Saturday, 19 November 2022 21:18

የ’ዲጂ ትራክ ኢትዮጵያ‘ ፕሮጀክት በይፋ ተጀመረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ተማሪዎችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ያደርጋል


      የሁዋዌ ፕሮጀክት የሆነው ዲጂ ትራክ፣ ከኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር እና ከአይኮግ ’ICog Anyone Can Code’ (ICOG ACC) ጋር በመተባበር፣ የገጠርና የሩቅ አካባቢ ተማሪዎችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ ሰሞኑን በይፋ ተመርቆ ተጀምሯል፡፡
ዲጂ ትራክ ኢትዮጵያ የላፕቶፕ ኮምፒውተሮችን፣ ሮቦቲክ መሳሪያዎችና ማይክሮ ኤሌክትሮኒክስን ጨምሮ የመማር ማስተማር ሂደቱን ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚያደርሱ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች የተገጠመለት ተንቀሳቃሽ የስልጠና ማዕከል ነው ተብሏል፡፡
በቅርቡም በመላው ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ዙር በተመረጡ ከተሞች ስልጠናው የሚሰጥ ሲሆን በስልጠናውም ተማሪዎች ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና፣ አርትና ሂሳብ “STEAM” ትምህርቶችን ፋይዳ ግንዛቤን ለማስጨበጥ እንደሚሰራ ተነግሯል፡፡
የዲጂ ትራክ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ከኮምፒዩተር፣ ከፕሮግራሚንግ፣ ከኢንተርኔት ዘርፎች (IOT) እና ሌሎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር እንዲተዋወቁ የሚያስችል ማዕቀፍ በማዘጋጀት የዲጂታል ክፍፍልን ለማጥበብ እንደሚሰራ ተጠቁሟል፡፡
ፕሮጀክቱ በመላው ኢትዮጵያ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመከታተል ከቴክኖሎጂ ጋር የተገናኙ ክህሎቶችን ሊታጠቁ እንደሚገባ የሚያምን ሲሆን፤ በዚህም መሰረት የሁዋዌ ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር እና የምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው የግል አርተፊሽያል ኢንተለጀንስ እና የሮቦቲክስ ምርምር እና ልማት የግል ኩባንያ ጋር በመተባበር፣ የሙከራ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግና የስልጠና ፕሮግራሙን በመላ ሀገሪቱ ለማስጀመር መቻሉ  ተጠቁሟል፡፡
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የሁዋዌ  ኖርዘን አፍሪካ ሪጅን ምክትል ፕሬዚዳንት ሊዮ ሊዩ  ባደረጉት ንግግር፤ “ሁዋዌ ኢትዮጵያ፣ በኢትዮጵያ ጠንካራ የአይቲ ተሰጥኦ ምህዳር ለመገንባት ምንጊዜም ቁርጠኛ ነው። ከሁዋዌ ቴክ 4ኦል ዋና ዋና ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነውን ዲጂ ትራክን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣታችን ደስተኞች ነን። ታዳጊ ልጆች ችሎታቸውን እንዲያዳብሩና በዲጂ ትራክ በኩል የዲጂታል ቴክኖሎጂን እንዲያገኙ ማስቻል የሁዋዌ ፍላጎት ነው” ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የተማሪዎችን ተነሳሽነትን፣ ትኩረትን፣ የግንዛቤ ሂደትን፣ የማንበብ ግንዛቤን፣ ሂሳዊ አስተሳሰብንና ፈጠራን በእጅጉ እንደሚያሳድግ የተገለጸ ሲሆን  የተነደፈው መርሃ ግብር ተማሪዎችን ከመደበኛ የትምህርት እውቀታቸው ባሻገር፣ እንደ ቴክኖሎጂ እውቀት፣ መረጃ አስተዳደር፣ ግንኙነት፣ የቡድን ስራ፣ ስራ ፈጠራ፣ አለምአቀፍ ግንዛቤ፣ የሲቪክ ተሳትፎና ችግር ፈቺነት እንዲሁም እንደ ሮቦቲክስ ያሉ የቴክኖሎጂ ችሎታዎችን በማዳበር ረገድ  አዎንታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል ተብሏል።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) እንደገለፁት፤ “የሁዋዌ ዲጂ ትራክ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ከ’Icog Anyone Can Code’ ጋር በመተባበር፣ የልጆቻችንንና የወጣቶችን እውቀት እጅግ በጣም መሠረታዊ በሆነው በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ላይ ለማዳበር ከተዘጋጁት ውጥኖች አንዱ ነው። በዚህም መሰረት ከአንድ አመት ዝግጅት በኋላ የትምህርት ሚኒስቴር፣ ሁዋዌ እና አይኮግ  በመተባበር የዲጂ ትራክ ኢትዮጵያ ፕሮጀክትን በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ አድርገዋል። በዲጂ ትራክ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በተቻለ መጠን የዲጂታል ቴክኖሎጂን ጥቅም ማግኘት እንደሚችሉና የዲጂታል ቴክኖሎጂን ልምድ በሚያስደንቅ ሁኔታ እንደሚያዳብሩ ተስፋ ተጥሏል” ብለዋል።
የ’Icog Anyone Can Code’ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቤተልሔም ደሴ በበኩላቸው፤ “ይህን ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ ሳስብ እኔ በልጅነቴ ያገኘሁትን ዕድል ለሌሎች ለመስጠት በማስብ ነው፡፡ የ21ኛው ክፍለ ዘመን መሰረታዊ ችሎታዎች መግቢያ የሆነው የቴክኖሎጂ ትምህርት ዛሬ ለወጣቶች በጣም አስፈላጊ መሆኑን አምናለሁ፣ ይህም እድል ለወጣቶች የሚፈጥረው የእውቀት ነፃነት ትልቅ ነው። ዲጂትራክ ቀጣዩን ኮድ አድራጊ ትውልድ በማነሳሳት፣ የአገሪቱን የቴክኖሎጂ ስነ-ምህዳር የወደፊት እጣ ፈንታ የሚቀርፁ የፈጠራ ባለሙያዎችን መረብ ይገነባል፡፡ ይህ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ያሉ ህፃናትንና ወጣቶችን በዲጂታል እውቀት ለማሳደግና በሮቦቲክስ ላይ ለማስተማር በምናደርገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡”  ሲሉ ተናግረዋል።
ዲጂትትራክ ኢትዮጵያ ሴት ተማሪዎችን በቴክኖሎጂ ትምህርቶች ላይ ያላቸውን ፍላጎት ለማሳደግ አቅዶ የሚሰራ ሲሆን በ’STEAM’ ትምህርት ላይ በራስ መተማመን እንዲፈጥሩና ፍላጎቶቻቸውን እንዲያገኙ በሚያስችሉ ተግባራት በመሳተፍ በዘርፉ ያለውን የፆታ ተሳትፎ በማጥበብ ረገድ እንደሚያግዝም ተነግሯል፡፡
ፕሮጀክቱ ለሚቀጥሉት ሰባት አመታት የኮዲንግ ጉዞውን የሚቀጥል ሲሆን ከተለያዩ የዞን ከተሞች ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከክልል ትምህርት ቢሮዎች፣ ከአጋር ድርጅቶችና ከሚመለከታቸው የትምህርት ተቋማት ጋር በመሆን በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ ከተሞችን ለማዳረስ እቅድ ይዟል።
የዲጂ ትራክ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት፣ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ፣ በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመመስረት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ትምህርት ዘርፍ፣ የመጀመሪያ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትና የዲጂታል ክህሎትን በመደገፍ በስራ ዕድል፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራና በህብረተሰብ ኑሮ መሻሻል ላይ ተጽዕኖውን እንደሚያሳድር ነው የተነገረው።    


Read 14318 times