ከዕለታት አንድ ቀን የተራቡ ጅቦች በየገደላ ገደሉ እየተዘዋወሩ የሚበላ ነገር ሲፈልጉ አንድ እጅግ ግዙፍ ዝሆን አዘቅት የሆነ ገደል ውስጥ ወድቆ ሞቶ አዩ።
አንደኛው ጅብ፤
“ጎበዝ ምን ትጠብቃላችሁ፤ እንግባና እንሸክሽከው እንጂ!” አለ።
ሁለተኛው፤
“ምን ጥርጥር አለው። ገብተን እንዘልዝለው እንጂ!”
ሦስተኛው፤
“ላሜ ወለደች ማለት ይሄ’ኮ ነው!”
ከሞላ ጎደል ሁሉም በሀሳቡ ተስማምተው ድጋፋቸውን ገለጡ።
ከሁሉም ወጣት የሆነው አንድ ጅብ ግን ተቃወመ።
“ምክንያትህን አስረዳ?” ተባለ።
ወጣቱ ጅብም፤
“እርግጥ ነው ስለራበን ገብተን መብላታችን ትክክል ይሆናል። ሆኖም ሙዙን ስታይ መዘዙንም እይ የሚባል ተረት አለ። ከበላን በኋላ ሆዳችን ሲሞላ ከዚህ አዘቅት ገደል እንዴት ሽቅብ ለመውጣት እንችላለን የሚለውንም አስቡ” አላቸው።
አንደኛው ለመብላት የቸኮለ ጅብ፤
“ኧረ ቶሎ እንግባ፤ እንብላና እዚያው ዘዴ እንፈልጋለን” አለ።
ሁሉም ተስማሙና እየተንደረደሩ ገቡ። ያ ወጣት ጅብም ምርጫ ሲያጣ ከወገኖቹ እንዳይለይ ብሎ አብሮ ገባ።
ያን ግዙፍ ዝሆን ቡጭቅጭቅ አድርገው ነጩት። ተቀራመቱት።
ሆዳቸው ሞላ! ጠገቡ።
ቀና ብለው የገደሉን አፋፍ ሲያዩት ለመውጣት የማይመች አቀበት ነው።
“ቀስ ብለን ነገ ከነገ ወዲያ ዘዴ እንፈልጋለን። የተራረፈውን አጥንት እየቆረጣጠምን እናስብበታለን” ተባባሉ፤ ተስማሙ!
ቀናቱ አንድ ሁለት እያሉ ሲገፉ ረሀብ መጣ። ደክሟቸው ተኙ። እኩለ ሌሊት እንዳለፈ አንዱ የነቃ ጅብ ጎኑ ያለውን ጅብ ቀስቅሶ፤ “በረሀብ ከምንሞት በጣም ያንቀላፋውን ጅብ ለምን ቅርጭጭ አናደርገውም?”
“እውነት ነው! እውነት ነው!” ብለው ተመሳጥረው ያንን እንቅልፋም ጅብ ሰፈሩበት! በየሌሊቱ ትርዒቱ ተደጋጋሚ ሆነ።
በመጨረሻ ሁለት ብቻ ቀሩ።
እየተፋጠጡ ማደር ሆነ።
በመካያው ግን አንደኛው ደከመና እንቅልፍ ጣለው። የነቃው የተኛውን በልቶ ለጥቂት ቀናት ነብስ ዘራ።
ሆኖም በመጨረሻ እንቅልፍ ጣለው። በዚያው እንደተዝለፈለፈ አንድያውን አሸለበ! ህይወቱ አለፈ።
***
ጅብ መቼም ጅብ ነው። አበው ሲተርቱ “ከጅብ ጅማት የተሰራ ክራር ቅኝቱ ´ልብላው ልብላው”´ ነው ይላሉ። አገራችን ኢትዮጵያ የጅብ ደሀ ሆና አታውቅም። የቀን ጅብም የሰው ጅብም፣ ነባር ጅብም መጤ ጅብም አስተናግዳለች። ያም ሆኖ አስፈጻሚና ክትትል አድራጊ አጥታ ነው እንጂ ዕቅዶችም አላጣችም!
