Saturday, 05 November 2022 12:46

እንደ ባንከ ቤት እስክርቢቶ...

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(3 votes)

       በትረ-ሕይወቱ ጫት ነው ይሉታል_አደምን። በምድረ በዳም ብሆን፤ዳገት ቁልቁለቱም ቢያዝለኝ አልረሳሽም ብሎ ይምል ይገዛታል _ለጫት። “ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” የምትለዋ ጥቅስ ከቤተ-እምነት ሸሽታ ከአደም ጉያ ሥር ከትማለች። አንተነትህን ድርጊትህ ሊገልጸው ለምን ትምል ትገዘታለህ? ላሉት ሁሉ ...ራሴ ዋሽቶኝ ያውቃል አላምነውም ይላቸዋል። እግሩን አጠላልፎ ፤ሁለቱ ጉልበቱ መሬት እየታከኩ ይቀመጣል። ተመሰጥኦውን ለሚቅመው _የሚቃመውም ምርቃናውን ለእሱ ይለዋወጣሉ። ሰው ባይወድለትም በቀን ሦስት ጊዜ ይቅማል ። ሁሉም መጠሪያ አላቸው። አጠቃላይ ሣይንሱን “በርጪዎለጂ” ይለዋል፤ እራሱን ደግሞ “በርጪዎሎጂስት”።
[ሲቅም፤ ውይት ውይቷን ይቀጥፋል፤ ሞትም ወጣት እንደሚመርጥ ሁሉ።]
ሐሙስ ረፋድ ላይ ከበአቱ ወጥቶ ራሱን ፀሐይ ላይ አሰጣ። ምድር መልክ ያለው ወጣት ሲታትር፣ ያልተቀባባችዋን ሴት ሲያሸክሟት፣ በመኪና ላይ ቆሻሻ  ተጭኖ፣ በቆሻሻው ላይ ጽዳቶች ተቀምጠው፣ ከጽዳቶች ልብስ ላይ ትርፍራፊ ቆሻሻ ...ብዙ ብዙ ነገር አይቶ አንገቱን አቀረቀረ። “አላህ ወይ እዝነተትህ እራቀን፣ መች ነው ዱንያ ምትሞላው?” ..ኀዘኑን በእንባ አስተጋባ። ከልቡ ማልቀስን ተቸሮታል። መንዙማ ሲሰማ የሚያፈሰው እንባ ቢጠራቀም ኃይል ያመነጫል።
[ተነሳ። ጀለቢያውን አራገፈ። ቅድሚያ ባያቅድ እንኳን እግሩ ወደ ጀሚላ ይመረዋል። ሕይወትን እዚያ ቢያወራት ይቀለዋልና።]
ጀሚላ በወርቅ ጥርስ የታጀበ ሣቋን ቸራ ተቀበለችው። አተኩሮ አያት። “ጀሚላ፣ በወርቅ ጥርስሽ ለእኔና ቢጤዎቼ ስትስቂ ከምትውይ ሸጠሽ ይህችን የፍየል ጉረንቶ የምታክል ምግብ ቤት ብታሰፊያት አይሻልም?..እያለ...እየቀለደ ተቀመጠ። ጀሚላ ከልቧ ሳቀች። ድሮም አደም ያለበት ቦታ ሐሳብና ሳቅ ይደራል ። ዛሬ ግን ያለወትሮው ግንባሩን ቋጥሮ ገባ። በራሱ ቀልድ የሚስቅ ሞኝ ነው ይላል ዘወትር። ቢሆንም ግን እንደዛሬው “ሃምሌ ፊት” ይዞ አያውቅም።
“አደም”
ስለጨነቃት ነው የጠራችው። “ከዚህ ፊትህ ጋር እኮ አንተዋወቅም። ምነዋ ምን ነካህ አደሜ...”
