Saturday, 19 November 2022 20:01

ምላስ... ከጤፍ ወደ ፍራንክ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

“--እናላችሁ...“እሱ ሰውዬ የት ገብቶ ነው ደብዛው የጠፋው!” “እከሌ ሳይነግረን ውጭ ሀገር ሄደ እንዴ! ምነው  የበላው ጅብ አልጮህ እለ!” ምናምን ስትሉት የነበረው ሰው፣ የሆነ ቀን በሰላም ቤታችሁ በተቀመጣችሁበት፣ የሆነ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ገጭ ብሎ  'ሲያድን' ልታዩት ትችላላችሁ! እውነቱን እንነጋገርና ግራ ግብት ነው ያለን!--”
       
         እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ይቺን ፌዝ ቢጤ ስሙኝማ... የፈረንጅ ሰባኪ ነው አሉ፡፡ እሱ በሚሰብክበት አካባቢ ለረጅም ጊዜ ዝናብ ይጠፋና ድርቅ ይሆናል፡፡ እናላችሁ... አንድ ቀን የአካባቢውን ሰዎች “እርሻ ቦታ እንሂድና ዝናብ እንዲዘንብ እንጸልያለን፣” ይላቸዋል፡፡ ሰዉም ግልብጥ ብሎ ይወጣል፡፡
“ወንድሞችና እህቶች፣ እዚህ የመጣነው ዝናብ እንዲዘንብልን ለመጸለይ ነው!”
“አሜን!”
“ሁላችሁም በእምነታችሁ ጽኑዎች ናችሁ!”
“አሜን! አሜን!”
“ጥሩ፣ በጣም ጥሩ፡፡ አሁን ሁላችሁንም የምጠይቃችሁ አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡”
ሰዉም ጸጥ አለ፡፡ ከዛ ሰባኪው ድምጹን ከፍ አድርጎ ምን ቢል ጥሩ ነው....
“ወንድሞችና እህቶች፣ የታለ ዣንጥላ የያዛችሁት!” አለና አረፈው፡፡ ልክ እኮ ከዝናቡ ጋር ቀጠሮ የያዘ ነው የሚመስለው፡፡
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ለነገሩ እኮ የዘንድሮ የእኛን ነገር ስታዩት አይደለም ዝናብ ማዝነብ፣ ስንትና ስንት ጉድ እየሰማን አይደል እንዴ! ማድረግ የማይቻል ነገር የሌለ ነው እኮ የሚመስለው! የደረሰበት ደረጃ ግርም የሚል ነው! ልክ ነዋ...የሚያድኑን፣ እናድናችሁ የሚሉን፣ ግዴላችሁም እናድናችኋለን የሚሉን በዙብንና ግራ ገባንሳ! ምናልባት...እንደው ምናልባት የሚሉትን ማድረግ የሚችሉ ይሆን ይሆናል...ምናልባት! ምናልባት! ግን ግራ ገባን፡፡ እናላችሁ...“እሱ ሰውዬ የት ገብቶ ነው ደብዛው የጠፋው!” “እከሌ ሳይነግረን ውጭ ሀገር ሄደ እንዴ! ምነው የበላው ጅብ አልጮህ እለ!” ምናምን ስትሉት የነበረው ሰው፣ የሆነ ቀን በሰላም ቤታችሁ በተቀመጣችሁበት፣ የሆነ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ገጭ ብሎ ''ሲያድን' ልታዩት ትችላላችሁ! እውነቱን እንነጋገርና ግራ ግብት ነው ያለን! እናላችሁ... አለ አይደል...”ምን አገባን ብለን ዝም አልን!” የሚለውን ታክቲክና ስትራቴጂ ይዘን ነው እንጂ ስንት የምናወራው ነገር ነበረን!
