ይልቅ የሚበዛው የድንቁርና እና የግብዝነት ንፍጥ ነው። የረቂቅ ልብ እንደ ጨርቅ ተገልጦ ቢታይ ከይሁዳ የባሰ የክህደት ሀሞት ፈሶበት  ታያለህ። ረቂቅ አካሏ እንጂ አዕምሮዋ ገና ከዝንጀሮነት ወደ ሰውነት የሚደረገውን የዝግመተ ለውጥ ሂደት አልጨረሰም። ስላነበበች አዋቂ ነች ማለት ነው እንዴ?  የማይረቡ ግጥሞቿን በሰው ላብ ማሳተም ደረት ያስነፋል እንዴ?  ለአስተማሪ እየተኙ ውጤት ሰብስቦ ፣ ተመርቆ ዲግሪ መያዝ ያኮራል ወይ? ቃላት ደርድሮ ግጥም መፃፍ ኒውክለር ሳይንስን መተንተን መሰላት እንዴ? እነዚያ ዜማቸው የተናጋ፣  ወደድኩህ፣ ሞትኩልህ ከሚል የነተበ ጭብጥ የሚጨለፉ ግጥሞቿን ፃፈችና ከሰው በላይ ነች ማለት አይደለም እኮ... ጥበብን ማፍቀር የሚጀምረው የሰው ልጅን ከማክበር መሆኑን እረስታለች አየህ። የግጥም ጉዳይ የሰው ልጅ የክብር  ጉዳይ መሆኑ ጠፍቷታል። ኪሷ ሲጎል፣ ሆዷ ሲራብ ፣  ጨብሳ መንዘላዘል ሲያምራት ያንተን ኪስ እንደ አባቷ መሬት እያረሰች ጥበብ ጥበብ ትላለች ... ከቴም ጥበብ! እነዚያ የምትኮራባቸው ቀሽም ግጥሞቿ በረሃብ የሚጮኸውን ሆዷን እንኳን መሙላት አልቻሉም። እናውቃታለን እኮ...  ግቢ እያለን ልብወለድ “ ፍቅር እስከ መቃብር”፣ ደራሲም ሀዲስ ዓለማየሁ  ብቻ የሚመስላት የዓለማችን ደደብ ነች እኮ። ረቂቅ ኪነትን የምትፈልጋት ወንዶችን አጥምዳ የኪሳቸው ወተት እስኪነጥፍ ለማለብ ነው። የእሷ ገጣሚነት ቋሚ ስራው ለሽርሙጥና  ማቃጠር ነው። መፅሃፍ ይዛ ሲያይዋት በንባብ የሰከረች፣ እውቀት የተርከፈከፈባት ትመስላለች። እንዳትናቅ ሃፍረቷን በገጣሚነት ብዕርና በአንባቢነት ጨርቅ ትከልላች። stupid ናት። ...  አትውደደህ ግን ለምን ትንቅሃለች? ለምን ትጠላሃለች? ግድ የለም ትጥላህ.. ትናቅህ... ታድያ በሚጠሉትና በሚንቁት ሰው ኪስ መተዳደር ለእሷ ስኬት ነው? በናቁት ሰው ገንዘብ ፊኟዋ ሞልቶ ማህፀኗ በሽንት እስኪጥለቀለቅ መጠጣት የገጣሚነት መርህ ነው? ......”
ይሄን ሁሉ ሲናገር እኔ ስድስተኛ መለኪያ ጨርሼ ስለ ሰባተኛ እያሰብኩ ነበር።
“አንተም ስትረግጥህ እንደ መሬት ዝም አልክ። No... ማለት መልመድ አለብህ። ፍቅርም ቢሆን ገደብ አለው። አንተ እንደ ክርስቶስ ተገርፈህ እስክትሰቀል አትጠብቅ...ቅድም እንደነገርኩህ አንዳንድ ችግሮች መፍትሄአቸው ተመሳሳይ ነው። እሱም መተው ወይም  መርሳት ይባላል።”
አረቄውን ደጋገምኩ።
ሰከርኩ። እዚያው ፍራሽ ላይ ተኛሁ።
ስነቃ ሞገስ የለም። ደወልኩለት። አያነሳም። “ከረቂቅ ጋር ነኝ” የሚል መልዕክት ከአሉበት ቦታ  ፃፈልኝ። ስከንፍ ሄድኩ። እሱ ይጮሃል። እሷ ክንፉ እንደተመታ አውሯ ዶሮ ተሸማቃ ትሰማዋለች።
“ሞገስ”
አልሰማኝም ያወራል።
“እሱን አለመፈለግ ትችያለሽ። በዚህ እኔ አይከፋኝም። እሱን የመናቅ፣ ንቆም ከዋሌቱ ስር  የመርመጥመጥ መብት ግን የሰጠሽ የለም። ካልፈለግሽው እራቂው። በሰው ገንዘብ መፅሐፍ እየሸመቱ እውቀት መሰብሰብ ያን ያህል አያኮራም።  እድሜውን ሙሉ እናቱን እንዳጣ ልጅ እየከፋው እንዲኖር መፍረድ በሰማይም ኃጢያት ነው፣ ነፍሴን ሰጠዃት ለምትያትም ኪነት  ጉድፍ  ነው።”
“ጨረስክ?”
