Wednesday, 16 November 2022 09:51

ድንበር አትግፋኝ ትዝታ....

Written by  ከድረስ ጋሹ
Rate this item
(8 votes)

 የፀሐይ አወጣጧን መሰልከኝ። በምሥራቅ ፈካ ብለህ ለፍቅር መጣህ ፣ ቀትር ላይ የተለየ የፍቅር ሙቀት ነበረህ ፣ ሲመሽ ግን በምዕራብ በኩል ጠለምክ። እኔም ፀሐይ ሟቂ ነኝ። በምሥራቅ ስትወጣ ልቤን ሰጥቼ ሞቅኩህ ፣ ቀን ላይ ጨረርህ በአናቴ አረፈ _መላ አካላቴን በፍቅር ገዛህ ፣ ወደ ማታ ሙቀትህ ከልቤ ሸሸ ፣ በዓይኔም ተከተልኩህ...ትመለሳለህ አይደል?]


       ውሱን ፍጡር መሆኔን አምናለሁ። ትንሿን እንቁራሪት እንኳ አልመስላትም አላክላትም። እንደሷ ወደ ጎን፣ ወደላይ ፣ ወደፊት ማየት አልችልማ። ብቻ!  የትዝታና የተስፋ ስንግ ነኝ። የሁለቱ ህልውና በእኔ መኖር  ላይ ነው፤ ካለኔስ ማን አላቸው? ለቅጽበታት ኹሉ ትርጓሜ፣ ለአፍታዎች ኹሉ ፍቺ እሠራለኹ።  ኀዘኔን ትቼ አንድ ጋት መራመድ እስኪያቅተኝ ተሸብቤያለሁ። ዳሩ እስሬን ለመፍታት የምታገል አንበሳ እንጅ ከአሰረኝ ገመድ የተላመደ ዝሆንን መሆንን መች እሻለሁ። ኹሌም ለዓይኔ ምስሏን፣ ለልቤ ፍቅሯን እመግባለኹ። በነግሕ ...
  [አፌ ለውዳሴ ይከፈታል ፤ውዳሴም
  ልቡን ለእሷ ይከፍታል። የልቤን
 የሚነግራት ግንባሬ ፣ ደስታዬን
  የሚገልጥላት  ደም ሥሬ ነው።]
እኔ መምሯም መርሗም ነኝ። ቃሌን እንደ ሩፋኤል ዝናብ ትጠብቃለች። የምነግራትን በልቧ ጽላት ልትመዘግብ ፣ግፋ ሲልም ልትጸንሰው። የልቧን ጎጆ በእኔ ምክር መቀለሷ፣ ያመለጣትን ቀልቧን መመለሷ ባልከፋ የእኔ አሽከር መሆኗ ባሰ እንጅ። ሌት በድፍን ጨለማ ...ቀን በእቶን እሳት መሐል ትመጣለች _ምክር ልትሞቅ። የእስትንፋሷን ወዝ አርግፌ ፣የነፍሷን ጥላ ገፍፌ ብመልሳት ዞራ ከእኔው።ከወዜ ወዝ ታመርታለች ፤ከቃሌም ቃል አታጣም። በሄድኩበት ሁሉ አለች ፤በቆምኩበትም አትታጣም። የእኔው ግርፍ ፣የእኔው ጭምት፤ የእኔው ውጥን የእኔው ቁጭት!
 ፌኔት።
ስሟን ስጠራው ይጣፍጠኛል። ወዬ ከማለቷ በፊት የምታሳየኝ መሽኮርመም የሆነ ስሜት ይጠራብኛል። ዓይኗ ወደ ጎን ሲያይ ልብ ይሰርቃል። መልኳ እስከዚህም ነች፤ ብዙ የደስ ደስ አlaት እንጅ። ለእኔ ከእሷ ሌላ በዓይኔ የሚሞላ የለም። የእኔ፤ ንግሥት ሂንዳኬ፣ ንግሥት ማርግሬት፣ ንግሥት ቢትሪክስ  ይላታል አፌ፤ ልቤማ መቼም ቤቷ ነው።
 ‹‹ውዴ ››
ድንገት ነበር የጠራኋት። ባልተለመደ አዟዟር ዞረች። እጇ ከምታጥበው ልብስ ተነስቶ ውኃ ያንጠባጥባል...በአረፋ በተነከረ እጇ ግንባሯን እየነካካች...
