Saturday, 12 November 2022 11:43

“አማሪካን አየን ከእግር እስከ ራሷ...”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

 “ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል... በተለይ እነኚህ የቦተሊካ ሰዎቻችን በሆነ ነገር ባኮረፉ፣ በተኮራረፉ ቁጥር የፈረንጅ በር ማንኳኳት መቼ ነው የሚለቃቸው! ኮሚክ እኮ ነው... “ይህን ነገር ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ እንዲያውቀው...” ምናምን የሚሉት ነገር አላቸው፡፡ የምን ጉልበተኛ ፍለጋ ዓለምን ማሰስ ነው!--”
   
       እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ...የሰሞኑን የአሜሪካን ምርጫ አያችሁልኝ! የሚገርም እኮ ነው፡፡ የምር በፊት እኮ...አለ አይደል...የ‘አማሪካን’ ምርጫ ማለት የዲሞክራሲያዊ ምርጫ ጥግ፣ እንከን የሌለው፣ ለሌሎች ሁሉ ምሳሌ የሚሆን ምናምን አድርገን ነበር የምንቆጥረው፡፡ እናማ...አሁን ፖለቲከኞቻቸው ምን የሚሉት ቡዳ ቢበላቸው ነው በአንድ ጊዜ እዛ ታች ወርደው ዘጭ ያሉት! ነገርየው በአንድ ጊዜ የሆነ ሳይሆን እኛ በውስጣችን ስለን የነበረው ስዕል ያልተሟላ ስለነበር አንጂ ይህን ያህል የተለወጠ  ነገር ኖሮ አይደለም፡፡ ዋናው ነገር ምን መሰላችሁ...የዓለም ሁኔታ እየተለዋወጠ ሲመጣና “እኛ ዘንድ አይደርስም” ያሉት ነገር ሁሉ በራቸውን ማንኳኳት ሲጀምር ምድረ ‘ቦተሊከኛ’ እየተፋቀ ቁጭ አላታ!
“እጅግ ወሳኝ የሆነ ምርጫ...”
“የአሜሪካንና የዓለምን እጣ ፈንታ የሚወስን ምርጫ....”
“አሜሪካን ከፈላጭ ቆራጭ አስተዳደር ለማዳን የሚደረግ ምርጫ...”
ያልተባለ ነገር አለ እንዴ! እንደውም ከባይደን ጀምሮ ዲሞክራቶቹ የሚደጋግሙት መፈክር ቢጤ ነገር “ዲሞክራሲ አንደር ትሬት’ (“ዲሞክራሲ በአደጋ ላይ” እንደማለት) ሲሆን፣ የሪፐብሊካኖቹ ዋነኛ መፈክር ደግሞ ‘ሴቭ አሜሪካ’ (“አሜሪካን እናድናት” አይነት ነገር) ነበር፡፡ ጽንፎቹን አያችሁልኝ! ሁለቱም ወገኖች “ለሀገሪቱ ችግሮች መፍትሄዎች እኛ ብቻ ነን፣” ባዮች ናቸው፤ ልክ እንደ እኛ ሀገር ማለት ነው፡፡ እኛ ሀገር መቶ ምናምኑ ቡድን ሁሉ “የኢትዮጵያ መዳኛ እኛ ብቻ ነን!” ባይ አይደል! የምር ግን...በዚህ ጉዳይ ‘ጊነስ’ ምናምን የማንገባሳ!
ደግሞላችሁ... ሪፐብሊካኖቹ ሲሰብኩ “ዴሞክራቶቹ በምክር ቤቶቹ አብላጫ ደምጽ ይዘው ከቀጠሉ የአሜሪካ ውድቀት ብቻ ሳይሆን የዓለም ጦርነት ሁሉ ሊነሳ ይችላል፤” ይላሉ፡፡ ዲሞክራቶቹ ደግሞ “ሪፐብሊካኖች አብላጫ ወንበር ከያዙ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይሸረሸራሉ፣ ዜጎች የሚያገኟቸውን አገልግሎቶች ሁሉ ያጣሉ፣ የህግ የበላይነት ይፈርሳል፣” አይነት ነገር ይላሉ፡፡ እና ከእኛ ምን ለያቸው..እነሱ ‘ቺክን በርገር’፣ እኛ ‘እርጥብ’ ከመብላታችን በቀር! ቂ...ቂ....ቂ...
