Wednesday, 16 November 2022 09:54

ልንፋታ ተስማምተናል?!

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  ሊፋቱ መሆናቸውም አስደነገጠኝ!!
ለመሆኑ እርስዎ ትዳርዎት በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው?
በትዳር ውስጥ ካልሆኑም  የእርስዎ ትዳር ምን ዓይነት እንዲሆን አስበዋል?
በእነዚህ ጥንዶች ቤት ውስጥ ነገሮች ጠረናቸውን ቀይረዋል። ትዳሩ ውስጥ ጭቅጭቅ በዝቷል!! አለመግባባትና መጠላላት ነግሷል!! መናናቅ ቤቱን ሞልቶታል!! በትዳር ውስጥ እናገኘዋለን ብለው ያሰቡት መልካም ነገር ሁሉ እንዳሰቡት አላገኙትም፤ ሁሉ ነገር እንደ ጉም በኖ ጠፍቷል!!
በሁሉ ነገር መግባባት አቅቷቸው ለመፋታት ግን ቁጭ ብለው ተስማምተውና ተግባብተው ጨርሰዋል። ለመፋታት የፈጠሩት መግባባትና መስማማት አብሮ ለመኖር ሲሆን ግን ጦርነትና መጠላላት ነገሰበት። ይህን መጽሀፍ ወደ እርስዎ ለማድረስ እያዘጋጀሁ ባለሁበት ወቅት ፍርድ ቤቶች አካባቢ ስላለው የባልና ሚስት ጉዳይ ሳጣራ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፍቺ ጉዳይ ሆኖ ፍ/ቤቶችን አጨናንቆ ይገኛል። በየቀኑ ፍቺ አለ። ያዙኝ ልቀቁኝ ብለው ተጋብተው፣ ሲደባደቡና ሲፋቱ ይውላሉ። አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሰናል!!
ዘንድሮ ልብስ ሲጋባ!! የሙሽራ ልብሶች ተጋቡ!! በወሬና በሶሻል ሚዲያው አጩኸው፣ በመኪና ክላክስ አደንቁረውን መድፍ ተኩሰው አስደንግጠውን፣ የለኮሱት ርችት ብልጭ ብሎ ሳይጠፋ ይፋታሉ!!
ያስታውሳሉ አይደል ሞባይልዎትን ሲገዙት ጋራንቲ  እንደነበረው? ድርጅቱ ምርቱ እንደማይበላሽ እርግጠኛ ስለነበር ለሆነ ዓመት ጋራንቲ ሰጥትዎት ነበር። ጋብቻን የፈጠረው አምላክስ የምን ያህል ዓመት ጋራንቲ ለፈጠረው ትዳር የሰጠው ይመስልዎታል።
ይህን በትክክል ለመመለስ የሰጠንን የትዳር መተዳደሪያ ማነዋሉን ማንበብ ግድ ይላል። አሁን መጽሐፍ ቅዱስ ገልጠን እንያዝ። በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ዋና ትኩረቱ ትዳር አይደለም። ዋና ትኩረቱ አምላክ ከሰው ልጆች ጋር ስላለው ግንኙነትና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የአዳም ዘር በሙሉ ያገኘው ደህንነት ዋና ትኩረቱ ነው።
ነገር ግን ከዚህ ዋና ጉዳይ ባሻገር የሰው ልጆች ኑሮን ትኩረት ሰጥቷል። ትኩረት ከተሰጣቸው ነገሮች ውስጥ ቀዳሚው ደግሞ ጋብቻ ነው። ሌላው መጽሐፍ ቅዱስ የየትኛውም ሃይማኖት የግል መጽሐፍ አይደለም። ለአዳም ዘር በሙሉ ከአምላክ ዘንድ የተሰጠ የተከበረ ስጦታ ነው።
