Saturday, 19 November 2022 20:15

ዳሽን ባንክ እና ሜክሲኮ ኤምባሲ በትብብር ያዘጋጁት የፎቶ ኤግዚቢሽን ተከፈተ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 ኢትዮጵያና ሜክሲኮ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 73ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው የፎቶ ግራፍ ኤግዚቢሽን ህዳር 8 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ በዳሽን ባንክ ዋናው መስሪያ ቤት ተከፈተ፡፡ ዳሽን ባንክና ሜክሲኮ ኤምባሲ በትብብር ባዘጋጁት በዚሁ ኤግዚቢሽን  የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው አለሙን ጨምሮ በርካታ የባንኩ ከፍተኛ አመራሮችና ከ100 በላይ አገራት አምባሳደሮች፤ ቆንስላዎችና ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
በፎቶ ግራፍ አወደርዕዩ ላይ ከ73 ዓመታት በፊት ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ሜክሲኮን ለመጎብኘት በሄዱበት ጊዜ ከአየር መንገድ ጀምሮ የተደረገላቸውን የክብር አቀባበል፤ የጎበኟቸውን ዋና ዋና ቦታዎች በወቅቱ በነበሩ ጋዜጦች ጃንሆይ የወጡባቸው የጋዜጣ ገፆች፤ የሜክሴኮ ሰዓሊ የሳላቸው ካርቱን ምስል፡ ጃንሆይ ያደረጓቸው በርካታ እንቅስቃሴዎችን የሚያሳዩ ፎቶዎች ለእይታ ቀርበዋል፡፡ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን የሜክሲኮ አምባሳደር በኢትዮጵያና የአፍሪካ ህብረት ቋሚ ተወካይ የሆኑት ሚስተር ቪክተር ኤም ትሬቪኖ ኢትዮጵያና ሚክሲኮ ስላላቸው ዘርፈ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አብራርተዋል፡፡
ሜክሲኮና ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት ኢጣሊያ ዳግም ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ ሜክሲኮ ወረራውን በመቃዎም ከኢትዮጵያ ጎን በቆመችበት ጊዜ ይህን ተከትሎ ጃንሆይ በ1954 ዓ.ም ሜክሲኮን ከጎበኙት ጊዜ ጀምሮ መሆኑ ይታወሳል፡፡ የፎቶ ኤግዚቢሽኑ እስከ ታህሳስ 15 ቀን ለእይታ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይም ታውቋል፡፡



Read 13434 times