‹‹እንደሱ ብለኸኝ አታውቅምኮ ›› አለችኝ።
ደነገጥኩ።ለውዴ ታንስ ኖሯል? ለፍቅር የሚገባትን ቦታ ነፍጊያት ነበር? ጨነቀኝ።
‹‹ፌኔቴ ይቅርታ! በአንድ ቃልማ መናደድ የለብሽም። ቦታ አትስጭው...›› (እንደ ማረሳሳት ዓይነት የለበጣ ንግግሬ ነው)
‹‹ለአንድ ቃል አትጨነቂ አልክ?..ስንት አለ አንድ ቃል የምንገዛለት? ...ፍቅር፣ እውነት፣ እምነት ፣ሕይወት፣ ሞት ...ባለ ስንት ቃል ናቸው በል?››
ከወትሮው በተለየ ገላመጠችኝ፤ ከወትሮው የተለየ ደነገጥኩ። መዘፍዘፊያውን በጎኗ ይዛ ወደ ቤት እየገባች ታጉተመትም ነበር። እኔም የምላስ ወለምታ አይታሽ ሆኖብኝ ወገቤን ይዤ ቆምኩ። ልቤ ከባድ ነበር" እንደ ቀጭኔ ልብ። ነገሮችን በመንታ የማይ የነበርኩት፣ መንታውን ወደ አንድ መጠምዘዝ ላይ ቀረሁ። ተገተርኩ። እንደ አራት በአራት የጠላ ቤት ችካል ቆሜ ቀረሁ፤ ምላሴ ዕዳን ጠርታለችና። ሰበብ ...ቀጠለና ፍቺ።
ከትዳር በፊት ..
በጭኔ አካባቢ ያሉ ሥሮቼ ሲወዳደሩ፣ ነርቮቼ ክንፍ አብቅለው የፍቅርን አበባ ሊቀስሙ ሲዞሩ ተያየን። እሷ ቆቅ፤ እኔ ወጥመድ ሆንን። ቀርቤ አቀረብኳት፤ አውርቼ አሳመንኳት። መስሎኝ ቃለ መሐላ ገባሁላት። የልጃገረድ ክብሯን አጎደፍኩ ንጽህናዋን አረከስኩ፣ የልቤ እሳት ይበርድ አልመሰለኝም ነበር። ልጅነቴ አዘናጋኝ_ቃሌን። ዕድገቴ አቀዘቀዘው ግለቴን። ተሸብሬ አሸበርኳት፣ ሳትዘጋጅ ማረኳት፣ ሳትገምት ጣልኳት። ፍሬውን ሳላውቅ፤ ነገን ሳልገምት ...አበዛሁት የልቧን ምት!
ግንባሯ እንደ አጋም እሾህ ወጋኝ። የለበስኩት የሐሰት ጥሩር አላስጣለኝም። የእውነት ነጎድጓድ ሲያዝገመግም የሐሰትን ግንብ ይጥሰ ዘንድ ኃይል አለው ለካ! እውነትን በዓይነ-ሥጋ መቋቋም እንዴት ይቻላል? .. ወሰን እስከ ወሰን የሚያካልለው ፣አንፋሮና ለምድ ያጠለቀ ሁነቷ ሥጋ ለበስ ፍጡርን ታርዳለች፣ላንቃ ይነቃል ፣ፍርሃት ያይላል _ ሁሉም ድል ይነሳል። ጀንበር ወደ መቃብሯ ምዕራብ መኼዷን ማን ያስቆማታል? እየሱስ ዳግም አለን? የማያልፍ ላይኖር እላፊ ውሸት ለምን አስፈለገኝ...
ትዳር ውስጥ...
