Wednesday, 16 November 2022 10:18

አቦል ወይስ አረጃ?

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(0 votes)

 የልቦለድ ድርሰት በነጠላም ሆነ በጥንድ እንዲሁም በጋራ ሊሰራ እንደ መቻሉ ፤ ከሁለት በላይ በሆኑ ሰዎች ህብረትና የጋራ ብዕርም ሊጻፍ የማይችልበት ምንም ምክንያት የለውም። ለምሳሌ ታሪክ እንደሚጠቁመው…በ1930 ላይ በ13 ሰዎች የተፃፈው አንድ ወጥ ልቦለድ መጽሐፍ “ዘ ፍሎቲንግ አድሚራል” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን፤ ድርሰቱ የተዋጣለትና አድናቆትንም ያገኘ ሆኗል፡፡ በዚህ የ13 ሰዎች የደቦ ስራ ውስጥ ከተሳተፉት ደራሲያን መካከል ዝነኛው ጄ.ኬ.ቼስተርትን፣ ዶሮ ዘ ሴየርስ እና አጋታ ክርስቲ ይገኙበታል፡፡ ወደ ሀገራችን መለስ ብለን ደግሞ ለመቃኘት ስንፈታትሽ…ከኢጣሊያ ወረራ በኋላ አያሌ የጋራ ፈጠራ ስራዎችና ሙከራዎች ብቅ ብለው ታይተዋል፡፡ ከእነርሱም መካከል ከድሉ አንፃር የተዘጋጀው “የአዲስ ዘመን  መዝሙር” የተሰኘው ባለ 150 ገጽ መጽሐፍ ውስጥ የይልማ ደሬሳና የብርሃኑ ዲንቃ ልብወለድ ድርሰት አብሮ መታተሙን ታሪክ ይነግረናል፡፡ ከዚህ ቀጥሎም ቢሆን በትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊነት አያሌ የተለያዩ የማስተማሪያና ልዩ ልዩ መጻሕፍት በጋራ ተሰርተው በስፋት ተነበዋል፡፡ የሃይጅንና ሳይኮሎጂ፣ ታሪክና ምሳሌዎች፣ እርምጃና ብርሃነ ህሊና የመሳሰሉትም በተከታታይ የታተሙት በዚህ ወቅት ነበር፡፡
ለዛሬ በዚህ ጽሁፍ ለማየት የመረጥኩት “አቦል” የተሰኘውን የጋራ ስብስብ ሥራ ነው፡፡ አዘጋጅና አሰናኙ ጉቺ ሽመልስ ነው፡፡ አንጋፋና ወጣት ጸሐፍት ያለ ቅደም ተከተል እንደዘበት ስራቸው የተዋቀረበት፣ አስራ ሰባት ፀሐፍት የተሳተፉበት (አንጋፎቹም አሉበት) የተለያየ ይዘት ያላቸው ፅሁፎች ተደራሲን ሳይሆን ስምን ተገን በማድረግ የተለቀሙ .. ያለ በቂ ልምድና ተሞክሮ ተሰንደው የቀረቡበትን  ስራ በወፍ በረር ለመቃኘት እሞክራለሁ ፡፡
የዚህ ስራ ጠቅላላ ቅርጽም ሆነ ይዘት የአለማየሁ ገላጋይ “መልክአ ስብሐት” ናሙና ነው ማለት ይቻላል፡፡ የመጽሐፉ መንፈስና ጠቅላላ ቁመና ከተስፋዬ ገብረአብ እፍታ ቅፆች ይልቅ ለመልክአ ስብሐት የቀረበ መዋቅርና አደረጃጀት አለው፡፡ በርግጥ የተረሳና የተዘነጋውን ከተለያዩ ደራስያን ላይ ጽሑፎችን በመሰብሰብ አስጠርዞ ለንባብ የማብቃት ስራ (ታዲያ እንደዛሬዎቹ ለጥቅም አይደለም እንጂ) ጀማሪ ባይሆንም ፈር-ቀዳጅ ሊባል የሚችል ሚና የነበረው ተስፋዬ ገብረአብ እንደሆነ እውቅ ነው፡፡ ተስፋዬ ከሀገር እስኪወጣ ድረስ “እፍታ” ተከታታይ ቅጽን እስከ አምስት ድረስ ገፍቶበታል፡፡ ይህንን የአደራ ርክክብ ስነ-ስርአት “ከጋዜጠኛው ማስታወሻ” ቀጥሎ ባስነበበን “የደራሲው ማስታወሻ” ውስጥ አንድ ምዕራፍ መድቦ ተርኮታል፡፡ እፍታ የዚያን ዘመን የስነ-ጽሁፍ አንድ የዘመን ቀለም  ነው ማለት ይቻላል። ያኔ ጽሁፋቸው እፍታ ውስጥ ከተካተቱላቸው ጀማሪ ፀሃፍት .. ዛሬ አንጋፋ ለመሆን ሩብ-ጉዳይ የቀራቸው ጥቂቱ አይደሉም፡፡ ከነዚህ መሀል እንዳለጌታ አንዱ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ጽሁፎቹ መታተማቸው በጊዜው የሞራል ስንቅ ሆኖለት የነበረው እንዳለ፣ ከራሱ ስራ ላፍታ  ፋታ ወስዶ  “ደቦ” በሚል ርዕስ ከእፍታ ተስተካካይ በሆነ ቁመና ከጥቂት አመታት በፊት አበርክቶልናል፡፡
የትውልድ የአደራ ቅብብሎሹን በኀላፊነት ተወጥቶታል ብለን አድንቀን የምንመሰክረው፣ ሳይታክት በትጋት የራሱን የስነ-ጽሁፍ ትሩፋቶች እየሰጠን በነበረበት ወቅት ላይ መሆኑንም ጭምር ደርበን ስናሰላው ነው፡፡ ከዚያ ወዲህ አልፎ-አልፎ እፍታ ቅብ የሆኑ ደቦ መሰል ይበል እሚያሰኙ ሙከራዎች ብቅ ብለው ቢያጋጥሙም፣ በንባብ ውስጣቸው ሲፋቅ አቦል መሰል የከሸፉ  ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ከመተቸት በቀር እውቅና ሰጥተን ለማበርታትም የምንቸገረው ለዚህ ነው፡፡ ለመተንተን እንኳን መነሻ የሚሆን ፍንጭ አይሰጡም፡፡ በሂሳዊ አይን ስንመዝናቸው ዝርዝር ጠቀሜታቸው ያን ያህል የጎላ አይደለም፡፡ በርግጥ ከግል ይልቅ በጋራ የሚሰራ ስራ ለአንባቢው የተለያየ ጣዕም ከመስጠት አኳያ ያለው የላቀ ፋይዳ አያጠያይቅም፡፡ ይሁንና ከማህበራዊ ድረ-ገጽና ከሌሎች ህትመቶች አፋፍሶ ሳይቦካና - ሳይከካ በወረት እንደ ወረደ በማቅረብ ግቡን መምታት አይችልም፡፡ በአንጋፋዎቹ ተሞክሮ እንኳን እንደልብ እምብዛም የማይሰምር ሙከራ በወጣቶቻችን  እየተለመደ መምጣቱ ዘርፉን አሳንሶ ከማየት የመነጨ የአላዋቂ - አርታኢ ድፍረት ነውና እንተቸዋለን፡፡ ወደ ውስጥ ከመዝለቃችን በፊት መግቢያው እንደሚነግረን ለመጽሐፉ ውጥን ሐሳቡ የተጠነሰሰው በፌስቡክ ወዳጅነት ላይ በተገናኙ ጓደኛማቾች  ነው፡፡ የትስስር ገጹ ለትውውቅ ምቹ ሆኖ በዚያው ቢቀር ያባት ነበር፡፡ ጥፋቱና ስህተቱ ወደ መጽሐፍ ለመቀየር ማሰባቸው ላይ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅርስ እንደመሆኑ መጠን እንደ ፈንጂ አምካኝ የካበተ ልምድና ጥንቃቄ ሳይለየው በአርትኦት መብሰልን ግድ የሚል መሆኑን ስተዋል፡፡ መጽሐፉ ከቅርስ ከጭብጥና ይዘት አንፃር ምን ስያሜ ሊሰጠው እንደሚችል እንኳን ግልጽ አይደለም፡፡  
መጽሐፉን ከአቦል እስከ በረካ ብንቀምስለትም ከንባባችን የምናተርፈው አረጃውን ብቻ ነው። አቦል ውስጥ የተሳተፉ የተለያየ ሙያና ልምድ ያላቸው አስራ ሰባት ፀሐፍትን አዘጋጁ ደራሲያን ሲል ቢሰይማቸውም፣ ሚዛን ደፍተውብን ተነባቢ ሆነው የምናገኛቸው ግን በጣት የሚቆጠሩትን ብቻ ነው፡፡ ከእነርሱም ለመጥቀስ ያህል የትእግስት ታፈረ “መሬት” ትረካ .. የአንተነህ አክሊሉ “በህያዋን መካከል” ስነ ግጥም .. የጋሽ ሳህለ ስላሴ “ጠራቂው” ወግ..። እንደመታደል ሆኖ የእኚህ ሶስት  ደራሲያን ስራ በአጋጣሚ ተካቶ መገኘት መጽሐፉን የመጨረሻ  እስትንፋስ በመሆን ከአቅመ ሞት