“ጀሚላዬ ታውቂ የለ አይጎድልብኝም። ስለ ሰዎች እየገደደኝ ነው።”
“እንኳንም ያልከፋህ። እሱማ ልክ ነህ በእምነታችን መተዛዘን ይደገፋል”
[ፌስታሉን ከጀለቢያው ኪስ አወጣ። እየቀነጠሰ ወደ አፉ ይለግት ጀመር። ምግብ ሊበሉ የሚመጡ ቀንበላዎች እየተጠቋቆሙ ይፈጉበታል።]
ጀሚላ የሸራ ምግብ ቤት በመክፈቷ የብዙ ድሆችን ጉሮሮ ዘግታ ትውላለች። በስመ ሆቴል የምግቡ ጣዕም ሳይታወቅ ሃላል በሚያስከፍሉት ዓይን የጀሚላ ሸራ ገነት ናት። ሽሮ እና ዘመዶቿ በሸራ ቤት ውስጥ ይጥማሉ። አጀኒ፤ በቅናሽ ዋጋ፤ ረሃቤን ልውጋ ብሎ ደንበኛዋ ከሆነ ቆይቷል። ግንበኛ ነው። ድንጋይ ሲከረክም ይውላል፤ የሰው ድንጋዮችን ራሱን ጨምሮ መከርከም ነው የተሳነው። አቧራ ለብሶ፣ ዱቄት ውስጥ የከረመች ዓይጥ መስሎ፣ ምሳ ዕቃውን አንጠልጥሎ ወደ ጀሚላ ይኼዳል። ምሳውን በያዘ ቀን ከጀሚላ ሻይ ይገዛል _ምግቡ እንዳያንቀው። ምሳ ካልያዘ እድሜ ለጀሚላ በቀላል ብር ዋጅማ የነፋው በሬ መስሎ ይመለሳል...።
‹‹አደሜ እንዴት ዋልክ››
አጀኒ ነው። በእጁ መከረኛዋን ምሳ ዕቃ ይዟል። አደም ለአጀኒ ምሳ ዕቃ “ማዘንጊያ” የሚል ሥም አውጥቶላታል። ረሃቡን የሚዘነጋባት፣ የሚረሳባት በሚል ምስጣሬ ...
‹‹እንዴት ዋልክ አጀኒ ወዳጄ። እኔ ከጫት አንተም ከእመጫት አንርቅ ››
አጀኒ ከት ብሎ ሳቀ።
‹‹ፈታኋትኮ ...እሙት አደሜ ፈታኋት።››
‹‹ድሮስ! ወንድ ልጅ እስኪሰጠው ነው ፍቅሩ። ከሰጠችው በኋላማ ዞሮ ማያ አንገት የለውም።››
‹‹እንደሱ አይደለም አደሜ። ስንጋባ በእኔ ቡክ የተቀመጠ  ብር ነበር። ከተጋባን በኋላ ብርህን በጋራ ቡክ እናስገባው አለች። ፈታኋት።››
‹‹“አንድ ላይ እያለን ተለያይተናል” ማለት ይኼ አይደል። ደግም አላደረግክ። ይችን ማዘንጊያህን ታዲያ ማን ነው ምሳ እየሞላ የሚሰጥህ..?››
‹‹አዲስ ሴት ተዋውቄ እሷ ነች የምትቋጥርልኝ። ልንጋባ ነው በቅርቡ። ደግሞ ሐብታም ናት። እሷን ካገባሁ ደሃ አልሆንም _የእሷ ብር አለ ››
አደም “የአላህ” እያለ ሳቀ። ተገራረመ።
‹‹ደሃዋን አግብተህ ቡኬን አትጋሪም እንደ አልካት ሁሉ ሃብታሟን ስታገባ ቡኬን አትጋራም እንደምትባል አልገመትክም?...ደግሞ ወላሂ እመነኝ” በሰፈሩበት ቁና መሰፈር አይቀርም”››
አጀኒ ደነገጠ። ማዘንጊያው የያዘችውን ጠራርጎ በልቶ ወጣ። ሲበላ ያንቀው የነበረው  ዛሬ ሻዩን እረሳ። ወደ ግንቡ..ወደ ማይናገረው...ወደ ህንጻው...ጥፋተኛ ወደማይለው ሔደ። ሰው ኹሉ ወቀሳን ከልቡ ይፈራል።
ጀሚላ ትጣደፋለች። አንዱ መጥቶ ዓይነት፣ ሌላው ፓስታ፣ ሌላው ድንች፣ ሌላው ፍርፍር...። ቤቷ አስር ሰው ትይዛለች፤ አንዷ ለአደም የተተወች ናት። ወንበሮቿና ጠረጴዛዎቿ ተመጣጣኝ አይደሉም፤ ጓዳ ጎድጓዳ የላት የምትገርም ቤት ናት። ላይዋ ሸራ ድልድሏ አፈር። የሚመጡት ሁለ በሥራ የዛሉ ስለሆኑ የጨበጡት ብርጭቆ ቢያመልጣቸው እንኳ አይሰበርም። አፈር ነውና ድልድሉ። ወድቆ መነሳት ሲኖር በሕይወትም ያስደስታል። ቤታችን ሁሉ ወድቆ የማይነሱበት እየሆነብን ነው እንጅ ይላል አደም። በስሚንቶ ወለሎ፤ ሕይወትን ሲመስላት።
ድንገት፣ ረጅም ጠይም ልጅ በሸራ ቤቷ በር ውልብ አለ። የአደም ልጅ ነው። አደም ዓይቶት ኖሮ ጠራው። በኋላ ሐኪም ቤት እንኼዳለን። የትም እንዳትኼድ ሲል የዛቻ ጣቱን ነቀነቀበት። ልጁ ተኮሳተረ። ተሽሎኛል የሚል ቃል በተደጋጋሚ ወረወረለት። አደምም “ትወጋለህ” ሲል ቁርጡን አሳወቀው።
 ጀሚላ ሥራዋን እያጣደፈች ...
