Saturday, 05 November 2022 12:47

“ከእለታት--ግማሽ ቀን” እና አሌክስን በጨረፍታ

Written by  በታምሩ ከፈለኝ
Rate this item
(2 votes)

“--በትረካው ግን አይደለም ከቀደሙት ዘመነኞቹንም ያስከነዳል፡፡ እሱ የሚወዳደረው ገና ከሚመጡት ደራሲያን ጋር ነው፡፡ ለዚህ ይመስለኛል አንዳንዴ ስለ አሌክስ አብርሃም ሳስብ ከቀደሙትና ከሚመጡት ተዳቅሎ የተሰራ የሚመስለኝ፡፡”
  
       መስከንተሪያ
አንዳንድ ደራሲ አለ፤ የሚፅፈው ጉዳይ ውስጡ ተከማችቶ ሳለ ብእር ሲያነሳ እሺ የማይለው፡፡ የግዱን የፃፈውም በተወሰኑ ሰዎች ብቻ ተነቦ የሚወረወርበት (ግን እኮ ጥሩ ጉዳይ ነው ያነሳው)፡፡
ሌላ ደራሲ ደግሞ አለ፤ መፃፍ የሚችል፡፡ የሚፅፈው ጉዳይ ኖረም አልኖረም ልክ ብእሩን ሲያነሳ ቃላት የሚታዘዙለት፡፡ አእምሮው ውብ ገለፃ አፍልቆ ፃፍ የሚለው፡፡ ይህ አይነቱ ሰው ምንም ቢፅፍ ይነበብለታል፡፡ (እማዬን!)
ደራሲ እነዚህ ሁለቱን አጣምሮ ይይዛል፡፡ ጉዳዩንም አፃፃፉንም፡፡
“ኪነት ጸጋ ናት!” ይላሉ መምህራኑም ባለፀጋዎቹም፤ ያው ከፈጣሪ የምትሰጥ እንጂ በትግል እማትመጣ ለማለት ነው፡፡ አፃፃፉ ፀጋ ነው ብንል እንኳ የሚፃፈውን ጉዳይ ማወቅና መምረጥ  ግን ትጋትን ይጠይቃል፡፡
 ወደ አሌክስ
ቃላት ታጥበው ታጥነው የሚጠብቁት፤ሊፅፍ ሲዘጋጅ (ሲናገር ሰምቼው አላውቅም) ተመርጠው የሚመጡለት ደራሲ ማነው? ብባል የመጀመሪያው መልሴ አሌክስ ነው፡፡ እያንዳንዷን አረፍተነገሩን በጉጉት አነባለሁ። አንዳንድ ጊዜ ምኑን ከምኑ አገናኝቶ ምስል እንደሚከስት እያሰብኩ እገረማለሁ፡፡ ልጁ ለመፃፍ የተፈጠረ መሆኑን በእርግጠኝነት እመሰክራለሁ፡፡
“ከእለታት ግማሽ ቀን”ን ቀድመው ከታተሙት ስራዎቹ ውስጥ በ”አንፈርስም አንታደስም” ቅር ቢለኝም በሌሎቹ አጨብጭቤያለሁ፡፡ በተለይ በ”ዶክተር አሸብር”፡፡
ስለ አሌክስ ልለው የፈለኩትና ውስጤ የተቀመጠውን አለማየሁ በመጽሐፉ ጀርባ ላይ አስፍሮታል፡፡ ልቀንጭበው፤
“…የአሌክስ አብርሃም ስራዎች ቀላል ከሚመስሉ ጉዳዮች ተነስተው በግል ጉዳይ ላይ እያጠነጠኑ ይቆዩና መጨረሻ ማሰሪያቸው አልያም የሆነ የታሪኩ ክፍል ላይ በውሱንና ድንገተኛ ቃላት ፖለቲክስ፣ ታሪክ፣ ፍልስፍና፣ ስነልቦና፣ እምነት፣ ባዮሎጂ ወይም ኬሚስትሪ በመሆን አጠቃላይ ታሪኩን ወደ አልታሰበ ጉዳይ ይወስዱታል፡፡…”
ይህች አንድ አረፍተነገር የአሌክስን ስራዎች ሁሉ ትገልጻለች፡፡ የአሌክስ ታሪኮች ተራ ታሪኮች አይደሉም፣ ታሪኮቹ ወደሆነ ድንቅ እይታ የሚወስዱ መንገዶች ናቸው፡፡ ግን ደግሞ እራሳቸውን ችለው ሲቆሙ የማይርገደገዱ፡፡ በተለይ ዶክተር አሸብር ውስጥ ያሉ ታሪኮች፡፡
