Print this page
Saturday, 19 November 2022 20:09

ብርታትሽ......ብርታቴ፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

 በየአመቱ የጥቅምት ወር የጡት ካንሰርን በሚመለከት የግንዛቤ ማስጨበጫ ወር ተብሎ በተለያዩ ሁኔታዎች እንቅስቃሴ ይደረጋል፡፡ በዚህም መሰረት የአለም ፀሐይ የጡት ካንሰር ፋውንዴሽን ጥቅምት 20/2014 ዓ/ም በአዲስ አበባ ከተማ ብርታትሽ ብርታቴ በሚል መሪ ቃል የታጀበ የእግር ጉዞ አከናውኖአል፡፡
የአለም ጸሐይ የጡት ካንሰር ፋውንዴሽን ስያሜውን ያገኘው አለም ፀሐይ የተባለች ኢትዮ ጵያዊት በጡት ካንሰር ሕመም ምክንያት ለህልፈት ከተዳረገች በሁዋላ ቤተሰቦችዋ በህይወት ላለ የሰው ልጅ በሙሉ በህመሙ ላይ ከፍተኛ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም መነደፍ አለ በት ከሚል የተነሳ ነው፡፡
የጡት ካንሰር ፒንክ ቀለም ያለው የደረት ሪቫን አለም አቀፍ ምልክቱ ሲሆን በአዲስ አበባ ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኘው የፋውንዴሽኑ ቢሮም ፒንክ ሀውስ ተብሎ ተሰይሞአል፡፡ ግድ ግዳው በሙሉ በፒንክ ቀለም የተቀባ ነው፡፡ የዚህ አምድ አዘጋጅም በዚያ በመገኘት ከመስ ራቾቹ አንድዋንና በህመሙ ተይዘው ማረፊያ ካገኙ ታማሚዎች ጋር ተወያይታ ለንባብ እነሆ ብላለች፡፡
ወ/ሮ ፍሬሕይወት ደርሶ ይባላሉ፡፡ የወ/ሮ አለም ፀሐይ (በጡት ካንሰር ህመም ለህልፈት የተዳረጉት) ታላቅ እህት ናቸው፡፡ ወ/ሮ ፍሬሕይወት ሲመሰክሩ አለምፀሐይ የፖሊስ ሰራ ዊት አባል እና የአምስት ልጆች እናት ነበረች፡፡ በጡት ካንሰር ሕመሙም ለሁለት አመት ያህል ከታመመች በሁዋላ መዳን ስላልቻለች አልፋለች፡፡ ለአለም ፀሐይ እኛ ቤተሰቦችዋ ከጎንዋ በመኖራችን አስታመን አስፈላጊውን ሁሉ አድርገን ብትሞትም በስነስርአቱ ቀብርዋን አስፈጽመናል ፡፡ ሌሎችስ ታማሚዎች …ምናልባት ቤተሰብ ወይንም ለሕክምና የመብቃት እና ለመታከምም ማረፊያ የማጣት ነገር ቢኖር ምን ያደርጋሉ ስንል ነበር ድጋፍ ማድረግን ያሰብነው ብለዋል፡፡ ወ/ሮ ፍሬሕይወት የሚኖሩት በአሜሪካ ሲሆን ይህንን ኢትዮጵያውያን ሴቶችን የመርዳት ሀሳብ ሲቀርብ በኢትዮጵያም በውጭም ያሉ የጡትና የማህጸን ካንሰር ታካሚዎች ሀሳቡ በጎ መሆኑን እና እንድንቀጥልበት ነበር የገፋፉን፡፡ በሁዋላም ከታማ ሚዎች ጋር በተለያዩ የመልእክት መለዋወጫ መንገዶች እየተነጋገርን ገንዘብ እና የመሳሰ ሉትን ከአሜሪካ በመላክ ድጋፍ ስናደርግ ለሰባት አመት ያህል ከቆየን በሁዋላ እኔ ወደ ኢትዮያ መጥቼ ሁኔታውን ስገነዘብ ችግሩን በከፋ መንገድ ተመለከትኩት ብለዋል፡፡