‹‹ልጅህን ምን አመመው አደሜ›› አለችው።
‹‹ጉርምስና›› (ሲስቅ የተፈጨ ጫት  አመለጠው)
‹‹የዋህ ልጅ አይደል እንዴ?››
‹‹የዋህ አልሽ? ልብ አርጉ እናንተ ቀንበላዎች “እንግዲህ ልጅህ እንዲህ አድርጎኝ “የሚል ስሞታ እንዳታመጭብኝ...››
‹‹ኧረ ቀና ብሎም አያዬኝ ››
‹‹እኔ አባቱን ግን ቀና ብሎ አየኝ። አሁን የእኛ ኑሮ ኑሮ ነው ጀሚሌ? ለፖለቲከኞች፤ በገመድ ታሰረን የምንውል ፣የኼደ የመጣው  የሚጽፍብን፣ ወጭ ገቢያቸውን ለማስተካከል ጫንቃችንን የሚጫኑን፣ ሲሹ የሚያነሱን፣ ሲሹ ደግሞ የሚጥሉን...ሌላ ፈትቶ እንዳይወስደን የሚያስሩን፣ እነሱ ጋር እንዳንዞር የማይፈልጉን .. የባንክ ቤት እስክርቢቶ ከሆንን ቆየን። ቢያንስ በልጆቻችን አንከበር እንዴ?››
ጀሚላ ዓይኗን ከድስቷ አንስታ ወደ አደም ላከችው። “እንደ ባንክ ቤት እስክርቢቶ በገመድ ታስረን” አልክ አደሜ ..ሆ ...ፈገግ ..ፈገግ፣ ሳቀች።
[አደም ወደ ጫቱ አቀረቀረ፤ ሦሥት ቅጠሎችን ይዞ ቀና አለ። የጀሚላን ጉንብስ ቀና ማለት አየ። መታከት አለ በልቡ፤ ምናልባትም ቂጡን ሲያለፋ የሚውል ባል እያላት ትቅመደመዳለች እያለ ይሆናል።]
ቡግራም ፊቱ ሳይጎረብጣቸው የበቀሉ ጺሞቹ በንፋስ ይዳራሉ፣ ይጠላለፋሉ፣ ይቆላለፋሉ። ስግደት ካበለዛት ግንባሩ ራቅ ብለው የመሸጉ የራስ ጠጉሮቹ ያስቃሉ። ጫት ለምን ይጠቅማል? ሲሉት “እንደ ዓላማችሁ” በማለት ይታወቃል። ለመጀዘብ ከቃማችሁት ለመጀዘብ፣ ለመጻፍ ከሆነ ለመጻፍ፣ ለማንበብ ከሆነም ለማንበብ... ብሎ ይደመድማል። ከልጁ ጋ ብዙ አይስማሙም። ልጁ የኳስ ሱስ አለበት። በዚህም የተነሳ ከአባቱ ኪስ ሳንቲም ያንጎዳጉዳል። “የአባዬ ኪስ ጫማ ሰቅሏል” ይላል ፈትሾ ሲያጣ። ጉርምስና ላይ ስለሆነ ትዕዛዝ ጠልቷል። ከአደም ጋር ትኩር ጥምድ የገቡት ለዚህ ነው።
‹‹አደሜ፤ ለምን ተከዝክ? ተጫወት እንጅ... ››
ከድብርቱ ነቃ አለ_በድንጋጤ። ሐሳቤ ሁሉ ተሰርቋል። በዚህ  ፖለቲካው እስክናልቅ የሚቀርጸን እርሳስ አድርጎ ይዞናል፣ በዚያ የልጅ አለመታዘዝ የመጨረሻው ዘመን መሆኑን እያሳበቀብኝ ነው...ወዴት ይደረሳል (በውስጡ ሊኖር የሚችል ሐሳብ ነው)
‹‹እሺ እሺ ጀሚላዬ።ይኼን ልጅ መርፌ ማስወጋት አለብኝ..ብዬ እያሰብኩ ነበር››
