Monday, 14 November 2022 00:00

ዳንቴ ከፑሽኪን አደባባይ ላይ …

Written by  ፍሬው ማሩፍ
Rate this item
(1 Vote)

የሀገሪቷ መዲና አዲስ አበባ የመንገድ መለያ ድልድዮቿና ተመሳሳይ የግንባታ ውጤቶቿ ላይ የተለያዩ የጎዳና ላይ ስዕሎችን መመልከት ከጀመረን ሰነበትን፡፡ የሲምንቶ ልሙጥ መልክ ካለው ኮንክሪት ጋር ዓይናችን ከሚፋጠጥ፣ የጥበብ እጆች ያሩፉባቸው ስዕሎችን መመልከት እጅጉን እንደሚሻል አከራካሪ አይደለም፡፡ እነዚህ ስራዎች ለከተማዋ ውበት የራሳቸውን አሻራ ማሳረፋቸው እንዳለ ሆኖ የሚመጣው ትውልድ ለሥነ ጥበብ ፍላጎት እንዲያድርበት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ እኛም ለአፍታም እንኳ ቢሆን  ስዕሎቹን ስንቃኝ በኑሮ መመላለሱ ውስጥ ከሚያባክነን የሀሳብ ጉዞ ለጥቂት ጊዜም መለስ እንድንል ያደርገን ይሆናል፡፡
በሌላ በኩል ከእነዚህ የጥበብ ስራዎች ጋር ተያይዞ ፈረንጆቹ ‘Graffiti’ የሚሉት፣ በተለይ የህዝብ መገልገያ በሆኑ ስፍራዎች ላይ ከሚመለከተው አካል ፍቃድ ሳይገኝ የሚሰሩ ስዕሎች በሀገራችን እንዳይለመድ ጥንቃቄ ማድረግ ይበጃል፡፡ በኮንክሪቶቹ ላይ የሚሰፍሩት ስራዎች ምን ይዘት ሊኖራቸው ይገባል የሚለው ሌላኛው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡
ሰሞኑን የሳር ቤት አደባባይ የመንገድ ላይ የድልድይ ግድግዳዎች (ኮንክሪቶች) ላይ በይዘት፣ በዓይነት ሆነ በውበት የላቁ ስዕሎችን ስጎበኝ፣ የታዘብኩትን ለማጋራት ነው፡፡ በዚህ አደባባይ ላይ ካሉ የድልድይ ተሸካሚ ግንብ ላይ ከተሳሉት ስዕሎች አንዱ፤ ‘Dante 700’ የሚል ርዕስ የተሰጠው የጣልያናዊ ጸሐፊ ዳንቴ ምሥል ነው፡፡ መጀመሪያ ይህን ስዕል እንደተመለከትኩ ‘‘የፑሽኪን ሀውልት ወደ ቦታው መቼ ይሆን የሚመለሰው? እያልን ስንጠብቅ፣ ዳንቴ በየት በኩል ቀድሞ ከፑሽኪን አደባባይ ላይ ተገለጠ?’’ ብዬ  ነበር ለራሴ የጠየኩት፡፡ ሆኖም የዳንቴ መልክ በቀለማት አሸብርቆ ከግንባታው ላይ መገኘቱ፣ ለፑሸኪን ከመቆርቆር እንደሚያልፍ ለማወቅ ብዙ ማሰላሰል አያስፈልገውም። ‘እንዴት?’ የሚለውን ከማንሳቴ በፊት ግን አስቀድሜ ስለ ፑሽኪን እና ስለ ዳንቴ ጥቂት ልበል፡፡
ፑሽኪን
አሌክሳንደር ሰርገየቪች ፑሽኪን ነው ሙሉ ስሙ፤ በ1807 ነው የውልደት ዘመኑ፡፡ ከቆዳው ላይ የጥቁር ቀለም ይታይበት ነበር የሚባልለት ፑሽኪን፤ ሩስያ ካፈራኋቸው ጸሐፍት መካከል እንደ ሃገር ምልክት፣ በዘመናት ከሚገኙ ብርቅዬ ደራስያን ዋናዬ ነውም ትለዋለች፡፡ ይህ ደራሲ በ1823 ላይ ‘Yevgeny Onegin’ የሚለውን እውቅ ስራ ለአንባብያን ካደረሰ በኋላ፣ በሌሎች ድንቅ ድርሰቶችም ይታወቃል፡፡(ከእኔ ጋር የመጀመሪያ ትውውቃችን በመስፍን ዓለማየሁ ተርጓሚነት በተዘጋጀው ‘ካፖርቱ እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች’ ላይ ነው)፡፡ በሰላሳ ስምንት ዓመቱ ሚስቱን ናታሊያ ኒኮላይቫን ዳንቴስ በተባለ ግለሰብ ተቀምተሃል መባሉን ችላ ብሎ ሊያልፍ የተሳነው ፑሽኪን፤ ከሚስቱ ውሽማ ጋር ያደረገው የጥይት መፋለም ይቺን ምድር እንዲሰናበት ምክንያት ሆኖታል፡፡