(ስለ ከእለታት… ግማሽ ቀን እያወራሁ ዶክተር አሸብርን ደጋገምኩት አይደል!? ስለምወደው ነው፡፡ በተለይ “እግዚኦኦኦአኦ” የሚለውን ፅሁፍ … በተሰቀለው!)
እስኪ ስለ አዲሱ መጽሐፍ አንዳንድ ነገር እንበል፡፡
የአሌክስ ሴቶች - ከሀኑን እስከ ማምሻ
የአሌክስ ሴቶች ሁለት ጽንፍ ላይ የቆሙ ናቸው፡፡ ወይ ሀኑንንና ዙቤይዳን ናቸው ወይ ደግሞ ማምሻን ናቸው፡፡ (ስሟን  የዘነጋሁት ዶክተር አሸብር ውስጥ ያለች እንደ ማምሻ አይነት መልከ ጥፉም አለች… ያቺ እንደውም ባሏ  ታዝዤሽ ካልሞትኩ የሚልላት) አሌክስ ገለፃ ላይ የሚጠቀመው ግነት አስገድዶት ይሁን አስቦበት የሴቶቹን ውበት ከገለፀ ወይ ተፈልፍለው የተሰሩ ከመልአክት የሚወዳደሩ ውቦች ናቸው፤ አልያም ደግሞ ዲያቢሎስን የሚያስደነግጡ አስቀያሚዎች፡፡ አስቀያሚ ሲሆኑ በማህበረሰቡ ይገፋሉ፤ ቆንጆ ሲሆኑ ይወደዳሉ፡፡ የአሌክስ ሴቶች እንዲህ ናቸው፡፡
ውበትና ማህበረሰብ አተያይ ላይ እያነሳው ያለው ጭብጥ፣ ከዶክተር አሸብር ወደ ዙቤይዳ ሲመጣ በተወሰነ ተደጋግሟል፡፡ ግን ከሁለቱ መፅሐፎች ተርፎ እምብዛም የጭብጥ ለውጥ ሳይኖረው ወደ “ከእለታት.. ግማሽ ቀን” መጥቷል፡፡ ከዚህ ስንነሳ ውበትን በተመለከተ ያነሳው ጭብጥ እያለቀበት ይመስላል፡፡
(የዶክተር አሸብሯ አስቀያሚ የገጠማት እክል መልኩን ቀይሮ ማምሻ ጋር ይመጣል፡፡ በማምሻና የዶክተር አሸብሯ (ስሟን ዘንግቼው ነው) ሴቶች በመልክ የሚለያዩ እራሱ አይመስለኝም። የተገለፁበት መንገድ ግን እጅጉን ይለያያል። ለዚህ ነው አሌክስ ገለፃ ተክኗል የምለው። (አስቀያሚ የሴት መልክ እያነበብን እንኳ የአሌክስ የገለፃ ውበት ይታየናል)
አሌክስ ሶስተኛ ሴት ካለችው ስለ አካላዊ ቁመናዋ ምንም አይባልም፡፡ በስሟ ብቻ የምናውቃት አጫዋች ትሆናለች፡፡
አሌክስ ውስጥ የተደበቀ “ዳንኤል ክብረትነት”
የዳንኤል ክብረት ስራዎች ውስጥ የሚመጡ ታሪኮች ወደ ምክር የሚያንደረድሩ ናቸው። አሌክስ ደግሞ በቀደመው ስራው አለማየሁ ገላጋይ እንዳለው፤ የማይነካው ነገር የለውም፡፡ ታሪክ ነሽ ፍልስፍና ፖለቲካ ነሽ ስነልቦና ብዙ ነገር ይነካካል፡፡ እዚህኛው መፅሐፉ ላይ ግን የቀደመ አቅሙ እየፈሰሰ ሊመክረን ዱብ ዱብ ማለት ጀምሯል፡፡
እንደውም በመፅሐፉ ውስጥ ዘለግ ያለው ታሪክ የመፅሐፉም ርእስ የሆነው ከእለታት … ግማሽ ቀን ነው፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ መሃሪ ልጅቷን እንደደፈራት እንዲሰማን አድርጎን ከመጣ በኋላ እውነታውን የምናውቀው መጨረሻ ላይ ነው፡፡ ሆኖም ግን በመጨረሻዎቹ ገፆች አሌክስ “የመጠጥን አስቀያሚነት በፌስቡክ ለነገርኩት ህዝብ እንዲህ በግልጽ አልነግረውም፤ ትንሽ ቀየር ላድርገው” ብሎ በሚመስል መልኩ ደፋሪውን ይቀይርልናል፡፡ ምክሩን በቀጥታ ከማድረግ በዘወርዋራው አደረገው እንጂ መጨረሻ ላይ “ለምን ደፈራት?” ብለን ብንጠይቅ  በስካር የሚል መልስ እናገኛለን፡፡