“አዎ”
እየተመናቀረች ወጣች።
“ያምሃል እንዴ?”
“ወይ እሷን ወይ እኔን መምረጥ መብትህ ነው” ብሎኝ ጥሎኝ ሄደ።
 ሞገስ ላይ ያየሁትን እሳት ገሃነብ እንኳን የማገኘው አልመሰለኝም። በዚያ ላይ እሁድ ነው። ወደ ቤቴ አዘገምኩ። ገብቼ አልጋዬ ላይ ወደቅኩ። ሊያሸልበኝ ሲዳዳ በሬ ተቆረቆረ። ተነስቼ ከፈትኩ። ረቂቅ ናት።
“ስማ፣ ለዚያ ጓደኛህ ህይወት በምርቃን ዓለም ውስጥ ሆኖ  የሚያስባት ሁነት ብቻ እንዳልሆነች ንገረው። ጓደኛዬ ነህ ብዬ ነው ስቸገር የማስቸግርህ እንጂ ሌላ አይደለም። እሱም ሊቀር ይችላል።” ብላ ፣ ወንበር ላይ ቁጭ አለች። ዓይኖቿን አየዃቸው።  እንባ አርግዘዋል። አቀፍኳት። ተንሰቅስቃ ማልቀስ ጀመረች። ምን እንደምል ጠፋኝ። ማንን መስማት እንዳለብኝ ግራ ገባኝ።

ከሞገስ ጋር መራራቅ ጀመርን። ከረቂቅ ጋር ደግሞ ይበልጥ መቀራረብ ጀመርን። እኔ ቤት ደጋግማ ማደር፣ እኔ ቤት ማንበብ እና ምግብ ማብሰል ጀመረች። ሞገስ ስለ እሷ ያለው አመለካካት የተሳሳት እንደሆነ አሳመነችኝ - በቃል ሳይሆን በተግባር። ድብርቱ እየተጫነኝ ጎድቼህ ሊሆን ይችላል እንጂ ጠልቼህም ንቄህም አላውቅም አለችኝ። አመንኳት። ግጥሞቿን ታነብልኛለች። ባይገባኝም እሰማታለሁ።
በእንዲህ አይነት ሁኔታ ወራት ተቆጠሩ።
ሞገስን ማሰቤ ግን አልቀረም። አንድ ቀን ቤቱ ሄድኩ። እንደተለመደው እየቃመ ነው። ፈገግ አለ። ኩርፊያው ከፈገግታው ጋር ተቀይጦ አልጥምህ አለኝ። ጥቁር መልኩ ይበልጥ ጠቁሯል። ዓይኖቹ ሁሌ ደም እንዳረገዙ ናቸው። ፍራሽ ላይ ተቀመጥኩ።
“ጠፋህ” አልኩት።
“አለሁ”
“ኩሪፊያውን ተወዋ “ ብዬ በቦክስ ክንዱን መታሁት...
ሳቀ..ሳቅሁ...ስለ ረቂቅ ሳናነሳ ስለ ብዙ ነገር አወራን።
“የምፈልገውን ህይወት  እየኖርኩት ነው። ብዙ ነገር አጉድዬ ሊሆን ይችላል። ብዙ ሰው በድዬ ሊሆን ይችላል። ህይወትን በጥሩ መንገድ አልተረዳኋት ይሆናል። ደስተኛ ላልሆን እችላለሁ። ገንዘብ ሊቸግረኝ ይችላል። ግን አየህ ህይወትን በገባኝ መልክ ኖሪያታለሁ። ባልደሰትም ሙሉ ነኝ። ቢከፋኝም የተገኘሁት በተረዳሁት ህይወት ውስጥ ነው። ህይወትህ ምን ይመስላል ስትባል መመለስ ካልቻልክ፣ ደደብ ነህ አሊያም እብድ ነህ ወይም አስመሳይ ነህ። በእርግጥ ህይወት እንደገባኝ አልነበረችም። ወድጃቸው ጥለውኝ የሚሄዱ ሰዎች ነበሩ። ህይወቴ የእድል ሾተላይ ነው መሰል የምወዳቸው ሰዎች አይበረክቱም። ...”