 ስለ ፑሽኪን ሌሎች ዝርዝር ነገሮች ለሌላ ጊዜ ይቆይና ከተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ አንጻር ‘ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ጥቂት የማይባሉ ደራሲዎችን ካፈራችው ሩስያ ፑሽኪንን መርጣ ሳር ቤት አደባባይ ላይ ሀውልት አቁማለት የነበረው፤ በስሙም የባህል ማዕከል የሰየመችለት በምን ምክንያት ነው?’ ለሚለው ጥያቄ አጭር ማብራርያ ላስቀምጥ፡፡
የተለያዩ መዛግብት እንደሚተርኩት፤ የፑሽኪን እናት ሰርጊያ ላቭሮቪች ትባላለች፤ አያቷ ደግሞ አብርሃም ሃኒባል የሚባል ጠይም መልክ ያለው የራሽያ ጀኔራል። በሩስያ ምድር ጥቁር ቀለም የነበረው ጀኔራል የመገኘቱ ዋንኛ ሚስጥር ምን ይሆን? አብርሃም ሩስያ ውስጥ ከሚገኙት ጎሳዎች አይደለም የዘር ሀረጉ የሚመዘዘው፤ ከምስራቅ አፍሪካ እንጂ! የአብርሃም አባት የመረብ መላሽ ባህረ-ነጋሲ መቀመጫ የነበረችው ከተማ አስተዳዳሪ ነበሩ፡፡ በወቅቱ ታድያ የኦትማን ኢምፓየር ወደ ምስራቅ አፍሪካ ባደረገው ወረራ፣ አብርሃም በወታደሮቹ ይማረክና ወደ ኢስታምቡል ይላካል፡፡ እዛ ብዙም ሳይቆይ በወቅቱ በቱርክ የሩስያ ተወካይ የነበሩት ግለሰብ አብርሃምን ገዝተው ወደ ሞስኮ ይልኩታል፡፡
 በዛም በወቅቱ በነበረው ጥቁር ቀለም ያላቸው ሰዎች ከገዢዎች ቤት የመገኘት ልማድ አሊያም እጣ ፋንታው ሆኖ፣ አብርሃም የወቅቱ የሩስያ ዛር ለታላቁ  ጴጥሮስ በስጦታነት ተበረከተ፤ ንጉስም አብርሃምን ከሉትንያ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን እንዲጠመቅ፣ስሙም አብርሃም ፔትሮቪች ሃኒባል እንዲሆን አደረገ፡፡ ከቤተ መንግስትም አካባቢ ሳይጠፋ አደገ፡፡ በኋላም ላይ የጉዲፈቻ ሃገሩን በውትድርና በማገልገል የጀኔራልነት ማዕርግን ተጎናጽፏል፡፡ ታድያ አብርሃም ከወለዳቸው ልጆች መካከል አንደኛው ታድየሰ የሰርጊያ ላቭሮቪች (የፑሽኪን እናት) አባት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው እንግዲህ የፑሽኪን ቆዳ ከነጭነቱ መለስ ማለቱ፡፡
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሁለት ሃገር እስኪሆኑ ድረስ ፑሽኪን ኢትዮጵያዊ ደም አለው የሚባለው ለዚህም ነው፡፡(ፑሽኪን በአንድ ጎኑ አፍሪካዊ ነው ማለቱ ይቀላል መሰል!) ኢትዮጵያም ከላይ የተጠቀሰውን ታሪክ ተቀብላ፣በሙሉ ድፍረት ዜጎቼ ናቸው ልትላቸው የምትችላቸውን ድንቅ ፀሐፍቶቿን ወደ ጎን አድርጋ፣ የሩቅ ዘመዷን በአደባባይዋ ላይ ሃውልት በማቆም ያከበረችው። ታድያ ይህ ሃውልት በመንገድ ግንባታ ከተነሳ በኋላ እስከዛሬ ድረስ ወደ ቦታው አልተመለሰም፡፡ ባይሆን ለሃውልቱ መነሳት ምክንያት በሆነው የመንገድ ድልድይ ሰፊ ደረት ላይ የዳንቴ መልክ በትልቁ ተሳለበት፡፡ እንግዲህ ፑሽኪን ሚስቱን ዳንቴስ በተባለ ፈረንሳዊ፣ በኢትዮጵያ ቆሞለት የነበረውን መታሰቢያ ደግሞ በጣልያናዊ ደራሲው ዳንቴ ተቀማ!