የብዙዎቹ ችግር ምን መሰላችሁ..ራሳቸውን ከምንም በላይ አደርገው መቁጠራቸው፡፡ ሰሞኑን ግሌን ቤክ የተባለ ታዋቂና ወግ አጥባቂ የሬድዮና ቴሌቪዥን አቅራቢ ፍርጥ ነው ያደረጋት...“እኛን ከሌሎች ጋር ለምን ያወዳድሩናል፣ እኛ የተለየን ነን፣” አይነት ነገር ነው ያለው፡፡  አይ አማሪካን! ስትፋቂ ለካስ እንደዚህ ነሽና! ይሄ ‘ሚድተርም’ የሚሉት በምርጫ ዘመን መሀል ላይ የሚያካሂዱት ፉክክር ጉድ ሲያሳየን ሰነበተ እኮ! የምር ግን... ሁኔታው እንዳሳሰበን መግለጫ ያላወጣንሳ! አለ አይደል...“አሜሪካ ውስጥ ህዝቡ ተረጋግቶ ድምጽ እንዳይሰጥ የሚደረጉ ቀጥተኛና የተዘዋዋሪ ጫናዎችን እናወግዛለን!” የሚል አይነት፡፡ አሀ...የእኛ ሲሆን በመግለጫ መአት አይደል እንዴ መከራችንን የሚያበሉን! “አይደርስ መስሏት በምን ምን አለች...” ይባል የለ!
የአሜሪካ ሪፐብሊካኖች አብዛኛዎቹን የምክር ቤቶቹን መቀመጫዎች ጠቅልለው እንደሚያሸንፉ ሲዝቱ ነበር፡፡ “ሬድ ዌቭ” ነበር ሲሉ ነው የሰነበቱት፡፡ አለ አይደል... “በማዕበል እናጥለቀልቀዋለን” አይነት ነገር። ሚዲያዎቻቸውንም ከነምናምናቸው አየንላቸው፡፡ ቅልጥ ብለው ወገን ይዘው ነበር እኮ መከራቸውን ሲያዩ የሰነበቱት፡፡ አይ ነጻ ሚዲያ!
ደግሞላችሁ... እነኚህ የህዝብ አስተያየት አሰባሳቢ ድርጅቶችማ “ዲሞክራቶች ወዮላችሁ! ከሁለቱም ምክር ቤቶች ተጠራርጋችሁ ትወጣላችሁ!” ምናምን ሲሉ ነበር... የሆነ አይመስልም እንጂ፡፡ እናላችሁ... በትንሽ፣ በትልቁ ‘ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ’ ምናምን የምንለው ነገር በዚህ ዘመን ቀሺም ነገር ነው ለማለት ያህል ነው፡፡ ልክ ነዋ...አይደለም ስለእኛ ጉዳይ ሊጨነቁ ቀርቶ ይኸው ምድረ አውሮፓ፣ ምድረ አሜሪካ፣ ምድረ ምናምን በስንትና ስንት ችግር ተጠፍሮ የሚይዘው የሚጨብጠው ጠፍቶት የለ እንዴ!
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል... በተለይ እነኚህ የቦተሊካ ሰዎቻችን በሆነ ነገር ባኮረፉ፣ በተኮራረፉ ቁጥር የፈረንጅ በር ማንኳኳት መቼ ነው የሚለቃቸው! ኮሚክ እኮ ነው... “ይህን ነገር ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ እንዲያውቀው...” ምናምን የሚሉት ነገር አላቸው፡፡ የምን ጉልበተኛ ፍለጋ ዓለምን ማሰስ ነው!  
ታዲያላችሁ... የአንዳንዶቻችን ነገር በዚህም ዘመን “የእኛ ሙሽራ ኩሪባቸው በእንግሊዝ አናግሪያቸው፣” አይነት እኮ ነው፡፡ በእንግሊዝ አፍ መናገር ኮራ የሚያደርግበት ዘመን አላለፈም እንዴ! እናማ... ዓለም እንዲህ ምኗ ምናምኗ ክፍትፍት ባለበትና ስንት ጉድ እያየን ባለበት አሁንም፣ ፈረንጅ፣ ፈረንጅ የምንለው ነገር ቀሺም ነው፡፡ እኔ የምለው... እንዴት ነው የራሳቸው ሳሎን እንዲህ ተመሰቃቅሎ ስለእኛ ጓዳ ሊጨነቁ የሚችሉት! እነሱ ራሳቸው ከምርጫ ጋር ተያይዞ በአሜሪካ ረብሻ ሊነሳ ይችላል እያሉ፣ በየትኛው የሞራል ከፍታቸው ነው እኛን ሊመክሩን የሚችሉት! ልክ ነዋ! አሀ...አሁንም ፈረንጅ፣ ፈረንጅ የምንል መአት ስላለን እቅጩን መነጋገር ነዋ!
የሚዲያዎቻቸውን ነገርማ  ተዉት፡፡ እኛም  እኮ አናርፍ! ለእኛ የሚመቸን ነገር ካየን በቃ አለቀ፣ እነሱ ከፈጣሪ በታች ያሉ ሀቀኞች ናቸው። 
“ማታ ሲ.ኤን.ኤን ላይ የተላለፈውን ዶኪዩመንታሪ አየኸው!”