ውሸቴ ስር ሰደደ። እሷ ገር ነች፤ እኔ ግራር። ታለቅሳለች ቁልቋል ቢጤ ናት፤ አጋሙ እኔ ከአጠገቧ ብኖር አይደል? የፍቅሬ መፍዘዝ ሰበብ ነኝ ብላ ታስባለች፤ ራሴው ሆኜ ሳለ። በላተኛ ወስፋት አለኝ ...የግፍን ጣዕም መቅመሻ ምላስ ጭምር። ሥጋ በቃኝ አያውቅም ሆድን እንደሁ ሞልቶ አይመርጉትም። ቁርስ በልተን ምሣ፣ ምሣ በልተን እራት የሚያምረን ድኩም ፍጥረቶች ነን። ከአዕዝርት የጎላ አረም፣ በእንግጫ የተዋጠ ተክል ... መጉበጥን አንጅ መቅናትን የማያውቅ ጠማማ ሕይወት፣ እኔን ልሁን አይሉበት ዕድል የሰነፍ ተስፋ። ከጉግ ማንጉጉ፣ ከዱር ከጢሻው ያመልጡበት ሁላ የሌለ _በጨለማ ጉዞ ዝናብ ተጨምሮ_እኔ ነኝ ኹሉንም።
አዳም በሔዋን ሔዋን በእባቡ ምክንያትን ሰበብን ቢለጥፉም ከቅጣት አልዳኑም። ሰበቤን ልናገረው ...ትዳሬን ከመፍረስ ባይታደገውም።
ልጅነት ላይ ደፈርኩ። አበባዬ መፈንዳት ጀመረ ። የልጅነት ፈተናዎች ብዙ ናቸው፤ ጓዝ መዘዙ አያልቅም። አሳቻ ወጥመድ መንገዱን ሞልቶታል። ሌት እና ቀኑ በሥጋት ይገፋል። ከቀንም የቀን ጎደሎ ..ከሰውም የሰው ጎደሎ አደረገኝ። የአእምሮዬ በር በአመጸኞች ተከፈተ። ላድግ ሳቆጠቁጥ የንዴት መርዝ ጋቱኝ። ሰው ኹሉ አውሬ መሰለኝ። ቀበሮ እንኳ ሚስቱን ይታመናል። ምነው እኔ ሆይ አመኔታ-ቢስ የሆነችዋን ቀበሮ ጸባይ ተዋረሰ?  በግዳጅ ውስጥ ያለ እርካታ ጣዕሙ እንዴት ነው? ... መፍራትን እንደሞኝነት እቆጥረው ነበር_በፈራሁ ኖሮ፤ በነቃሁ ኖሮ። አጓጉል ድፍረት ለስብረት ዳርጎኝ አየሁት። የትዳሬ መቋጫ የትዝታዬ መጀመሪያ ይኸው ነው። ራሷን እንደ ጥፋተኛ የምታይ ሴት ነበረች_ፌኔት። ባሏ እኔ ብልል ያርገኝና በአጎረሰችኝ እጇን ነከስኩ አፈር በባላሁ።
ከትዳር በኋላ...
ወቀሳዬን ለራሴ ቸርኩት። የኑሮ መልሕቅ ተነቅሎ ሞት ሆዬ እንዳይዳፈረኝ ሰጋሁ። በረገጥኩት መሬት ሁሉ አፌ ላይ ስሟ አለ። ምላሴ ሐሳቤን ቀድማ ልትመራኝ ትሞክራለች። ቀልቤ ሚዛን ላይ ወድቆ አልተሰፈረም፣ ምንነቴን ሳትገመግም የተላመደችኝን፤ ምንነቷን ሳልገመግም ገፋኋት። ስፈራ ስቸር የተናገርኳትን ክፉ ቃል በብረት መቀነቷ መቋጠሯ ጨነቀኝ። ጸጸት። ከጠብ ርቄ ኖርኩ። ከቀረብኩም መቅደምን ፈለግኩ። ቃሌን በውስጤ አሸሁት። ትዝብቴን ይመዘግብ ዘንድ የልቦናዬ ጽላት ሥራ አልፈታም። ወጌን፣ ጉራዬን ዋጥ ክትት አደረግኩት። እንደነሱ ሳይሆን እንደራሴ መጓዝ ጀመርኩ። መሄዴን እንጅ ወዴት የሚለውን አላውቅም። ለሰው ላካፍልም ከሰው ልካፈልም አልፈቀድኩም። ጥልን ፈራሁ። በልቤ እንዲያድር ቃል ሰጠሁ። እንደ ወራት/ቀን ተከታትሎ የሚመጣውን ሁሉ ልመክት። ሌሎች ላይ በሐሰት ላልመሰክር ፤ከረዘምኩበትም ላላጥር። በጥቂቱ ልታመን በሰፊው ልሾም።
ሌሊት ምድር ጸጥ ረጭ ስትል ወጣሁ። ጉዴን ልተያይ። አደፈጥኩ ከቋጥኝ ሥር። ትኩስ ስሜቴ ፣የአፍታ ኹነቴ የዘላለም መልኬ እንዳይሆን ፈራሁ። እንደ ወግ እንደ ልማዱ በፈገግታዬ ሳለዝባት ኖሬ ፤ዛሬ ለራሴ ሞረድ ቸገረኝ። ነጋ ጠባ እሳለማት ደጀ ሰላሜ አልነበረችም? ነበረች እንጅ! ነፍሴ ለእሷ ፍላጎት ተጥላ፣ አታሳግድ አታግድ፣ ክብሯ ክብር ተነፍጎት፣ ስልቷ ሳይቃኝ ፣ችሎቷ ሳይዳኝ። ልቤ ነፍስ አካሏን ያውቃል። አካሏ በጌጥ ነፍሷ ግን በግድፈት ታንጿል። መሠረት የሌለው ህንጻ እንዳይቆም ነፍስ የሌለው ሥጋስ ምኑ ሊበጅ? አዬ ምድር! በዕፀዋት ፈንታ አሜኬላ ታብቅል ብዬ ልርገማት። የልብ እክል የሌለበት ንጹህ ሰው ከወዴት ይገኛል?