እኔ የምለው... ይቺኛዋ ዓለማችን የእውነት ስትሬንጅ ነገር ነች እኮ! እንግዲህ እዚህም እዛም የ''ኤንድ ታይምስ' (‘ምጽአት’ም በሉት) መአት ነገሮች እየሰማን አይደል! ስማ ተስፈኛው ወዳጄ ጉድህን ሰማህ ወይ? አንተ በየ‘ሲፕ’ ቤቱ እየዞርክ “ድራፍቱ ጎደሎ ነውና ሙሉ!” እያልክ የሆነ 'ምናምን ሼቪክ ሪቮ' ለመጀመር መከራህን ታያለህ፣ ቁርጥህን እወቀው... የጎደለ ሳይሆን የደረቀ ነገር አለልህ፡፡ ኤፍራትስ ወንዝ ደርቆልሀል፡፡ እናስ! ምንድነው እናስ ብሎ ነገር! ደረቀ ነው እኮ የምልህ! አጅሬው በቃ አንተ ይሄ 'የመረጃ ዴፊሸንሲ' የሚሉት ነገር ላይለቅህ ነው! ለነገሩ ብዙ ቁጥር ውስጥ አንድ ብቻ ስለሆንክ ምን በወጣህ ብቻህን 'ታርጌት' ትሆናለህ! ስማኝማ... ኤፍራትስ ሲደርቅ የምን ምልክት ነው እንደሚባል ሰምተህ አታውቅም ማለት ነው! እኔማ ያሰብከውን ነገር እንኳን ልትጨርስ ሲሶ ሳታደርሰው ወንዙ ደርቆ ይኸውልህ “ወዮላችሁ! ወዮላችሁ!” እየተባልን ነው፡፡ (እኔ የምለው...ሲያስፈራሩን ለምንድነው የማያከብሩን! እድሜ ለክርስትያኖ ሮናልዶ መንገዱን ከፍቶልናል፡፡ “እነሱም አያክብሩን፣ እኛም አናከብራቸውም!” የማለት ‘ግሪን ካርድ’ አግኝተናል ለማለት ያህል ነው፡፡ ስሙኝማ... ሲ.አር. ሰቨን ምን ሆነ! በስንትና ስንት ልፋትና ላብ የተገነባ ስም እንዲሁ በ”አለ፣ አሉ” ሊፈርስ!)
እናላችሁ...ይቺን ነገር አንድ ሁለቴ ሳላወራችሁ አይቀርም፡፡ በወዲያኛው ዘመን የሆነ ነው፡፡ የሆነ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የሥራ ሰዓት አልቆ በመሥሪያ ቤቱ ሰርቪስ ወደየሠፈራቸው እየሄዱ ነበር፡፡ ታዲያ በአራት ኪሎ በኩል ሲያልፉ “ተፈጥሮን በቁጥጥር ስር እናውላለን!” የሚል መፈክር ያያሉ፡፡ እናማ ከመሀላቸው አንደኛው አየት አድርጎ “ድንቄም!” ብሎ ያጉረመርማል፡፡ እሱ ሰው አልሰማኝም ብሎ ነዋ! በማግስቱ ያው ከ‘እነዛ ቦታዎች’ በአንዱ ተጠራላችኋ! እናማ... የማይመቻችሁን መፈክር ሰው አይሰማኝም ብላችሁ “ድንቄም!” ምናምን ማለት ዋጋ የሚያስከፍልበት ዘመን ነበር ለማለት ነው፡፡
ስሙኝማ...በቁም ነገር ደግመን ደጋግመን የምንጠይቀው ነገር አለን፡፡ የሆነ እምነት ተከታይ ነን የሚሉ ሰዎች በአደባባይ የሌሎችን እምነቶች መሰረታዊ ጉዳዮች እያነሱ በአደባባይ ሲያንቋሽሹ ሀይ ባይ መጥፋቱ ግርም፣ ግርምርም እያለን ነው! የሚፈጥረው የዘለቄታ ችግር አይታይም ወይ!? ወይስ ለዚህም የሆነ ሀገር ተሞክሮ ምናምን መጠበቅ አለብን! ያሳዝናል፡፡ ሀሳብን በነጻነት በመግለጽና ድንበሮችን ሁሉ ጥሶ የሌላውን ሰው አፍንጫ በመንካት መሀል ያለው መስመር በዚህ መልኩና በዚህ ፍጥነት እየሳሳ መሄዱ “ወዮልኝ ለነገ!” ቢያሰኝ አይገርምም፡፡ እናማ... ገሚሶቻችን ሀይ ባይ ጠፍቶ እንደልባችን እየሆንን ገሚሱ ደግሞ “ምስኪን! ምስኪን!” እየተባለ የት ድረስ መሄድ ይቻላል ለማለት ያህል ነው፡፡
ስሙኝማ...እግረ መንገድ አሪፍ ፍራንክ የሚያስገኙ ነገሮች እኮ ድሮ የምናውቃቸው አይነት ብቻ መሆናቸው እየቀረ ነው፡፡ ቀላል ረብጣ ነው እንዴ የሚያሳፍሱት!
“አንተ ብቻ ቁጭ ብለህ ስትቸክችክ ኑር!”
“እና ታዲያ ምን ባደርግ ይሻላል!”
“ቢዙ ወደሚያስገኝ ሙያ ለውጣ!”
“ኢንጂነር ነኝ ብዬ ለሦስትና ለአምስት ወራት ነቅነቅ ሳይሉ የሚቆዩ ህንጻዎች የሚገነባ ኮርፖሬሽን ምናምን ላቋቁም እንዴ!”