ይሄን ሲናገር ጥቁረቱ ይበልጥ ደመቀብኝ.... በጉንጩ የያዘው ጫት አደገብኝ። በእርግጥም ሞገስ ከእነ ድምፁ ናፍቆኝ ነበር። ...
“እኔ ካንተ በላይ መረዳት የለኝም። ግን በማጣት ውስጥ የምታገኘው ንቃት ይኖራል”
“Wow! ይሄን ነበር ልልህ የፈለኩት። ህይወቴ ትርጉም ያገኘው በህይወቴ ውስጥ ትርጉም አላቸው ብዬ የማስባቸውን ሰዎች ካጣሁ በዃላ ነው። ይገርማል አይደል?”
“በጣም”
እያወራን አደርን። ሊነጋ አካባቢ ትንሽ እንቅልፍ ተኛሁ። ስነቃ እረፋድ ሆኗል። ሞገስ የለም። ቁርስ ሰርቶ እንዳስቀመጠልኝ አየሁ። በላሁ እሱን። በእርግጥ ሞገስ ፓስታ መስራት ይችላል። ቤቱን ቆልፌ...ቁልፉን አከራዩ ጋር አስቀምጬ ወደ ቤቴ አዘገምኩ።
ስገባ... ወረቀት ጠረጼዛው ላይ አየሁ። አነሳሁት። የረቂቅ እጅ ፅሁፍ ነው። ብዥ አለብኝ... ለማንበብ ፈራሁ። ቃላት አይኔ ላይ የሚደንሱ መሰለኝ። ከራሴ ጋር ታግዬ ማንበብ ጀመርኩ። እንዲህ የሚል አጭር ፅሁፍ ነው፤
“እንደበደልኩህ አውቃለሁ። ይቅር እንደምትለኝም አውቃለሁ። ውጪ አግብቶ የሚወስደኝ ሰው ዛሬ ይህቺን  አገር እረግጧል። ሁሉም ነገር በእንደዚህ አይነት ክፉ ክህደት ይደመደማል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር። ባልወድህም አዝንልህ ነበራ... ደህና ሁኑ...”
ቃላት ጅራፍ ሆነው ጀርባዬ ላይ አረፉ። የጀርባዬን ሽንትሮች ማየት አልቻልኩም። አላነባሁም። አልሳቅሁም። ዝምታ ውጦኝ ደጋግሜ ፅሁፉን አነበብኩት። ምናልባት ቃላቱን የሚቀይር ድግምት ዓይኔ ላይ እግዜር ካስቀመጠ በሚል። ምንም የተለወጠ ነገር የለም።
አዎ...አንዳንዴ እንዲህ ይሆናል። አንዳንድ የምትወዳቸው  ሰዎች እንደ ክርስቶስ ተሰቅለህ ፍቅርህን እንድትገልፅ እንኳን እድል አይሰጡህም። በእነሱ ህይወት ውስጥ የችግራቸውን ወንዝ መሸጋገርያ የድንጋይ ድልድይ ብቻ እንድትሆን ይፈርዱብሃል። ልታወራቸው ስትጓጓ እንኳን ምግባቸው መሃል እንዳገኙት ፀጉር በመጠየፍ ካጠገባቸው ያርቁሃል።  ፍቅራቸው እርቦህ ስትፈልጋቸው መስጊድ መሃል እንደተገኘ ውሻ በድንጋይ እየወገሩ ያባርሩሃል። ሰው ሆነህ እንደ ድንጋይ የመቆጠርን ሃፍረት መሸከም ካልቻልከው እራስህን ወደ ሞት ገደል ወርውረህ ትገላገላለህ።  ሳትጠረጥር፣ ድንገት ከህይወታቸው ውስጥ እንደ ቆሻሻ ጠርገው ያስወጡሃል።  አንተ የችግርን ወንዝ መሻገርያ የድንጋይ ድልድልይ ብቻ ነህ።  ጀርባዋ ላይ ያየሁት ካርታ ለእኔ ሳይሆን ለእሷ መሸሻ ነበር። ጓደኛዬ የተናገረው ልክ ሆነ አይደል? አንዳንድ ችግሮች መፍትሄአቸው ተመሳሳይ ነው። እሱም መተው ይባላል። እሷን ለመርሳት ስንት ዓመት ይፈጅብኛል? ምናልባት ሶስት አራት...ምናልባት  አስር ... የእሷን ፍቅር ለማምለጥ ስንት የስቃይን ሰርጥ ማቋረጥ አለብኝ? ናፍቆቷን ለመሸሽ የት ድረስ ነው መሮጥ ያለብኝ...  አላውቅም...
ዝምምም....
ወደ ጓደኛዬ እቅፍ ልሸሽ ተነሳሁ... የረቂቅን መሄድ ላልነግረው ለራሴ ቃል ገባሁ።
ዝምምም....Read 246 times