ጨረቃ ትወጣለች ምድርን በብርሃኗ ልትለኩስ እንደ ሻማ። የፀሓይንና የጨረቃን ያህል መተላለፍ አለፍኳት፣ ወትሮም የጨለማንና የብርኅንን ያህል ድንበር ነበረን...የማይታይ..የማይዳሰስ...የማይጨበጥ..ከስስ  የሳሳ...ሞቴም ሕይወቴን በዚሁ ድንበር ይካለላታል። በማይጨበጥ፣ በማይዳሰስ ..አመጣጡ ሕይወቴን ወስዶ ራሱን ያነግሳል። ከብርኀንና ጨለማ ቅብብሎሽ የሚለየው “መጠበቅ “ባለመቻላችን ነው። መጠበቅ ግብሩ አይደለም?_ምጽዓትን መጋፋት እንዳይሆንበት ይሰጋል።
እሷን የሸኘሁበት ሸሚዝ ወዙ ገና አለቀቀም። እቅፋቷ ደረቴ ላይ ነው። ስሞሿ ከንፈሬን ተወዳጅቷል። ከዘፍጥረት እስከ ጽዮን ስለሚታተትለት ሞት መስበኩን አልፈልገውም። የዱር አራዊት ከመሐላቸው አንዱ ቢሞት ሥጋው እስኪሸት ይጠብቃሉ፤ አንቺ የሄድሽበት ዱካሽ ሳይጠፋ ብደርብ ይቅር ማን ይለኛል። አክብሮ ያጋደመሽ እጄ ሌላ ሊያቅፍ ተስኖታል። የክብር አልጋሽ ላይ ፍትወት የሚሆን አይደለም።
ያኔ ሳገኛት ግንባሬ ሲፈካ፤ ልቧ ሲፈካ ታወቀኝ። መድፍ ተተኮሰ፣ እምቢልታ ተነፋ። ደስታ በመሐላችን ሲንከላወስ ነበር። እንደ እስስት ቆዳ መቀያየርን ለደስታ ማን አለመደው? _አሁን ደስታ ነገ ኀዘን ሊሆንስ ማን አደራ ጣለበት?...
ምነው አንጀትሽ ከምጽዓት ራቀ ፌኔት?አንቺ የእንባ ጋን፣ የመከራ ቋቱ። ጊዜን ጊዜ ያሮጣታል _ሰው ሰውን እንደሚያሳድደው፣ ለእንባ ማድረቂያ የለም። የቦዘ ዓይን፣ የናወዘ አእምሮ፣ ናላው የዞረ ብቻ ...የገረጣ ፊት ሊያዩት ሲያሰንፍ፣ ከዓይን የሚቆረጡ እንባዎች ምነው እንጀራ አይሆኑ? ውለታሽ ለእኔ በዛ እላታለሁ በሐሳቤ...
.የዓይን አዋይ ስለሆነች እሷ ፣ትዝታ ምስሏን ሰላገዘፋት፣ ልቤም ሲያጣት ስላከበዳት ሴት! ለራሴ ነገርኩት ...እሷን የሚያስታውሱኝን ነገሮች ከአጠገቤ አራቅሁ፣ ሥጦታዎቿን አቃጠልኩ፣ ያለበሰችኝን ጃኬት ወዲያ ጣልኩት። ለልቤ ያለበሰቻትን የፍቅር ኮት ማውለቅ እንዴት ቀላል ይሆንልኛል? ይለኛል እራሴ_ፀጥ።
ራሴን ከጸጸት መቃብር ውስጥ አገኘሁት። ከመቃብር ስነቃ ሥጋዬ የእኔ አልመስልህ አለኝ። ነፍሴ እስትንፋስ አጥታለች። በመኖር እና ባለመኖር፤ በመሞት ባለመሞት መሐል ነበርኩ። ከሙታን መንደር ብቻዬን...ላልናገር ላልጋገር ነቅቼ ተሰየምኩ። ከራስ ፀጉሬ እስከ እግር ጥፍሬ ገላዬን ቃኘሁ። በጎኔ ወሽመጥ የገቡ አፈሮች አሉ። አንገቴን ሰደድ ባደርግ መቃብር ቆፋሪ አየሁ ፤እንዲሁ በደረቀ ሌሊት ደርቄ ቀረሁ። ተራውን እየጠበቀ ሰው ወደ እኔ እንደሚመጣ ሳውቅ ወደ ሞቀ ጉድጓዴ ተመለስኩ። ራሴን አፈር አለበስኩ። አፈርም ጸጸት ..ጸጸትም ክፉ እርግማን ነው።
ይኸው ጊዜ ይነጉዳል...
