Sunday, 13 November 2022 00:00

ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ሰርፀ ፍሬስብኃት ስለ አርቲስት አሊ ቢራ፤


     ዓሊ ሞሐመድ “ብራ”
ዓሊ፥ የጥዑም ድምጽ ባለተሰጥዖነቱ ብቻ አልነበረም የሚያስደንቀው። ፈረንጆቹ “genius” የሚሉት ዓይነት የሙዚቃ ሰው ስለነበረም እንጂ። ሙዚቃን፤ በዕውቀት ምሥጢሯን ዐውቆ የተጫወታት ታላቅ ድምጻዊ፣ ዓሊ ሞሐመድ “ብራ” ነበር።
ዓሊ፥ ሙዚቃዎቹን ራሱ ያቀናብራል። ዑድ፣ ጊታር፣ ኪቦርድ፣ ፒያኖ፣ አኮርዲዮን እና ሐርሞኒካ አሳምሮ ይጫወታል። ከክብር ዘበኛ፣ ከአይቤክስ፣ ከኢትዮ ስታር ሙዚቀኞች ጋር በሠራቸው የሙዚቃ ሥራዎች፣ አድማጮቹ ብቻ ሳይኾኑ፣ አብረውት የሠሩት ሙዚቀኞች ኹሉ እንደተደነቁበት፣ ሙዚቃን እንዳስከበረ ዕድሜ ልኩን የኖረ ታላቅ ሙዚቀኛ ነበር።
የኦሮሚኛ ሙዚቃን፥ ቋንቋውን የማንናገር እና የማንሰማ  ትርጉሙን ሳንጠይቅ በተመሥጦ እንድናዳምጥ ያደረገን፣ የኦሮሚኛ ሙዚቃ ባለውለታ ነበር። ዓሊ፥ የሐረሪን፣ የሶማሊኛን፣ የሱዳኒኛን እና የዐረቢኛ ቋንቋ ሙዚቃዎችን አሳምሮ የተጫወተ ታላቅ ድምጻዊም ነበር።
ዓሊ፥ በመድረክም፣ በስቱዲዮም፣ በአጠቃላይ ሙዚቃዊ ሰብእና፣ የሙዚቃን ፈተና በብቃት የተወጣ ታላቅ ሙዚቀኛ ነበር።
ዓሊ፥ ለሀገርህ ያለህን ኹሉ አበርክተሀል፣ እስከ መጨረሻይቱ ሰዓት ድረስ ሙያህን እና ሀገርህን አክብረሀል። ምድራዊ ስንብትህ ከልብ ያሳዝነኛል። ግን ከዚህ ኹሉ በላይ፣ ክብርህ ልቆ ይታየኛል።
ቸር አምላክ፥ ለነፍስህ ይዘንላት። ሰላማዊ ዕረፍተ ነፍስ ይሥጥህ። መላውን አድናቂዎችህን፣ ቤተሰቦችህን፣ የሙያ ጓደኞችህን እግዚአብሔር ያጽናናልን።
***
ከጋዜጠኛና ደራሲ ሔኖክ ስዩም
የክብር ዶክተር ዓሊ ሞሐመድ “ብራ” አንጋፋ ድምፃዊ ብቻ አይደለም። ከዚያ የሚያልፍ፣ አፍሪቃ ቀንድ ላይ የተደመጠ፤ ጅቡቲ ጆሮ የሰጠችው፣ ሞቃዲሾ የሰማችው፣ ሀርጌሳ አብራው ያዜመችለት ድምፃዊ ነው። ምን እንደሚል መረዳት ሳያስፈልጋቸው የሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች በሙዚቃዎቹ ፍቅር አብደዋል። ለእኔም ከልጅነቴ ጀምሮ ስሰማቸው ከማልጠግባቸው ድምፃውያን አንዱ ነው።
ነፍሱ በሰላም ትረፍ።
መፅናናትን ለአድናቂዎቹ እመኛለሁ።
***
ሥነጥበብ ምን ዳር አለው!
አሊ ቢራ ከአንጋፋና ወጣት ድምጻዊያን ጋር የተለያዩ ሙዚቃዎችን ሰርቷል። ከነዚህ ውስጥ አንደኛው ከድምጻዊ አብርሃም በላይነህ ጋር ከዓመት በፊት የለቀቁት “ዳርም የለው” የተሰኘው ሙዚቃ አንደኛው ነው። ስለዚህ ሙዚቃ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ  እንዲህ ብሎ ነበር፡-
አሊ ቢራ ‹‹ዳርም የለው!››
መነሻ
አንዲት ወጣት አውቃለሁ፤ ወጣት ሳለሁ። ጆሮዋን ቢቆርጧት ኦሮምኛ አትሰማም። አሊ ቢራ ሲዘፍን ግን ጆሮዋን ቢወትፏት ትሰማዋለች፡፡ ቃላቱን ስትደረድር፣ ቅላጼውን ስትቀልጽ ለጉድ ነው! ስትዘፍን የሰማት ሰው፣ ‹‹ኦሮምኛ ትችያለሽ?›› ሲላት፤‹‹የአሊን እችላለሁ›› ትል ነበር፡፡ ስቀንባታል፡፡ ጥበብ የሰዎች ሳይሆን የተፈጥሮ ቋንቋ መሆኑ ያኔ - ድሮ ገና ገብቷት ነበር፡፡
ዋና ጉዳይ-
ሥነጥበብ ምን ዳር አለው? ከህይወትም ይገዝፋል፡፡ ከዘመንም ያልፋል፡፡ ዘላለም ነው። ተፈጥሮ ያለ ሰው እርቃኗንም ጥበቧ ይበዛል። ተፈጥሮ ጥበቧን ያኖረችበት አይጠፋትም፡፡ ጥበበኛ ስትሆን ከጥበቧ ትቀይጥህና ዘላለሟ ትሆናለህ፡፡
አሊ ቢራን ተፈጥሮ ከኗሪ ጥበቧ ቀይጣዋለች። ኗሪ ጥበብ በቋንቋ አይታጠርም። በባህል አይሰፈርም፡፡ ዘመን ይሻገራል፡፡ በወጣትነቱ ‹‹BIRRAA DHAA  BARIHE›› ብሎ የጨበጣትን ጥበብ፣ ዛሬም በአዛውንትነቱ ከዘራ ተመርኩዞ ‹‹ዳርም የለው›› ይላታል። ርእሱ የዘፈኑ ሳይሆን የህይወቱ ነው፡፡ የአሊ ቢራ የጥበብ ስራዎች (ዘፈኖች አላልኩም) ሞት እንኳን የወሰን ድንጋይ ሊያስቀምጥላቸው አይቻለውም፡፡ ተፈጥሮ በጥበብ ህዋዋ ላይ አንድ ኮከብ አድርጋዋለችና ስራው ዳር የለውም፤ ዘላለም ነው፡፡
አሊ ቢራ፣ የተፈጥሮን የጥበብ ስጦታ በየሰበቡ (መቼም ሰበብ አይገድም) አድበስብሰህ ሰው ባለመሆንህ፣ ጥበበኛ ሆነህ የተፈጥሮን ለተፈጥሮ በመመለስህ እናመሰግናለን፡፡ ዳር የለህም፡፡ ተፈጥሮ ምን ዳር አላት!Read 264 times