ወ/ሮ ፍሬሕይወት እንደሚሉት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በሁዋላ መጀመሪያ ወደጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነበር ያመሩት፡፡ በዚያም ብዙ የካንሰር ታማሚዎች የጨረር ሕክምናን በመጠ ባበቅ ላይ የነበሩ ሲሆን ወደ መጡበት ክልልም ለመመለስ ገንዘብ ስለሚቸግራቸው…እን ዲሁም በአዲስ አበባ የሚያውቁት ሰው ባለመኖሩ መጠጊያ የሌላቸው መሆኑን ለመታዘብ ቻልኩ፡፡ ስለዚህ በሌላ መልክ ተደራጅቶ እርዳታውን ማድረግ ይሻላል ከሚል ፒንክ ሐውስን ለመፍጠር ችለናል ብለዋል፡፡
በፒንክ ሐውስ ካረፉት የጡት ካንሰር ታማሚዎች መካከል የተወሰኑትን አነጋግረናል፡፡ አንድዋ ታማሚ የመጣችው ከሰበታ ነው፡፡ የግራ ጡትዋ በጣም በሚያስደነግጥ ወይንም ለመገመት በሚያስቸግር ሁኔታ አብጦአል፡፡ እስዋ እንደምትመሰክረው ሕመሙ ሲሰማት ቶሎ ወደሕክምና አልሄደችም፡፡ ወደ ህክምናው ከሄደችም በሁዋላ ሐኪሞቹ ጡትሽ በካንሰር ተይዞአልና በቀዶ ሕክምና መወገድ አለበት ሲሉአት ምላሽዋ እምቢታ ነበር፡፡ እምቢ ያለ ችበትን ምክንያትም ስትናገር ሰዎች እንዳትቆረጪ…ከተቆረጥሽ ትሞቻለሽ ብለውኝ ነው ትላለች፡፡ አንዴ ጸበል …ሌላ ጊዜ ደግሞ የባህል ሐኪም ስትል ቆይታ ሲብስባት እንደገና ወደሆስፒታል ትሄዳለች፡፡ አሁን ቀዶ ሕክምና ማድረግ ስለማይቻል ጨረር እንድትጠብቅ ተነግሮአት በአለምጸሐይ የጡት ካንሰር ፋውንዴሽን ማረፊያ ተሰጥቶአት ትገኛለች፡፡
ወ/ሮ ፍሬሕይወት ደርሶ የአለም ፀሐይ የጡት ካንሰር ፋውንዴሽን መስራች እንደሚሉት ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኘው ፒንክ ሐውስ የካንሰር ህሙማን ማረፊያ እስከ ሰላሳ ሕመም ተኞችን ማሳረፍ የሚችል ሲሆን አስታማሚዎች ካሉም አብረው ይከርማሉ፡፡ በቀን ሶስት ጊዜ ምግብ ያቀርባል፡፡ በቤቱ ያረፉት እንደሚመሰክሩት ወደአመሻሹ ላይ መክሰስም ይሰጣ ቸዋል፡፡ በተረፈ ንጽህና እንዲጠብቁ ማድረግ እና ሕክምናቸውን እንዲከታተሉ መኪና አቅ ርቦ ማመላለስን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችንም ይሰጣል፡፡