ለዳንቴ በዚህ መልኩ መከበር እንደ ፑሽኪን ዓይነት ምክንያት ይኖር ይሆን?
ዳንቴ
ዳንቴ አሊጊሪ ጣልያን አለኝ የምትለው ጸሐፊ እና አሰላሳይዋ ነው፡፡ የጣልያን ቋንቋ ወደ ሥነ ጽሑፉ እንዲገባ ካደረጉ ልጆቿም መካከል ፊተኛ ነውም ይሉታል፡፡ በተለይ በእንግሊዝኛው ‘The Divine Comedy’ የሚባለው ስራው ከሌሎች ድርሳኖቹ ይልቅ ስሙ እንዲገን እና እስከ ዛሬ ድረስ ለቅኔ ቦታ ያላቸውን አንባብያን ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት ፍልስፍና ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ግለሰቦችም በተለይም ከክርስትና አስተምህሮ ጋር ተያይዞ ጥናት በሚያደርጉ ሊቆች ድርሳናት ላይ ስሙ ሳይጠቀስ እንዳያልፍ አድርጎታል፡፡ (ለእኔም የዳንቴ ስራዎችን ለማገላበጥ ምክንያት የሆነኝ ነገረ እኩይ ወይንም The problem of evil ስለተሰኘ የሃይማኖት ፍልስፍና ርዕሰ ጉዳይ ጥናት በማደርግበት ወቅት ነው፡፡)
ታድያ የዳንቴን ግለ ታሪክ በተመለከተ የተከተቡ ጽሑፎችን ሳገላብጥ፣ በተለይ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያያይዘው የማንነትም ሆነ የሀሳብ ገመድ ላገኝ አልቻልኩም፡፡ በእውቅና ደረጃ እንኳን ብዙ መጽሐፍትን ያነባሉ ያልኳቸው ወዳጆቼን ስጠይቅ ከጥቂቶቹ በስተቀር ከስሙ ጋር እንጂ ከስራዎቹ ጋር አይተዋወቁም፡፡እናም እንዲህ ጠየኩ ራሴን፡-‘‘ዓለም ላይ ካሉ እውቅ ደራስያን መካከል ዳንቴ በምን መስፈርት ተመርጦ ይሆን እግራችን የሳር ቤት አደባባይን በረገጠ ቁጥር መልኩን እንድንመለከተው የተገደደነው? በዚህ አደባባይ ላይ የአንድ የውጭ ደራሲ ምስል መስፈር አለበት ከተባለ ከዳንቴ ይልቅ ፑሽኪን ታሪካዊ መብት የለውም?’’
ከአመታት በፊት የቦብ ማርሊ ሃውልት ገርጂ አካባቢ ሲቆም፣ ለማርሊ የሙዚቃ ስራዎች ያለኝ አድናቆት ሳይገድብኝ፣ ‘‘ከጥላሁን ገሰሰ ይልቅ ቦብ ማርሊን በአዲስ አበባ ቅድሚያ ሰጥቶ ማቆሙ በምን ሚዛን ይሆን ልክነቱ?’’ የሚል ጥያቄን መሰረት ያደረገ ጽሑፍ ጽፌ ነበር፡፡ ዛሬም የዳንቴን መልክ በተመለከትኩ ቁጥር ከዚህ ጣልያናዊ ደራሲ ይልቅ ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁ፣ ማሞ ውድነህ፣ ጸጋዬ ገብረመድኅን፣ ዳኛቸው ወርቁ፣ በአሉ ግርማ፣ ስብሀት ገ/እግዚአብሄር፣ አዳም ረታ፣…አይቀርቡንም፤የግድ ከሌላ አህጉር መሆን አለበት ከተባለም ኢትዮጵያ ውስጥ መጽሐፍ ማከፋፈልን ሀ ብሎ ያስጀመረው ሚስተር ዴቪድ ቢሆን አይሻልም ወይ እላለሁ!