ቅዳሜ ዕለት ከቤት ወጣሁ። ለሆዴ ምግብ ላበስል _ጨው ይዤ ተመለስኩ። ጨው የተቋጠረበት ጋዜጣ ነበር። ፈትቼ በዓይኔ ቃኘሁት። ጽሑፉ የፌኔት ነበር።  ጥበብ አምድ ላይ መጻፍ ትወዳለች ፤ይኼን ዛሬ እኔ ወርሻታለሁ። “ያገናኛል ወይ መንገዱ?” ይላል የጻፈችው። ወደ ራሴ አስታከኩት ...”ምናልባት” ብዬ ገለጥኩት። ይኼ ቁጥብ ገለጻ አለው።
[መኼድህ ካልቀረ ኺድ። ለልቤ የቂም ስንቅ ግን አትተው። እኔም መኼዴ ካልቀረ እኼዳለሁ_ጠባችንን በመልካም ቃል አለዝቤ። ክፉ ቃል ለመለያያ ፍሪዳ አይደለም። በኼድክበት ድሎት ይግጠምህ። ወድጄ ያኖርኩህን በጥላቻ አላሟሽም። እወድሃለሁ።]
ዝቅ ብዬ ደገምኩ...
[የፀሐይ አወጣጧን መሰልከኝ። በምሥራቅ ፈካ ብለህ ለፍቅር መጣህ፣ ቀትር ላይ የተለየ የፍቅር ሙቀት ነበረህ ፣ ሲመሽ ግን በምዕራብ በኩል ጠለምክ። እኔም ፀሐይ ሟቂ ነኝ። በምሥራቅ ስትወጣ ልቤን ሰጥቼ ሞቅኩህ፣ ቀን ላይ ጨረርህ በአናቴ አረፈ _መላ አካላቴን በፍቅር ገዛህ፣ ወደ ማታ ሙቀትህ ከልቤ ሸሸ፣ በዓይኔም ተከተልኩህ...ትመለሳለህ አይደል?]
ዝቅ ብዬ ሌላ ደገምኩ...
[መለያየት እውነት ሞት ነው? ከሆነ የተለየሁህ’ለት ሞትኩኝ። ልብህ ከሸፈተ ቆየ። አካልህ እንጅ መንፈስህ ከእኔ ከራቀ ቆየ። ለፍቅር ያጣደፈኝ ምላስህ ለጠብ ሊጠራኝ ሲቃጣው አየሁ ። ውዴ ሆይ፤ ሲሄዱ መቶ ሃምሳ ሲመለሱ ሃምሳ መባልን አልሻም ነበር_ዳሩ ሞት ተፈርቶ ከኑሮ አይቀር። እለምደዋለሁ..]
አብረን እየኖርን ሳለን ጋዜጣ ላይ የጻፈችው ነው።በጊዜው አላነባትም ነበር ፤ ዛሬ ግን በመጠቅለያ መልኩ ጽሑፏ ደረሰኝ። ለቃላት የምትማልለዋ ፣ትንቢት የአፍ መፍቸዋ የሆነችው ፌኔት በሌለችበት አለች። ይኸው በጋዜጣ መጣችብኝ። መንገድ ላይ የእሷን አልባሳት የመሰለ ካየሁ እንቀዋለላሁ። ወደ ነገ እየኼድኩ ነው? አዎ ካላችሁኝ ፊቴን አዙሬ ነው ወደ ነገ የምኼደው። ልቤ ትዝታ ላይ ነው። ልቤ ትናንት ላይ። የምላስ ወለምታዬ አለ...ደጋግሜ የሰበርኳት አይረሳኝም። ዛሬም ነገም አለች ፤በምልዓት። እኔም፣ እለዋለሁ ትዝታን...
[ሰጥቸኽ ሳለ ...
 ትናንትን ያክል ቦታ
ተው ግን....
 ድንበር አትግፋኝ ትዝታ።]

Read 949 times