ለወ/ሮ ፍሬሕይወት ካቀረብናቸው ጥያቄዎች መካከል የጡት ካንሰር ሕመሙ በቤተሰብ አለ ወይ የሚል ይገኝበታል፡፡ እሳቸውም ሲመልሱ ‹‹….መኖሩን የምናውቅበት ምንም መንገድ አልነበረንም፡፡ ምክንያቱም ወላጆቻችን የሞቱት በተለያዩ ምክንያቶች ስለነበር የካንሰር ሕመ ሙም በቤተሰብ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየነው በአለምፀሐይ ነው፡፡ ነገር ግን እኔ ነርስ ስለሆንኩ እና በተለያዩ ደረጃዎች ብዙ ስራን በአሜሪካ እሰራ ስለነበር ለነገሩ እንግዳ አልነ በርኩም፡፡ ከኢትዮጵያ የወጣሁትም በልጅነቴ ስለነበር እህቴ ሁሉን ነገር ነግራ እኔን ማስ ጨነቅ ስላል ፈለገች በካንሰር መያዝዋን ሳትነግረኝ የቀዶ ሕክምና ከተደረገላት በሁዋላ ነበር የሰማሁት፡፡ እስዋ እራስዋን በመደበቅዋ እንጂ የካንሰር ሕመሙም በ2ኛ ደረጃ ላይ ስለነበር አትሞትም ነበር፡፡ ነገር ግን በትክ ክለኛው መንገድ ህክምናው ሳይደረግ የዳነች መስሎ …ነገር ግን ተመልሶ ሲመጣ በሳንባዋ፤ በጀርባ አጥንትዋ፤በእግርዋ….ባጠቃላይ በሰውነትዋ ተሰራጭቶ ስለነበር መዳን አልቻለችም፡፡ ስለዚህ እኔ በካንሰር ዙሪያም የሰራ ሁዋቸው ስራዎች ስለነበሩ እና ምን ያል አስከፊ ሕመም መሆኑን አውቀው ስለነበር ወዲ ያውኑ ለቤተሰብ በሙሉ ነበር መረጃውን ያስተላለፍኩት፡፡ ለእህቶቼ በሙሉ ምርመራ ውን እንዲ ያደርጉና እራሳቸውን እንዲያውቁ አስጠነቀቅሁ፡፡ እኔም ለራሴ ምርመራ ሳደርግ አንደኛ ደረጃ ላይ ያለ ካንሰር ጡቴ ላይ ተገኘብኝ፡፡ በጣም ነበር የገረመኝ፡፡ ወዲያው እርምጃ ወስጄ ጡቴን አስወገድኩ፡፡ የጡት ካንሰር ካለ ወደ ማህጸን ካንሰርነትም ሊተላለፍ ስለሚችል ማህ ጸኔንም አስወጣሁ፡፡ የቤተሰቦቻችንን ሁኔታ ሳናውቅ ብንኖርም ካንሰር ለካስ በቤተሰባችን ውስጥ አለ ብለን አመንን…ብለዋል፡፡
በፋውንዴሽኑ ያረፈችው ሌላዋ ሕመምተኛ እንደሚከተለው ነበር ታሪክዋን የገለጸችው፡፡
‹‹….እኔ ትውልዴ ከወደ ግሸን ማርያም ቢሆንም የነበርኩት ግን እዚሁ አዲስ አበባ ነው፡፡ ጡቴን ሲያመኝ እንደጠጣር ነገር ነበር የወጣብኝ፡፡ ወደሐኪም ቤት ስሄድ ናሙና እንዳሰራ ስለታዘዝኩ አሰርቼ ወደሐኪሜ ስቀርብ በአስቸኩዋይ ቀዶ ሕክምና ሊሰራልሽ ይገባል፡፡ መዝገብ ቤት ሄደሽ አስመዝግቢና ወረፋ ያዥ፡፡ ግን ከቀናት ያለፈ መሆን የለበትም አለችኝ፡፡ መዝገብ ቤት ሄጄ ሁኔታውን ሳስረዳ ከሁለት ወር በፊት መሰራት