“አላየሁትም፡፡ ስለምን ነበር?”
“ዩቲዩብ ፈልገሀ እየው፡፡ እንዴት አሪፍ ነገር መሰለህ!”
ይህኛው ለእኛ ተስማምቶናል ማለት ነው፡፡
በሌላኛው ቀን ያው ሰው አስተያየት ሲሰጥ...
“ስማ፣ ይሄ ሲ.ኤን.ኤን የሚሉት ጣቢያ... ማታ ያስተላለፉትን አየኸው?”
“አላየሁትም፡፡ ምን አስተላለፉ?”
“የለየላቸው ዘረኞች ናቸው፡፡ እኔ እኮ ድሮም አይመቹኝም ነበር!”
እንዲህ ነው የእኛ ነገር... ሲመቸን ዙፋን ላይ ማስቀመጥ፣ ሳይመቸን አሽቀንጥረን መወርወር።
ወይ አማሪካን...ኮሚክ ነገር እኮ ነው! የምር ግን አሁን፣ አሁን  ከዛ የሚወጡ ዜናዎች እኮ ልክ ስለእኛ ቺስታዎቹ የተሠሩ ሆነው በቴክኒክ ስህተት በ‘አማሪካን’ ስም የተላለፉ ነው የሚመስሉት፡፡ ‘ፌሚን’ (ረሀብ) የሚለውን ቃላ ማመሳከሪያ አድርገው ዲክሺነሪ ውስጥ የከተቱን እኛኑ አልነበር! አሁን እነሱ አንዳንድ ግዛቶች ላይ የ‘ፌሚን’ አደጋ አንዣቧል እያሉ ነው፡፡ የፑቲን ሀገር ቀላል አድርገዋታል!
ስሙኛማ...የሚወራውና የሚሆነው ለየቅል ነው፡፡ እናላችሁ.. ራሳችንን ተንኮለኞች ምናምን እናደርጋለን እንጂ በተለይ ከምዕራባውያኑ የባሰ ስር ለስር የሚሄድ ተንኮለኛ አለ እንዴ! የሆነ ዌብሳይት ላይ ያየሁትን ስሙኝማ... በአሜሪካ ፊትአውራሪነት ሩስያ ላይ የማዕቀብ ናዳ አውርደውባት የለ፡፡ በዚህም በበርካታ የሩስያ ባንኮች ላይ ማዕቀብ ተጥሎ የአሜሪካና የሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት ባንኮች ከእነሱ ጋር እንዳይሠሩ እገዳ ተጥሏል፡፡ ምን ቢሆን ጥሩ ነው...የአሜሪካ መንግሥት ባለስልጣናት በድብቅ ለተወሰኑ የሀገሪቱ ታላላቅ ባንኮች ከሩስያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዳያቋርጡ ነግረዋቸዋል አሉ! ምክንያቱ ደግሞ የምግብ እጥረትና በአንዳንድ ግዛቶች ረሀብ እንዳይከሰት ነው ተብሏል፡፡ ታዲያ ማን ማዕቀብ ጣሉ አላቸው!
“የሰላም ስምምነቱን የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ደግፎታል፣” ምናምን እንላለን፡፡ ዋናውና ቀዳሚው እኛ መደገፋችን ነው፡፡ እንደ እውነቱ ታሪኩ እዛ ላይ ያበቃል፡፡ “ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ” የሚባሉት ጥቂት፣ በጣም ጥቂት ሀገራት ማንኛውንም ነገር  የሚሠሩት ከእነሱ ፍላጎት አንጻር ብቻ ነው፡፡ አለቀ፡፡ ‘አማሪካን’ ያሉ ወዳጆቻችን ሲነግሩን ‘ሜይንስትሪም ሚዲያ’ ከሚባሉት ዋና፣ ዋናዎቹ ስለ ሰላም ስምምነቱ ትንፍሽ አላሉም፡፡ ምክንያቱም እነሱ የሚያተርፉት ነገር የለምና፡፡
 እናላችሁ... “አማሪካን አየን ከእግር እስከ ራሷ” ማለት ዘንድሮ ነው፡፡ የሁለቱ ፓርቲዎች ተወዳዳሪዎችና ደጋፊዎቻቸው እርስ በእርስ ሲሰዳደቡ ስትሰሙ ግርም ነው እኮ የሚለው። ሁለቱም በሀገር አጥፊነት ሲወነጃጀሉ ነው የከረሙት፡፡ ልክ እኮ መሰዳደቡ የምርጫ ዘመቻው አካል ይመስል ነበር፡፡ ደግነቱ ቅኔ አለማወቃቸው! ቂ...ቂ....ቂ...
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 810 times