Saturday, 19 November 2022 20:38

የቢጂአይ ኢትዮጵያ የሥራ ላይ ልምምድ የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና ተጠናቀቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ሠልጣኞቹ ተገምግመው በኩባንያው ውስጥ ይቀጠራሉ ተብሏል

        ቢጂአይ ኢትዮጵያ፣ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያዘጋጀው  የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም (BGI Excellence program/BGI XP)  የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና በስኬት መጠናቀቁን፣ ባለፈው ማክሰኞ፣ በስካይላይት ሆቴል  ባዘጋጀው  የመዝጊያ ሥነሥርዓት አስታወቀ፡፡
ከ30 ምልምል ተማሪዎች መካከል 18ቱ የሥራ ልምምድ ሥልጠናውን በተሳካ ሁኔታ በማጠናቀቃቸው በዕለቱ ዕውቅና የተሰጣቸው ሲሆን፤ ሁለት ሠልጣኞች በድርጅቱ  ውስጥ የሰሩትን የጥናት ውጤት አቅርበዋል፡፡ ተማሪ አላዛር እሸቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ “Price and Portfolio Analysis” እና ተማሪ  ዮሐንስ ደመቀ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ “Database Project for International Procurement” በሚሉ ርዕሶች ነው ጥናታቸውን ያቀረቡት፡፡
የቢጂአይ ኢትዮጵያ የሰው  ሃብት (HR) ዳይሬክተር ወ/ሮ ጃላሊ ጀሬኛ  እንደገለጹት፤ ቀሪው ሥራ የመጨረሻ ግምገማ ሲሆን፣  ከዚያ በኋላ ያለው ሂደት ቅጥርና ከመደበኛው ሠራተኛ ጋር መቀላቀል ይሆናል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ4ኛ ዓመት የኢኮኖሚክስ ተማሪና የቢጂአይ ኢክስፒ ሰልጣኝ የሆነው ኢዮብ ጌታሁን ከፕሮግራሙ ምን እንደተጠቀመ ተጠይቆ ሲመልስ፤ “ ዩኒቨርሲቲ  በንድፈ ሃሳብ ደረጃ (ቲዮሪ) ነው የምንማረው፡፡ እንደ ቢጂአይ ባሉ ድርጅቶች ውስጥ ግን መሬት ላይ ምን አለ የሚለውን በተግባር ለማየት ዕድል ይሰጠናል፡፡ የህይወት ክህሎትን ለማዳበር ይረዳናል፡፡ ነገ የራሴን ሥራ ብፈጥር እንዴት ነው ራሴን መሸጥ፣ ምርቴን ማስተዋወቅ የምችለው የሚለውን እንማርበታለን፡፡ ከኢንዱስትሪው አሰራርና ባህል ጋር ያስተዋውቀናል፡፡” ብሏል፡፡
በመዝጊያ ሥነሥርዓቱ  ላይ የቢጂአይ ኢትዮጵያን ፕሮግራም መነሻ በማድረግ፣ በዩኒቨርሲቲ - ኢንዱስትሪ ትብብርና የብቁ ባለሙያ ምልመላ ላይ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን፤ በውይይቱ ላይ የታለንት ልማት ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚና መሥራች ዶ/ር ገመቹ ዋቅቶላ፣ የቀድሞው የAAIT ኢንዱስትሪ-ዩኒቨርሲቲ ትስስር ዲን ዶ/ር ወንድወሰን ቦጋለ እና የቢጂአይ ኢትዮጵያ HR ዳይሬክተር ወ/ሮ ጃላሊ ጀሬኛ  ተሳትፈዋል፡፡
የቢጂአይ የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም  ዓላማ፣ በአገራችን ከሚገኙ የሁለተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች  መካከል ከፍተኛ ውጤት ያላቸውን መልምሎ ሥልጠና በመስጠት፣ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩና ወደፊት በየኢንዱስትሪው ለሚጠበቅባቸው የመሪነት ሚና እንዲዘጋጁ ማድረግ ነው ተብሏል፡፡
ፕሮግራሙ እ.ኤ.አ በ2020/21 ዓ.ም ከአዲስ አበባና ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች የተመለመሉ 30 ከፍተኛ ውጤት ያላቸውን ተማሪዎች በመቀበል ነው የተጀመረው፡፡
ተማሪዎቹ ባለፉት ሁለት የክረምት ጊዜያት በአብዛኛዎቹ  የቢጂአይ ዲፓርትመንቶች ገብተው በሚመለከታቸው የሥራ መሪዎች ሥር ሆነው የልምምድ ሥራቸውን ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን፤ ተለማማጅ ተማሪዎቹ ከድርጅቱ ባለሙያዎች ጋር ተቀላቅለው በየሥራ ሂደቶች ውስጥ በመሥራት፣ ኩባንያውንና አሠራሩን በጥልቀት ለማወቅና  ልዩ ልዩ ችሎታዎችን ለመቅሰም የሚያስችል ዕድል ማግኘታቸው ተጠቁሟል፡፡


Read 1185 times