ወጣትና አዋቂ ልጆችም አሏት። ከጥንት ከዘመነ-ስካውት ጀምሮ፣ የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር (ወወክማ) የወጣት ሴቶች ክርስቲያናዊ ማህበር (ወሴክማ) ውሎ አድሮም፣ አኢወማ (የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ወጣት ማህበር) እና የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች ማህበር (አኢሴማ) በወቅቱ የነበረው ትኩስ ኃይል ማሰባሰቢያ ነበሩ። በዚህ ላይ የተደራጁት የፖለቲካ ፓርቲዎች የየራሳቸው የወጣት ክንፍ ነበራቸውና የወጣቱን ጉልበት ይዘዋል። አሰልፈውታል። በየፊናቸው ኢትዮጵያን የተወሰነ ርቀት አስኪደዋል። የተወሰነ ርቀትም የኋሊት አንደርድረዋታል። የብዙ ልጆቿ ደምም ፈስሶባታል። ከባባድ መስዋዕትነት ተከፍሎላታል! “ጉዟችን ረጅም ትግላችን መራራ” ተብሎላታል። መራራ ከሆነ አጠር ይበል እንጂ ለምን ረጅም ይሆናል? ተብሎም ተሹፎባታል። ይህ ሁሉ ታልፎ ሲያበቃ ዛሬ ደግሞ አዲስ ጦርነት፣ አዲስ መፈናቀል፣ አዲስ ስደት እንዳመረቀዘ ቁስል እየደገመን ነው! የአንድ አገር ልጆች ደም እየፈሰሰ ነው።
“እንደካራ ማራ፣ እንደ ጭናክሶን
ሰሜንም ደማቅ እሳት አሳየን!”
ብለን ዘምረን ያቀጣጠልነው እሳት በተለያየ አቅጣጫ እያዳረሰ ይገኛል። መላና መፍትሄ ያጣው ህዝብ በከንቱ ህይወቱን መገበሩ ያሳዝናል። የተባበሩት መንግስታት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ ወዘተ ከጀርባ የሚጭሩትን እሳት ከፊት ለፊት እናጠፋለን በሚል እንደተለመደው ድርድር…ድርድር እያሉ ተደርድረው፤ ጉብ - ቂጥ ይላሉ፡፡ መንግስታችንም ያው እንደተለመደው እጁን ተጠምዝዞ መፈራረሙን ይያያዘዋል። የማይነጥፍ የፖለቲካ አዙሪት! ለዘመናት የማይዘጋ በር! አገራችንም ዕቃውን እንዳላወጣ ቤት ለቃቂ፤
“እንኳን ቤትና የለኝም አጥር?
እደጅ አድራለሁ ኮከብ ስቆጥር”
እያለች መዝፈኗን ትቀጥላለች! መታከትን የማያውቅ ረዥም ሙሾ!
ዕርቅና ድርድር የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ መሆኑ የማያጠያይቅ መሆኑ ግልጽና ይፋ የወጣ ጉዳይ ሆኗል። ጊዜ የማይፈታው ጉዳይ የለም! እያንዳንዱ ቀን አንዳንድ ለውጥ ማርገዙ እየታየ ነው። ይህም በጎ ምልክት ነው! ቶሎ-ተናኝ (Volatile) በሆነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ፤ ያሁኑ መልካም ጅምር ይመስላልና፣ ወጣቱ ትውልድ ልቡና ውስጥ እንዲሰርጽ ተስፋ እናደርጋለንና፡-
“ዕቅድህ የ1 ዓመት ከሆነ (ጤፍ) ሩዝ ዝራ
ዕቅድህ የ5 ዓመት ከሆነ ባሕር ዛፍ ትከል
ዕቅድህ የዘላለም ከሆነ ልጅህን አስተምር”
የምንለው ለዚህ ነው!!
Saturday, 12 November 2022 11:40
ዕቅድህ የ1 ዓመት ከሆነ (ጤፍ) ሩዝ ዝራ ዕቅድህ የ5 ዓመት ከሆነ ባሕር ዛፍ ትከል ዕቅድህ የዘላለም ከሆነ ልጅህን አስተምር
Written by Administrator
Published in
ርዕሰ አንቀፅ