ታድጎታል፡፡ ጉቺ ሽመልስ ከሁሉም ጸሐፍት የሰበሰባቸውን ጽሁፎች በወጉ ቅርጽ በመስጠት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ ከመትጋት ይልቅ በግድ የለሽነት እንደወረደ ማቅረብን  መርጧል፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም ለጋሽ ሳህለ ስላሴ ወግ ባይተዋር መሆኑ ይበልጥ ያስቆጫል፡፡ የርሳቸው ዘመን ዘለል ትርጉም መጽሃፍትን አንብበን የተማርንባቸውን ያህል ከትርጉም ውጪ ጥቂት ቢሆኑም ወጥ ስራዎቻቸው ዛሬም ለነፍሳችን ቅርብ ናቸው። ታዲያ ለኛ-ለኛ በእንዲህ ያለ አጋጣሚ የማናውቀው ስራቸውን ማግኘታችን (የሎተሪ ያህል) መታደል ነበር፡፡ ባልበሰለ አዘጋጅ እጅ የገባ ጽሁፍ በቂውን ያህል ማስተካከያ ሳይደረግለት መቅረቡ የሚጠበቅ ነውና አናዝንም፡፡ በዚህ ረገድ ለወትሮ  ቢሆን ኖሮ እንዲህ መሰል ስብስብ ለጀማሪም ሆነ ለአንጋፎቹ ጸሃፍት ያለው እድል በጣሙን የላቀ ነበር፡፡ የአቦልን ስንመለከት ግና ሀሳብ አልባ ፈጠራዎች የተዋቀሩት (ታምራት ገሰሰ  እቀባጥራለሁ የአርታኢው “ወደ ፀሐይ መውጫ”) አዳዲስ አቀራረቦች የነጠፉበት (የሄኖክ ስዩም “የቀባጥሬ ክዋክብት” የዳዊት ንጉሱ “አፍሪካዊ ስትሆን” .. ማለፍያ የታሪክ ነገራ ስልትና ዘዴ የማይተዋወቁበት (የጥላሁን  ግርማ አንጎ “የምርቃት መጽሄት” የያዕቆብ ብርሃኑ “ሃምራዊ አመሻሽ” እና ሌሎችንም ነቅሶ ማሳየት ይቻላል፡፡  
በለጋ ብዕር የተሞከሩ ወግ ነክ ጽሁፎች ሳይታሹ እንዳሉ አቦል ውስጥ ተካተዋል። የታምራት ገሰሰ “ልዕልት”፣ የአመልማል ደምሰው “የህያዋን ቀብር”፣ የሌዊ ዮሐንስ “የቆሎ ተማሪ”፣ የአፀደ ኪዳኔ “ጠይም ሎጋ” ማሳያ የሚሆኑ ናቸው:: በመጨረሻ ስንጠቀልል በጣምራ የተዋቀረው አቦል የረባ  ፈጠራ ታይቶበታል ለማለት አያስደፍርም፡፡ የተሻሉና የነጠሩ ስራዎችን በቂ ጊዜ ወስዶ ለተደራሲ ከማቅረብ ይልቅ ደረጃቸው ዝቅ ያለ፣ ተረስተው እንዳይቀሩ ሲባል ብቻ አሰባብሶ ማቅረቡ (ከነዚህ ስብስብ የምናውቃቸውም አሉበት፤ ቀደም ሲል በተለያዩ ጋዜጣና መጽሄቶች የተነበቡ ገጥመውኛል “የቱ ነው ኦርጅናሌው .. ቢሆንስ ባይሆንስ ከዛስ”) የሚያስቀጥለው አላማ፤ የሚያሳድገው ጥበብ ስለመኖሩ ለመገመት እንኳን ያሻማል፡፡ እንዲህ ያሉ ገበያ ተኮር የስነ-ጽሁፍ  ዝንቆች የእፍታን መንፈስ በወጉ ማስረፅ ካልቻሉ መታተማቸው ጉድለትና ኪሳራ እንጂ የተለየ ሀባ ትርፍ የለውም፡፡ ይህን ሥራ የአዘጋጁ የስሜት መነሳሳት የወለደው ጅምር ሙከራ ነው ብለን ብቻ በቅንነት ልናየው አንችልም፡፡ የሆነው ሆኖ አርታኢው ከዚህ አላዋቂ ስህተት ታርሞ ቢበቃው ያባት ነበር፡፡ ግን የአቦል ለጣቂ ቶናን ለማስከተል በዝግጅት ላይ መሆኑን ስናውቅ ነገሩ ስላቅ ይሆንብናል፡፡ ቀጣዩ ቶና ከመምጣቱ በፊት ይህ ሂሳዊ ዳሰሳ በቅንነት ቢነበብ፣ ለአዘጋጁ እንደ ጥቆማም እንደ ማስጠንቀቂያ ደውልም ሊያገለግል ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡

Read 179 times