አትችይም አሉኝ፡፡ እኔም በጣም ተናድጄ ህክምናውን ትቼ ወደገዳም ሄድኩ፡፡ በዚያ እያለሁ በከፋ ሁኔታ እያበጠ መጣ፡፡ ሕመሙን መግለጽ አልችልም፡፡ እብጠቱ ሲበቃው ፈነዳ፡፡ ከዚያ በሁዋላ ሽታውም ሰው አላስቀርብ አለ፡፡ ማመን ሚያስቸግር ፈሳሽ እና ደም እስከ ትል ድረስ ከጡቴ ውስጥ ይወጣ ነበር፡፡ እኔም በጣም ታመምኩ፡፡ መንቀሳቀስ አልቻልኩም፡፡ የሚረዳኝ ሰውም የለ ኝም፡፡ ገንዘብም የለኝም፡፡ ከዚያ በሁዋላ አንድ በጎ ፈቃደኛ ተገኝቶ እኔ ወጪዋን ችዬ አሳክ ማለሁ በማለቱ ይሄው ዛሬ በሱ ኃይል ቀዶ ሕክምናው ተሰርቶልኝ እገኛለሁ፡፡ ማረፊ ያዬ የሆነው የአለምፀሐይ የጡት ካንሰር ፋውንዴሽንንም በጣም አመሰግናለሁ ብላለች፡፡
ሌላዋ በማረፊያ ያገኘናት ከራያ የመጣች ስትሆን ህመምዋ የማህጸን ካንሰር ነው፡፡ ከአሁን ቀደም መጥቼ ተመርምሬ ቀጠሮ ሲሰጠኝ አገሬ ደርሼ ልምጣ በማለት ሄድኩ፡፡ ወዲያውኑ ግጭቱ ስለተጀመረና መንገድ ስለተዘጋ መመለስ ሳልችል በመቅረቴ አሁን ህመሙ በከፋ ደረጃ ደርሶአል፡፡ ደግሞም የጨረር ህክምናው ስለተበላሽ እና ወረፋዬም እሩቅ ስለሆነ አሁን ከዚህ ማረፊያ ከገባሁ ስምንት ወር ሆኖኛል ፡፡ ቁጭ ብዬ ሕክምናው እስኪደረግልኝ እየጠ በቅሁ ነው፡፡ ግን ሕመሙም እየከፋ ነው፡፡ እግዚሀር ይርዳኝ እንጂ መዳኔን እንኩዋን እጠራ ጠራለሁ፡፡ ነበር ያለችን፡፡
ወደ ወ/ሮ ፍሬሕይወት ስንመለስ ለማጠናቀቂያ ያህል የነገሩንን እናስነብባችሁ፡፡ ሴቶች ምንጊዜም እድሜአቸው ወደ አርባ አመት ሲደርስ በህክምና መታየት አለባቸው፡፡ የካንሰር ሕመም ገና ከጅምሩ ከሆነ መዳን የሚችል ሕመም ነው፡፡ ይህንን በማስገንዘብ በኩል በአሜ ሪካም በኢትዮጵያም በጎንደር እና አዲስ አበባ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እንሰ ራለን፡፡ የእግር ጉዞውም የዚሁ አካል ነው፡፡ በተረፈ ግን ሕመምተኞችን ለማሳረፍ የተለያዩ አካላትን ድጋፍ እንሻለን፡፡ አነሰ በዛ ሳይባል የተቻለውን ያህል በተቋም ወይንም በግለሰብ ደረጃ እገዛ ቢደረግልን ህመምተኞችን የማስታመም እድል በማግኘት ከእግዚአብሔር በረከት ይገኝበታል ብለዋል፡፡ በይበልጥ የማሳረፊያው ቦታ ችግር ስላለው በመንግስት በኩልም እገዛ ቢደረግልን ዜጎችን መርዳት ነውና በተስፋ እንጠብቃለን ብለዋል የአለምፀሐይ የጡት ካንሰር ፋውን ዴሽን መስራችና የአለምፀሐይ ታላቅ እህት ወ/ሮ ፍሬሕይወት ደርሶ፡፡


Read 13432 times