Saturday, 12 November 2022 11:36

ታጣቂዎች ለዜጎች ደህንነት ስጋት መፍጠራቸው ተገለፀ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

   የወታደራዊ ኦፕሬሽኖችና የህግ ማስከበር ስራዎች እየተሰሩ ነው ተብሏል
                   
       በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ነፍጥ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በዜጎች ደህንነት ላይ ትልቅ ስጋት መፍጠራቸውን የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱአለም ገልጸዋል።
ችግሩን ለመፍታት ወታደራዊ ኦፕሬሽኖችና የተለያዩ የሕግ ማስከበር እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑንም ተናግረዋል። ሚኒስትሩ ከትናት በስቲያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጪ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የሚኒስቴር መ/ቤታቸውን የ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ በአገሪቱ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የታጠቁ ሃይሎች ለዜጎች ደህንነት ከፍተኛ ስጋት ሆነዋል። በሸኔ እና በሌሎች ነፍጥ ታጥቀው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ሳቢያ ዜጎች ለከፍተኛ ጉዳት ተዳርገዋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ታጣቂዎቹ በተለይም በምዕራብና በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኙ አካባቢዎች ላይ በስፋት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነም ገልጸዋል።
ታጣቂዎቹ ጽንፈኞችና ፍላጎታቸውን በሃይል ለመጫን የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ናቸው ያሉት የሰላም ሚኒስትሩ፤ እነዚህ አካላት ለዜጎች ደህንነት ትልቅ ስጋት መፍጠራቸውን ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹ ያላቸው የፖለቲካ ፍላጎት በግልጽ የማይታወቅ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ብናልፍ፤ ንፁሃንን በግፍ መጨፍጨፍ፣ አስገድዶ መድፈርና መሰል ወንጀሎችን በንፁሃን ላይ እየፈጸሙ እንደሆነና በዚህ መንገድ የሚመጣ የፖለቲካ ድል በፍጹም እንደማይኖርም አሳውቀዋል።
መንግስት እነዚህ ታጣቂዎች በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እያደረሱ ያሉትን የጅምላ ግድያና የደህንነት ስጋት ለማስቀረት በሰላም ሚኒስቴር ብቻ ሳይወሰን ከመከላከያ ሰራዊትና ከህግ አስከባሪ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። መንግስት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትሩ ይህ ጥረት ውጤት ባላመጣበት ጊዜ ግን የዜጎችን ደህንት የመጠበቅ ኃላፊነት ስላለበት ወታደራዊ ኦፕሬሽንና የተለያዩ የሕግ ማስከበር ስራዎችን ለማከናወን እንደሚገደድ ተናግረዋል። እስከ አሁንም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወታደራዊ ኦፕሬሽኖችና የህግ ማስከበር ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ለአባላቱ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ነፍጥ አንግበው የሚንቀሳቀሱት ታጣቂ ኃይሎች የዜጎች ደህንነት ስጋት ሆነው መቀጠላቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

Read 12441 times