Saturday, 19 November 2022 20:02

“እያስታጠቃችሁ አታፋጁን”ብሎ አስቀድሞ መጮህ ይገባል!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 “የእነ አቶ ስብሐት ቡድን የተሳተላይት ስልክ፣ የጦር ሜዳ መገናኛ፣ ለጦሩ የሚያገለግል ነዳጅ ወዘተ ያገኘው፣ በእርዳታ ስም ከገቡ አካላት መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ስለዚህም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፤ “እያስታጠቃችሁ አታፋጁን” ብሎ አስቀድሞ መጮህ ይገባል፡፡”
           
መንግስት በግልጽና ጥርት ባለ ቋንቋ የእነ ስብሐት ነጋን ቡድን ማለትም ትሕነግን የሚገልጥበት ቃል  ሊኖረው ይገባል።  ጠ/ሚኒስትሩ ትሕነግና የትግራይ ህዝብ  ይለይ እንዳሉት ሁሉ፣ትሕነግ የትግራይ ሕዝብን ይወክላል ተብሎ መታሰብና መታመን የለበትም። የመንግስት ባለሥልጣናትም የእነ አቦይ ስብሐትን ቡድን ሲገልጹ፤እንደ ትግራይ ህዝብ ተወካይ መቁጠራቸውን ፈጽሞ ማቆም አለባቸው። የተምታታ አተያይ፣ የተምታታ ውሳኔ ላይ ስለሚያደርስ መጠንቀቅ ይኖርበታል። የእነ አቶ ስብሐትን ቡድን ማለትም ትህነግ፣  በመንግስት አተያይና ግንዛቤ እንዲህ ነው ብሎ በመዘርዘር፣ ለሕዝብና ለበታች አካላቱ ግልጽ ማብራሪያ መስጠት አለበት።
መንግስት የተቀመጠበት ወንበርና ያለበት ኃላፊነት በመንግስትነት እንዲያስብና እንዲሰራ ያስገድደዋል፡፡ እንደ እነ አቶ ስብሐት ቡድን ጠዋት የተናገረውን ማታ ሊለውጥ አይችልም። መንግስት ለምንም አይነት ሕግ የመገዛት ፍላጎትና ዝግጁነት ከሌለው ቡድን ጋር እየተፋለመ መሆኑንም ለአፍታ መዘንጋት የለበትም፡፡ ሥርዓት ማስያዝ የሚጠበቀው ከመንግስት እንጂ ከህገ-ወጡ ወገን አይደለም።
ትሕነግ ስሙም እንደሚጠቁመው፣ የፖለቲካ ድርጅት ሳይሆን መሳሪያ የታጠቀና በማዕከላዊ መንግስት ላይ ያመጸ ቡድን ነው። ከድርድሩ በኋላ እራሱን እንደ ፖለቲካ ድርጅት በመቁጠር፣ የትግራይ መከላከያ ኃይል እያለ የሚጠራውን ታጣቂ እንደማያውቀው አድርጎ ለማቅረብ ሲሞክር ተስተውሏል፡፡ በዚህም የደቡብ አፍሪካውን ስምምነት ለማፍረስ ዳር ዳር እያለ መሆኑን መንግስት መረዳት ያስቸግረዋል ብዬ አላምንም፡፡
የእነ አቶ ስብሐት ቡድን እራሱን “የትግራይ መንግስት” እያለ መጥራቱን የፌደራሉ መንግስት ማስቆም አለበት። “መፈራገጥ ይቻላል” እያሉ ንቆ ማለፍም ከውጭ ላለው ተመልካች የሚሰጠውን ግንዛቤ አለመረዳት ይሆናል።
መንግስት የዕለት ደራሽ እርዳታ ወደ ክልሉ እንዲገባ እያደረገ ባለው ጥረት ሊመሰገን ይገባዋል። ግን ደግሞ እርዳታው ያለ ምንም መስተጓጎል ወደ ክልሉ  መግባት አለበት ስለተባለ ብቻ፣ የጭነት መኪና ሲንጋጋ መንግስት ከዳር ቆሞ እያየ ዝም ብሎ ያሳልፋል የሚል ግምት እንዳይኖር ከወዲሁ አቋሙን በግልጽ ማሳወቅ ይገባዋል፡፡ በመኪናም ሆነ በአውሮፕላን የሚደረገው የእርዳታ እህልና መድሃኒት አቅርቦት እጅግ ጥብቅ በሆነ ፍተሻ ውስጥ እንዲያልፍ ማድረግ ይኖርበታል።
የእነ አቶ ስብሐት ቡድን የተሳተላይት ስልክ፣ የጦር ሜዳ መገናኛ፣ ለጦሩ የሚያገለግል ነዳጅ ወዘተ ያገኘው፣ በእርዳታ ስም ከገቡ አካላት መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ስለዚህም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፤ “እያስታጠቃችሁ አታፋጁን” ብሎ አስቀድሞ መጮህ ይገባዋል፡፡
መንግስት የትግራይ ክልል ሰባ በመቶ የሚሆነው አካባቢ በመከላከያ ቁጥጥር ሥር መሆኑን በግልጽ አሳውቋል። ስምምነቱን ተጠቅሞ ቀሪውን ክፍል በመንግስት ኃላፊነት ሥር ማስገባት ፈጥኖ ሊያከናውን የሚገባው ተግባር ነው። በእነዚህ አካባቢዎች የእነስብሐት ነጋን ቡድን ቆይታ ማራዘም ሌላ ጉዳት መጋበዝ መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው።
እንዲያውም ከአካባቢው የሚወጡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ትህነግ ለሌላ አዲስ ጦርነት ሠራዊት ምልመላ ውስጥ ገብቷል፡፡ ይህን እድል ካገኘ ደግሞ ያለ ጦርነት መኖር የማይችለው የእነ ስብሀት ቡድን፣ ሌላ መተላለቅ በአገር ላይ ሊያመጣ ይችላል። ለዚህ መፍትሔው ደግሞ ትህነግን የውጊያ አቅምና እድል ማሳጣት እንደሆነ ለአፍታ መዘንጋት አይገባም፡፡ ይህን የምናደርገውም የተጀመረውን የሰላም ስምምነት ከአደናቃፊዎች ለመታደግና ለትግራይም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ የናፈቃቸውን ሰላም በዘላቂነት ለማስፈን ነው፡፡
ፈጣሪ ለኢትዮጵያ ሰላሟን ያስፍንላት!

Read 13845 times