አሌክስ በፌስቡክ ሁሌ የሚመክረንን አስታወሳችሁት? እስኪ አብረን እንበላት፤  “መጠጥ በየትኛውም መጠን…”
እረጅም መንገድ ሲሄዱ ወለምታ
የአሌክስ እረጃጅም ግጥሞች ይምጡብኝ። ወዮዮዮ.. ሰባቱን ገፅ ግጥም አንብቤ ስጨርስ ሰባት ስንኝ ያነበብኩ ላይመስለኝ ይችላል፡፡ እራሳቸው ስንኞቹ እያንደረደሩ ከምፈልግበት ቦታ ወስደው ያስቀምጡኛል፡፡ ወላ አሁን ያነበብኩትን ሰባት ገፅ ግጥም እዛው ልደግመው እችላለሁ፡፡
ዝርው ፅሁፍ ላይ ግን ትንሽ እረዘም ማድረግ ይከብደዋል፡፡ አሁን ከእለታት… ግማሽ ቀን፣ ቀስ ብሎ ይቆማል፣ ዶክተር አሸብርን አንብቡ እስኪ፡፡ በተለይ  ከእለታት… ግማሽ ቀን ብዙ ጊዜ እያለቀ እኮ ነው ታሪኩ በቀጭን ክር ተስቦ የሚነሳው፡፡  በዛ ላይ ወደ መሃል ሲደርስ መተረክ እንኳ ይከብደውና የመጀመሪያ ሃይሉን እያጣነው “አሁን ይሄ ምኑ የአሌክስን አረፍተነገር ይመስላል በስላሴ?” የሚያስብል አረፍተነገር ይገጥመናል፡፡
ማፈትለኪያ
ኢትዮጵያ ዘመናዊውን ሥነፅሁፍ በአፈወርቅ ገብረእየሱስ ጦቢያ ከመታተሙ በፊት አጫጭር ፅሁፎችን የሚፅፉ ደራሲያን ነበሯት። (የቴዎድሮስ ገብሬን “አደፍርስ፤ ዘመናዊው ልቦለድ” የሚል ጥናት አልረሳሁትም፡፡ ግን ጦቢያ ዘመናዊ የሚሆነው ለሥነፅሁፍ ታሪካችን፤ አደፍርስ ደግሞ ለሥነፅሁፍ ጽንሰሃሳብ ነው፡፡ modernism, post modernism, post post modernism ለሚባለው) እነዚህን አጫጭር ታሪኮች ዘሪሁን አስፋው “ልቦለድ አዋጅና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች ከቀደምት የኢትዮጵያ ደራሲያን 1898-1948” በሚል ሰብስቦ በ1995 ላይ አሳትሟቸዋል፡፡ ታሪኮቹ በጣም ደስ ይላሉ፤ ነገር ግን እያንዳንዳቸው ለስብከት የተቀመጡ ናቸው፡፡ ሌብነትን ዝሙትን ሰው አለማክበርን ወዘተረፈ ለማውገዝ የመጡ ናቸው፡፡ ይሰብካሉ ብንል ይገልጻቸዋል፡፡ ትረካቸውም የተረት ቅርፅ አለው፡፡ እነዛ ትረካዎች ለአሁን ዘመን ሰው እንዲህ ነበር ለካ ያስብሉት ይሆናል እንጂ ማርከውት አያነባቸውም፡፡   
የአሌክስ ጽሁፎች ደግሞ ከእነዚህ ጋር የሚመሳሰለው የሞራል ጉዳይ አይሁን እንጂ አለማየሁ እንዳለው በታሪኩ የሆነ ቦታ ላይ አንድ ነገር ማንሳቱ ነው፡፡ ይህን ልምድ በጣም አዘምኖት፣ አሻሽሎት ይሆናል እንጂ ከቀደመው የቀዳው ይመስለኛል፡፡
በትረካው ግን አይደለም ከቀደሙት ዘመነኞቹንም ያስከነዳል፡፡  እሱ የሚወዳደረው ገና ከሚመጡት ደራሲያን ጋር ነው፡፡ ለዚህ ይመስለኛል አንዳንዴ ስለ አሌክስ አብርሃም ሳስብ ከቀደሙትና ከሚመጡት ተዳቅሎ የተሰራ የሚመስለኝ፡፡  


Read 942 times