አሁንም ‘ኢትዮጵያ ደራሲዎቿን፣ ሙዚቀኞቿን፣ ሰዓሊዎቿን፣ … እና በመሰል የጥበብ ዘርፍ ተሰማርተው የነበሩ፣እንዲሁም አሁንም አንዳችም ሳይሰስቱ ሁሉን ለሚሰጧት ዜጎቿ በወጉ ክብርን መስጠት የሚሳናት ለምንድነው?’ የሚል ጥያቄን አነሳለሁ፡፡
ከላይ ባነሳሁት ጥያቄ ላይ ታድያ ‘ኢትዮጵያ’ ስል ከዝርዝሩ ውስጥ በቅድምያ ከሚገኙት ጥቂቶቹ፡-
መንግስት፡- ለሚፈለገው ዓላማ ጥሪ ሲያደርግ፣‘አለን’ ብለው የእጅ ስራቸው እንደፈቀደላቸው ምላሽ ለሰጡት የምስክር ወረቀትና ዋንጫ መሸለሙን ያለፉትም ገዢዎች፣ ያሉትም እያደረጉት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለጥበበኞቹ በወግ ክብርን ከመስጠት ምሳሌ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ (ከወራት በፊት በእንጦጦ ፓርክ በተለያየ ዘርፍ ለጥበበኞች በመንግስት የተሰጠው እውቅና ይበል የሚያሰኝ መሆኑ እንዳለ ሆኖ!)
ተቋማት፡- በእዚህ ውስጥ ብዙ አካላትን ማንሳት ቢቻልም፣ በተለይም አንድም እንደ የሙያ አይነቱ የተቋቋሙ ማህበራት ሌላ ሌላውን ጉዳይ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን አቆይተውት የደራስያን ማህበሩ ጸሐፊዎችን፣ የሙዚቃ ማህበሩም በኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉት ሙያተኞችን፣  … ሌሎችም ማህበራት በተመሳሳይ ጥበበኞች በቋሚነት እንዲከበሩ፣ እንዲመሰገኑ እና እንዲዘከሩ ቢያደርጉ ነው የሚበጃቸው፡:፡ (አንዳንዴ ነሸጥ ሲያደርጋቸው አሊያም ለሪፖርት ማሟያነት ከሚደረጉ ዝግጅቶች ባለፈ ማለቴ ነው፡፡)
እንዲሁም በሀገሬ የምትገኙ ዩኒቨርስቲዎች ሆይ፤ በጥበብ ሙያ ለተሰማሩ ዜጎች የክብር ዶክትሬት መስጠታችሁ ደግ ሆኖ፣ ግና በሰፈር ማድረጋችሁ ነውር ሆነ እንጂ! ጥበብ  ክልል የለውም፤ ጥበበኛው እንጂ ስራው ጎሳ አይገኝለትም፡፡ ለአስቴር አወቀ ከጎንደር ዩኒቨርስቲ ይልቅ ጅማ ዩኒቨርስቲ፣ ለአሊ ቢራ ከጅማ ዩኒቨርስቲ ይልቅ ጎንደር ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ሰጥተው ቢያከብሯቸው ኖሮ እንዴት ድንቅ ነበር!
እኛ፡- ቀን ሌሊት ተጨንቀው ለነፍሳችን የቀረበ የጥበብ ስራ ላበረኩቱልን የሀገሬ ልጆች የምንሰጠው ክብር ከሚዛን ቢቀመጥ ልሳኑ ይመዘን ይሆን? በስራዎቻቸው እንዳሰኘን ከሆንን በኋላ፣ ባለ ስራውን ‘ኑርልን’ ብለን የምንመረቅ ስንቶቻችን ነን? የእኛ የማድነቅ፣ የማክበር እና ለጥበበኞቻችን የሚገባውን የልፋት ዋጋ ከፍለን ’ክበሩልን’ የምንል ምን ያህሎቻችን ነን?
መልሱን ለእናንተ ልተው!
በነገራችሁ ላይ …
1፡- አዲስ አበባ አሉኝ ከምትላቸው አደባባይ በዋንኛው ላይ የዳንቴን ምስል አላይም ቢሉ እንኳ አስገድዶ እንዲመለከቱ በሚያደርግ ቁመትም ሆነ ስፋት ትልቅ ተደርጎ እንዲሳል ስፖንሰር ያደረገው በኢትዮጵያ የጣልያን የባህል ማእከል ነው ቢባል ያስገርም ይሆን?
2፡- በአዲስ አበባ የጎዳና ስዕሎች እንዲሳሉ ፍቃድ የሚሰጡት ኢትዮጵያውያን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ለነገሩ ስዕሉን በዋነኝነት የሰሩትም የእኛው ልጆች ናቸው፡፡ ይደንቃል፡፡

Read 6251 times