ወደ ዋናው ጉዳያችን እንመለስ። የትዳር መተዳደርያ ደንቦችን እንይ።
መተዳደሪያ ደንብ አንድ
“መፋታትን እጠላለሁ”
ትንቢቱ ሚልክያስ ምዕራፍ 2፤ ከቁጥር 16
ጋብቻን የሰራው አምላክ፤ ለጋብቻ የሰጠው ጋራንት የእድሜ ልክ ዘመን ነው። ፈጣሪ ጋብቻን ሲፈጥረው መፋታት ከሚባል ሀሳብና ድርጊት ውጪ እንዲሆን አድርጎ ነው የፈጠረው። ጋብቻ ኤክስፓየርድ ዴት አልታተመበትም።
ወይኔ ሲያናድድ!!
ፈጣሪ መፋታትን እንደዚህ ከጠላ ሳንፋታ እንድንኖር ሊያደርገን ነው እንዴ? ዶክተሮች፣ ዘማሪዎች፣ ቄሶች፣ ሼኮች፣ ፓስተሮች፣ አርቲስቶች፣ አትሌቶች ተፋተው የለ እንዴ እያሉ ነው ያሉት? እነዚህ ሁሉ በፈተና የወደቁና ከዜሮ በታች ያመጡ ሰነፍ ሰዎች ናቸው። ለምንም ነገር ምሳሌ አርገው አይውሰዷቸው!! እርስዎ እንዳይበላሹ እነዚህ ቀሽሞች ካሉበት አካባቢ ይራቁ።
“መፋታትን እጠላለሁ” ያለው ፈጣሪ ነው።
እርስዎ ማንን ነው የሚሰሙት?
ፈጣሪን ወይስ ተሸንፈው የወዳደቁ ሰዎችን? ፈጣሪን ቢሰሙት ያዋጣዎታል። ባልና ሚስት ጋብቻቸውን በፍርድ ቤት በህግ በኩል ቢፋቱና ቢለያዩ እንኳን በፈጣሪ ዘንድ ግን ጋብቻው ፈጽሞ ሊፈርስ የማይችል መለኮታዊ ተቋም ነው። ሁለቱም በህይወት እስካሉ ድረስ ቤተ ክርስቲያንም በእግዚአብሔር እንደተሳሰሩ ትቆጥራቸዋለች። ስለዚህ ቢለያዩም አልተፋቱም። ከሌላ ሰው ጋር ተጋብተውም ከሆነ የሚያደርጉት ግንኙነት እንደ ዝሙት ይቆጠራል።
እንደሚያውቁት ሰይጣን በአምላክና በሰው መካከል ያለውን ድልድይ እየሰባበረ የሰው ልጅን ከአምላኩ ጋር ህብረት እንዳያደርግ እርቃኑን ለማስቀረት ለብዙ ዘመናት እየሰራ ይገኛል። በእኔና በእርስዎ ዘመንም ይሄ እረጅም እድሜና ብልሃት ያለው ሰይጣን ስራውን ያለ እረፍት እየሰራና እያከናወነ ይገኛል።
ትዳር ሌላኛው የአምልኮ ስርዓት የሚፈጽምበት ቤተ ክርስቲያን ነው። ይህን ተቋም አፍርሶ ከአምላክ ጋር የምናደርገውን አምልኮ ለማቋረጥ ሰይጣን በተለያየ መንገድ ትዳራችንን እየፈተነው ይገኛል። አንዳንድ ትዳራቸው የፈረሰ ሰዎች እንዳጫወቱኝ ከሆነ፤ ትዳራቸው በምን ምክንያት እንኳን እንደፈረሰ አያውቁትም።
ወደ ሚጠላኝ ሰውዬ ትዳር ታሪክ እንመለስ
የሚስቴ ማንበብ ኑሮዬን በጠበጠው። አሁን ላለሁበት የውድቀት ደረጃ ዋና ተጠያቂዋ ሚስቴ ናት። ስለዚህ በዚህ ሁኔታ መኖር ስለማልችል “ልንፋታ ተስማምተናል”
ነበር ያለኝ!! በተጋቢዎቹ እንፋታለን ስምምነት እና ጋብቻን በፈጠረው ፈጣሪ “መፋታትን እጠላለሁ፤ በፍጹም አትፋቱም” በሚል ክርክር ውስጥ ጥንዶቹ ለመፋታት ከበቂ በላይ ነው ያሉትን ምክንያታቸውን አቅርበዋል። አብረው መኖር የማይችሉበት ምክንያቶችን አንድ ሁለት እያሉ በዝርዝር አስቀመጡ።
(ከደራሲ ሱራፌል ኪዳኔ “እንዳትገቡ” መፅሐፍ የተቀነጨበ)

Read 1728 times