“ህዝቤ ወዲህ ወዲያ እያለ ይስፈነጠራል፣ አንተ ብቻ ቀልድ! ለምን ሲትዳውን ኮሜዲ አትጀምርም! ‘ስታንድአፕ’ ያላልኩት ቆምክም፣ አልቆምክም ለውጥ የለውም ብዬ ነው፡፡ ፊት ከተቀመጡት በስተቀር ሊያይህ የሚችል የለም።” (እንደልባቸው የሚያወሩ በዝተዋል ስንል በምክንያት ነው፡፡ ...ቂ...ቂ...ቂ...)
“እሺ፣ ሀሳብ ስጠኛ!”
“ስማኝ... ዘንድሮ የሚያስፈልግህ ዋናው ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለህ! ምላስ...ምላስ ነው የሚያስፈልግህ፡፡”
“እና...  የፖለቲካ አክቲቪስት ልሁን እንዴ!”
“ፌዙን ተውና ስማኝ...ሌላውን ሰው በምላሱ ጤፍ እንዲቆላ ትተወውና የአንተን ምላስ ፈረንካ ቁላበት ነው እያልኩህ ያለሁት፡፡ ገባህ!”
“ሥራው ቋሚ ነው ኮንራት?”
“አየህ ዘላለማችሁን ከዚህ ሀሳብ አትወጡም። ሀያና ሠላሳ ዓመት መከራህን ከምትበላ በአንድ ዓመት ትቀውጠዋለህ ነው የምልህ! “
“እሺ የሥራውን አይነት ንገረኛ፡፡”
“ዙሪያህን ዓይንህን ከፍተህ እይና ትደርስበታለህ፡፡ ወይም መቶ ምናምኖቹን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስትለዋውጥ ትደርስበታለህ፡፡”
እናላችሁ... ዘንድሮ ጂ ፕላስ ምናምን የሚሏቸውን ቤቶች፣ ...ምናምን የሚሏቸውን መኪኖች፣ ምናምን ምናምን የሚሏቸውን ‘ስም አይጠቀሴዎች’ በአንዴ ‘ፕራይቬት ፐሮፐርቲ’ ለማድረግ ቀላል መንገዶች አሉ ይባላል ለማለት ነው፡፡
ስልጣንና ፍራንክ እንደ ልብ ያናግራል ይባል የለ...ይኸው እድሜ ለኤሎን መስከ ፍራንክ እንዴት እንደልብ እንደሚናገር ብቻ ሳይሆን እንደሚያደርግ እያየን ነው፡፡ ሰውየው ብዙ ነገሮች እየተባለ ነው፡፡ የትኛውን እንደሆነ አንድዬ ይወቀው፡፡ ተራ ሰው የለ፣ የዓለም ጉልቤ የለ! ባይደን ምናምን የለ፣ ዴሞክራት ምናምን ብሎ ነገር የለ...ዓለምን ጢባ ጢቤ እየተጫወተባት ነው፡፡
የምር ግን...አለ አይደል... በባዶ ኪስ፣ በባዶ ሻንጣ፣ በባዶ ጭንቅሌ ምናምን ለምንኩራራ ሁሉ እንደው አራት፣ አምስት ኤለን መስኮች መጥተው ጉድ ባየን!
የምር እኮ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...በቃ በኮትና በሱሪ ሽክ ማለት ላይቻል ነው! አሀ...ነፍስ ያለው በሰው ፊት ‘የማያስጠጣ’ ሙሉ ልብስ አይለበስ ነገር 'መካከለኛ ገቢ' ላለው ሰው የሚሆነው ስምንትና አስር ሺህ ብር ምናምን ደርሷል አሉ፡፡ የሆነ ኮሚክ ነገር እኮ ነው፡፡ ይሄን ያህል ፍራንክ እኮ ከዕለታት አንድ ቀን አንድና ሁለት ሺህ ብር ተጨምሮበት ዘመድና ጓደኛ ብቻ ሳይሆን መንደሩ ሁሉ 'ፕራውድ' የሚሆንባት መኪና ያስገዛ ነበር! ‘ነበር’ የምናላቸው ነገሮች መብዛት አያሳስባችሁም! አለ አይደል... የሆነ የሳተ ነገር አለ ማለት ነው፡፡
እናላችሁ... በ‘ኤይትና በቴን ታውዘንድ’ ልብስ ሽክ የሚያስደርጉ አዳዲስ ፈረንካ በሽ የሆነባቸው ‘ሙያዎች’ አሉ ይባላል ለማለት ነው፡፡ ማለትም ምላስን ጤፍ ከመቁላት ወደ ፍራንክ መቁላት የሚያስፈነጥሩ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1483 times