‹‹እንዴ ለምን?››
‹‹ታሞ ነበር በዛ ሰበብ ጥጋቡ ተንፈስ እንዲልለት። አይ ይወጋ...ይወጋ እንጅ ››
‹‹እህ..ተው እንጅ አደሜ..››
‹‹ይኸውልሽ ጀሚላ፣ ሰውዬው ሐኪም ቤት ሄዶ ምን አመመህ ሲለው መላ አካላቴን ይለዋል። ሐኪሙ ትንሽ ያስብና ወደ ቤትህ ሔደህ ውጭ እደር ይለዋል። ሰውዬው ውጭ አድሮ ተመልሶ ይመጣና ብርድ መታኝ ዶ/ር ይለዋል። ሐኪሙ ምን ያለው ይመስልሻል?...ጥሩ! ለብርዱ መድሐኒት እንካ።››
‹‹ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው ይላሉ እቴ። እንዳሻህ አደሜ...›› ከልቧ አይደለም።
‹‹በፍቅር ያበደ ሰው የሚድነው ያፈቀራትን ካያት ነው። ጥጋብም የሚተነፍሰው ጥጋበኛ መርፌ ሲጥልበት ነው... ይወጋ!›› ፊቱ ላይ የማያቃጥል እሳት ይታይበታል።
‹‹ያኛው..ትልቁ ልጅህ ግን የት ደረሰ አደሜ›› (ስርቅ አርጋ እያየች)
‹‹የእሱን ነገር ተይው። ስታድግ “አገር ትለውጣለህ” እያልኩ ነበር ያሳደግኩት። ይኸው አገር ለውጦ አረብ ሄዷል...›› (ቂም ፊቱ ላይ ይነበባል)
ጀሚላ በሰው ቤት ጉዳይ መፈትፈቱ ከብዷት ስራዋ ላይ አተኮረች። እኛ ኗሪዎች፣ እኛ ተመሪዎች፣ የባንክ ቤት እስክርቢቶ ነን፤ በሲር የታሰርን... ያላትን እያመነዠከች ፍርፍር ታፈረፍር፣ ፓስታ ትፐሰስት (?) ጀመር። ድንች ያዘዘው፣ ጠና ያለው ሰውዬ አደምን ወሬ አስቀጠለው። ተመሳሳይ ብሶት ቢኖርበት ጊዜ መሰለኝ። “ሁሉንም ቢያወሩት ሆድ ባዶ ይቀራል” አለ ተናገር እያለ የገፋፋውን ስሜት ለመቋቋም። ለማንኛውም ትሰማለህ ሼህ አደም... እንዳንተ የጨነቀውን ሰው ...
[ሚስትህ ከፋች ቢሉት እፈታት አለ፣
ላምህ ከፋች ቢሉት እሸጣት አለ፣
ልጅህ ከፋች ቢሉት ግን፤ አሁን አገኘኸኝ አለ ይላሉ።]
የልጅ ክፉ የት ይጣላል? ከአንተ ወገብ ከፍሎ የወጣ ዘር፣ ከእናቱ ቦታ ተውሶ ያደገ ልጅ ከከፋ ምን መፍትሔ አለው? አንድዬ መርቆ ይስጥ እንጅ የአንተስ “ይወጋ” እያሉ መብሰልሰል ለውጥ ያመጣል  ብሎ መጠበቅ ዘበት ነው ብሎ ወጣ ።ጠና ያለው _ዕድሜ ጠገቡ ሰውዬ። አደም ይቆርብ ይነግስበት የሚመስለውን ጫቱን ጣል አድርጎ “አሁን አገኘኸኝ” ማለቱን ቀጠለ...

Read 345 times